የዋልያዎቹ ዝግጅት በአሰልጣኞቹ እይታ
ግንቦት 29, 2007

“በደላላና በቲፎዞ የምመርጠው ተጫዋች የለም”  ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ

Walya's Coaches

የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን በ2017 በጋቦን ለሚዘጋጀው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እንዲሁም ለአራተኛው የቻን ዋንጫ ለመቅረብ ለማጣሪያ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። የቡድኑን ዝግጅት በተመለከተም ትናንት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና ረዳቶቹ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የብሔራዊ ቡድኑን የተጫዋቾች መረጣ ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለዚህም 24 ከአገር ውስጥ እና አራት ደግሞ ከውጭ ሀገር የሚጫወቱ ተጫዋቾችን መምረጡን ገልጿል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ “በሁሉም ቦታዎች ሁለት እና ከዚያ በላይ ልጆችን ይዘናል። በግብ ጠባቂ በኩል ደግሞ ሶስት ግብ ጠባቂዎችን ይዘናል” ያለ ሲሆን በመጀመሪያ ጥሪ ካደረገላቸው 44 ተጫዋቾች መካከል አምስቱ በጉዳት በመጨረሻው ምርጫ ያልተካተቱ መሆናቸውን ተናግሯል። በተለይ በተጎዱት ተጫዋቾች ዙሪያ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተጫዋቾቹ የተጎዱት የአሰልጣኙ ልምምድ ከብዷቸው ነው ተብሎ መዘገቡ ፍጹም ከእውነት የራቀ እና የሙያውን ስነ ምግባር ያልጠበቀ ነው” ብሎ በጋዜጠኞች ላይ ትችቱን ያቀረበ ሲሆን “ተጫዋቾቹ በተለይ የሲዳማ ቡናዎቹ ተከላካዩ አብዱልከሪም መሃመድ እና ግብ ጠባቂው ለዓለም አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት በራሳቸው ጊዜ ጉዳታቸውን በግልጽ ተናግረው የተለዩ ሲሆን አስራት መገርሳ ደግሞ ገና በመጀመሪያው ቀን የልምምድ ግጥሚያ ላይ 20 ደቂቃ እንኳን ሳይጫወት ቀድሞ የነበረበት ጉዳት ተነስቶበት ነው ከሜዳ የወጣው። በልምምድ ግጭት ደርሶበት የተጎዳው ብቸኛ ተጫዋች ሙሉዓለም ጥላሁን ብቻ ነው” ብሏል።

የተጫዋቾችን ምርጫ በተመለከተ ደግሞ “አገሪቱ ካፈራቻቸው የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች ውስጥ ለቡድናችን ይመጥናል ያልናቸውን ተጫዋቾች በመምረጥ በተከላካይ በኩል ዘጠኝ ተጫዋቾች በአማካይ መስመር ላይ ስምንት እና በአጥቂ መስመር ደግሞ አራት ተጫዋቾችን ይዘናል። ተጫዋቾችን የመረጥነው በድለላ ወይም በቲፎዞ ሳይሆን በትክክለኛ በችሎታቸው ላይ ተመርኩዘን ነው” በማለት ተናግሯል። “በአንዳንድ አካባቢ ሜዳ ገብቶ ያልተጫወተን ተጫዋች እንድንመርጥ ጥያቄ ያቀረቡልን ሰዎች አሉ” ያለ ሲሆን “እኛ በዚህ ስራ ሀላፊነት ላይ እስካለን ድረስ እንደዚህ አይነት አሰራር ቦታ የለውም። እኔ በስራው ላይ እስከቆየሁ ድረስ የስፖርቱን ሳይንስ ተከትዬ እንጅ በቲፎዞ ወይም በድለላ ስልክ እየተደወለልኝ አይደለም ተጫዋች የምመርጠው። የስፖርቱ ሳይንስ የሚለው ደግሞ አንድ ስፖርተኛ ስፖርተኛ ነው የሚባለው ለውድድር ሜዳ ላይ ሲገኝ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያት እገሌ ተመርጦ ነበር አሁን ደግሞ አንተ ምረጠው አይባልም” በማለት ጠንከር ብሎ ተናግሯል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል። ለአሰልጣኙ ከተነሱለት ጥያቄዎች መካከል “የሴካፋ ካጋሚ ካፕ የክለቦች ዋንጫ በቅርቡ ይካሄዳል። በዚያ ውድድር ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚሳተፍ ከሆነ ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ የክለቡ ተጫዋቾች ተደራራቢ ጫና አይበዛባቸውም ወይ? ከሜዳ ውጭ የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ የፌዴሬሽኑ ዝግጁነት ምን ያህል ነው? በጨዋታ ፎርሜሽን በኩል በተለይ አራት አራት አንድ አንድ አሰላለፍ ከዚህ በፊት ውጤታማ አላደረገንም አንተ ለዚህ ድክመት ምን መፍትሔ ይዘህ ቀርበሃል?” የሚሉት ይገኙበታል።

በሴካፋ ካጋሚ ካፕ ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን በተመለከተ አሰልጣኙ ሲመልስ “በደንቡ መሰረት አንድ ክለብ ተጫዋቾቹ ለብሔራዊ ቡድን ከተመረጡበት ቅድሚያ የሚሰጠው ለብሔራዊ ቡድኑ ነው። ስለዚህ በሴካፋ ውድድር ፌዴሬሽኑ ባወጣው ደንብ መሰረት የምንሄድ ይሆናል። ነገር ግን አሁን እየተዘጋጀን ያለነው ለቻን ማጣሪያ ደርሶ መልስ እና ለሌሴቶው ጨዋታ ብቻ ስለሆነ የሴካፋውን ዋንጫ ጉዳይ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል። ተጫዋቾችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውሳኔ እናሳልፋለን” ያለ ሲሆን ከሜዳ ውጭ የሚደረግ የወዳጅነት ጨዋታን በተመለከተ ደግሞ “የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ወጭያችንን ሸፍኖ ጋብዞናል። ፌዴሬሽኑም በራሱ አሰራር የያዛቸው ጉዳዮች አሉ ወደፊት ፍጻሜ ሲያገኙ ይፋ ያደርጋል” በማለት መልሷል።

የአጨዋወት ፎርሜሽንን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ደግሞ “ይህ የባለሙያው ስራ ነው። ለባለሙያው እንተውለት እና ከዚያ ውጤቱን እንጠብቅ” በማለት መልስ መስጠት የጀመረ ሲሆን አያይዞም “ገና ባልታየና ባልተሞከረ ነገር ላይ መናገርም ሆነ መልስ መስጠት አይቻልም። ከዚህ በፊት ለነበሩት ግን እኔ መልስ መስጠትም ሆነ መናገር አልችልም። ሳይከካ ተቦካ በሆነ ጉዳይ ላይ ባንነጋገር መልካም ነው። አራት አራት ሁለት አሰላለፍ ደግሞ ሁሌ አንድ አይነት አይደለም። እያንዳንዱ አሰልጣኝ የራሱ አስተሳሰብ እና አካሄድ አለው። እኛ የምንፈልገው ካለ ልጆቹ የሚቀበሉት ከሆነ ያ ነው ተግባራዊ የሚሆነው። ሳይሞከርና ገና ምንም ሳይፈጠር ከመሬት ተነስቶ መናገር ግን አይቻልም” በማለት መልሷል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ብሔራዊ ቡድኑን ካገለገሉት ተጫዋቾች መካከል እንደ አበባው ቡታቆ አይነት ተጫዋቾችን የሙከራ እድል ለምን እንዳልሰጣቸው እና በልምምድ ሜዳ ላይ ተጫዋቾቹ ከቀድሞው በተለየ ከሳጥን ውጭ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አይተናል። ይህ ደግሞ ያልተለመደ ነው። ተጫዋቾቹ አንተ በነገርካቸው መመሪያ መሰረት እየሄዱ ከሆነ ያለፈው ልምዳቸውና አዲሱ አስተሳሰባቸው ተቀናጅቶ ይሄዳል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበውለት መልስ ሰጥቶባቸዋል። 

“አበባው ቡታቆን ስላልመረጥነው ሙከራ ልንሰጠው አንችልም። በአበባው ቦታ በቂ ተጫዋቾች ስላሉኝ አበባውን መምረጥ አልፈለኩም እሱን ብቻ ሳይሆን የሱፍ ሳላንም አልመረጥኩትም” በማለት መልስ ሰጥቷል። ከቦክስ ውጭ ሙከራ ሲያደርጉ አይተናል ለሚለው ጥያቄ ደግሞ በብሔራዊ ቡድን የሚመረጥ ተጫዋች የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን አካሄድ ሊላመድ ይገባል። እኛም ምርጫውን ስናካሂድ የእኛን አካሄድ ሊረዱ የሚችሉ ተጫዋቾች አሉ ወይ ብለን ጠይቀን ነው ወደ ምርጫ የገባነው። በእኔ አመለካከት ብሔራዊ ቡድን ከክለብ የተሻለ ደረጃ ሊኖረው ይገባል። በብሔራዊ ቡድን የሚመረጡ ተጫዋቾች ከክለባቸው የተሻሉ የሆኑት ናቸው” በማለት መልሷል።

ኢንስትራክተር ዮሃንስ ጥሪ ካደረገላቸው በውጭ አገር የሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ዋሊድ አታ ካለበት ጉዳት የተነሳ ላለፉት ሁለት ወራት ያልተጫወተ በመሆኑ ተጫዋቹም በግሉ “ከአዲሱ ቡድኔ ጋር አንድ ጨዋታ ሳልጫወት ለብሔራዊ ቡድንስጫወት ድንገት ጉዳት ቢደርስብኝ እዚህ ለሚኖረኝ ቆይታ ጥሩ ሊሆን አይችልም ብሎ ስለነገረን መቅረቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን ሌሎቹ ግን በተለይ ኡመድ እና ሽመልስ ሰኞ ቡድኑን ይቀላቀላሉ። ሳላዲንም በቅርቡ የሚመጣ ሲሆን ጌተታነህ አገር ውስጥ ስለሚገኝ ቡድኑን እንዲቀላቀል በፌዴሬሽኑ በኩል ጥሪ ቀርቦለታል” በማለት ተናግሯል።

በአጠቃላይ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ጋዜጠኞች ጠንከር ጠንከር ያለ ጥያቄዎችን አቅርበው ከአሰልጣኞቹ መልስ የተሰጠበት ሁኔታ ጥሩ የነበሩ ቢሆንም አንድ አንድ ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች ትችትን ያዘሉ ነበሩ።  ገና በዝግጅት ላይ ያለን አንድ ጨዋታ እንኳን ያላደረገን አሰልጣኝ ከወዲሁ በሆነው ባልሆነው መሞገትና መተቸት አግባብነት ያለው አይመስለንም። ቢያንስ ቢያንስ ትችታችንን የፊታችን እሁድ አሰልጣኙ ያመኑባቸውን ተጫዋቾችና አሰላለፍ ካየን በኋላ ብናደርገው መልካም ነው እንላለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን እሁድ ከቀኑ አስር ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከዛምቢያ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ በሳምንቱ ደግሞ ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና ለአራተኛው የቻን ዋንጫ ማጣሪያ በተከታታይ ሁለት ሳምንታት ከሌሴቶ እና ከኬኒያ ጋር በባህርዳር ይጫወታል።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
mebrate markos [959 days ago.]
 ምንም ይሁን ምን ከዮሀንስ ሳህለ ውጤት አይጠበቅም፡፡የሱ ሀላፊነት ፖለትካ ነው

Babi [957 days ago.]
 I never saw like this stupid silly coach !

jaimi [957 days ago.]
 funny coach even he didnt call senior player Abebawe ( Boutako )

Mule [957 days ago.]
 ምን የሚያስቅ አሰልጣኝ ነው ፌዴሬሽኑ የሾመብን ? ስራው ሁሉ የፖለቲካ ነገር ነው የራሱን ቲም ሰራ ለመባል መመረጥ የሚገባቸውን ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ዘለላቸው. ሌላው ብሔራዊ ቡድኑን ፓርላማ ወይም የብሔር ብሔረሰብ ቡድን ይመስል ከእያንዳንዱ ክለብ ተጫዋቾችን መረጠ በኮታ ይመስል. ኧረ ይደብራል የምትሰራው ስራ ይሄ እኮ ስፖርት እንጂ ፖለቲካ አይደለም ልክ እንደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ መንግስት ሲቀየር የራሱን ወታደርና ፖሊስ እንደሚያቛቁመው የአንተም ስራ እንደዛ አይነት ነው ኧረ ይደብራል ይሄ እኮ ስፖርት እንጂ ፖለቲካ አይደለም shame on you Yohanes !

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!