ወጣቶች ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ያሳዩበት የዋልያዎቹና ቺፖሎ ፖሎዎቹ ጨዋታ
ሰኔ 02, 2007

ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የዋልያዎቹን ኃላፊነት ከተቀበለ ከሳምንታት በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከዛምቢያ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ አንድ ብሎ ጀምሯል። የአጥቂና የግብ ጠባቂ ድርቅ የመታው ሊግ እየተባለ በሚተቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ የሚጫወቱ 44 ተጫዋቾችን በመጥራት ከእነዚያ መካከል 24ቱን በመያዝ ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እና ለቻን ማጣሪያ የሚዘጋጀው የኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ስብስብ፤ ከቺፖሎ ፖሎ ጋር ባደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ከበሀይሉ አሰፋ ውጭ ሌሎቹ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጫወት እድል ያላገኙ ወይም ከረጅም ዓመታት በፊት በውስን ጨዋታዎች ብቻ ተጫውተው የሚያውቁ ተጫዋቾች ነበሩ ወደ ሜዳ የገቡት።  
The Walyas Ethiopian National Team

የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች በሀይሉ አሰፋ በአምበልነት እየመራው ወደ ሜዳ የገባው ብሔራዊ ቡድኑ ከእረፍት በፊትና በኋላ የተለያየ አጨዋወት አሳይቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ወጥ አቋም አሳይቶ የከረመው ወጣቱ አማካይ ምንተስኖት አዳነ እና የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም የመሃል ሜዳውን ክፍል ይዘው የገቡ ሲሆን የሜዳውን ግራ እና ቀኝ መስመር የያዙት ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ በሀይሉ አሰፋ እና በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ወጥ አቋም ማሳየት ከቻሉት ከአንድ እጅ እጣት በታች የሆኑ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አስቻለው ግርማ ናቸው።

በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት በኩል በተጋጣሚያቸው የተበለጡ ሲሆን የመስመር አማካዩ በሀይሉ አሰፋ ደግሞ በሊጉ ያሳየውን ብቃት መድገም ተስኖት ታይቷል። በአጥቂ መስመር የተሰለፉት በፕሪሚየር ሊጉ 16 ጎሎችን በማስቆጠር ብቸኛው የአገር ውስጥ ተጫዋች የሆነው የቡናው ቢኒያም አሰፋ እና በወላይታ ድቻ ተስፋ ሰጭ ብቃት አሳይቶ የከረመው ባዬ ገዛኸኝ የተጠበቁትን ያህል መጫወት አልቻሉም ነበር። በዚህም ምክንያት ከሜዳው አጋማሽ በኋላ ያለውን ቦታ ብሔራዊ ቡድኑ በአስቻለው ግርማ ብቻ የገባ አስመስሎታል።

በተከላካይ መስመር በኩል የተሰለፉት አራቱም ወጣት ተከላካዮች ቢሆኑም በደጋፊውም ሆነ በአሰልጣኛቸው ሙገሳን አግኝተዋል። በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የግራ መስመር ተጫዋቹ ዘካሪያስ ቱጂ እና የሃዋሳ ከነማው ሙጂድ ቃሲም የብሔራዊ ቡድንን ማሊያ ለረጅም ጊዜ የለበሱ እንጅ ገና የመጀመሪያ ጨዋታቸው አይመስልም ነበር። የደደቢቱ አስቻለው ታመነም ሆነ የሲዳማ ቡናው ሞገስ ታደሰ በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን የግብ ክልሉን በአደራነት የተረከበው የሙገር ሲሚንቶው አቤል ማሞም ከወጣት ግብ ጠባቂ በላይ ሆኖ ታይቷል። በተለይ ከዛምቢያዎች በኩል የተሞከሩትን ሁለት ያለቀላቸው ኳሶች በብቃት መልሷል። ይህንን አሰላለፍ ይዞ የገባው የዋልያዎቹ ቡድን ከእረፍት መልስ ሶስት ተጫዋቾችን በመቀየር ተወስዶበት የነበረውን የመሃል ሜዳ የበላይነት ማስመለስ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው የገቡት ፍሬው ሰለሞን እና ብሩክ ቃልቦሬ በዋልያዎቹ የመሃል ሜዳ ላይ በሚገባ ተቀናጅተው የተጫወቱ ሲሆን ቡድኑም ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል በተደጋጋሚ መቅረብ ችሎ ነበር። በዚሁ ክፍለ ጊዜ አንድ የፍጹም ቅጣት ምትም ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በተለይ ፍሬው ሰለሞን ከበሀይሉ አሰፋ፣ አስቻለው ግርማ እና ቢኒያም አሰፋ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ለተመልካች ማራኪ የኳስ ቅብብል ከማሳየትም አልፎ ለተጋጣሚ የግብ ክልል ፈተና መሆንም ችለው ነበር።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን ለጋዜጠኞች የሰጠው ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ “ ማየት የምንፈልገውን አሳይተውናል። ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ቀላል አለመሆኑን ተጫዋቾቼ የተረዱበት ጨዋታ ነው። ምክንያቱም ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ጫናው ቀላል አለመሆኑን የህዝብ ጫና፣ የመገናኛ ብዙሃን ጫና፣ የተጋጣሚ ቡድን ጫና ምን ያህል ቀላል እንዳልሆነ አይተዋል” በማለት የተናገረ ሲሆን አያይዞም “በቻን ውድድር ከውጭ የሚመጡትን ተጫዋቾች መጠቀም ስለማንችል ወጣቶቹን መጠቀም ስለሚኖርብን ልጆቹ እድል እንዲያገኙ አድርገናል” ብሏል።

በጨዋታው ዙሪያ ከተጫዋቾቹ ከወጣቶቹ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ማየቱን የተናገረው ኢንስትራክተር ዮሃንስ “ልምድ ከሌላቸው እንደ ዘካሪያስ፣ አስቻለው እና ሙጅድ እንዲሁም ግብ ጠባቂዎቹ ያሳዩት ብቃት ጥሩ ነበር” ያለ ሲሆን ልምድ ያላቸው እንደ በሀይሉ አሰፋ አይነት ተጫዋቾች ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ ተናግሯል። “ከዚህ በኋላ ልምምዳችን እየተሻሻለ ሲመጣ ቡድናችንም ይበልጥ እየተሻሻለ ይመጣል” ሲል ተናግሯል። አሰልጣኙ የፊታችን እሁድ ባህር ዳር ላይ ከሌሴቶ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ በርካታ የአሰላለፍ ለውጥ ይዞ እንደሚገባ ተናግሯል።

በእሁዱ ጨዋታ በዋልያዎቹ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየው የፈረሰኞቹ ወጣት የግራ መስመር ተጫዋች ዘካሪያስ ቱጂ የእለቱ ክስተት ሆኖ አምሽቷል። በዚህም አሰልጣኙ በግራ መስመር ልምድ ያላቸውን እንደ ብርሃኑ ቦጋለ እና አበባው ቡታቆ አይነት ተጫዋቾችን ያልመረጡበትን ምክንያት በትክክል ያሳየ ነው ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም ተጫዋቹ ግን ተስፋ የሚጣልበት ነው። ከተስፋ ቡድን በዚህ ዓመት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሃሪ መና ተጠባባቂ ይሆናል ተብሎ ቢታሰብም ሳይጠበቅ ዓመቱን ሙሉ ኮከብ ሆኖ መክረሙ ይታወሳል። ዘካሪያስ በክለቡ ያሳየውን ብቃት በብሔራዊ ቡድኑም የሚደግመው ከሆነ የቦታው ትክክልኛ የአበባው ቡታቆ ተተኪ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Mamush [921 days ago.]
 በእሁዱ ጨዋታ በዋልያዎቹ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየው የፈረሰኞቹ ወጣት የግራ መስመር ተጫዋች ዘካሪያስ ቱጂ የእለቱ ክስተት ሆኖ አምሽቷል። በዚህም አሰልጣኙ በግራ መስመር ልምድ ያላቸውን እንደ ብርሃኑ ቦጋለ እና አበባው ቡታቆ አይነት ተጫዋቾችን ያልመረጡበትን ምክንያት በትክክል ያሳየ ነው ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም ተጫዋቹ ግን ተስፋ የሚጣልበት ነው። ከተስፋ ቡድን በዚህ ዓመት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ በክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሃሪ መና ተጠባባቂ ይሆናል ተብሎ ቢታሰብም ሳይጠበቅ ዓመቱን ሙሉ ኮከብ ሆኖ መክረሙ ይታወሳል። ዘካሪያስ በክለቡ ያሳየውን ብቃት በብሔራዊ ቡድኑም የሚደግመው ከሆነ የቦታው ትክክልኛ የአበባው ቡታቆ ተተኪ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል Bravoooooooo Zeki berchilin You are St.George fc Marcelo !

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!