25 ጎሎች በ25ኛው ሳምንት
ግንቦት 20, 2007

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታዎች ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ተካሂዷል። ዓመቱን ሙሉ የጎል ድርቅ የመታው ሊግ እየተባለ ሲታማ የከረመው ፕሪሚየር ሊግ በ25ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ግን በጎል ተንበሻበሹና በድራማዊ ጨዋታዎች ታጅቦ ተጠናቋል። ኮከብ ጎል አግቢዎቹ በጎል ተንበሽብሸው ባሳለፉበት 25ኛው ሳምንት መርሃ ግብር በሰባት ጨዋታዎች 25 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም በየጨዋታው በአማካይ 3 .57 ጎሎች ተቆጥረዋል ማለት ነው። ከተቀጠሩት 25 ጎሎች መካከል ሶስት ናይጄሪያውያን ተጫዋቾች ሰባት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ አንድ የሃይቲ ዜግነት ያለው የመብራት ሀይል ተጫዋች ሳውሬል አልሪሽ ደግሞ አንድ ጎል አስቆጥሯል። ኤሌክትሪክ ደግሞ ብቻውን በተጋጣሚው ላይ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠር የሳምንቱ በጎል የተንበሸበሸ ክለብ ሆኗል። 

በሳምንቱ ከተካሄዱ ጨዋታዎች ያለምንም ጎል የተጠናቀቀ ጨዋታ አንድ ብቻ ሲሆን ባህር ዳር ላይ በዳሽን ቢራ እና አዳማ ከነማ መካከል የተካሄደው ጨዋታ ነው። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎል ያልተቆጠረበት ብቸኛው የሳምንቱ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ለተመልካችም አዝናኝ ያልነበረ ጨዋታ መሆኑን ከባህር ዳር የደረሰን መረጃ አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የሸነፉበት ምሽት 

Coffee 3-0 Sidama

ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ የዝግጅት ጊዜ ላይ ከአገር ውስጥ እስከ ምዕራብ አፍሪካ በደረሰው የተጫዋች ግዥው በንቃት የተሳተፈ ቢሆንም ሜዳ ላይ ያስመዘገበው ውጤት ግን ለደጋፊዎቹ አንገት የሚያስደፋ ሆኖ ቆይቷል። ከሜዳ ላይ ብቃቱ መውረድ በተጨማሪም የክለቡ ካምፕ በተጫዋቾች ስነ ምግባርና በቅጣት እንዲሁም በእገዳ እና በስንብት ሲታመስ የከረመ ክለብ ነው። ከአምበሉ ዳዊት እስጢፋኖስ ስንብት እስከ ዴቪድ በሻህ ጫማውን መስቀል ድረስ ክለቡ በተጫዋቾች ስብስቡ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ውስጥ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ክለቡ በሰባት ተከታታይ ጨዋታ አንድም ጎል ሳያስቆጥር ከመቆየቱም በላይ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች የሽንፈት ጽዋን ተጎንጭቷል። 

ከላይ የተጠቀሱት የክለቡ አሉታዊ ውጤቶች እንዳሉ ቢሆንም የክለቡ ደጋፊዎች ግን “ለክለባችን ያለንን ድጋፍ ለመግለጽ ውጤት አይወስነንም” ያሉ ይመስላሉ። የደጋፊ ትርጉሙ ውጤት ሲጠፋ እና ችግር ላይ ሲወድቅ የሚደግፍ እና የሚያበረታታ መሆኑን ጠንቅቀው የሚያውቁት የቡና ደጋፊዎች በትናንትናው ጨዋታም ሙሉውን 90 ደቂቃ ክለባቸውን በታማኝነት ሲደግፉ ታይተዋል። ወጣቱ ተከላካይ አስናቀ ደረጀ ምርጥ ሆኖ ባመሸበት የቡና ደርቢ ጨዋታ ቢኒያም አሰፋ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የክለቡን ደጋፊዎች ከደስታቸው ላይ ተጨማሪ ደስታ አጎናጽፏቸዋል። ቢኒያም ከእረፍት በፊት ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አማካዩ ዮናስ ገረመው እና የክንፍ አጥቂው አስቻለው ግርማ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በተለይ ሁለተኛዋን ጎል ሲያስቆጥር አስቻለው ግርማ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን አታልሎ ያለፈበት ችሎታው በስታዲየም የታደሙ ተመልካቾችን ሳይቀር አድናቆታቸውን እንዲለግሱት ያስገደደ ነበር። 

ከእረፍት መልስ ደግሞ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይ በ68ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችን አታልሎ ካለፈ በኋላ የሞከራት ኳስ ከጎሉ በቅርብ ርቀት ወጥታበታለች። በመጨረሻም አስቻለው ግርማ በእለቱ ሲደክም የዋለበትን ጥረቱን በጎል ያጀበበትን አጋጣሚ አግኝቷል። ወጣቱ ኳስ አቀጣጣይ ሚኬኤል በየነ ከመስዑድ መሀመድ ጋር ተቀባብለው በመጨረሻም መስዑድ መሀመድ ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ የሲዳማ ቡና ተከላካዮችንና ግብ ጠባቂ አታልሎ ግሩም ጎል አስቆጥሯል። ውጤቱም ሶስት ለባዶ ሆኖ ተጠናቅቋል።  

በእለቱ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለክለባቸው ያሳዩት ክልብ የመነጨ ድጋፍ የሚያስደንቃቸው ነበር።  የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች “ክለባችንን የምንደግፈው ዋንጫ ስለሚያነሳ ሳይሆን ሜዳ ላይ ማራኪ ጨዋታ ስለሚያሳየን ነው” ማለታቸውን ከሳምንታት በፊት መዘገባችን ይታወሳል። ትናንት ሜዳ ውስጥ የገቡት የቡና ተጫዋቾችን ደጋፊዎቻቸው የሚፈልጉትን ጨዋታ ማሳየት ችለዋል ማለት ይቻላል። ማራኪ የመሃል ሜዳ የኳስ ፍሰት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አስቻለው ግርማ እና አስናቀ ደረጀ ልዩነት ፈጣሪ ሆነው አምሽተዋል። አጥቂው ቢኒያም አሰፋም የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበለት እንዲሁ እንዳልሆነ ያሳየበትን አቋም አሳይቷል። 

በጎል የተንበሸበሸው ኤሌክትሪክ

የመውረድ ስጋት ያንዣበበበት ኤሌክትሪክ ከሃዋሳ ከነማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ስድስት ለባዶ በማሸነፍ በጎል ተንበሽብሿል። ወጣቱ የጋምቤላ ተወላጅ ራምኬል ሎክ ሁለት ጎሎችን ባስቆጠረበት ጨዋታ ማናዬ ፋንቱ፣ በሀይሉ ተሻገር፣ ፒተር ንዋድኬ እና ከሃይቲ የመጣው ሳውሬል አልሪሽ እያንዳንዳቸው የጎሎቹ ተቋዳሽ ሆነዋል። በሃዋሳ ከነማ በኩል  ግብ ጠባቂው ክበረዓብ ዳዊት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ውጤቱን ተከትሎም ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየት እድሉን ለመወሰን በቀሪው ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘት በቂው ሆኗል። 

ክልል ላይ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ከወላይታ ድቻ ጋር አንድ እኩል በመለያየት በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየት እድሉን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል። ሙገር ከፕሪሚየር ሊጉ ላለመውረድ በፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብር እሱ ተጋጣሚውን አሸንፎ ኤሌክትሪክ ደግሞ ሊሸነፍ ይገባዋል። 

በሌላ ጨዋታ አርባ ምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ በሜዳው በደደቢት ሶስት ለባዶ ተሸንፏል። አሰልጣኙን ዳንኤል ጸሀዬን በልብ ህመም ምክንያት አገልግሎቱን ማግኘት ያልቻለው ደደቢት በምክትል አሰልጣኙ እየተመራ ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ ላስመሰገበው የሶስት ለባዶ ውጤት ናይጄሪያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኖሜ ሶስቱንም ጎሎች በማስቆጠር የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል። ሳኖሜ በ22 ጎሎች የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ደረጃ እየመራ ይገኛል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርጉት በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ሶስት ጎሎችን ማስቆጠር ከቻለ በዮርዳኖስ አባይ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን በአንድ ጎል ማሻሻል ይችላል። 

በፕሪሚየር ሊጉ ወልድያ ከታች ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ ሆነው ማጠናቀቃቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሲሆኑ ደደቢት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን ተረጋግቶ መያዝ ችሏል። የውድድር ዓመቱ ክስተት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሲዳማ ቡና በመጨረሻም በተከታታይ ሽንፈቶችን በማስተናገድ ከወራት በፊት ይዞት በነበረው 38 ነጥብ ላይ ተረጋግቶ መቀመጥ ችሏል። በያዘው ነጥብ ላይ ለረጅም ሳምንታት ረግቶ በመቀመጥ ሲዳማ ቡና የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል። 

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
jossy sanjaw [967 days ago.]
 s.t george is a real champions viva sanjaw

Babi [967 days ago.]
 በጣም እኮ ነው የሚገርመው ቢኒያም አሰፋ ስንት ዓመቱ ነው ? ለብሄራዊ ብድን የተመረጠው በወጌሻነት ነው እንዴ ? እነ አዳነ ግርማ ገና ብዙ ነገር ለለብሄራዊ ብድናችን መስራት እየቻሉ ለወጣቶች ቦታቸውን ሲለቁ ቢኒያም ደግሞ ኮች በመሆኛው ሰዓት ናሽናል ቲም መጠራቱ ይገርማል ይደንቃልም ሃሃሃሃሃ ! አይ ኮች ዮሃንስ ገና ከጅምሩ አስቂኝ የተጫዋቾች ምርጫ መርጠህ አስደምመኸናል አስቀኸናል፥፥ መመረጥ የሚገባቸው ሃገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁለቱ ምርጥ የአማካይ ተካላካዮች ተስፋዬ አለባቸው እና ናቲን መዝለልህ የስፖርት ቤተሰቡን ማነጋገሩን ቀጥሏል ገና ወደፊት ብዙ የሚያስቁ ነገሮች ሰርተህ ስፖርት ቤተሰቡን ዘና ፈታ የምታደርገው ይመስለኛል

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!