ወልድያ ወደ መጣበት ሲመለስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫው አንድ እጁን ዘረጋ
ግንቦት 08, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ እንደተለመደው በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ስታዲየሞች ተካሂደዋል። የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ጎንደር ተጉዞ ዳሽን ቢራን በአዳነ ግርማ ሁለት ጎሎች ሁለት ለአንድ በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን በስምንት በማሳደግ መሪነቱን አጠናክሯል። የሊጉ ተከታይ የነበረው ሲዳማ ቡና ደግሞ በሜዳው ከመከላከያ ጋር አቻ በመለያየቱ ደረጃውን ለደደቢት ለማስረከብ ተገዷል። የሳምንቱን ጨዋታዎች አንዳንድ ነጥቦች ከዚህ በታች እናቀርባቸዋለን።

የዓመቱ ሶስተኛው ሶስታ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚተችባቸው ነጥቦች አንዱ በርካታ የጎል ሙከራዎች የማይደረጉበት መሆኑ እና የሚቆጠሩት ጎሎችም በእጅጉ ውስን መሆናቸው ነው። ለአብነት ያህልም ያለፈው ዓመት የሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ዑመድ ኡክሪ ያስቆጠረው ጎል ብዛት 11 ብቻ ነው። በዚህ ዓመትም የመጀመሪያው ዙር የሊጉ መርሃ ግብር ላይ የጎሉን መስመር ለይቶ የሚያውቅ አጥቂ አልታየም ነበር ከኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ ውጭ።

በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አስር ጨዋታዎች ግን ሁለት ተጫዋቾች ማለትም የአዳማ ከነማው ዮናታን ከበደ እና የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኖሜ እያንዳንዳቸው ሃትሪክ መስራት ችለዋል። ይህም በመጀመሪያው ዙር ቢኒያም አሰፋ ብቻ ሃትሪክ የሰራ ቢሆንም በሁለተኛው ዙር ግን በመጠኑም ቢሆን አጥቂዎች ተጠናክረው መቅረባቸውን ያሰየ ሆኗል። በተለይ ሳሙኤል ሳኖሜ፣ ዮናታን ከበደ፣ ፍሊፕ ዳውዝ እና አዳነ ግርማ በሁለተኛው ዙር የተሻለ የጎል ማግባት ሪከርድ ይዘው ቀርበዋል። ሳኖሜ ዘጠኝ ጨዋታዎች 10 ጎሎችን በማስቆጠርም በመጀመሪያው ዙር ከነበረው ስምንት ጎል ላይ የአሁኖቹን 10 ጨምሮ ድምሩን 18 በማድረስ የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃ እየመራ ይገኛል። በ23ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታም በቀድሞ ክለቡ ኤሌክትሪክ ላይ ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ለአሁኑ ክለቡ ውለታ ሰርቷል።

ከአምስት ጨዋታ በኋላ የተገኘ አንድ ነጥብ

ኢትዮጵያ ቡና በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በመሸነፍ ደጋፊዎችንም ሲያሳዝን የስፖርት ቤተሰቡን ደግሞ ግራ አጋብቶ ነበር። ትናንት በተካሄደው የሳምንቱ የመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ ላይ ግን ከወላይታ ድቻ ጋር ባዶ ለባዶ በመለያየት ከአምስት ጨዋታ ሽንፈቱ ማገገም ችሏል። ያም ሆኖ ግን ክለቡ አሁንም በሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ያላስቆጠረበትን ደካማ ሪከርዱን እንደያዘ ቀጥሏል።

Ethiopian Coffee vs Dicha

በቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በዛ ያሉ ያለቀላቸው የጎል እድሎች የተፈጠሩ ቢሆንም አንዳቸውም መረብ ላይ አለማረፋቸው አስገራሚ ነው። በተለይ የወላይታ ድቻው ባዬ ገዛኸኝ ያደረጋቸው ስድስት የጎል ማግባት እድሎች አንድ ጊዜ በግብ ጠባቂው ጌቱ ተስፋዬ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግቡ አግዳሚ ብረት እየተመለሱበት ሲከሽፉ ቀሪዎቹ ደግሞ በራሱ ተጫዋቹ ባዬ ተረጋግቶ አለመምታት ሙከራዎቹ ጎል ከመሆን ታቅበዋል። በነገራችን ላይ ባዬ ገዛኸኝ በ2005 ዓ.ም በሰባ ሺህ ብር ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቅሎ ቡናን አይመጥንም ተብሎ ወደ ወራቤ ከነማ በውሰት ተዘዋውሮ በዚያው ወላይታ ድቻን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው።
Ethiopian Coffee vs Wolayta Dicha

በቡና በኩል በተለይ ጉዳት ላይ የቆየው አስቻለው ግርማ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ይበልጥ ተጭኖ ለመጫወት ሞክሯል። ጨዋታው እንደተጀመረ በአንደኛው ደቂቃ ጥላሁን ወልዴን በጉዳት ያጡት ቡናዎች እስከ እረፍት ድረስ አንድም ጊዜ የረባ የጎል ማግባት ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር። ከእረፍት መልስ ግን የተሻለ መጫወት በመቻላቸው ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በተለይ ቢኒያም አሰፋ በ56ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት እና አስቻለው ግርማ በ76ኛው ደቂቃ ሞክሮ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ የመለሰበት ይጠቀሳሉ። ለወትሮው የክለቡ የሽንፈት በር እየተባለ ይተች የነበረው የቡናው ግብ ጠባቂ ጌቱ ተስፋዬ በትናንቱ ጨዋታ መሻሻል ታይቶበታል። በተለይ በ80ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻው አሸናፊ ሽብሩ የመታውን ቅጣት ምት እና ባዬ ገዛኸኝ ያደረጋቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎች ማዳኑ የግብ ጠባቂውን መሻሻል ያሳዩ ነበሩ።  

በአቻ ውጤት የተጠናቀቀው የኦሮሚያ ደርቢ

በፕሪሚየር ሊጉ የመወከል እድል ካገኙ ክልሎች ኦሮሚያ ክልል አንዱ ሲሆን ለረጅም ዓመታት አዳማ ከነማ እና ሙገር ሲሚንቶ ክልሉን የወከሉ ክለቦች ናቸው።አዳማ ከነማ ባለፈው ዓመት በብሔራዊ ሊጉ ሲወዳደር ቆይቶ በዚህ ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ በኋላ ከክልሉ ተወካይነት ባለፈ ጠንካራ ተፎካካሪ የሆነ ክለብ ሆኗል። የበርካታ ወጣት ተጫዋቾች መገኛ የሆነው ሙገር ሲሚንቶ በበኩሉ በዚህ ዓመት የቀድሞ ብቃቱ ክዶት ወደ ታችኛው ሊግ የሚወስደውን ባቡር ለመሳፈር እየተንደረደረ ይመስላል። ወደ ታችኛው ሊግ የሚወስደውን ባቡር ቀድሞ የተሳፈረው ወልድያ ከነማ ብቻ ሲሆን የቀረችዋን አንድ ቦታ ለማግኘት ከሙገር ሲሚንቶ ጋር የሚቀናቀኑት ዳሽን ቢራ፣ ኤሌክትሪክ እና ሃዋሳ ከነማ ሲሆኑ ሙገር ሲሚንቶን ጨምሮ አራቱም ወራጅ ቀጠናዎች በ23ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብራቸው ነጥብ መጣላቸው ሌላው አስገራሚ ክስተት ነው።

ሙገር ሲሚንቶ በሜዳው አሰላ አረንጓዴው ስታዲየም ላይ ጎረቤቱን አዳማ ከነማን አስተናግዶ አንድ ጎል አስቆጥሮ አንድ ደግሞ ተቆጥሮበት አንድ አንድ ነጥብ ተካፍለው ተለያይተዋል። ውጤቱን ተከትሎ ሙገር ከያዘው 19 ነጥብ ላይ አንድ በማከል የነጥብ ድምሩን ወደ ሃያ ከፍ ቢያደርግም በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ግን መሻሻል ሊያደርግ አልቻለም ከያዘው 13ኛ ላይ ተቀምጧል። አዳማ ከነማ በበኩሉ ነጥቡን 38 በማድረስ ወደ መሪዎቹ ጎራ መቀላቀል ችሏል።

የፈረሰኞቹን የዋንጫ ባለቤት ያመለከተው ፋሲለደስ ስታዲየም

ዳሽን ቢራ ባለፈው ሳምንት ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ እስከ እረፍት ድረስ በባለሜዳው አንድ ለባዶ ሲመራ ቆይቶ በመጨረሻ ሁለት ለአንድ አሸንፎ መመለሱን ዘግበን ነበር። ከአርባ ምንጭ ተመልሶ በሜዳው ፋሲለደስ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያስተናግድ ለፈረሰኞቹ ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሁለት ለአንድ በመሸነፍ የፈረሰኞቹን የድል ጉዞ አሳምሯል። ለፈረሰኞቹ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው “ከዚህ በኋላ የብሔራዊ ቡድን ጥሪን የምሰማበት ጆሮ የለኝም” ሲል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጠው አዳነ ግርማ ነው።

አዳነ ግርማ የትናንቱን ሁለት ጎሎች ጨምሮ በዚህ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ያገባቸውን ጎሎች ብዛት አስር ማድረስ ችሏል። ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች በረብሻ ምክንያት ተቋርጦ እንደነበረ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ጨዋታው የተቋረጠበትን የረብሻ ምክንያት ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ግን ሊሳካልን አልቻለም።

ወደመጣበት የተመለሰው ወልድያ ከነማ

ወልድያ ከነማ ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለ በመጀመሪያ ዓመቱ ተመልሶ ወደ ብሔራዊ ሊጉ የመውረድ መጥፎ እድል አጋጥሞታል። ካደረጋቸው 23 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በሶስቱ ብቻ አቻ የወጣውና በ16ቱ የተሸነፈው ወልድያ ከነማ ትናንትም በሜዳው በአርባምንጭ ከነማ አንድ ለባዶ ተሸንፎ ወደመጣበት ተመልሷል። በሊጉ ሁለተኛ ዙር በርካታ ገንዘብ ወጭ በማድረግ በርካታ ተጫዋቾችን አዘዋውሮ የነበረው ወልድያ ከነማ የቀጣይ ዓመት እድሉ ባለፈው ዓመት በተወዳደረበት ሊግ መጫወት እንደሚሆን ትናንት አረጋግጧል። አሁን ወልድያ የሚቀረው ብቸኛ ሂሳብ ቀሪ የመርሃ ግብር ጨዋታዎችን ማጠናቀቅ እና የሚከተለውን ክለብ ማወቅ ብቻ ነው። ወልድያ ከነማ ሊጉ በተጀመረበት እለት በደደቢት ስድስት ለአንድ ከተሸነፈበት ጨዋታ ጀምሮ የፕሪሚየር ሊጉን 14ኛ ደረጃ ለማንም ሳያስረክብ ነው የወረደው።

በሌሎች ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሃዋሳ ከነማ አንድ እኩል ሲለያዩ ለሁለቱ ቡድኖች ጎሎችን ያስቆጠሩት ጋዲሳ መብራቴ ለሃዋሳ እና ፍሊፕ ዳውዝ ለንግድ ባንክ ናቸው። ይርጋ ዓለም ላይ ሲዳማ ቡና ከመከላከያ ጋር ተጫውተው ተከባብረው ባዶ ለባዶ ወጥተዋል።

የቁጥር መረጃዎች

ፕሪሚየር ሊጉን ፈረሰኞቹ በ48 ነጥብ ሲመሩ መውረዱን ያረጋገጠው ወልድያ ከነማ ከፈረሰኞቹ አራት እጥፍ ያነሰ ነጥብ ሰብስቦ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሜ ወልድያ ከነማ በዓመቱ ካስቆጠራቸው ጎሎች በላይ አስቆጥሮ በግሉ 18 ጎሎችን በመያዝ ኮከብ ጎል አግቢነቱን ይመራል። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሳሙኤል ሳኑሜ ብቻውን አስር ጎሎችን ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ ቡና ግን አንድም ጎል ማስቆጠር አልቻለም።

ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ደደቢት 21 ነጥብ ሲያገኝ ክለቡ ካስቆጠራቸው ጎሎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑትን ያስቆጠረው ሳሙኤል ሳኑሜ ብቻውን ነው። በሰባት ጨዋታዎች ከሳኑሜ ውጭ ለደደቢት ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሽመክት ጉግሳ ዳዊት ፈቃዱ እና በረከት ይሳቅ ብቻ ናቸው። እነዚህ ሶስት ልጆችም እያንዳንዳቸው ማስቆጠር የቻሉት አንድ አንድ ጎል ብቻ ነው። ሳሙኤል ሳኑሜ በሰባት ጨዋታዎች አስር ጎሎችን ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በተመሳሳይ ሰባት ጨዋታዎች አስር ጎሎች ተቈጥረውበት አንድም ጎል ማስቆጠር አልቻለም። 

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!