ቢኒያም አሰፋ ከ7ት ጨዋታ በኋላ ያስቆጠራት ጎል ቡናን ወደ አሸናፊነት መለሰች
ግንቦት 12, 2007

አሰልጣኝ ጥላሁን መንገሻን ያሰናበተው ኢትዮጵያ ቡና ከሰባት ጎል አልባ ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ትናንት ጎል ማስቆጠር ቻለ። በፕሪሚዬር ሊጉ 24ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደዋል። ከእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች አንዱ በኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ መካከል የተካሄደው ጨዋታ ሲሆን በውጤቱም ቡና አንድ ለባዶ በሆነ ጠባብ ውጤት ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል። ይህ ውጤትም ቡናን ከሶስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያገኘበት ጨዋታ ሆኗል።

ለቡና ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኘችዋን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው ቢኒያም አሰፋ ሲሆን ጎሏ የተገኘችውም አስቻለው ግርማ ተጠልፎ በመውደቁ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት በማስቆጠሩ ነው። ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ ቢኒያም አሰፋ ለመጨረሻ ጊዜ ኳስ እና መረብን ያገናኙት ከስምንት ሳምንታት በፊት ማለትም በሊጉ 16ኛ ሳምንት ከኤሌክትሪክ ጋር በተደረገ ጨዋታ ላይ ነበር። በዚያ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች 90 ደቂቃ ያለ ጎል ሲፋለሙ ቆይተው በጭማሪው ሰዓት ቢኒያም አሰፋ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራት ጎል ለቡና ሶስት ነጥብ ያስገኘች ጎል ነበረች። ከዚያ ጨዋታ በኋላ ግን ቡናም ሆነ አጥቂው በግሉ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም ነበር።

ከቡና እና መከላከያ ጨዋታ ቀደም ብሎ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የተካሄደው የደደቢትና የዳሽን ቢራ ጨዋታ ሁለት እኩል በሆነ ውጤት ነው የተጠናቀቀው። ለሁለቱም ቡኖች አንድ አንድ ፍጹም ቅጣት ምቶች በተሰጡበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በሳሙኤል ሳኑሜ እና በረከት ይሳቅ ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ለእንግዳው ቡድን ደግሞ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው “አዲስ አበባ ላይ የጎል አኬሩ ይቆምለታል” የሚባለው ይተሻ ግዛው ነው።

የመውረድ ስት ውስጥ የቆዩት የካሊድ መሃመድ ልጆች “ጎንደሬዎቹ” የትናንቱ ውጤታቸው በሊጉ የመቆየት እድላቸውን ያሰፋላቸው ሆኗል። ደደቢት በበኩሉ ትናንት ባለማሸነፉ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በጊዜ ዋንጫውን ማንሳት አስተዋጽኦ አድርጎለታል። ዛሬ ከአመሻሹ 11 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ፈረሰኞቹ ከአርባ ምንጭ ከነማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ የዋንጫው ባለቤት መሆናቸውን ያረጋግጣሉ ማለት ነው። ይህንን ጨዋታ ኢትዮፉትቦል ዶትኮም በቀጥታ የሚያስየላልፈው መሆኑንም ከወዲሁ እንገልጻለን።

ሳሙኤል ትናንት ያስቆጠራትን ፍጹም ቅጣት ምት ጨምሮ በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 19 በማድረስ ኮከብ ጎል አግቢነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ርቀት ቀጥሎ ሊጉን የሚያጠናቅቅ ከሆነም ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ  ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ የመጀመሪያው የውጭ አገር ዜጋ ይሆናል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2007 ዓ.ም ታሪክ ለተከታታይ ሰባት ጨዋታ ጎል ሳያስቆጥር የዘለቀ እና በተከታታይ ደግሞ አምስት ጨዋታዎችን ያለምንም ጎል በሽንፈት ያጠናቀቀው ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ብቻ ነው።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!