በዳዊት እስጢፋኖስ ስንብት አትራፊ ክለቡ ወይስ ተጫዋቹ?
ግንቦት 01, 2007

ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ አምበሉን ዳዊት እስጢፋኖስን ማሰናበቱን ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ማስነበቡ ይታወሳል። ክለቡ ተጫዋቹን ለማሰናበት የወሰነበትን ምክንያት “ተጫዋቹ የአቋም መውረድ ስለታየበት፣ ሙያውን አክብሮ ባለመስራቱ እና የተጫዋች በተለይም የአምበል ስነ ምግባር ሰለሌለው ነው” ሲሉ የክለቡ ዋና ጸሃፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዱ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም በስልክ ተናግረዋል። አቶ ገዛኸኝ ክለቡ እዚህ ውሳኔ ለይ እንዲደርስ የተገደደባቸውን ነጥቦች ሲያብራሩም “ዳዊት አምበል እንደሆነ እየታወቀ እሱ ግን ቡድኑን ከማነሳሰትና ብቃቱን ጠብቆ ከመጫወት ይልቅ የዲስፕሊን ችግር እና የቡድን መንፈስ የሌለው በመሆኑ ነው” ሲሉ ነበር የተናገሩት። 
Dawit Estifanos

ኢትዮጵያ ቡና ዳዊት እስጢፋኖስን የኮንትራት ማራዘሚያ ውል የስፈረመው ባለፈው ክረምት ላይ ሲሆን በወቅቱ ለተጫዋቹ የፊርማ ክፍያ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደከፈለው አሳውቆ ነበር። በዚህ ውላቸው መሰረትም ተጫዋቹ ክለቡን ለተከታታይ ሁለት ዓመታት እንዲያገለግል ይደነግጋል። በደጋፊዎች የሚወደደውና በሌለበት ሳይቀር የሚዘመርለትን አምበሉን ለማሰናበት ክለቡ እዚህ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ተጠቃሚው አካል ማን ነው? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን። 

ዳዊት እና 2007 ዓ.ም

ከ2006 ዓ.ም መገባደጃ ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም  አጋማሽ ድረስ ያሉትን ጊዜያት ጉዳት ላይ መሆኑን ቀደም ባሉት ጊዜያት ድረ ገጻችንም ሆነ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ያለፉትን ስምንት ወራት ከጉዳት ጋር እየታገለ መሆኑን ተጫዋቹም ገልጿል። ክለቡ ለሁለት ዓመታት እንዲያገለግለው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር የፊርማ ክፍያ የከፈለው ቢሆንም በዚህ የውድድር ዓመት ግን ተጫዋቹ ለክለቡ መጫወት የቻለው በስምንት ጨዋታዎች ብቻ ነው። ክለቡ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ጨምሮ በአጠቃላይ 26 ጨዋታዎችን ተጫውቷል። ከዳዊት ያነሰ ጨዋታ ያካሄዱት የክለቡ ተጫወቾች ቁጥር ውስን ሲሆን እነሱም የተሰላፊነት እድል ያልተሰጣቸው ተጫዋቾች ብቻ ናቸው። 

ክለቡ ዳዊት እስጢፋኖስን ለማሰናበት በመወሰኑም ለተጫዋቹ የከፈለውን የፊርማ ክፍያ ታሳቢ ያደረገ አይመስልም። ምክንያቱም ዳዊት ቡናን እንዲሰናበት የተደረገው በክለቡ ግፊት በመሆኑ ተጫዋቹ የተቀበለውን የፊርማ ገንዘብ የመመለስ ግዴታ የለበትም። በዚህም መሰረት ለሁለት ዓመታት ቢያንስ ለ48 ጨዋታዎች እንዲያገለግለው የተከፈለውን ገንዘብ በስምንት ጨዋታ ብቻ አገኘ ማለት ነው። ይህም ማለት የወር ደመወዙን ሳይጨምር ለአንድ ጨዋታ 150 ሺህ ብር የተከፈለው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ያደርገዋል ማለት ነው።  
 
የዳዊት ባህሪ

ክለቡ ተጫዋቹን ለማሰናበት የተገደደበቸውን ምክንያቶች ሲያቀርብ “ተጫዋቹ የቡድን ስሜት የለውም” የሚል ነጥብ ይገኝበታል። በዚህ መመዘኛ ካየነው የተጫዋቹን ተፈጥሯዊ ባህሪ እንድንፈትሽ እንገደዳለን። በርካቶች “ዳዊት እስጢፋኖስ አድመኛ እና ግልፍተኛ ነው” እያሉ ቢጠሩትም ተጫዋቹ ግን በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ እንደገለጸው አድመኛ የሚለውን ፍረጃ እንደማይቀበለውና “ግልፍተኛ ነው የምባለውም ለቡድኔ ካለኝ ፍቅር የተነሳ ነው” ሲል ተናግሮ ነበር። 

ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት ጋር ባደረገው የሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ ዳዊት በእረፍት ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል። በዚያ ጨዋታ ላይ ደደቢቶች የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ተቆጣጥረውት ስለነበረ ዳዊትም እንደ አምበልነቱ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ከአቅም በታች ሲጫወቱ ስላየ ሲሳደብና ሲቆጣቸው ታይቷል። እንደዚህ አይነት ባህሪ ከአንድ የእግር ኳስ አምበል የሚጠበቅ ቢሆንም ክለቡ ግን “በራሱ አይን ያለውን ምሰሶ ሳያይ የሰው ጉድፍ እየለቀመ ተጫዋቾቹን ይኮንናል” ሲል ወቅሶታል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተጫዋቹ በልምምድ ቦታ ላይ ተግኝቶ እንደማይሰራ ይነገራል። በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ ከብሔራዊ ቡድንም ሆነ ከክለብ አሰልጣኞች ጋር መስማማት ሲሳነው ይታያል። 

የዳዊት ብቃት

“ዳዊት እስጢፋኖስ እግሩ ስር ኳስ ስትገባለት በኳሷ ተደስቶ ያስደስታታል” እየተባለ ይነገርለታል። በዚህ ሃሳብ በርካቶች ይስማማሉ። ዳዊት እስጢፋኖስ ተፈጥሯዊ የኳስ ክህሎት የማይጎድለውና ጥበበኛ ተጫዋች መሆኑን የክለቡ ደጋፊዎችም ሆኑ ከደጋፊነት ውጭ ያሉ የስታዲየም ተመልካቾች ይመሰክሩለታል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የተጫዋቹ ትልቁ ድክመት ተደርጎ የሚነሳው “ተሯሩጦ የሚጫወት ተጫዋች አለመሆኑ እና የአካል ብቃቱ አስተማማኝ አይደለም” እየተባለ ነው። 

ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቹን ለማሰናበት የወሰነው ከላይ የተነሱት የተጫዋቹ ድክመት አሁን ስለገባው አይደለም። ምክንያቱም ዳዊትና ቡና ከአምስት ዓመታት በላይ አብረው ክፉውንም ደጉንም ያዩ ናቸው። በእነዚህ አምስት ዓመታት ክለቡ የዳዊትን ድክመት ዳዊትም የራሱን ድክመት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለአሁኑ የክለቡ ቆፍጠን ያለ ውሳኔ ያበቃው ምክንያት ግን ዳዊት እስጢፋኖስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከብቃት በታች ተጫውቷል የሚል ነው። “ክለቡንም ሆነ ደጋፊዎችን አላከበረም” ያሉት የክለቡ ዋና ጸሃፊ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ “ዳዊት ከጉዳት ነጻ ሆኖ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎችም እንኳ የቀድሞውን ብቃቱን መድገም አይደለም የተቀራረበ ብቃት ሊያሳይ አልቻለም። ይህ የሆነው ደግሞ ተጫዋቹ ለሙያው ክብር ባለመስጠቱ ተግቶ ባለመስራቱ ነው” ብለዋል። 

ከስንብቱ ውሳኔ ተጠቃሚው ማነው?

ዳዊት እስጢፋኖስ ለኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ብቻ አልነበረም። ተጫዋቹ ላለፉት አምስት ዓመታት ለክለቡ ያለውን ሁሉ የሰጠ ተጫዋች ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ በእጅጉ የሚወደድና በሌለበት ሳይቀር የሚዘመርለት ተጫዋች ነው። ቡና ይህንን ተጫዋች ማሰናበት የፈለገበት ምክንያት ማንም ተጫዋች ከክለብ በላይ ሊሆን አይገባውም በማለት ነው። በዚህ መርህ ማንም ይስማማል። በ2003 እ.ኤ.አ ማንቸስተር ዩናይትድ ዴቪድ ቤካምን በ2009 ደግሞ ኤሲ ሚላን ሮናልዲንሆ ጎቾን የሸጧቸው በተጫዋቾቹ የልተገባ ግለኝነትና ከአቅም በታች መጫወትን ምክንያት በማድረግ ነበር። 

ኢትዮጵያ ቡናም በዳዊት ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ሲያሳልፍ ከተጫዋቹ የተመለከተው ችግር ጎልቶ ከወጣ ሊያሰናብተው እንደሚገባ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከስንብቱ ጋር በተያያዘ ፋይናንሳዊ እና ስነ ልቦናዊ በሆኑ ጉዳዮች ክለቡ አትራፊ ሊሆን ይገባዋል። በዚህ በኩል ካየነው ቡና ተጠቃሚ የሆነ አይመስልም ምክንያቱም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የከፈለውን ተጫዋች ችግሩን ከምንጩ መርምሮ በመለየት ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ተጫዋቹን ማሰናበት የክለቡን ፋይናንሳዊ ስርዓት የሚጎዳ መስሎ ይታያል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የልጁ አድናቂዎች በክለቡ ውሳኔ ተቃውመቸውን ሊያሰሙ ይችላሉ። እንደሚታወቀው ቡና ሃብቱ ሰው ነው እየተባለ ይነገራል። ሃብቱ ሰው ከሆነ ደጋፊውን ከማስከፋት ይልቅ የተጫዋቹን ችግር ተቀምጠው ቢወያዩበትና ዘለቄታዊ መፍትሔ ቢሰጡበት ይሻል ነበር። 

ቅጣትና ስንብት መፍትሔ ይሆናል?

ኢትዮጵያ ቡና ከዳዊት በፊት ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ቅጣትና ስንብት ሲያስተላልፍ የቆየ ክለብ መሆኑ ይታወቃል። ክለቡ የአጥቂ ችግር እያለበት ሙሉዓለም ጥላሁንን፣ የተከላካይ መስመሩ ችግር እንዳለበት ግልጽ ቢሆንም ቶክ ጀምስን እንዲሁም የክለቡ ዋና ችግር የሚባለው የግብ ጠባቂዎች ቦታ መሆኑ ለእግር ኳስ ቤተሰቡ ግልጽ መሆኑ እየታወቀ እንኳ ኔልሰን የተባለውን ናይጄሪያዊውን ግብ ጠባቂውን ከአምስት ወራት ላላነሰ ጊዜ ቀጥቶታል። ከእነዚህ ተጫዋቾች በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች ሶስት ተጫዋቾችን ከጨዋታ እና ከልምምድ መቅጣቱን ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ቀደም ሲል ዘግቧል። አሁን ለዳሽን ቢራ በውሰት ተሰጥቶ የሚጫወተውን ቶጓዊው ኤዶም በመኖሪያ ካምፑ ውስጥ ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽም በመገኘቱ ከወር ደመወዙ ላይ ግማሹን ማለትም አስር ሺህ ብር ቀጥቶት እንደነበር ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገልጸዋል። 

ክለቡ በአንድ ዓመት አራት ተጫዋቾችን ከጨዋታ እና ከልምምድ አንድ ተጫዋች ደግሞ በደመወዝ ቀጥቷል። ይህ አልበቃ ብሎት የቡድኑን አምበል እና በደጋፊዎች በእጅጉ የሚወደደውን ዳዊት እስጢፋኖስን ማሰናበት ችሏል። ይህ ሁሉ የቅጣት እና የስንብት ውሳኔ ማስተላለፍ ለክለቡ ችግርም ሆነ ለተጫዋቾች ባህሪና ችሎታ መሻሻል ይጠቅማል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ክለቡ ይህንን ያህል ቅጣት ለመጣል የተገደደው ቀድሞ ያልሰራው የቤት ስራ ስላለው ነው ተብሎ እንዲተችስ አያደርገውም ወይ? ብለን እንጠይቃለን። 

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!