የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሣህሌ ፈተናዎች ክፍል ሁለት
ግንቦት 06, 2007

አዲሱ የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ ፌዴሬሽኑ ካስቀመጠለት ግዴታ አኳያ ተመልክተን ግዴታዎቹን ፈተናዎች” ብለን የመጀመሪያውን ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። ይህኛው ጽሁፍ የቀዳሚው ክፍል ተከታይ ነው። አንድ አሰልጣኝ የትኛውንም ቡድን ሲረከብ የራሱ የሆኑ ፈታኝ ነገሮች እንደሚኖርበት ግልጽ ነው። ብዙ ጊዜ ፈተናዎቹ ውጫዊና ውስጣዊ ሲሆኑ በተለይ ውስጣዊ አስተዳደራዊ ፈተናዎች የአሰልጣኙን ውድቀት የሚያፋጥኑ ናቸው። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም “የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ፈተናዎች” ሲል ውጫዊ ፈተናዎቹን እንጅ ውስጣዊ አስተዳደራዊ  ችግሮችን እንዳልሆነ ይታወቅልን። 

31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ትልቁ ሀላፊነት

ድረ ገጻችን ከዚህ ጽሁፍ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ “ለጋቦኑ ጉዞ ዝግጅቱ አሁን ቢጀመርስ” በሚል ርዕስ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና በማጣሪያው የነበረውን ታሪክ አስነብቧል። ቀደም ብሎ ባስነበብነው ሀተታ እንደሚታወሰው አገራችን በአፍሪካ ዋንጫ ለዘጠኝ ጊዜያት የተካፈለች ስትሆን አንዱንም ጊዜ በምድብ ማጣሪያ የምድቡ የበላይ ሆና በማለፍ አይደለም። ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ማለፍ የተሳነው በተደጋጋሚ ጊዜ የእግር ኳስ ደረጃቸው የላቁ አገሮችን በምድብ ማጣሪያው ስለሚያገኝ፣ የአሰልጣኞች ቅጥር ወጥነት ያለው አለመሆንና ለስራቸው የሚገባቸውን ጥቅማጥቅም አለመከፈል እንዲሁም ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ጊዜ ስለሚጠፉ የሚሉት ምክንያቶች ውሃ የሚያነሱ ሆነው ተገኝተዋል።
Yohannes Sahle Head Coach

 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴረሽን ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ለአሰልጣኞች የስራ ኮንትራት ውል እንደ ድሮው በሁለት ወር የተገደበ ሳይሆን በትንሹ የሁለት ዓመት ኮንትራት ስለሚያስፈርምና ከስፖንሰር ሽፕ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በፈጠረው ስምምነት ምክንያት የአሰልጣኞች ደመወዝም እንደ ቀድሞው መናኛ አለመሆን አሰልጣኞች አነሰም በዛም ተረጋግተው ስለሚሰሩ በስማቸው ሊጠራ የሚችል የተለየ የአጨዋወት ስልት ያለው ቡድን የመገንባት እድልን ያገኛሉ። ለምሳሌ የጋርዚያቶ፣የሰውነት ወይም የባሬቶ እንደምንለው። 

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የገጠመው መልካም አጋጣሚም አንዱ ይሄ ሲሆን ሌላው ደግሞ በምድብ ማጣሪያ የሚገናኛቸው ብሔራዊ ቡድኖች ከቀድሞው ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው አገሮች መሆናቸው ነው። በዚህም ምክንያት ዋልያዎቹ በ2017 ጋቦን ላይ ለሚካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።  

የተጋጣሚ ቡድኖች ድክመትና የዋልያዎቹ ዝግጅት

የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በተለምዶ “ሁለተኛው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን” በሚል ስም ይጠራል። ብሔራዊ ቡድኑ የተዋቀረው የአልጄሪያ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ወይም አልጄሪያ ውስጥ ቢወለዱም የእግር ኳስ ሀሁን ፈረንሳይ ውስጥ የተማሩ ተጫዋቾች ናቸው። አብዛኞቹ እንዲያውም የፈረንሳይን ወጣትና ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ወክለው በዓለምና በአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያዎች የተሳተፉ ተጫዋቾች ናቸው። ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወጣትነታቸውን አሳልፈው ዋናውን ብሔራዊ ቡድን መቀላቀል እንደማይችሉ ሲያውቁት አልጄሪያን እንደ ማምለጫ የሚቆጥሩ ተጫዋቾች ናቸው። 

በዚህም ምክንያት ጠንካራ የጌም ልምድ እና የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግንና የእንግሊዝን ፕሪሚየር ሊግ ጨምሮ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የመጫወት ልምድ ያካበቱ ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ለዋልያዎቹ ፈታኝ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ግን ዋልያዎቹ ከዚህ ቡድን ላይ ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ሊከተሏቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ። ዋልያዎቹን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ከሚችሉ ነጥቦች መካከል አንዱና ዋነኛው አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ጨዋታ የበርሃ ተኩላዎቹ በማያውቁት ሜዳ የሚጫወቱ በመሆናቸው የሜዳ የበላይነትን መጠቀም፤ እንዲሁም በተለምዶ የአዲስ አበባ አልቲቲዩድ ከፍተኛ በመሆኑ በተለይ ከሰሜን አፍሪካ ለሚመጡ ዜጎች አየሩ ከባድ ነው። በዚህ ምክንያትና የራስን የቤት ስራ ቀድሞ በመስራት አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ጨዋታ ዋልያዎቹ እንዳለፈው ዓመት ሙሉ ሶስት ነጥብ ለእንግዳው ቡድን አስይዘው መሸኘት የለባቸውም። 
Addis Ababa Ethiopia Vs Algeria

ከአልጄሪያ ውጭ ያሉት ሁለት ተጋጣሚዎቻችን የእግር ኳስ ደረጃቸውም ሆነ የውስጥ ሊጋቸው “ከዚህ ግባ” የሚባል አይደለም። ነገር ግን ለቡድኖቹ ክብር አለመስጠት በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹ በቡርኪናፋሶ እንደደረሰባቸው አይነት ያልታሰበ ሽንፈት ሊገጥም ይችላል። የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ፈተና የሚሆነውም ከአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ላይ የሆነ ነገር መውሰድ ማለትም ቢያንስ አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት አለዚያ ከሁለቱም ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ማግኘት እንዳለበት የሚገደድ መሆኑ ነው። አሰልጣኙ ካለው ልምድና የትምህርት ዝግጅት ተነስተን ስንገመግመው የተሰጡትን ሀላፊነቶች መወጣት እንደሚችል እናምናለን። ለአሰልጣኙና ለብሔራዊ ቡድኑ ስኬት ማማር ግን እኛ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከከታቸው አካላት ከቡድኑ እና ከአሰልጣኙ ጎን ስንቆም ነው። 

ካሳ ሀይሉ
ለኢትዮ ፉትቦል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!