ዓሊ ረዲ የግብ ጠባቂ ችግራችንን ሊቀርፍ ይችላል?
ግንቦት 11, 2007

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ እንዲሰለጥን ከተወሰነ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠው ባሳለፍነው ሳምንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ነበር። በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ለአሰልጣኙ ከቀረቡለት በርካታ ጥያቄዎች መካከል “ግብ ጠባቂዎች እና አጥቂዎች በውጭ አገር ዜጎች የተሞሉ ናቸው በምርጫህ ላይ እና በምታስመዘግበው ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አይፈጥርም ወይ?” የሚለው አንዱ ነው። አሰልጣኙ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ትክክልኛ ነው ያለውን መልስ የሰጠ ሲሆን በተለይ በውጭ ተጫዋቾች የተሞላው ሊግ ላይ እንዴት ልትወጣው ነው ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ግን አስገራሚ ነበር።
Ali redi and Assegid tesfaye

አሰልጣኙ ሲመልስ “እኔ ምክንያት መደርደር አልፈልግም ላሰለጥን የተስማማሁት የሊጉን ደረጃ እያወቅኩ ነው። ስለዚህ አገር ውስጥ ባሉን ልጆች ተጠቅሜ ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት እሰራለሁ” አይነት መልስ ነበር የመለሰው። በተለይ የግብ ጠባቂዎች ችግር ሲነሳ አገራችን በእጅጉ እየተጎዳች መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም አሰልጣኙ ግን በድፍረት  ባሉን ተጫዋቾች ላይ እምነት አሳድሬ እሰራለሁ ብሎ ሲናገር አስገራሚ ሆኗል።

የዓሊ ረዲ ሹመትና የዮሃንስ ሣህሌ ፍላጎት

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ የስራ ውል ስምምነት ላይ ከተቀመጡ አንቀጾች አንዱ አሰልጣኙ ምክትል አሰልጣኞቹን የመምረጥ ነጻነት ያጎናጸፈበት ይጠቀሳል። በዚህ የውል ስምምነት መሰረትም ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጣን ሲነሳ ክንዱን እንዲደግፉለትና የጥንካሬው አጋር እንዲሆኑት የመረጣቸው አሰልጣኞች ፋሲል ተካልኝን እና ዓሊ ረዲን ነው። የፈረሰኞቹ ጊዜያዊ ተጠባባቂ ዋና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከዚህ ቀደምም የብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝነት ስራን መስራት ከጀመረ የቆየ ቢሆንም የዓሊ ረዲ ግን በዋናው ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዚህም መሰረት ስለ ዓሊ ረዲ ሹመትና የስራ ኃላፊነት ላይ አንዳንድ ነጥቦችን አንስተን እናቀርባለን።

የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ቀደም ብሎ ይሰራበት በነበረው ጋዜጣ ላይ ዓሊ ረዲን እንግዳ አድርጎ አቅርቦት ነበረ። በወቅቱ ዓሊ ከተናገራቸው ንግግሮች መካከል አንዱ “በዚህ ሰዓት አገራችን ውስጥ ጠንካራ በረኛ አለ ብዬ መናገር አልችልም። በዚያ ላይ ከርቀት አክርሮ በመምታት በረኞችን የሚፈትን አጥቂም አለ ብሎ መናገር ይከብዳል። እኔ በዚህ እድሜዬ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጬ ብጫወት በጥሩ ብቃት መወጣት እችላለሁ” ብሎ ነበር። ዓሊ የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሆኖ ለመጫወት ያለው ፍላጎት ባይሳካም ጠንካራ ግብ ጠባቂዎችን ለአገር የማብቃት ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሣህሌ ዓሊ ረዲን በምክትል አሰልጣኝነት ሲመርጥ ታሳቢ ያደረገውም ይህንኑ የልጁን የቀደመ ወርቃ የግብ ጠባቂነት ዘመን በአሰልጣኝነቱ እንዲተገብርለት አስቦ ነው። ለመሆኑ ዓሊ ይህንን የአገር አደራ መወጣት ይችላል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጊዜው ገና ቢሆንም የዓሊን ወርቃማ የግብ ጠባቂነት ዘመን ሳያነሱ ማለፍ ተገቢ ስላልመሰለን የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት እንገደዳለን።  

ዓሊ በኦሜድላ

ዓሊ ረዲ እግር ኳስን “ሀ” ብሎ የጀመረው በኦሜድላ ስፖርት ክለብ ውስጥ መሆኑን ቀደም ብሎ ተናግሯል። በኦሜድላ የግብ ጠባቂነት ዘመኑ ያሰለጠነውን አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን ለማመስገንም ቃላት እንደሚያጥሩት ተናግሯል። በአጭር ጊዜ የኦሜድላ ቆይታው ራሱን ከክለቡ ወሳኝ ተጫዋቾች ተርታ ያሰለፈው ዓሊ ረዲ ከኦሜድላ ጋር ያለውን እህል ውሃ ከጨረሰ በኋላ ያመራው ወደ ኢትዮጵያ ቡና ነው።

ከኢትዮጵያ ቡና የምንጊዜም ኮከብ ተጫዋቾች ውስጥ የሚመደበውና በበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ “ጥንቁቅ እጆች ያሉት” እየተባለ ነው የሚጠራው። ከክለቡ ጋርም የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ጨምሮ በርካታ ድሎችን ያጣጣመ ሲሆን በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ የነሃስ ሜዳሊያ ያገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከእነ ካሳዬ አራጌ አንዋር ያሲንና አሰግድ ተስፋዬ በተጨማሪ የዓሊ ረዲ ጠንቃቃ እጆች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የግብጹን ጠንካራ ክለብ አል ሃሊን ከውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስወጣው ኢትዮጵያዊ ክለብ ቡና ሲሆን የዚያ ወርቃማ የቡና ዘመን ስብስብ አባልም ነበር። በሌላ ጊዜ በዛማሊክ በመለያ ምት ተሸንፎ ከውድድር የወጣውን የቡናን ቡድን የግብ ክልል የጠበቀውም ይሄው መለሎው ዓሊ ረዲ ነበር። በብሔራዊ ቡድን ውስጥም የራሱን አሻራ በጉልህ አስቀምጧል።

የዓሊ ረዲ ክፉ ቀናት

በጠንካራ ብቃቱ እና በረጅም ቁመናው ተለይቶ የሚታወቀው የብሔራዊ ቡድናችን እና የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ የነበረው ዓሊ ረዲ ከእለታት በአንድ ቀን በህይወቱ ያላሰበውና በእጅጉም አስከፊ የሆነ አጋጣሚ ተጋረጠበት። በወቅቱ ዓሊን እስከ ህይወት ማለፍ ሊያደርስ የሚችልው አደጋ የደም ካንሰር የሚባለው አስከፊ በሽታ ነው። የዓሊን እና የደም ካንሰሩን በሽታ በተመለከተ ቀደም ሲል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር አድርጎት በነበረው ቃለ ምልልስ ሲናገር “እነዚያ ቀናት የህይወቴ እጅግ አስከፊዎቹ እና ሳስታውሳቸው አሁንም የሚያስደነግጡኝ ቀናት ናቸው” ሲል ነበር እንባ እየተናነቀው የተናገረው።

 ነገር ግን ከህመሙ ሙሉ በሙሉ አገግሞ እንዲነሳ በሼህ መሃመድ ዓሊ አላሙዲ የገንዘብ ድጋፍ እና በፈጣሪ እርዳታ የመዳን እድሉ በእጅጉ ዝቅተኛ ከነበረው በሽታ ሙሉ በሙሉ ድኖ ዛሬ የአገር አደራ ለመቀበል ደረሰ። ይህንን በተመለከተ ሲናገርም “ምስጋና ለአላህ ይግባውና ለዚህ በቃሁ። አላሙዲ አሁንም አላህ ይስጣቸው” ሲል በደስታ ነበር የተናገረው።

አሁን ዓሊ ረዲ ከደም ካንሰር ሙሉ በሙሉ ነጻ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም በ2005 ግማሽ ዓመት ለሲዳማ ቡና እንዲሁም በ2006 ዓ.ም ለውሃ ስራዎች ተሰልፎ ተጫውቷል። በ2006 መገባደጃ ላይ ደግሞ ከ17 ዓመት በታች የሆነውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምክትል አሰልጣኝነት መምራት ችሎ ነበር። ዛሬ ደግሞ የዋናው ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ የአገር አደራ ለመሸከም በቅቷል። አገራችን የቸገራትን የግብ ጠባቂዎች ድክመትም ለመቅረፍ ጠንካራ ስራ እንደሚጠብቀው ይታወቃል። ይህንን አደራስ እንደ ደም ካንሰሩ ድል አድርጎ ይወጣል? ወደ ፊት እናያለን።

እኛ ግን የዓሊ ረዲን ምርቃት ተውሰን እሱን መልካም ምኞት እንመኝለታለን “ዓሊ ረዲ አላህ ከአንተ እና ከቡድን አጋሮችህ ጋር ይሁን” ብለን መልካም ምኞታችን ተመኝተንለታል።

መልካም ጊዜ ለእግር ኳሳችን!!!

ይርጋ አበበ ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!