የስቴዲየሙ ጉዳይ ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም ብዙ ጊዜም ፈጅቷል። በሚቀጥለው አመት አካዳሚውን ጨርሰን በሙሉ ሐይላችን እንረባረብበታለን።
ግንቦት 21, 2007


አሸናፊዎቹ እና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ -ክፍል አራት- 

ፈለቀ ደምሴ እና ይርጋ አበበ

ባለፉት ሶስት ዝግጅቶቻችን የ2007 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠውን ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብን በተመለከተ ተከታታይ ጽሑፎችን ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው የማጠቃለያ ዝግጅታችን ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮ ፉትቦል ዘጋቢዎች ፈለቀ ደምሴ እና ይርጋ አበበ ከቅዱስ ጊዮዮርጊስ ስፖርት ክለብ ፕሬዚደንት ከሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀል ጋር ያደረጉትን  ቃለ መጠይቅ ፈለቀ ደምሴ እንዳቀናበረው ይዘን ቀርበናል። ቃለመጠይቁ  ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ስለሚገኝበት የወቅቱ ሁኔታ፣ የውስጥ አሰራር፣ የወደፊት እቅዶቹና ስጋቶቹ፣ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፣ ስለ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ዝውውር፣ የተጫዋቾች ክፍያ፣ በካፍ አመራር ኢትዮጵያ ስለአላት ሚና፣ እንዲሁም በርከት ያሉ ሌሎች ጉዳዮችን ያካተተ ነው። አንባቢዎቻችን በጥሞና እንድታነቡት በትህትና እንጋብዛለን።  

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡-  የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለ12ኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን በመሆኑ ምን ተሰማዎት?

StGeorge Sport Club President Ato Abinet Gebremeskel

አቶ አብነት፡- 80ኛ አመት የምስረታ በአላችን በምናከብርበት ወቅት በሴቶቹም በታዳጊዎችም በተለይ ደግሞ በዋናው ቡድን ጥሩ ውጤት እንድናገኝ ከአመራር ጀምሮ ከላይ እስከታች ሌት ተቀን እየሰራን ባደረግነው ጥረት ያገኘነው ድል ስለሆነ በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ።


ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡-  አሰልጣኝ ዶሳንቶሰን ካሰናበታችሁ በኋላ ቡድኑ የተገነባው በወጣቶቹ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ ላይ  ነበር እምነቱን የጣላችሁት እርስዎ እንደነገሩን ለ8ዐኛ አመት ክብረ በአላችሁ ማድመቂያ ዋንጫውን የምትፈልጉት ከሆነ እውን በነዚህ አሰልጣኞች ውጤቱ ይመጣል ብላችሁ ጠብቃችሁ ነበር?


አቶ አብነት፡- እምነት ባይኖረን ኖሮ አንዲት ምሽት እንኳን አናመሽም ነበር። በዛውን ወቅት ብቃት ያላቸው የውጪ አሰልጣኞች አምጥተን ለሚቀጥለው አመት ጨዋታውን እየተከታተሉ ለአፍሪካ ሻምፒዮን ሊግ እንዲያዘጋጁት አድርገን ነበር። ሆኖም ሁለቱ ወጣት አሰልጣኞች ይኸንን ቡድን ይዘው ቢጓዙ ዋንጫውን እንደሚያነሱ ሙሉ እምነት ስለነበረን ሃላፊነቱን ሰጠናቸው። ሃላፊነቱን ስንሰጣቸው የነገርናቸው ነገር ቢኖር  የመጡት አሰልጣኞች ቡድኑን እየገመገሙ እንዲቆዩ ነው። እናንተ ግን ሙሉ ብቃት አላችሁ የሚያስፈልጋችሁ አንድነትና ፍቅር ብቻ ነው።  ከናንተ በላይ ለዚህ ቡድን የቆሰለ የደማ እና የተጫወተ የለም። ስለዚህ ያሉንም ተጫዎቾች ምርጥ ምርጥ ስለሆኑ በሙሉ እምነት  በማሳደር ነው ሐላፊነቱን የሰጠናችሁ ነው ያልናቸው።


ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡-  የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ለ8ዐ አመት በተለያዩ አመራሮች የሽግግር ለውጥ አካሂዷል ቢሆንም ውጤቱን ጠብቆ የመሄዱ ሚስጢር ምንድነው?


አቶ አብነት፡- በአመራር ላይ የነበሩት ሰዎች በጠቅላላ በፍቅር የሚሰሩ እና እንደወርቅ ተፈትነው ያለፉ ብቃት ያላቸው ሲሆኑ ብዙ ትግል ብዙ መከራ ያዩ ናቸው። እኔም እንደነሱ ብዙ ችግር እና መከራ አይቸበታለሁ። ግን አላለቅስም በየሚዲያው መግለጫ አልሰጥም ችግሬን እየታገልኩ ከአጋሮቼ ጋር በመሆን እወጣዋለሁ ጊዮርጊስ የሚጫወተው 14 ቡድን ካለ ለሁሉም ቡድን ዋና ዋና ወሳኝ ግጥሚያው ከኛ ጋር ነው። ለኛ ግን እያንዳንዱ ግጥሚያ የሞት ሽረት ጦርነት ማለት ነው። ይህ ለተጫዋቾቻችን ትግልና ፈተና ነው። አንድ ተጫዋች ሌላ ክለብ ኮከብ የነበረው እኛ ጋ ሲመጣ ለመታየት ጊዜ ይፈጅበታል ፈጽሞ ላይታይም ይችላል። በእያንዳንዱ ጨዋታ ሲፈተን ነጥሮ ለመውጣት ይከብደዋል። ይህ ብቻ  አይደለም እኛ በሜዳም ሆነ በፌደሬሽንም ሆነ በሁሉም አቅጣጫ አመቱን በሙሉ ያለችግር የሚገጥመን ነገር የለም። እንደሌሎች በአመት አንድና ሁለት ችግር ደረሰብን ብለን አንጮህም። በሥራ እና በትግል ነው የምንወጣው ይህ ደግሞ የመጣው ጊዮርጊስን የሚመሩት አመራሮች እግር ኳሱን የሚያውቁ እና በእውቀት የሚመሩ በመሆናቸው እና የሊደር ሽኘ ኳሊቲው የተሟላ በመሆኑ ነው። እኛ ታሪክ ያስተማረን የብቃትና የትግል አካሄድ አለን ተጫዋቾቻችን ጭንቅላታቸው እግራቸው አይናቸው በአንድ ላይ እንዲሰራ እንፈልጋለን። በትምርት ቤት ያላገኙት ካለ እንኳን እዚህ እንዲያገኙ ይደረጋል። የሚጠቀም ይጠቀምበታል። ባጠቃላይ ጊዮርጊስ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚሰራበት የሕዝብ ክለብ በመሆኑ ከምስረታው አንስቶ ችግር እና መከራዎችን በማለፍ ለዚህ በቅቷል።


ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- እርስዎ በቅዱስ ጊዮርጊስ እንደማይደራደሩ እና ወሳኝ እና ትላልቅ ስራዎችዎንም ትተው ቢሆን የቡድኑን ውጤት እንደሚከታተሉ ይነገራል ይህ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምንድነው?


አቶ አብነት፡- አንደኛ ፍላጐት ሁለተኛ ሐላፊነት ሰአት አይገድበውም ከእንቅልፍም ተነስቼ የታወሰኝ ነገር ካለ  ለስብሰባ እንዲቀርብና መፍትሄ እንዲያገኝ በመጻፍ በነጋታው ውሳኔ እንዲያገኝ እጥራለሁ። ይህ ለኛ እንደ ፉልታይም ስራ ነው የሚታየው። ለሰው ሰጥተህ ብቻ የምትተወው አይደለም። ቦርዱም ተጫዋቾችም በሙሉ የሕዝብ ሐላፊነት አለብን። ዝም ብሎ ደሞዝ ተቀብሎ መተኛት አይቻልም እኛ ጋ አንድ ተጫዋች አመመኝ ብሎ መቅረት የለም። የምንፈልግበት ሐኪም ቤት ልከነው እንዲድን እንጥራለን። አሞኛል ብሎ ቤቱ መተኛት አይቻልም።  ሜዳ ላይ ያንን ሁሉ እየተቆጣጠርን እከሌ ታመመ ከተባለ በምን ምክንያት ታመመ ምን ትሪትመት ተደረገለት የትኛው ዶክተር አየው እግሩን ከተመታ ከአንገት በላይ ሐኪም መሄድ መዋሸት አይቻልም ይህንን ሁሉ እንቆጣጠራለን። ለዚህም በየደረጃው ሐላፊዎች አሉን እኛም እነሱን እየተከታተልን እንቆጣጠራለን ። ስለዚህ ከላይ እስከታች እንደዋወላለን እኔ ከኢትዮጵያ ውጭ ሆኜ እንኳን አራት እና አምስቴ ከደወልኩ ለቤቴ አንዴ ብቻ ነው የምደውለው እንዴት ናችሁ እና ሰላም እደሩ ነው። የተቀረው ግን ትሬሊንጉ እንዴት አለቀ ከሰአት ስብሰባ ካለ እንዴት አደረጋችሁ  እያልኩ እናወራለን የታየኝ ነገር ካለ ደግሞ ደውዬ ሀሳብ እሰጣለሁ ስለደጋፊውም አይቀረንም። ስለዲሲፒሊኑ ጉዞ ካለ ስለጉዞ ስለሁሉም ነገር እናነሳለን ጊዮርጊስን ማስተዳደር የሙሉ ጊዜ ሥራ ነው። አንድ ድርጅትን መምራት  እና ቅዱስ ጊዩርጊስ ስፖርት ክለብን መምራት እጅጉን ይለያያል። አይወዳደርም። ከብሔራዊ ቡድን በላይ እንኳን እጅጉን አስቸጋሪ መሆኑን ደፍሬ መናገር የምችለው ነው።


ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነበረበት ድርጅት ወደ ሕዝብ ከመጣ በኋላ በቦርድ እንደሚተዳደር ይታወቃል። አብዛኛውን ጊዜ ከቦርድ አባላት የእርስዎ እና የአቶ ንዋይ ሚና ነው ጐልቶ የሚታየው ይባላል። ከዚህ አስተያየት አንጻር የሌሎች ቦርድ አባላትን ሚና እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አብነት፡-  የቦርድ አባላት ሳያውቁት ምንም ነገር አይወሰንም። እኔ እና ንዋይ ኘሬዚዳንት እና ፀሐፊ ስለሆንን የእለት ተእለት ስራዎችን ስለምንሰራ ነው እንጂ ማንኛውም ውሳኔ ለቦርድ ቀርቦ ተጨቃጭቀን የማንስማማበት ጊዜ ሁሉ አለ። ካላያችሁ ልታውቁት አትችሉም።  አብዛኛውን ጊዜ በድምጽ ነው የምንለያየው። እኔ ባለኝ የሰብሳቢነት ስልጣን እንኳን ተጠቅሜ አላውቅም። ለመስማማት እና ለመረዳዳት የምናጠፋው ጊዜ ከ3 ሰዓት ይበልጣል። አንዳንዴ በጣም አስቸኳይ ጉዳይ ከመጣ ቢያንስ 4 የቦርድ አባላት እና ከቴክኒክ ዳይሬክተሩ ጋር ሆነን ተወያይተን እንወስናለን እንጂ ዝም ብዬ እኔ ተነስቼ የምወስንበት አይደለም አሰራራችንም ለዚህ የተመቻቸ አይደለም። ዲስፒሊን ደግሞ ከኛ አመራሮቹ ከሌለ እና እኛ ካልተግባባን ወደታች ሊወርድ አይችልም።

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡-የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በክልልም ሆነ ከሀገር ውጪም እየወጡ ክለባቸውን ይደግፋሉ በዚህ ጠንካራ ናቸው። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የመበታተን እና የመነጣጠል ሁኔታ ይታያል በተወሰኑ ደጋፊዎችም የዲስኘሊን ግድፈት አለ። እዚህ ላይ በናንተ በኩል ምን ለመስራት አቅዳችኋል?

አቶ አብነት፡- ምን መሰህ ደጋፊ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቶት ክለቤ ነው ብሎ መምጣት አለበት። ደጋፊው ለኛ አንድ ነው። የሚከፋፍለው ነገርም እንደሚፈጠርም አንፈልግም። እንደክለብ አመራር ግን ይህ በርካታ  ደጋፊ ያለው ክለብ ነው። ይህን ሁሉ ደጋፊ አንድ ገጽታ አለው ለማለት ያስቸግራል። አንዱ የሚያደራጀው ከሌሎቹ ጋር ጠጋ ሲል ላይስማማ ይችላል ይህም ባልተረጋገጠ ወሬ በሐሜት በተለያዩ ምክንያት ወዳጅነት ሊሸረሸር ይችላል። እኛ እያንዳንዱን ነገር ውስጥ ልንገባ አንችልም። ችግሩም የሚመጣው ሁሉ ነገር ውስጥ ልግባ ስትል ነው። ደጋፊው ነፃ ሆኖ በራሱ መንገድ እንዲደግፍ ነው የምንፈልገው። በየክልሉ ሲሄድ የትራንስፖርት አውቶብሶችን እናዘጋጃለን ደጋፊ ሲመጣ ግን ለቦርዱ ወይም ለኔ ወይም ለአንድ ተጫዋች ብሎ ሳይሆን ክለቡን እና ማሊያውን ብሎ ነው መምጣት ያለበት። ክለቡ ሲወርድ ለምን ወረደ ሲነሳ  ጥሩ ነው ስህተቶች ካሉ ስህተቶችን ማረም ነው።  እኔ በደጋፊዎቻችን በጣም ነው የምኮራው በርካታ ደጋፊዎች ያላቸው ክለቦችን እያየን ነው። ብዙ ችግሮች አለባቸው እኛ ግን የራሳችን ደካማ  የሆኑ ጉድለቶች ማረም ይገባናል። አንዳንዱ ትኩስ ሐይል ነው። አንዳንዱ ደግሞ ቀዝቀዝ ያለ ነው። ግን ሁሉም መደማመጥ አለበት። ማጥፋት ያለብን ጉዳይ ቢኖር ብልግናን ነው። ርካሽ ስድብን ነው። ይሄ መጥፋት አለበት እኛን አይመለከትም ጊዮርጊስን አይወክልም። ምንአልባት ከሌላ የመጣ ተላላፊ በሽታ ገብቶብን ከሆነ እሱን ማጥፋት አለብን እንጂ ስድብ የቅዱስ ጊዮርጊስ መገለጫ አይደለም። ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ በጨዋታዎች የተመሰረተ እና እዚህ የደረሰ ክለብ ነው። ክለባችን አባል ሆኖ አርማውን ይዞ ክለቡን የሚያሰድብ ደረጃውን ያልጠበቀ አደጋገፍ የሚሰጠውን ግን ሐላፊነት ስላለብን እርምጃ እንወስዳለን። በዚህ ላይ ብዙ ሰርተናል ባለፈው 1ዐ እና 15 አመታት ደክመናል ደጋፊዎቻችንም  አያሳፉሩንም እርስ በርሳቸውም ይማማራሉ።

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- በደብረዘይት ከተማ ትልቅ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ  ተቋም በማሰራት እያጠናቀቃችሁ  ነው። የተጀመረውን የስቴዲየም ግንባታ ለማፋጠን ምን እየሰራችሁ ነው የአካዳሚውስ አላማ እና ግብ ምንድነው?

አቶ አብነት፡-የስቴዲየሙ ጉዳይ ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም ብዙ ጊዜም ፈጅቷል። እናቃለን በፊትም ቃል እንደተገባው ሳይገነባ የሚቀር አይደለም። በሚቀጥለው አመት ይሄን አካዳሚ ጨርሰን በሙሉ ሐይላችን  እንረባረብበታለን። በሚቀጥለው የልማት እቅዳችንም ሆነ ስራችን እሱ ነው።    አካዳሚውን በተመለከተ በዚህ አንድ ሁለት አመት ውስጥ የተሰራው ሥራ ቀላል አይደለም ይህ አካዳሚ ሲያልቅ  6ዐ ሚሊየን ብር ሊያወጣ ይችላል። የዶርም እቃዎቹ የተሟሉ ናቸው ሜዳው የሳሩ ንጣፍ  የጂሙ ኳሊቲ የመመገቢያ ቦታው የመፀዳጃው የጫማ ሎከር ክፍሎች ለየብቻ ናቸው። መኝታ ቤት የሚገቡት በነጠላ ጫማ ብቻ ነው። ስፔሻል ቬንትሌሽን ሲስተም የገባለትም አለ ከጽዳት ጋር የተያያዙ ነገሮች ተሟልተዋል። ሰልጣኞቹ ትምህርት ቤት ውለው ሲመጡ ኳስ ብቻ አይደለም ራሳቸውን ዘና የሚያደርጉበት ጌም ሩም አላቸው። የክልሉ መንግስት የሰራነውን አይቶ ከጐኑ ያለውን መሬት ጨምሮ ከሰጠን ደግሞ ለአሰልጣኞቹ እና ለሰልጣኞቹ ተጨማሪ መኖሪያ ቤት መስሪያ እና አንድ ቴኒስ እና ባስኬት ቦል መጫወቻዎችን ለመስራት እቅድ አለን። አንድ ተጫዋች በኳስ ብቻ አይደለም ማደግ ያለበት በአትሌቲክስ ጭምር ማደግ አለበት። በተለያዩ የስፖርት ሙያዎች መሰልጠን አለበት። መንግስቱ ወርቁን እንደምሳሌ ብናነሳው ፈጣን ሯጭ ነበር። ቫሊቮል ላይ በጣም ጐበዝ ነበር። እንደዚህ በመሆኑ የእግር ኳስ ሕይወቱ የተሳካ ነበር። የዓለማችን ምርጥ ተጫዋች የነበረው ፔሌ ብላክ ቤልት ነበረው። በካራቴም ጐበዝ ነበር። እና የኛ ልጆች ግን ኳስ ላይ ብቻ እንዲያተኮሩ ነው የሚደረገው። በተለያዩ ስፖርቶች ጭምር ታንፀው ቢያድጉ እና ከአሰልጣኞቻቸው ጋር መግባባት ከቻሉ ጥሩ ውጤት እናመጣለን። ሌላው አለም ላይ ያለውን ነገር አገራችን ላይ ለመፍጠር እየሞከርን ነው። እያየን ያለነው አንድ ክለብ የውጪ እገዛ እና ድጋፍ ሳይኖረው የስፖርት አካዳሚ የሰራነው። ምን አልባት ከአፍኛሪካ ውስጥ እኛ ብቻ ልንሆን እንችላለን። አውቃለሁ ግብፅ ትላልቅ አካዳሚዎች አሉ እያንዳንዱ አካዳሚ ግን ከሌላ አገር ክለቦች በሚደረግ ስምምነት እና ድጋፍ ወይም በመንግስት ወይም በትላልቅ ኩባንያዎች እገዛን ያገኛል። እኛ ግን በራሳችን ጥረት ጀምረን  ነው የሰራነው ወደፊት ደግሞ እየተጠናቀቀ ሲመጣ ከበቂው ማስረጃ ጋር እንሰጣችኋለን።

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- ስለአካዳሚው እርስዎ ቀድመው በሚገባ አብራርተውልናል። አካዳሚው ስራ ሲጀምር የሌሎችም ሀገራት አካዳሚዎች እንደሚያደርጉት በስፖርቱ በዓለም ላይ የነገሱ ባለሙያዎችን በማስጐብኘት ለሰልጣኞቹ ተሞክሮዋቸውን እንዲያካፍሉና እንዲያስተምሩ እቅድ አላችሁ? ሰልጣኞችስ ስልጠናውን ሲጨርሱ እዴት ነው ወደየክለቡ የሚከፋፈሉት?

አቶ አብነት፡- አሁን ዝርዝር ውስጥ አልገባም። የዚህ አካዳሚ ዳሬክተር አድርገን የሾምነው የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ወንድም  ሲሆን  ከሱ ጀምሮ ሌሎች የሚያውቃቸው ትላልቅ የስፖርት ሰዎች ስላሉ እነሱን እነሱን እያመጣ ለአንድ ቀንም ቢሆን ለተጨዋቾቹ የነሱን ፈለግ እንዲከተሉ እና ራእይ እንዲኖራቸው እንፈልጋለን። ይህንን  ሲደርስ ነው የምናየው ። ይህ አካዳሚ ሲጀምር 1ዐዐ ሰልጣኞች ነው የሚይዘው ይህ ሁሉ ለጊዮርጊስ አይደለም ለሌሎች እና ለብሔራዊ ቡድንም የሚጠቅም ይሆናል ምናልባት ጊዮርጊስ 5 እና 6 ተጫዋቾች ቢወስድ ሌሎቹ በየክልሉ ሄደው የሚያገለግሉ ይሆናል። የዛን ጊዜ ክለቦች ለተጫዋቾች ይከፍላሉ ልጆች መጠቀም አለባቸው ያኔ ለተጫዋች የፊርማ ክፍያ 1ዐ ሺ ብር በመክፈል ስንጀምር ብዙ ብዙ ተብሎ ነበር ዛሬ ተጨዋቾች ከሀገር የማይኮብልሉበት ዋናው ምክንያት በቂ ክፍያ ስለሚያገኙ እና የተሻለ ኑሮ ስላላቸው ነው። ሰይፈ  የሚባል የመብራት ሐይል ተጫዋች 1ዐሺ ብር  በከፈልንበት ጊዜ ተቃውሞ ደርሶብን ነበር በሚዲያ ሳይቀር ዛሬ ለአንድ ተጫዋች አንድ ሚሊየን እና ከዛ በላይ እየተከፈለ ነው። እኔ በበኩሌ እግር ኳስ በዓለም ላይ ከገንዘብ ጋር ተያይዟል እና አንድ ተጫዋች በሚገባ ተከፍሎት ሲሰራ ይነቃቃል። ቤተሰቡን ያግዛል  ተረጋግቶ ይሰራል እና እኔ በዚህ ምንም ተቃውሞ የለኝም። የእግር ኳስ ተጫዋች ሌላው ዓለም ላይ የተከበረ እና በችሎታቸው በላቡ የፈለገውን ጠይቆ ያገኛል። ይህ መብቱ ነው። ሌላ ሰው ሊወስንለት አይችልም እና ግን እራሳችን ለመወሰን እና ተጫዎችን ለመገደብ ካሰብን አደጋ አለው። ደግሞም ብንወስንበት እንኳን ከክለቦች ጋር በመስማማት ወደ ደሞዝ ሊቀየር ይችላል ይህ ደግሞ ሌላ ችግር መፍጠር ነው። ከዚህ ይልቅ የአገራችን እግር ኳስ ለማሳደግ ችግሮቻችን ላይ መስራት ነው። የቢ እና የሲ ቡድን ተጫዋች ዛሬ ብታይ ከቀኑ 6 እና 7 ሰዓት ይጫወታሉ። በጠራራ ፀሐይ ይህ በጣም ስህተት ነው። ይህን በጥሞና ማየት ነው። ለመሆኑ ማነው ከቀኑ በ7 ሰዓት በጠራራ ፀሐይ 1ዐ እና 2ዐ ደቂቃ መሄድ የሚችለው። ሌላው ታዳጊ ቡድን ቢበዛ 15 አመቱ ከሆነ ለመሆኑ ትምህርት የለውም እንዴ በስራ ቀን በጠራራ ፀሐይ የሚጫወተው። ምሳሌ ልስጥህ ትናንትና የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን ከኢትዮጵያ ቡና ወጣት ቡድን ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ተጫውቷል አይደለም ዝናብ ነው። ከዛ ዋናው ቡድናችን እዛው ሜዳ ላይ ተጫውቷል። ዛሬ ጠዋት የሴቶች ቡድን እየተጫወቱበት ነው። ሁለት የኘሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በቀጣይ ያካሂዳል አንድ ሜዳ ይህ ሁሉ ውድድር ሲደረግበት ለመሆኑ ሳሩስ ይችላል ወይስ በኮንክሪት ነው የተሰራው። ይልቅ የዚህን እና ወሳኝ የሆኑ መፍትሄዎችን ነው መፈለግ ያለበት። 

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወጥና ተከታታይ የሆነ አስተዳደር የለውም አንዱ ይመጣል ሌላው ይሄዳል አንዱ የሰራውን ሌላው ሲያስቀጥለው አይታይም። ወጥና ተከታታይ የሆነ አስተዳደር እንዲኖር ምን ቢደረግ ይሻላል ይላሉ?

አቶ አብነት፡- ይህ በኔ ሀሳብ ብቻ የሚፈታ አይደለም እንዲህ ነው እንዲያ ነው ልልህ አልችልም።

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- በቅርቡ ለአንድ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ በ1ዐ ዓመት ውስጥ የውጭ ተጫቾችን ግዥ ልናስቀር እንችላለን ብለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በያዘው እቅድ ይሄንን ማሳካት ይችላል?

አቶ አብነት፡- ይቻላል ኢትዮጵያ ውስጥ  ከ90 ከሚሊዮን ሕዝብ በላይ ነው ያለው ከተሰራ ይቻላል፡፡ ከችግሮቹ ዋናው ችግር የእግር ኳስ በቂ ሜዳ የለም። አንድ ትልቅ እሰቴዲየም ከመገንባት 10 ትንንሽ ሜዳዎች ቢሰሩ በየሜዳዎቹ በርካታ ተጨዋቾችን ማፍራት ይቻላል፡፡ ቦታ ሲገኝ ኮንደሚኒየም  እንደሚሰራው ሁሉ የእግር ኳስ ሜዳዎችም ጎን ለጎን ቢሰሩ በርካታ ተጨዋቾችን ማፍራት ይቻላል፡፡ ውድድሩም ቢሆን በአንድ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ውድድሮች ቢዘጋጁ መልካም ነው፡፡ በውጭ ሀገራት በተለያዩ ኩባንያዎች እገዛ ውድድሮች ይካሄዳሉ ለምሳሌ የኮካኮላ እና የቶታልን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ የተለያዩ ውድድሮች ውስጥ የሚወዳደሩ ቡድኖች እንዲኖሩ አቅማችንን እያሳደግን ክለቦቻችንም ከእነዚህ ውድድሮች ተጨዋቾችን እየመለመሉ ሊጠቀሙ ይችላሉ። እኛ አካዳሚ ስለገነባን ብቻ ይሳካል ማለት አይደለም። ልጆቹ ከኛ ወጥተው በተለያዩ ውድድሮች ውስጥ እንደአቅማቸው መወዳደር አለባቸው ያለበለዚያ ግን ስልጠናውን የወሰዱ ልጆች የሚረከባቸው ካጡ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ዋናው ችግራችን እንደነገርኩህ የሜዳዎች እና የውድድሮች ማነስ ነው፡ ለዚህ ነው ተተኪ ተጨዋቾች እየጠፉ ረጅም ዓመት የተጫወቱ ተጨዋቾች ከክለብ ክለብ የመዘዋወራቸው ዋናው ምክንያት ይሄ ነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡-  ሆላንዳዊው የቅዱስ ጊዮጊርስ አሰልጣኝ ማርቲን . ኩፕማን አርሰናል፣ ቼልሲን ማንችስተር ሲቲን የማሰልጠን ብቃት እንዳላቸው ቀደም ብለው አርስዎ ከአንድ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። በሀገራችን የሊግ ደረጃ የሰውየው የሥራ ብቃት ይጣጣማል ይላሉ?

አቶ አብነት፡- አይጣጣምም። እሱ ወደኛ ወርዶ መስራት አለበት ግን የኛ ሊግም ባለበት መቀጠል የለበትም እያደገ መሔድ አለበት። ነገር ግን የፕሪሚየር ሊጉን ዕጣፋንታ የብሔራዊ ተካፋዮች ጭምር እንዲወስኑበት እየተደረገ ነው ለምሳሌ የውጪ ተጨዋቾችን ቁጥር ለመቀነስ እየታሰበ ነው፡፡ ነገር ግን የኛ ተጨዋቾች በፊት የውጪ ተጨዋቾችን የሚያዩት ከብሄራዊ ቡድን ጋር ሆነው ከሌላ ቡድን ጋር ሲጫወቱ ብቻ ነበር አሁን ግን ከውጪም ይመጣሉ የኛዎቹም እየወጡ ነው። ይህ ደግሞ በኔ በኩል ክፋት የለውም ሲወጡም ልምድ ይዘው ይወጣሉ እነዛም ሲመጡ በጉልበትም ሆነ በሌላ ከኛ በሚሻሉበት ነገር የኛዎቹ ልምድ ይቀስማሉ፡፡ ይህም በመሆኑ የተወሰኑ መሻሻሎች እና ለውጦች ታይተውበታል። በፊት እኛ የውጭ ተጨዋቾች ስናመጣ በጣም ሲቃወሙን የነበሩ አሁን እነሱም በሰፊው ገብተውበታል። አሁን ግን ጊዮርጊስ ለምን በተደጋጋሚ ዋንጫ በላ ስለዚህ ተጨዋቾቹን እንቀንስበት የሚል አካሄድ የተያዘ ይመስላል፡፡ ይህ በጎ አመለካከት አይደለም አንድን ክለብ በማድከም የሚመጣ እድገት የለም። እኔ ደካማ ከሆንኩ እሱም ደካማ ይሁን ብለህ ካሰብክ ይሄ ተራ ምቀኝነት ነው፡፡ አንድ ሰው ደክሞና ሰርቶ ውጤት ሲያመጣ ሰርቆ ነው ሌባ ነው በማለት አንተ ልታድግ አትችልም ይልቅስ ይህ ሰው እንዴት ነው ያደገው እኔስ እንዴት ብሠራ እሱ ላይ እደርሳለሁ ባማክረውስስ ብለህ ነው ማሰብ ያለብህ። እሱም ያማክርሃል። እኛ እቅዳችንን የምንሰራበትን መዝገብ ለብዙዎቹ አሳይተናል። እንዴት ክለቦቻቸውን ኦርጋናይዝ ማድረግ እንዳለባቸው አሳይተናል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ የበለጠ እንዲጠናከር ከታሰበ ሊደር ሺፑን ማስተካከል ነው። ደካማ አስተሳሰብ ካለው ከዚያ መውጣት አለበት።  እግር ኳሱን ከማሳደግ ይልቅ ትልቅ ትልቁን ጎትቶ ወደትንንሾቹ ጎራ ለማስተካከል የገባ ካለ እኛ እራሳችንን  መጠበቅ ብቻ ነው። ጋዜጠኞችም ኃላፊነት አለባችሁ የጋዜጠኝነት ሞያ በጣም የተከበረ እና ታላቅ ሚያ እንዲሁም አስተማሪ ነው። የተስተካከለና እውነትን ያዘለ መረጃ ማስተላለፍ ይጠበቅባችኋል። በርግጥ እዚህላይ እውነቱን ስትናገር ላትወደድ ትችላለህ ልትገለልም ትችላለህ ቢሆንም አንተ ሳትፈራ እውነቱን ነው መናገር ያለብህ የዚያን ጊዜ አንተም ለእግር ኳሱ ለውጥ ለማስመዝገብ የበኩልህን ተወጣህ ማለት ነው።

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- ምን አልባት በክለብ ውስጥ የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር 3 ብቻ እንዲሆን ከፀደቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከያዘው እቅድ አንጻር ገንዘብ እንኳን ቢኖረው ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር ከሚመድቡ  የአፍሪካ ክለቦች ጋር መወዳደር ይችላል?

አቶ አብነት፡- አሁን እንደማየው ፖሊሲው የሚወጣው ከአፍሪቃ ቡድኖች ጋር እንዴት መፎካከር እንዳለብን ሳይሆን አንድን ቡድን እንዴት እንጉዳው እየተባለ ነው። በአፍሪቃ ውድድር ያቀድነውን ለማሳካት ሎተሪ እንደመቁረጥ ነው የሚሆነው። እስከ 60 ሚሊዮን ብር እያወጣን እዚህ ተርመጥምጠን እንድንቀር ከሆነ ያሳዝናል። ዛሬ ጎረቤታችን ጅቡቲ ብትሄድ 5ት ኮንጐ፣ 6ት ሩዋንዳ፣ 7ት ሌሎች ክለቦች እነ ቲቲ ማዜምቤ  እስከ 16 የውጪ ተጫዋቾች አሏቸው። ከነዚህ ጋር ስንጫወት ደጋፊው ከኛ ውጤት ይጠብቃል ። ከአፍሪካ ምርጥ ተጫዋቾች ጋር ነው የምንጋጠመው። እንዴት አድርገን ነው ባሉን ተጫዋቾች እንዳቀድነው 8 ውስጥ የምንገባው? በበጎ ፈቃድ ለተሰጠን ውድድር እያመሰገንን ሄደን መምጣት ብቻ ነው። ሀገራችን ላይ ተጋጥመን እኩል እንኳን ብንወጣ እዚያ 6ትና 7ት ጎል እንድናስተናግድ ነው። የታቀደውን ምንም ማድረግ አንችልም። ባለፉት ጊዜያቶች በኮንፌዴሬሽን ውስጥ ያገኘነውን አበረታች ውጤት እንዳይቀጥል ከማደናቀፍ ውጪ ሌሎች ክለቦችንና ተጨዋቾችን ለማጠናከር አይጠቅምም። ስፔን ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ሁለት ክለቦች ናቸው። እንግሊዝም ከአራት አምስት አይበልጡም። እነሱን ለማዳከም ሌሎች ክለቦች ሲጥሩ ግን አይታይም።  በሁሉም የሊግ ውድድር የሚወሰኑት በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ብቻ ናቸው ለሊጋቸው ማደግ እና መውረድም የሚጠየቁት እነሱ ራሳቸው ናቸው እኛ እኮ በሚፈቀደው ሶስት ኮታ እንኳን ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውን የውጪ ተጫዋቾች እናምጣ ብንል ተጫዋቾች ሊጉ የወረደ እና ደካማ ስለሆነ ስለማይታዩበት አይመጡልንም። እንዴት ነው እዚህ ቢመጡስ በኛ ሜዳዎች ላይ መጥተው የሚጫወቱት። የሜዳዎቻችን ጥራት እንዲሻሻል  መሰራት አለበት። ብዙ ባለሙያዎች ስላሉ ከታሰበበት ለመስራት ቀላል ነው።

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- ባለፈው መስከረም ወር ላይ ፊፋ በበላይነት በሚመራው የአፍሪካ  እግር ኳስ ፈደሬሽን የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ተመርጠዋል። በዚህ በተመረጡበት  ቆይታዎ የኮሚቴውን አሰራር እንዴት አዩት? ከዚህ በፊት አቅርበውት የነበረው የሀሳብ ማሻሻያ ካለ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቶአል?

አቶ አብነት፡- አዎ እንግዲህ እኔ የሚደርሰኝን ሪፖርቶች አይቼ በርካታ ውሳኔዎች ላይ የራሴን ሀሳብና ውሳኔ አሳውቃለሁ፡፡ በርካታ ጊዜ የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች በዲስፕሊን ምክንያት ለቅጣት ሲዳረጉ ይታያል፡፡ ይሄ ደግሞ የሆነበት ምክንያት በየስቴድየሙ በሚደረጉ ጨዋታዎች ከደጋፊዎች በሚወረወር እሳት እና ችቦዎች እና በመሳሰሉት አጥፊ ነገሮች በዚህም የሚገኘው የቅጣት ገቢ ብዙ ነው። እስከ አምስት ሺ ዶላር ይቀጣሉ። ወደ ደቡብ ሄደው ሲጫወቱም  እዛም ሄደው እንዲሁ ይበጠብጣሉ በተጨማሪም በቢም የግብ ጠባቂን አይን እያጭበረበሩ የተቃራኒ ቡድንን ያውካሉ እና እነዚህ ነገሮች መቅረት እንዳለባቸውና  እና በተጨማሪም ሴት ደጋፊዎች ለብቻቸው  ኬር ውስጥ ታፍነው መቀመጥ የለባቸውም። የደጋፊዎች ዲሲፒሊን  መኖር አለበት፡፡  አስቸጋሪ  የሆኑት ደጋፊዎችም ተቀጣጣይ ነገሮችን እንዳያስገቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግና አሳማኝ የሆነ ቅጣት እንዲቀጡ ብዬ የራሴን ሀሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ ባለፈው ጊዜ ከሶስት ሳምንት በፊት ስብሰባ ነበረን እኔም ባጋጣሚ አሜሪካን አገር ሌላ ስብሰባ ስለነበረኝ አልተገኘሁም ነበር። ቢሆንም የስብሰባውን ሪፖርት ልከውልኝ ነበር የሚገርመው ግን አብዛኛው አጀንዳ ቅድም እንደተናገርኩት ባብዛኛው የሰሜን አፍሪካ አገሮች የዲሲፕሊን ግድፈት እና ቅጣት በተመለከተ ነበር፡፡ በናይጄሪያ ቡድን እና በአልጄሪያ ቡድን የሚደረግ ጨዋታ ነበር የናይጄሪያው ቡድን በሰዓቱ ስላላደረሰኝ ዝናብ ይዞኛል ወደ ኤፖርት ሲወስዱኝም በሩቅ መንገድ ወስደውኛል በማለት የተሰጠበትን ፎርፌ ተገቢ አይደለም ብሎ ክስ መስርቶ ነበር፡፡ በዛ ላይም እኔ ውሳኔ እድሰጥ ተጠይቄ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ከውድድሩ በፊት መገኘት ነበረበት በማለት በኔ በኩል የራሴን ውሳኔ ሰጥቼአለሁኝ፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- የእርስዎንና የሌሎች ኢትዮጵያውያን በኮሚቴው ውስጥ መገኘት ለሀገራችን ጠቀሜታው ምን ያህል ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ አብነት፡- አላስፈላጊ ጥቃቶችን  ለመከላከል ማንን እንደምታነጋግር እዛው ከሆንክ በቅርብ ታቀዋለህ ችግሮችህን ቀርበህ ስታስረዳ እና እዚህ ሆነህ በኢሜል ስትጻጻፍ በጣም ብዙ ልዩነት አለው፡፡  ስለዚህ ለዳኞቻችን ለተጫዋቾቻችን ባጠቃላይ  ሀገራችንን ለሚወክሉ ሁሉ ቀርቦ  የሚያስረዳ  ተወካይ ሲኖርህ የበለጠ ጠቀሜታ አለው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡- ኢትዮጵያ ከካፍም አልፋ ፊፋን የመምራት አቅም እንደነበራት  የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ  ህያው ሥራ ምስክር ነው። ጋዜጠኛ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔም ኢነትተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሀፊነት ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡ እንደእርስዎ አስተያየት አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ባለሙያዎችን ለማፍራት ምን መስራት ይጠበቅብናል፡፡

አቶ አብነት፡- በጀመሪያ ቅን አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። አብሮ እና ተስማምቶ መስራት መቻቻል   ያስፈልጋ። ከዛ ዋናው እራስን ብቻ ሳይሆን ሀገርህን ለማሳደግ እና ለመጥቀም የሚያስችል አስተሳሰብ ያስፈልገናል። እኔ አብነት ገ/መስቀል ክለቤን ለማስተዳደር በቂ እውቀት ሊኖረኝ ይችላል።  ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ግን የዛን አካባቢ አስተሳሰብ፣ እወቀት፣ በእግር ኳስ እውቀት ራሴን ማሳደግ ማንበብ በርካታ እውቀቶችን ማካበት ያስፈልጋል።   ክቡር  አቶ ይድቃቸው ተሰማ በተፈጥሮ ከተሰጣቸው የአስተዳደር ችሎታ በተጨማሪ በጣም አንባቢ ነበሩ። በስፖርቱ ውስጥ እየቆየህ ስትመጣ በልምድ በትምህርት እየዳባርክ ትመጣለህ ሀሳብና ፍላጎቱ ካለ ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ዶት ኮም፡-  በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ።

አቶ አብነት፡- የፊታችን እሁድ ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ ለ12ኛ ጊዜ በክብር ዋንጫውን የሚያነሳበት ቀን ስለሆነ ደጋፊው በሙሉ እዲገኝ እና ጨዋታው እደተጠናቀቅ በሚሊነየም አዳራሽ ትልቅ የራት ግብዣ ስላዘጋጀን ደጋፊዎች  መታወቂያቸውን በመያዝ ወደ 25 የሚጠጉ አውቶቢሶች ስለተዘጋጉጁ አብረን ሄደን በሙዚቃ ሴሌብሬት እናደርጋለን።

ኢትዮ ፉትቦል፡-  ለቃለመጠይቁ ስለተባበሩን እናመሰግናለን።

አቶ አብነት፡- እኔም አመሰግናለሁ።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Tadesse Meshesha [966 days ago.]
 Muyawi tenetanie yalebet teru aseteyayet selehone yemidenek newu leSt.G yemetenal asetemarim newu Beravo Abenet!!

jossy sanjaw [966 days ago.]
 Abenet le sanjaw yeseral gena le sanjaw yeseral gena bravo abnet

xi1 [965 days ago.]
 Abinet Sanjaw

Mule V [965 days ago.]
 Mr.Abinet is St.George fc Florentino Perez ! long live for you !

Babi [965 days ago.]
 Abinet le sanjawe ye serale genna. ere ye stadiumu neger yefeten ! Always St.George fc !

Naod [965 days ago.]
 i am proud by St.George fc VVVVVVVVVVVVVVVVVVVVVV

jaimi [965 days ago.]
 St.George fc is more than a club !

clube st. george [962 days ago.]
 thank you

ፍስሃከወልድያአሪፍመረጃ ደር [949 days ago.]
 arifmereja

GOMEZ MAN GOBENA [834 days ago.]
 ke biraw menem endemayetebek derom enakalen.ETHIOFOOTBALL gen bbbbeeeettttaaaammmm new madekachuh

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!