በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ግንቦት 03, 2007

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየምና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል። ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ በተጠናቀቁበት የ22ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሳሙኤል ሳኖሜ የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት በብቸኝነት መምራት የቻለበትን ጎል በሙገር ሲሚንቶ መረብ ላይ አሳርፏል። በሳምንቱ ከተካሄዱት ሰባት ጨዋታዎች ላይ 17 ኳሶች ከግብ ጠባቂዎች ጀርባ በተወጠረው መረብ ላይ ሲያርፉ የአዳማ ከነማው ዮናታን ከበደ ብቻውን ሶስት ጎሎችን በንግድ ባንክ መረብ ላይ በማሳረፍ በዓመቱ ሁለተኛውን የፕሪሚየር ሊግ ሃትሪክ ሰርቷል። በዮናታን ሶስት ጎሎች የታጀበው አዳማ ከነማ በሜዳው ንግድ ባነክን አስተናግዶ አራት ለሁለት አሸንፏል። ለንግድ ባንክ ሲሳይ ቶላ እና አኪም ኦኬንዳ ሁለት ጎሎችን ቢያስቆጥሩም ባለሜዳዎቹ አዳማ ከነማዎች በዮናታን ከበደ ሶስታ እና በዳኛቸው በቀለ ተጨማሪ አንድ ጎል አራት ለሁለት በማሸነፍ በዓመቱ በሜዳቸው ያለመሸነፍ ሪከርዳቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል። 

ለሊጉ ዋንጫ ከፍተኛ እድል ይዞ የቆየው ሲዳማ ቡና ትናንትም በወላይታ ድቻ በመሸነፍ የዋንጫ ተስፋውን አጨልሞ ተመልሷል። ለወላይታ ድቻ ጎሎቹን ዮሴፍ ድንገቶ እና አላዛር ሽፈራው ሲያስቆጥሩ ሲዳማ ቡናን ከሽንፈት ያልታደገች ጎል ያስቆጠረው ደግሞ ብሩክ አየለ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት በአዳማ ከነማ ሶስት ለአንድ ከተሸነፈ በኋላ ትናንትም በተከታታይ ሶስተኛ ሽንፈቱን በዘወትር ተቀናቃኙ ወላይታ ድቻ በመሸነፍ ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ እንዲልበት አድርጎታል። በአንጻሩ ተከታታይ ጨዋታዎችን እያሸነፈ የመጣው ደደቢት ከሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ችሏል። 

ሃዋሳ ላይ በተካሄደው የሃዋሳ ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ደግሞ ሃዋሳ ከነማ በማሸነፍ የኢትዮጵያ ቡናን የቁልቁለት ጉዞ አፍጥኖበታል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አጥቂው ታፈሰ ተስፋዬ የቀድሞ ክለባቸውን ገጥመው በድል አድራጊነት የተወጡ ሲሆን ለሃዋሳ ከነማ ጎሎቹን የቀድሞው የቡና አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ እና ጋዲሳ መብራቴ አስቆጥረዋል። ኢትዮጵያ ቡና በተከታታይ ያደረጋቸውን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ በመሸነፍ በዓመቱ መጥፎ ሪከርድ ያስመዘገበ ሲሆን በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች አንድም ጊዜ ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻለም። 

አርባምንጭ ላይ አይሸነፍም የሚባልለት አርባ ምንጭ ከነማ ትናንት በዳሽን ቢራ ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግዷል። እስከ እረፍት ድረስ ተሾመ ታደሰ ባስቆጠራት ጎል አንድ ለባዶ ሲመራ የቆየው ባለሜዳው አርባ ምንጭ ከነማ ከእረፍት መልስ ሚኬኤል ጆርጆ እና ኤርሚያስ ሀይሉ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ዳሽን ቢራ ማሸነፍ ችሏል። በአሰልጣኝ ካሊድ መሃመድ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት የሚሰለጥነው ዳሽን ቢራ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፉ እና ተከታዮቹ ኤሌክትሪክና ሙገር ሲሚንቶ በመሸነፋቸው የመውረድ ስጋት እንዲቀልለት አስችሎታል። 
ወልድያ ላይ የተካሄደውን የወልድያ ከነማ እና መከላከያ ጨዋታ መከላከያ በሳሙኤል ታዬ ብቸኛ ጎል አንድ ለባዶ አሸንፎ ተመልሷል። ወልድያ ከነማ መሸነፉን ተከትሎ የመውረዱ ጉዳይ ይበልጥ እየቀረበው መጥቷል። በ12 ነጥብም የደረጃውን ግርጌ በብቸኝነት ተቆጣጥሮታል። 

አዲስ አበባ ላይ የተካሄዱት ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ተጠናቀዋል። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የተገናኙት ያለፈው ዓመት የጥሎ ማለፍ አሸናፊው ደደቢት እና የመውረድ ስጋት ያንዣበበበት ሙገር ሲሚንቶ ናቸው። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሙገር ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ደደቢት ደግሞ ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ግን እንደተጠበቀው ሳይሆን ማብቂያውን ሰዓት በጉጉት እንዲጠበቅ የሚያስገድድ ነበር። 

ከኤፍሬም ቀሬ ብቸኛ የጎል ሙከራ ውጭ ተጨማሪ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ የተሳናቸው የሙገር ሲሚንቶ አጥቂዎች ለደደቢት የተከላካይ ክፍል ሙሉውን 90 ደቂቃ  ምንም ስጋት ሳይሆኑ ወጥተዋል። ደደቢት በበኩሉ በዳዊት ፈቃዱ እና ሳሙኤል ሳኖሜ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ ቆይቶ በሳሙኤል ሳኖሜ ብቸኛ ጎል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል። በእለቱ የተቆጠረችው ብቸኛ ጎልም ሳሙኤል ሳኖሜን በአንድ ጎል ብልጫ የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃ በብቸኝነት መምራት አስችለዋለች። በዚህ ጨዋታ የእለቱ ክስተት የሆነው ለአንድ ዓመት ያህል ከጉዳት ጋር ሲታገል የቆየው የቀድሞው የአዳማ ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ የነበረው ያሬድ ዝናቡ ለአዲሱ ክለቡ ደደቢት የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረጉ ነው። ያሬድ ባለፈው ዓመት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ደደቢት ከተዘዋወረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገባው ትናንት ሸይቩ ጅብሪልን ቀይሮ በመግባት ነው።   

ከአመሻሹ 11፡30 ላይ የተጀመረውና በበርካታ የጎል ሙከራ እና በከባድ ዝናብ ታጅቦ አንድ ጎል ብቻ የተቆጠረበት የፈረሰኞቹና የኮረንቲዎቹ ጨዋታ የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነበር። ተከታያቸው ሲዳማ ቡና መሸነፉን ሰምተው የገቡት ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን አጠናክረው ለመያዝና ከወዲሁ የሊጉ አሸናፊነታቸውን ለማረጋገጥ ቆርጠው የገቡ ሲሆን በአንጻሩ ኤሌክትሪክ በዳሽን ቢራ እና ሀዋሳ ከነማ ማሸነፍ ዜና ተደናግጦ ነበር የገባው። ከአስር ያላነሱ የጎል ሙከራዎች የታዩበትና በሀይሉ አሰፋ እንደተለመደው ኮከብ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው አዳነ ግርማ ነው። ለጎሏ መቆጠር የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አብርሃም ይርጉ እና ተከላካዮቹ የሰሩት ስህተት ተጠያቂ ነው። 
በኤሌክተሪክ በኩል 14 ቁጥር የሚለብሰው ተከላካዩ አማረ በቀለ ከእረፍት በፊትና በኋላ በተደጋጋሚ ያደረጋቸውን የጎል ሙከራዎች የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በብቃት የመለሰ ሲሆን ናይጄሪያዊው ፒተር እና ከሃይቲ የመጣው ሳውሬል አልሪሽ ያደረጓቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎችም በኤሌክትሪክ በኩል የታዩ የጎል ሙከራዎች ናቸው። በተለይ በ40ኛው ደቂቃ ፒተር ንዋድኬ የፈረሰኞቹን ተከላካይ አለማየሁ ሙለታን ካለፈ በኋላ ወደ ጎል ሞክሮ ሮበርት ኦዶንካራ ያወጣት ኳስ ለጎል የቀረበች ሙከራ ነበረች። 

በፈረሰኞቹ በኩል ብሪያን አሙኒ ከእረፍት በፊት ሞክሮ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አብርሃም ይርጉ የመለሰበት እና ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት ሙከራ ተጠቃሽ ናቸው። ከእረፍት በፊት ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ያላደረጉት ፈረሰኞቹ የመስመር አማካዩ በሀይሉ አሰፋ ያሳየው ብቃት ግን በበርካቶች አድናቆትን ያሰጠው ነበር። 

ከእረፍት መልስ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ፈረሰኞቹ የጎል ሙከራ በማድረግ ከኤሌክትሪክ የተሻሉ ነበሩ። ተደጋጋሚ ሙከራቸው ተሳክቶላቸውም በአዳነ ግርማ አማካኝነት የዕለቱን ልዩነት ፈጣሪ ጎል ማግኘት ችለዋል። ድሉን ተከትሎም ሊጉን በብቸኝነት እየጋለቡበት እንዲገሰግሱ አስችሏቸዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ብሪያን አሙኒ ያገኛትን የጎል እድል ሊጠቀም አለመቻሉ እንጅ ጨዋታው ሁለት ለባዶ ሊጠናቀቅ የሚችልበት እድል ነበረ።  

ይርጋ አበበ 
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ASSEGED [943 days ago.]
 ጊዮርጊስ ሁሌም ሻምፒዮን

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!