ከብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታ የታዩ አዎንታዊ ጎኖች
ሰኔ 07, 2007

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ዋልያዎችን እየመራ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን በድል ተወጥቷል።  ከዚህ ቀደም ከቀድሞው ክለቡን ደደቢትን እየመራ ለግዙፉ የባህርዳር ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም የመጀመሪያው በነበረው የኢንተርናሽናል ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣቱ ይታወቃል። ከሰዓታት በፊት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና በሌሴቶ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድናችን የተሻለ ሆኖ በታየባቸውና ይበልጥ ሊሻሻል በሚገባቸው ቦታዎች ላይ የታዘብነውን ከዚህ በታች እናቀርባለን።

Walya 2 -1 Lesetho


በተከላካይ መስመሩ እና የግብ ጠባቂ መካከል ያለው ክፍተት ጠብቦ መታየቱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትልቁ ድክመቱ ተብሎ ተለይቶ የሚታወቀው የተካላካይ መስመሩ እና የግብ ጠባቂው ቦታ ላይ ነው። ከዓመታት በፊት የብሔራዊ ቡድኑ አምበል የነበረው ደጉ ደበበ በግሉ ጨዋታን በማንበብም ሆነ ቡድን በመምራት በኩል የተካነ መሆኑ የማይካድ ነው። ነገር ግን ደጉም ሆነ አጣማሪው የነበሩት ተከላካዮች በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ከናይጄሪያ እና ቡርኪናፋሶ ጋርም ሆነ በቻን ውድድር በሊቢያ የተፈተኑት በመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ስልት ነበር። ለዚህ ደግሞ ችግሩ በበርካቶች ተደጋግሞ እንደሚባለው ተከላካዮቹ ፍጥነት ስሌለላቸው ብቻ ሳይሆን ከግብ ጠባቂው ርቀው ይቆሙ ስለነበረ በመልሶ ማጥቃት ፈጣን የተጋጣሚ ቡድን አጥቂ በቀላሉ ያልፋቸው ስለነበረ ነው።

በዛሬው ጨዋታ ግን ይህ ተለምዷዊ የዋሊያዎች ድክመት በመጠኑም ቢሆን ተቀርፎ ማየት ችለናል። ለዚህ መሻሻል ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሾች ወጣቱ ሳላዲን ባርጌቾ እና ልምድ ያካበተው ስዩም ተስፋዬ ወጣቶቹን ዘካሪያስ ቱጂን እና አስቻለው ታመነነ በሚገባ መምራት በመቻላቸው ይመስለኛል። ሁለቱ ተከላካዮች ማለትም ስዩምና ሳላዲን በክለቦቻቸውም ሆነ በብሔራዊ ቡድኑ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሲሆን ከልምዳቸው የተማሩትም ሆነ በአዲሱ አሰልጣኛቸው የተነገራቸው በመልሶ ማጥቃት ቡድኑ አደጋ እንዳይጋረጥበት ከግብ ጠባቂው በቅርብ ርቀት መቆም እንዳለባቸው የተነገራቸው ይመስላል።

ያለፉትን የብሔራዊ ቡድናችንን ጨዋታ ተመልክተው የመጡት ሌሴቶዎች ብሔራዊ ቡድናችንን በመልሶ ማጥቃት ለመፈተን ሙከራ ማድረጋቸው ያሳብቅባቸው ነበር። በእለቱ የተቆጠረብንን ብቸኛ  ጎል ያስቆጠሩት ግን መሃል ሜዳ ላይ በሀይሉ አሰፋ የተሳሳተውን ኳስ ተጠቅመው እንጅ እንደ እቅዳቸው በመልሶ ማጥቃት አልነበረም። ለዚህም አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና ረዳቶቹ የቡድኑን ግልጽ ድክመቶች እየተመለከቱ ከዚህ የተሻለ ቡድን ይዘው እንደሚቀርቡ አመላካች ሆኖ አግኝቼዋለሁል።

የወጣቶች ተስፋ ሰጭነት

በዚህ ንዑስ ርዕስ ላይ በድጋሚ ተመልሼ እንደምጽፍ ቃል እየገባሁ ለዛሬው መነሻ ሃሳብ የሆነኝን ነጥብ ላንሳ። በደቡብ አፍሪካ ቬትስዌትስ ክለብ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ብዙ ጊዜውን ያሳለፈው   ጌታነህ ከደበ በብሔራዊ ቡድኑ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ዳሩ ግን በዛሬው ጨዋታ እንደተጠበቀው ጥሩ ሳይሆን የታየ በመሆኑ እሱን ተክቶ የገባው ባዬ ገዛኸኝ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሰራውን ስራ መመልከቴ ነበር የወጣቶችን ተስፋ ሰጭ እቅንቅስቃሴ ማድረግ ዙሪያ እንድጽፍ ያነሳሳኝ። ባዬ በወዳጅነት ጨዋታ ጥሩ አልተጫወተም ተብሎ ቢተችም በወቅቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ “ከልምድ ማጣት እና ከተለያዩ ጫናዎች በመጣ ምክንያት ጥሩ አልሆነም” በማለት በወቅቱ ባዬ ያሳየውን የወረደ አቋም ተከላክሎለት ነበር። በዛሬው ጨዋታ ግን የአሰልጣኙን እምነት የሚያጠናክር እንቅስቃሴ አሳይቷል። በዚህ በኩል የዘካሪያስ ቱጂ ጋቶች ፓኖም እና አስቻለው ታመነ ብቃትም ሳይረሳ።

የሳላዲን ሰይድ ወሳኝነት

ይህ ልጅ የወቅቱ የአገራችን እግር ኳስ “ቀንዲል” ነው ማለት ይቻላል። ለረጅም ጊዜ በጉዳት ምክንያት ክለቡን ማገልገል ያልቻለው የአሶሳ ተወላጁ ሳላዲን ሰይድ በብሔራዊ ቡድኑም የተለመደውን ወጥ አቋም ማሳየት አይችልም ተብሎ ተሰግቶ ነበር። ዳሩ ግን ገና በመጀመሪያው ደቂቃ የደረሰበት ግጭት በብቃቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሳያሳድርበት 80 ሺህ ደጋፊዎችን ያስፈነደቀች ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከዚህም በላይ ቡድኑን የመራበት መንገድም የልጁን ወሳኝነትና ትክክለኛ አምበልነት ያሳየ ነበር።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
kassahun ayalew [983 days ago.]
 ለጎሉ መቆጠር ትልቁን ድርሻ የሚወሰደው የተከላካይ አማካኙ ነው።ይሄ እንዴት አልታየህም? ልጁ ቦታውን መሸፈን አልቻለም ነበር።ማንም ሊሳሳት ይችላል ነገር ግን ኳሱን ይዞ ወደ ተከላካይ አማካኙ ቀጠና ዝም ብሎ ሲገባ እና ኳሱን መቶ ሲያገባው እንደ ተከላካይ አማካኝ ምን አደረገ? መጨረሻ ላይም እኮ ትልቅ ስህተት ሰርቶ ነበር።የተከላካይ አማካኝ እንደዚህ እየተሳሳተ ጥሩ ነው ከተባለ ይቅርታ አድርግልኝና ለኔ አይገባኝም።ይልቅስ አስቻለው እና ሳላዲን በነፅፅር የተሻሉ ነበሩ።

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!