ሻምፒዮኖቹ ሻምፒዮን ሆኑ
ግንቦት 13, 2015

ፈረሰኞቹ 12 ደጉ ደበበ በበኩሉ ሰባት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ተፎካካሪ የላቸውም

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2007 ዓ.ም አሸናፊ ፈረሰኞቹ መሆናቸው ታወቀ። ያለፈው ዓመት የዋንጫ ባለቤቶቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫውን ክብር ባለቤት መሆናቸውን ያረጋገጡት ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም አርባ ምንጭ ከነማን ሶስት ለአንድ በማሸነፋቸው ነው። እንደተለመደው በሀይሉ አሰፋ ኮከብ ሆኖ ባመሸበት የትናንቱ ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ቀዳሚ ያደረገችዋን ጎል ያስቆጠረው አንጋፋው አዳነ ግርማ ነው። አዳነ ያስቆጠራት ጎል የተገኘችው የአርባ ምንጭ ተከላካዮች በራሳቸው የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመንካታቸው በተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምት ነው። አዳነ ፍጹም ቅጣት ምት ካስቆጠረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የፈረሰኞቹ ተከላካይ ቢያድግልኝ ኤሊያስ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ አርባምንጭ ከነማዎች ፍጹም ቅጣት ምት አግኝተው ነበር። አርባምንጭ ከነማዎች ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት አጥቂው ተሾመ ታደሰ ለቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ሲሳይ አድርጓታል።
St.George 2007 EC Champions Team

የመጀመሪያ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀው ብልጭ ድርግም በሚል የመሃል ሜዳ ቅብብል እና አልፎ አልፎ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ ጥልቅ በሚሉ የጎል ሙከራዎች ታጅቦ ነው። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይ እንግዳዎቹ አርባምንጭ ከነማዎች ፍጹም ከሜዳ ጠፍተው የታዩበት ሲሆን በፈረሰኞቹ በኩል አጥቂዎቹ ፍጹም ገብረ ማሪያም እና ብሪያን አሙኒ ሁለት ያለቀላቸው የጎል እድሎችን አበላሽተዋል። የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተጠናቅቆ በተሰጠው አንድ ደቂቃ ጭማሪ ሰዓት ብሪያን አሙኒ የሞከራትን ኳስ የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ መሳይ አዳኖ ለመያዝ ሲሞክር በመትፋቱ ምንተስኖት አዳነ በቅርብ አግኝቶ ፈረሰኞቹን በሁለት ለባዶ መሪነት ለእረፍት እንዲወጡ አድርጓል።

ከእረፍት መልስ የተወሰነ መሻሻል ያሳዩት የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች አልፎ አልፎ የፈረሰኞቹን የግብ ክልል ቢያንኳኩም በሩን ለመክፈት ፈቃደኛ ያልሆነው የፈረሰኞቹ የጎል ክልል ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ሙከራቸውን አክሽፎባቸዋል። በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ አጥቂው አዳነ ግርማ ለግሉ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ሶስተኛዋን ጎል ከበሀይሉ አሰፋ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጠረ። የአዳነ ጎል ከተቆጠረች ከአምስት ደቂቃ በኋላ አርባምንጭ ከነማዎችን በመጠኑም ቢሆን ያጽናናችና በባዶ ከመሸነፍ የታደገችዋን ኳስ አስቆጠሩ። ግቧን ያስቆጠረው በ67ኛው ደቂቃ አስማማው ብሩን ተክቶ የገባው ፀጋዬ አበራ ነው።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች የሰጡት የፈረሰኞቹ ኮከቦችና አሰልጣኞች በድሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ድሉንም ለደጋፊዎቹ ስጦታ ይሁንልን ብለዋል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ “ለታማኝ ደጋፊዎቻችን የሚገባቸውን ክብር የሰጠ ድል ነው” ሲል የገለጸ ሲሆን አማካዩ በሀይሉ አሰፋ በበኩሉ “ከአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ሽንፈት በኋላ እንደገና ተነቃቅተን ወደ አሸናፊነት በበመለሳችን ለድል በቅተናል። ይህ ድል የተገኘው ደግሞ በደጋፊዎቻችን ጽናትና የማያቋርጥ ድጋፍ በመሆኑ ድሉን ለእነሱ ማስታወሻ ሰጥተናል” ብሏል። በሀይሉ አሰፋ አያይዞም “ዋንጫውን ማንሳታችን ዛሬ ቢረጋገጥም በቀሪዎቹ ጨዋታዎቻችንም ክብራችንን አስጠብቀን ለማሸነፍ እንጫወታለን” ብሏል።

ሌላው አስተያየቱን የሰጠው አጥቂው አዳነ ግርማ ደግሞ “የዓመቱ ኮከብ በሀይሉ አሰፋ ነው” ሲል ለቡድን አጋሩ ያለውን ክብርና አድናቆት ተናግሯል። አዳነ ከሃዋሳ ከነማ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያነሳ ሲሆን ከፈረሰኞቹ ጋርም የሊጉን ክብር ደጋግሞ ያነሳ ቢሆንም “አሁንም ለድል የተራብኩ ነኝ። ድል ይበቃኛል ማለት አልወድም የተፈጠርኩት ለማሸነፍ ነው እየተጫወትኩ ያለሁትም ከአሸናፊ ክለብ ጋር ነው። ገና በተደጋጋሚ ጊዜ የሊጉን ክብር ለመቀዳጀት እጫወታለሁ” ሲል ተናግሯል። አሰልጣኝ ዶሳንቶስን ያሰናበተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያውያኑ ዘሪሁን ሸንገታ እና ፋሲል ተካልኝ መሰልጠን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ጊዜ የሽንፈት ጽዋን አላስተናገደም።

ፈረሰኞቹ የዘንድሮውን ጨምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጉት የ17 ዓመታት ጉዞ ውስጥ 12 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት መሆን ችለዋል። ይህ ሪከርዳቸውም ከየትኛውም የአገሪቱ ክለብ በላይ ያስቀምጣቸዋል። በፕሪሚየር ሊጉ አራት ክለቦች ማለትም ሃዋሳ ከነማ መብራት ኃይል ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና በጋራ ስድስት ጊዜ ዋንጫውን ያነሱ ሲሆን የፈረሰኞቹ ታማኝ አምበል አመለ ሸጋው ደጉ ደበበ ብቻውን ሰባት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ባለሪከርድ ሆኗል።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
sami [1007 days ago.]
 Tnx Ethiosport nice and fair zegebba !

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!