የዋልያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ
ሰኔ 04, 2007

ይርጋ አበበ

ምዕራብ አፍሪካዊዯ ጋቦን በ2012 የአፍሪካ ዋንጫን ከጎረቤቷ ኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ካዘጋጀች ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና ትልቁን የአህጉሪቱን የስፖርት ድግስ ለማዘጋጀት እድል ተሰጥቷታል። አዘጋጅ አጥቶ “የአዘጋጅ ያለህ” ሲል የነበረውን 31ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት የተመረጠችው ጋቦንም ከአራት ዓመታት በፊት የሰራቻቸውን ስታዲየሞች መጠነኛ እድሳት አድርጋ ለውድድሩ ለመቅረብ የተዘጋጀች ቢሆንም ሌሎቹ 15 አገራት ግን ወደ ጋቦን የሚያደርሳቸውን አውሮፕላን ቲኬት ለመቁረጥ የመጀመሪያ ሰልፋቸውን ነገ እና ከነገ በስቲያ በተለያዩ አገራት ውድድር ያካሂዳሉ። የአፍሪካ ዋንጫን የመሰረተችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከነገ በስቲያ በግዙፉ የባህር ዳር ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም ከሌሴቶ አቻው ጋር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።
Walyas

በእድሜ እና በአገልግሎት ብዛት ደህንነቱ ከእለት ወደ እለት አስጊ እየሆነ የመጣው አንጋፋው አዲስ አበባ ስታዲየም “ሰኔ ግም” ማለት ሲጀምር ሆድ ይብሰዋል። “በቡሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ ድሮውንም ሆድ የባሰው አዲስ አበባ ስታዲየም በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ የውድድር መደራረብና በእርጅና ምክንያት አህጉር አቀፍ ውድድር ማስተናገድ ከማይችልበት ደረጃ የደረሰ ይመስላል። የስታዲየሙን የኑሮ ደረጃ ከግምት ያስገባው እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ግንባታው ያልተጠናቀቀውን የባህር ዳሩን ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም ለእሁዱ ጨዋታ መርጧል።

ከቀናት በፊት በአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ የተናገረው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ “እግር ኳስ ወዳድ በሆነው የባህር ዳር ከተማ ህዝብ ፊት በመጫወታችን ደስታ ተሰምቶኛል” ያለ ሲሆን የባህር ዳር ከተማ ነዋሪም ጨዋታው የሚጀመርበትን ሰዓት በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ አመልክቷል። ከዋልያዎቹና ሌሴቶ ጨዋታ ቀደም ብሎ ደደቢት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ከሲሸልሱ ዎሪ ዎልቭስ እና ከናይጄሪያው ክለብ ጋር ሲጫወት ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ በዚሁ ስታዲየም ቡድኑን ይዞ መቅረቡ ይታወሳል። ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የቀድሞ ክለቡን ደደቢትን እየመራ ባካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች የባህር ዳርን ህዝብ ለእግር ኳስ ያለውን ፍቅር የተረዳ ይመስላል።

ከደደቢት በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአልጀሪያው ክለብ ጋር የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ አካሂዶ ሁለት ለአንድ ማሸነፉ ይታወሳል። በእነዚያ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ኢትዮጵያውያኑ ክለቦች ከተጋጣሚዎቻቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸው አይዘነጋም። ደዲት አንዱን ሁለት ለባዶ ሲያሸንፍ በአንደኛው ባዶ ለባዶ ተለያይቷል። ፈረሰኞቹ ደግሞ ምንም እንኳ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ባይችሉም ተጋጣሚያቸውን ሁለት ለአንድ አሸንፈዋል።

ኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!