አሸናፊዎቹ እና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ -ክፍል ሶስት-
ግንቦት 20, 2007

ይርጋ አበበ እና ፈለቀ ደምሴ 

ባለፉት ሁለት ዝግጅቶቻችን የ2007 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠውን ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በተመለከተ ተከታታይ ጽሁፎችን ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው ዝግጅታችን ከደጋፊዎቹ እና ከክለቡ የቡድን መሪዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ የምናቀርብ ይሆናል። 

ዘሪሁንና ፋሲል አደራ ተወጥተዋል

ያሬድ ወልደሚካኤል ይባላል። እድሜው ገና ወጣት ሲሆን ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ በመከታተል ድጋፉን ከመስጠት ወደ ኋላ እንደማይል ይናገራል። እኛም ያገኘነው ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ 12ኛውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ማንሳቱን ባረጋገጠ ማግስት በክለቡ መለማመጃ ሜዳ ልምምድ እየተመለከተ ነበር። 
StGeorge fan

በዚህ ዓመት የክለቡን ጉዞ በተመለከተ የተሰማውን እንዲነግረን ጠይቀነው “በዚህ ዓመት ክለባችን በብዙ መልኩ የተፈተነበትና ፈተናዎቹንም በጽናት የተወጣበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል። ያነሳነው የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫም ለእኛ ለደጋፊዎቹም ሆነ በአጠቃላይ ለክለቡ ቤተሰብ ልዩ ነው ማለት እችላለሁ” ብሏል። ምክንያቱን ሲናገርም 80ኛ ዓመቱን እያከበረ ባለበት ሰዓት ዋንጫው ስጦታ እንደሆነ ተናግሯል። 

ፈረሰኞቹ ፕሪሚየር ሊጉ አጀማመራቸው ጥሩ ባለመሆኑ በርካታ የስፖርት ተከታታይ ዋንጫውን ላያነሳ ይችላል ተብሎ የተሰጋ ቢሆንም ደጋፊው ያሬድ ግን “ዋንጫውን እናጣለን ብዬ አልሰጋሁም” ይላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ክለቡ ችግር ሲገጥመው በራሱ መንገድ ችግሮቹን የሚፈታበት መንገዱ ለድል እንደሚያበቃው እርግጠኛ ሆኗል ብሎ ያምናል። “በዚህ ዓመት ለእኛ ፈታኝ የሆነ ክለብ አልነበረም” የሚለው ያሬድ ወልደሚካኤል ሲዳማ ቡና ካለፉት ዓመታት ይልቅ የተሻለ ሆኖ መቅረቡን ይናገራል። የክለቡ ኮከብ ማን ይሆናል ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ “በግል ሁለት ተጫዋቾችን ልመርጥ እገደዳለሁ። የክንፍ አማካዩን በሀይሉ አሰፋን እና ወጣቱን የግራ መስመር ተከላካይ ዘካሪያስ ቱጅን። ነገር ግን ኮከብ ተጫዋች ሊሆን የሚገባው አንድ ብቻ ስለሆነ በሀይሉ አሰፋን እመርጣለሁ” ብሏል። 

በመጨረሻም “አሰልጣኞቻችን ዘሪሁን ሸንገታ እና ፋሲል ተካልኝ በክለባችን ውስጥ እንደነገሱ ይኖራሉ። አሰልጣኞቹ እድሉን ሲያገኙ ምን ማድረግ እንደሚችሉ አሳይተዋል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል። 

43 ዓመታትን ከፈረሰኞቹ ጋር
StGeorge fan


አንጋፋው ደጋፊ አቶ መርሻ ገብረ መስቀል በአዲስ አበባ ስታዲየም ክቡር ትሪቡን ተቀምጠው ክለባቸውን ሲደግፉ ይታወቃሉ። አንጋፋው ደጋፊ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለ43 ዓመታት እንደደገፉ ይናገራሉ። ስታዲየም ገብተው መደገፍ በቂ ሆኖ ያላገኙት አቶ መርሻ ክለባቸውን በልምምድ ሜዳ ድረስ በመሄድ ይከታተላሉ። በክለቡ የመለማመጃ ሜዳ ተገኝተን ላቀረብንላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። 

“በሀይሉ አሰፋ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ሆኖ ይጨርሳል ብዬ አስባለሁ” የሚሉት አቶ መርሻ “የሊጉን ዋንጫ ማንሳታችን ለ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ድምቀት ይሆናል። የጥሎ ማለፍ ዋንጫውንም ማንሳት ይችላል። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድርም ጥሩ ተወዳዳሪ ይሆናል” ሲሉ ክለቡ 12ኛውን የሊግ ዋንጫ በማንሳቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። 

የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ቃል
St.George Technical Director At0 Efrem
አቶ ኤፍሬም ግዛቸው በበኩላቸው “በመጀመሪያው ዙር አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አልነበርንም። በሁለተኛው ዙር ለተገኘው ውጤት ፋሲል እና ዘሪሁን ቀጥተኛ ተመስጋኝ ናቸው” ብለዋል። አቶ ኤፍሬም ብራዚላዊውን አሰልጣኝ ማሰናበት ቦርዱ የወሰደውን እርምጃ “የሚደነቅና ወቅቱን የጠበቀ ነው” ብለዋል። በተለይ በወጣቶቹ አሰልጣኞች ላይ ቦርዱ እምነት ማሳደሩ የሚደነቅ እንደሆነ ይናገራሉ። ለአሰልጣኝ ዶ ሳንቶስ ስንብት ምክንያቱ ምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ኤፍሬም ሲመልሱ “ብዙ ጊዜ የውጭ አገር አሰልጣኞች ወደ አገራችን ሲመጡ ከተጫዋቾች ጋር በተለይ በፕሮፌሽናሊዝም ዙሪያ መግባባት ይከብዳቸዋል። ዶ ሳንቶስን የገጠማቸውም ይህ ነው። እነ ፋሲል ቡድኑን ሲረከቡም በቡድኑ ላይ የሰሩት ትልቅ ስራ የተጫዋቾች አያያዝ ላይ ነው” ብለዋል።  “ቡድኑ እንደ ቡድን በአንድ ላይ ተቀናጅቶ የሰራ ቢሆንም በተወሰነ መልኩ “በሀይሉ አሰፋ የዓመቱ ኮከብ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። አቶ ኤፍሬም አያይዞም በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ ሁሉም ክለቦች ለፈረሰኞቹ ፈታኝ ናቸው ነገር ግን በተለይ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ክለብ የዘወትር ተቀናቃኛቸው ሲሆን ጥሩ ባልሆነበት ጊዜም እንኳን ለፈረሰኞቹ ፈታኝ ነው ይላሉ። 
 
የቡድን መሪው ቃል

አቶ ታፈሰ በቀለ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የቦርድ አባል እና የክለቡ የቡድን መሪ ናቸው። “ክለባችን ለዲሲፕሊን ቅድሚያ ይሰጣል” የሚሉት አቶ ታፈሰ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቃለ ምልልስ አድርግዋል። “በዓመቱ የዘካሪያስ ቱጂ ብቃት አስደምሞኛል” በማለት የሚናገሩት አቶ ታፈሰ በቀለ “ፕሪሚየር ሊጉ አጀማማራችን ላይ የነበረውን ደካማ ቢሆንም በተለይ ከባንክ እና ከመብራት ኃይል ጋር የምናደርጋቸው ጨዋታዎችን በድል ከተወጣን ዋንጫውን ማንሳት እንደምንችል እርግጠኛ ነበርኩ። ሁለቱን ቡድኖች ቡድኖች በድል ስናሸንፍ ዋንጫውን እንደምናነሳ ተስፋ አደረኩ” ብለዋል። 

የዓመቱ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ማን ሊሆን ይችላል? ተብለው የተጠየቁት አቶ ታፈሰ “በዚህ ዓመት ከሁሉም ክለቦች ጋር የተደረጉ ጨዋታዎችን በሙሉ አንድም ሳያልፈኝ ተከታትያለሁ። እውነት ለመናገር ከበሀይሉ አሰፋ የተሻለ ዓመቱን ሙሉ በሙሉ ብቃት ያሳለፈ ተጫዋች አላየሁም። ለክለባችን የውጤታችን መሰረትም እሱ ነበር” በማለት የክለባቸው የመስመር ተጫዋች የዓመቱ ኮከብ ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል። 

አቶ ታፈሰ “ሁሉም የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ምንጊዜም ፈታኞቻችን ናቸው” ያሉ ሲሆን ነገር ግን ሁሉም የሊጉ ክለቦች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወቱ የሚያሳዩትን ብቃት በቀጣዮቹ ጨዋታዎቻቸው መድገም አይችሉም” ሲሉ በዚህ ዓመት በተለየ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበ ክለብ እንደሌለ ተናግረዋል። 

አበባው ቡጣቆ ወደ ሱዳን ሊግ በመጓዙ በቦታው ተተኪ ይሆናል ተብሎ የተገዛው መሃሪ መና ነበር። ነገር ግን ከተስፋ ቡድን ያደገው ዘካሪያስ ቱጂ የአበባውን ቦታ ሲሸፍን ነው የታየው። ይህንን እንዴት አዩት? ተብለው የተጠየቁት አቶ ታፈሰ “አበባው እንደሚሄድ እናውቅ ነበር። ለዚህም ነው መሃሪ መናን የገዛነው። ነገር ግን ከሁለት ጨዋታ በኋላ ዘካሪያስ ያሳየውን ብቃት ስንመለከተ ወደ ተቀያሪ ወንበር ማውረድ ተገቢ እንዳልሆነ አመንን። እሱም በሚገባ ቦታውን ሸፍኖ በመጫወቱ መሃሪን ወደ ተቀያሪ እንዲሆን አስገድዶታል። ዘካሪያስ የአሁኑን ብቃቱን ጠብቆ መጫወትም አለበት” ብለዋል። 

ቡድኑ ውስጥ ያለውን የካምፕ ሰላም በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በዲሲፕሊን ጉዳይ አንደራደርም” ያሉ ሲሆን በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጋር ሲጫወት ምንያህል ተሾመ በወላይታ ድቻው ተከላካይ እሸቱ መና ላይ ያልተገባ ድርጊት በመፈጸሙ ፌዴሬሽኑ አራት ሺህ ብር እና ስድስት ጨዋታ ሲቀጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ተጨማሪ አምስት ሺህ ብር መቅጣቱን ያወሳሉ። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Mule [1000 days ago.]
 Tnx Ethio sport ይርጋ አበበ እና ፈለቀ ደምሴ ! nice and farir zegebba ! Mengizem Giyorgis !

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!