ሻምፕዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2007 ዓ.ም. ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን አነሳ
ግንቦት 23, 2007

- 18ኛው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በ18 ጎሎች ታጅቦ ተጠናቀቀ

. ፈረሰኞቹ 12ኛ ዋንጫቸውን ሲረከቡ ደደቢት ትልቁን የስፖርት ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

. ሙገር ሲሚንቶ ወደ ብሔራዊ ሊጉ በመውረድ ሁለተኛው ክለብ ሆነ

ይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ዓመቱን አጠናቅቆ ወደ 19ኛ ዓመት ጉዞው ሊሸጋገር ትናንት የዓመቱን ፋይል ዘግቷል። ዋንጫውን ማንሳቱን ቀድሞ ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተቀናቃኙን ደደቢትን በምንተስኖት አዳነ ብቸኛ ጎል አሸንፎ አጨራረሱን ሲያሳምር ላለመውረድ ይደረግ የነበረው ከፍተኛ ትንቅንቅም በኤሌክትሪክ የበላይነት ተጠናቅቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊጉ ዋንጫ በተጨማሪ በሶስት ዘፎች ኮከቦችን በማስመረጥ ሲመራ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ ደግሞ የሊጉን ኮከብ ጎል አግቢነት ክብር መቀዳጀት ችሏል። ዝግጅት ክፍላችን ስለ 26ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ጨዋታዎች አብይ ክስተቶችን ከዚህ በታች ያቀርባቸዋል።

ሙገር ወደ ብሔራዊ ሊግ የወረደበት አሳዛኝ ክስተት

ሁለት መንግስታዊ ክለቦች ማለትም ሙገር ሲሚንቶ እና ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ለመቆየት ያላቸው እድል በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት መርሃ ግብር ላይ በሚመዘገብ ውጤት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ጨዋታቸው በተመሳሳይ ሰዓት እንዲካሄድ ተወስኖ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ነበር የተደረገው።

አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት መከላከያ እና ሙገር ሲሚንቶ ያደረጉት ጨዋታ እስከ እረፍት ድረስ ጎል ሳይቆጠርበት ነበር የተጠናቀቀው። በርካታ ተጫዋቾቹን በጉዳት ምክንያት ያላሰለፈው መከላከያ ከሙገር ሲሚንቶ በተሻለ ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል ደጋግሞ ቢደርስም የጎሉን መስመር መለየት የተሳናቸው አጥቂዎቹ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች አካባቢ የሙገር ሲሚንቶው አጥቂ አዲሱ ኦላሮ ከመስመር የተሻገረችለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ከጀማል ጣሰው መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን አሸናፊ ማድረግ ቻለ።

ይህ ውጤት ሙገርን በፕሪሚየር ሊጉ ለማቆየት በቂ አልነበረም ምክንያቱም ተቀናቃኙ ኤሌክትሪክ ቦዲቲ ላይ የግድ መሸነፍ ነበረበት። የሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታው የተጠናቀቀው በዚህ የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ ቢሆንም ሰሞኑን የጣለው ዝናብ ስላበላሸው የኤሌክትሪክ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ የተካሄደው ቦዲቲ ላይ ነበር። በቦዲቲው ጨዋታ የግድ አንድ ነጥብ ማግኘትን ዓላማ አድርጎ የገባው ኤሌክትሪክ የእንግድነት ስሜት ሳያድርበት ቦዲቲ ላይ አንድ ጎል አስቆጥር አዲስ አበባ ላይ መከላከያን በማሸነፋቸው የተደሰቱትን ሙገር ሲሚንቶዎች ደስታቸው የቀበሮ ደስታ እንዲሆን አድርጓል። በዚህም መሰረት ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየቱን ሲያረጋግጥ ለረጅም ዓመታት በርካታ ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀው ሙገር ሲሚንቶ በቀጣዩ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎ እንደማይኖረው አረጋግጧል።

ተደራራቢ ድል የተቀዳጀው ቅዱስ ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 ዓ.ም በአዲስ መልክ መካሄድ ሲጀምር በአንደኛ ዲቪዝዮን ይወዳደር ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ። በዚያ የውድድር ዓመት ግን ፈታኙን የብሔራዊ ሊግ ውድድር በበላይነት በማጠናቀቅ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያልፍ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ኮከብ አሰልጣኝ፣ አማካዩን ፋሲል ተካልኝን ኮከብ ተጫዋች አጥቂውን ስንታየሁ ጌታቸው ቆጬን ደግሞ ኮከብ ጎል አግቢ በማድረግ አስመርጦ ነበር ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው።

በ1990 ዓ.ም በአስልጣኝ አስራት ኃይሌ እየተመራ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ያጠናቀቀው ፋሲል ተካልኝ ከ18 ዓመታት በኋላ እሱም እንደ ቀድሞ አሰልጣኙ ቡድኑን ለዋንጫ ሲያበቃ በግሉም የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝነት ክብርን መቀዳጀት ችሏል። ቀደም ብሎ በተጠቀሰው የውድድር ዓመት በመስመር አማካይነት ሚናው ኮከብ ተብሎ ተመርጦ የነበረው ፋሲል ተካልኝ በዚህ ዓመት የሚያሰለጥነው ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ የወቅቱ የክለቡ የመስመር አማካይ በሀይሉ አሰፋ ቱሳ ደግሞ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝና አማካዩ በሀይሉ አሰፋ ኮከብ ተብለው መመረጣቸውን ተከትሎ ለእያንዳንዳቸው የዋንጫ እና የ25 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

ሮበርት ኦዶንካራ ፈረሰኞቹን ከተቀላቀለ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ኮከብ በረኛነቱን በተደጋጋሚ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ለክለብ አሰልጣኞችና ለአምበሎች ባቀረበው የኮከብ ግብ ጠባቂዎች ምርጫ መጠይቅ ላይ የበርካቶችን ድምጽ በማግኘት ዘንድሮም የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ ተመርጧል። ልክ እንደ ቡድን አጋሮቹ ፋሲል ተካልኝና በሀይሉ አሰፋ እሱም የዋንጫ ተሸላሚ ቢሆንም በገንዘብ ሽልማቱ በኩል ግን ከጓደኞቹ በ10 ሺህ ብር ዝቅ ብሎ የ15 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል። ፈረሰኞቹም ከ12ኛ የሊግ ዋንጫቸው በተጨማሪ ኮከብ ተጫዋቾችንና አሰልጣኝ በማመረጥ ተደራራቢ ድል ተቀዳጅቷል። የዋንጫው ባለቤት በመሆኑም ከፌዴሬሽኑ የ150 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።

የትልቁ ዋንጫ ባለቤት ደደቢት


ስፖርት ለወንድማማችነትና ለወዳጅነት የሚካሄድ መሆኑ ይነገራል። በዚህም መሰረት በስፖርታዊ ውድድርች ከሚሰጡ ሽልማቶች በላቀ መልኩ ለጸባይ ዋንጫ አሸናፊ ክብር ይሰጣል። ሜዳ ላይ በሚደረግ የመሸናነፍ ፉክክር ላይ ቡድኖች ራሳቸውን ተቆጣጥረው ጨዋታቸውን የሚጨርሱ ተጫዋቾች አሸናፊዎች ናቸው ይባላል። ለዚህም የዓለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋን ጨምሮ በሁሉም የውድድር አዘጋጅ አካላት በውድድሩ የጸባይ ዋንጫ አሸናፊ ለሆኑ ቡድኖች የሽልማት ዋንጫ ይዘጋጃል። በ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሌሎች ቡድኖች በተሻለ የጸባይ ሪከርድ ያስመዘገበ ክለብ በመሆን ደደቢት አሸናፊ ሆኗል። በፕሪሚየር ሊጉ ፈረሰኞቹን ተከትሎ ያጠናቀቀው ደደቢት በአመለሸጋነት ግን የሚደርስበት አልተገኘም። በዚህም የጸባይ ዋንጫው አሸናፊ ሆኗል።

ደደቢት የጸባይ ዋንጫ አሸናፊ ከመሆኑ በተጨማሪ አጥቂው ሳሙኤል ሳኑሚ የውድድር ዓመቱን ከፍተኛ ግብ አግቢነት ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ የኮከብ ጎል አግቢነት ክብርም ወደ ደደቢት አምርቷል። ሳኑሚ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ በመሸለም ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ተጫዋች ያደርገዋል። የጸባይ ዋንጫ አሸናፊው ደደቢት በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቁም የብር ሜዳሊያ እና የ100 ሺህ ብር ሽልማት ከፌዴሬሽኑ ተበርክቶለታል።

በሜዳው የመጀመሪያ ሽንፈት ያስተናገደው አዳማ ከነማ


አዳማ ከነማ የውድድር ዓመቱ ክስተት ክለብ ነው። በአሰልጣሽ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት የስምጥ ሸለቆዎቹ እንቁዎች በ2006 ዓ.ም በብሔራዊ ሊጉ ሲወዳደሩ ቢቆዩም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ከተቀላቀሉ በኋላ ያሳዩት ብቃት በስፖርት ቤተሰቡ መነጋገሪያ ሆነዋል። በተለይ በሜዳቸው ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች አንዱንም ያልተሸነፉ መሆናቸው ብቸኞቹ አድርጓቸው ቆይቶ ነበር። በሊጉ የመጨረሻ ጨዋታቸው አርባምንጭ ከነማን አስተናግደው አንድ ለባዶ በመሸነፍ ያለመፈሸን ሪከርዳቸውን ሳያስጠብቁ ቀርተዋል።

አዳማ ከነማዎች ትናንት በሜዳቸው በአርባ ምንጭ ከነማ የአንድ ለባዶ ሽንፈት ቢደርስባቸውም በውድድር ዓመቱ ቀደም ብለው በሰበሰቧቸው ነጥቦች ብዛት የሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችለዋል። በዚህም የ75 ሺህ ብር ሽልማት ከፌዴሬሽኑ አግኝቷል። አዳማ ከነማ ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለ በመጀመሪያ ዓመት ቆይታው ያስመዘገበው ውጤት አድናቆት እንዲቸረው አድርጎታል።

በሌሎች ጨዋታዎች ቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ወልድያ ከነማ የዓመቱን የመጨረሻ ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሜዳው ተጫውቶ ሁለት ለባዶ ሲመራ ቢቆይም በመጨረሻ ቡናዎች ዮናስ ገረመው እና ጋቶች ፓኖም ባስቆጠሯቸው ጎሎች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን በማስተናገድ ትችት የበዛበት ሲዳማ ቡና በሜዳው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ሁለት እኩል ተለያይቷል። ባለፈው ረቡዕ በኤሌክትሪክ ያልተጠበቀ የስድስት ለባዶ ሽንፈት ደርሶበት የነበረው የውበቱ አባተ ቡድን ሃዋሳ ከነማ በሜዳው ዳሽን ቢራን አስተናግዶ አራት ለሁለት በማሸነፍ 10ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል።

በአጠቃላይ የ18ኛው ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመዝጊያ ጨዋታዎች 18 ጎሎች ተቆጥረውባቸው ተጠናቋል። በእለቱ በተካሄዱ ሰባቱም የመዝጊያ ጨዋታዎች ጎል ተቆጥሮባቸዋል። የውድድር ዓመቱን አጠቃላይ ምልከታ በቅርቡ ይዘን የምንመለስ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ የምንገልጽ ሲሆን አንባቢያንም ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉን እንጠይቃለን።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Babi [964 days ago.]
 Sanjawe Hule champions VVVVVVVVVVVVVVVVVVVVVVV

jaimi [964 days ago.]
 am very proud by this great club St.George fc ! mengizem hulem Giyorgis proud of Ethiopia !

Mikimaraki [964 days ago.]
 St.Geortge is east african Real Madrid ! our president Abinet is Florentino Perez.

lemisanjeye [964 days ago.]
 Kechalachu Deresoubin ...... Always St.George fc VVVVVVVVVVVVVV proud of Ethiopia.

Dani Sanjawe [964 days ago.]
 ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገር ውስጥ የሚችለው ስለጠፋ 12 ጊዜ ሻምፒዮን ሆናል ገናም ይሆናል.... ይቀጥላል ! በ 2008 ጊዮርጊስ 10 ነጥብ ተቀንሶብን ሊጉን እንጀምራለን ምክንያቱም የሚችለን ጠፋ የሚያቆመን ጠፋ. ቡላ ገለባ ግን ቁጭ ብሎ ወሬ ያወራል ቡላ ገለባዎች ወሬ ከነማዎች እባካችሁ ስራ ሰርታችሁ ተፎካከሩ በየአመቱ ኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡ አትበሉ በየ 13 አመቱ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን እየሆናችሁ ከተማውን የአፍሪካ ሻምፒዮን እንደሆነ ቲም አትረብሹ. ውስጣችሁን ፈትሹ መጀመሪያ ... ለሽንፈታችሁ ምክንያት ከመደርደራችሁ በፊት ! ታላቁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይከብዳቹሃል .... አዎ ይከብዳቹሃል ! ከቻላችሁ ድረሱብን በወሬ በሃሜት በስድብ ድንጋይ በመወርወር ግን ዋንጫ የለም ስራ ስሩ ወሬ አታውሩ !

ጌትነት [964 days ago.]
 ይርጋ ዘገባህ ጥሩ ነው ወገናዊነት የለበትም በዚሁ ቀጥል።

tanoo [963 days ago.]
 ኢትዮ ፉትቦሎች ዘጋቢ ይርጋ "አንድ ለባዶ አጨራረሱን ሲያሳምር" ብለህ የጻፍከው ሽወዳ ምን የሚያምር ጨዋታ አይተህ ነው። እንደ ጋዜጠኛ ቀሽም ጨዋታ ነበር ብላችሁ መጻፍ ነበረባችሁ። አለበለዚያ እንደዚህ የአሸናፊውን ቡድን ድክመት ስትሸፍኑ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ትጐዳላችሁ። ሳንጃው አንደኛ ነኝ ቢልም ጨዋታው አያሳምንም። ሌላው አንድ የታዘብኩት ነገር የዋንጫ አሰጣጥ ስነስርአቱ ያለቅጥ መንዛዛቱ ነው። ትራፊክ ፣ አስተባባሪ፣ ኳስ አቀባይ ምናምን ሲሸለም ከአንድ ሰአት በላይ ፈጀ። ዲጄው የሰርግ ቤት ምሳ ሰልፍ መጠበቂያ ዘፈን ከፍቶ ሲላዘዘዝ ። አስተዋዋቂው በበኩሉ ሲላዘዝ ደጋፊውን የጭፈራ ሞራል አዳክመው ዋንጫው ሲሰጥ ካታንጋ ጸጥ ብሎ ነበር ያለው። በእንደዚህ አይነት ቀን የደጋፊውን ፍላጐት ማንበብ የሚችል አራዳ አዘጋጅ አስልዋል ቡድኑ እንኳን ያራዶች ነበር። በተረፈ የሳንጃው ቋሚ ደጋፊዎች ከጨዋታው በፊትና በኋላ ቡድናቸውን በአርማቸው ዘንጠው ሲደግፉ ደስ ይሉ ነበር።

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!