የሌሴቶው ጨዋታ እና የባህር ዳር ቆይታ
ሰኔ 12, 2007

ጉዞ ወደ ባህር ዳር 

ለቅዳሜው ጉዞ ሐሙስ ከሰዓት የመጨረሻውን ትኬት ከሰላም ባስ ቆርጠናል። ከሌሊቱ 10 ሰዓት ድረሱ የትኬት ቆራጩ ማስጠንቀቂያ ነበር። ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት በቦታው ስንደርስ ከሌሎች አውቶቡሶች ይልቅ ወደባህር ዳሩ ባስ የዋልያዎቹን ማልያ ያጠለቁ የተለያዩ ሰዎች ብቅ ማለት ጀመሩ 11፡30 ከመስቀል አደባባይ የጀመረው ጉዞ በሱሉልታ አድርጎ ጫንጮ፣ ፍቼ፣ ገብረ ጉራቻ፣ ጎሃ ፅዮንን አቆራርጦ አባይን በመሻገር አማራ ክልል አድርሶን ደጀን እና ሉማሜን አሳልፎ ደብረ ማርቆስ ለምሳ ሲያሳርፈን 30 ደቂቃ ብቻ ነው ከሚል የረዳቱ ማስጠንቀቂያ ጋር ነበር። ከነበርነው ጥቂት ጋዜጠኞች ውጪ አብዛኛው ዋሊያዎችን ለመደገፍ እንደሚጓዙ በማነጋገር እና በለበሱት መለያ አረጋግጠናል፡፡ ከምሳ በኋላ ከደብረ ማርቆስ ተነስተን አማኑኤል፣ ደንቦጫ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ እንጅባራ፣ ዳንግላ እና መራዊን እየጎበኘን ባህርዳር ከመግባታችን በፊት በየከተሞቹ የተለያዩ ሰዎች የዋሊያዎችን ማልያ ለብሰው ስናይ የባህር ዳር ድባብ የበለጠ እንደሚያምር ለመገመት አልተቸገርንም፡፡ 

በተለይ የልማት አጠር የሚመልሰው የአንድ ወቅት የብሔራዊ ቡድናችን ማልያ በየቦታው ከገጠር እስከ ከተማ መዳረሱ ያስገርማል፡፡ ፌዴሬሽኑ ከተለያዩ ወገኞች ቢነገረውም ሊጠቀምበት ያልቻለው ትልቅ የገቢ ማስገኛ መንገድ ከቻይና የሚያስመጡ ግለሰብ ነጋዶዎችን ሚሊኒየነር እያደረገ ነው። ፌዴሬሽኑ ከመንግስት እና ከስፖንሰሮች ጥገኝነት ለመላቀቅ ከነጋዴዎቹ ጋር የጥቅም ተካፋይ የሚሆንበትን አቅጣጫ ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል፡፡

ከአጀማመሩ ሲፈጥን የነበረው አውቶቡስ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ ባህርዳር ይገባል ብለን በመገመት ጋዜጠኞቹ ደስ ብሎን ነበር። ምክንያቱም የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች እና የቡድን መሪው በ10፡00 ሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ስለሚሰጡ ለመድረስ በማሰባችን ደብረ ማርቆስ ላይ ምሳ ከተባለ ቦኃላ ሹፌሩ ጉዞውን ቀዝቀዝ በማድረጉ የኛ የልብ ትርታ ጨመረ። ባህር ዳር ስንደርስ የሰአት ቆጣሪው ከቀኑ 10፡10 ያሳይ ነበር። ከነሻንጣችን ብሄራዊ ቡድኑ ወዳረፈበት ሆቴል በባጃጅ ስንጓዝ የከተማው እርጋታ እና በብሄራዊ ቡድኑ አርማ ማሸብረቅ ዋሊያዎቹ ለዋንጫ ፍልሚያ የሚጫወቱ ያስመስል ነበር።

ጋዜጣዊ መግለጫ እና ቅድመ ዝግጅት 

በተለይ አሰልጣኙ በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ያመጡት የሰአት ማክበር ልምድ ተጀምሮ እንደርሳለን የሚል ግምት ቢኖረንም 10 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ ሳይጀመር ደርሰናል። በጋዜጠኞች በኩል የተለያዩ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የቡድን መሪው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከቡድኑ ዶክተር አያሌው ጥላሁን ጋር ጥያቄዎችን በየተራ መልሰዋል።

የተለያዩ የቴክኒክ እና የታክቲክ ጥያቄዎችን ወደ ጎን ትተን አንዳንድ ቀለል ያሉ ጥያቄዎች ሳይቀሩ አሰልጣኙን ሲያስቆጣቸው በተደጋጋሚ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ባስተውልም በቡድኑ ውስጥ የኮቺንግ ስታፍ ያልተሟላ በመሆኑ  ለአሰልጣኙም ሆነ ለቡድኑ ችግር ነው በማለት ስላሰብኩ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬን እና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን አዲሰ አበባ ላይ በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል የሰጡኝ መልስ በቂ መስሎ ስላልታየኝ በተለይ የሳይኮሌጂ እና የፊዚካል ባለሞያ ለምን እንዳልተመደበ በድጋሚ ጠይቄ ኮቺንግ ስታፍን በተመለከተ እኛ ለአሰልጣኙ ሙሉ ስልጣን ሰጥተናል በእኛ በኩል ሁሌም ዝግጁ ነን በማለት የቡድን መሪው እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ሲመልሱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በበኩላቸው የጥያቄውን አስፈላጊነት እንደሚያምኑበት በመግለፅ ሆኖም በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል ከቡድኑ ሃኪም ጋር በመሆን እሳቸው ደርበው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ሆኖም ግን በተደጋጋሚ ጋዜጠኞችን ያለሙያችሁ አትግብ ሲሉ ነበርና እሳቸውም በባለሙያ ቢታገዙ ጥሩ እና የተሻለ ይመስለኛል።

አሰልጣኙ ከዛምቢያው የወዳጅነት ጨዋታ ሽንፈት በኋላ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተጫዎቾቼ የተወሰኑት አዲስ ስለሆኑ እና የህዝብ እና የሚዲያው ጫና ስለነበረባቸው ነው በማለት ሲመልሱ ከሌሴቶው ጨዋታ በኃላም ጥቂት ተጫዋቾች ባልተጠበቀ ሁኔታ ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ በመግባቱ የመጀመሪያቸው ስለነበረ የመደናገጥ እና የልምድ ማነስ ታይቶባቸዋል፣ ከዕረፍት መልስ ግን ይህንን አስተካክለናል በማለት እንዲሁም ሜዳ ውስጥ ያየነው ሌሴቶ እና በሚዲያ የሰማነው ሌሴቶ በጣም የተለያየ ነበር ብለዋል። አሰልጣኙ በሚድያ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በተደጋጋሚ በሚሰጡት መግለጫ ላይ በደፈናው ሲያሰሙ ይስተዋላል እና እሳቸው ከሚሉት ጫና ለመውጣት  ብሔራዊ ቡድኑ ከፊቱ ረጅም ጉዞ እና ትግል ስላለበት ኮቺንግ ስታፉን ሟሟላት በተለይም የስነ ልቦና ባለሙያ መመደብ ይጠበቅባቸዋል እላለሁ።
 
 ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳለቀ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ወንድምኩን አላዩ ለበርካታ የሚድያው ባለሞያዎች እና የተለያዩ መረጃ ፈላጊዎች በስልክ እና በቃል መልስ በመስጠት ድምፃቸው ተዘግቶ በድካም መንፈስ የሚዲያ አባላትን አና የእንግዶችን የመግቢያ ትኬት ሲያድሉ በተለያዩ ወገኖች የሚደርሰው ወከባ እና ጥሪ ሳያግዳቸው በሚገባ ሁሉንም ማስተናገዳቸው የግለሰቡን ጥንካሬ እና ቀናነት ያሳየ ሲሆን ለፌዴዴሽኑ  መልካም ገፅታ የሰጡ በመሆናችው ከበርካታ ሚዲያዎች ምስጋና ሲደርሳቸው ተስተውሏል፡፡ በግራንድ ሆቴል የፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚዎች እና ከፍተኛ የስፖርት ኮሚሽን ባለስልጣናት ከባህርዳር ጊዜያዊ ኮሚቴ ጋር ሲዋከቡ እና ሲሯሯጡ ላየ በማግስቱ ምንም እንከን የሚፈጥር ባይመስልም ቅንጅቱ ግን ዘግይቶ የተጀመረ በመሆኑ አንዳንድ ግርታዎች ተሰተውሎበታል። ይህም በሚቀጥለው ውድድር መቀረፍ የሚገባ ጉዳይ ነው።

የዋዜማው ድባብ

 ባህዳር ከተማ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተለያዩ ማሊያዎች ባጠለቁ ከዋሊያዎቹ ጎን ነን የሚሉ ደጋፊዎች ተጥለቅልቃለች፡፡ ከቡና ቤት አስተናጋጅ  እስከ ምሸት ክበብ ተጫዎቾች፣የባጃጅ ሹፌሮች በጠቅላላ ነዋሪው ልጅ፣ አዋቂ፣ ሽማግሌ፣ አሮጊት ሳይል የሚቀጥለውን ቀን ጨዋታ በጉጉት እንደሚጠብቁ ያሳብቃል፡፡ በፒካፕ መኪና እየዞሩ የሚቀሰቅሱት ወጣቶች ጥረት እና ፍላጎት ሲታይ የከተማው መስተዳድር ከተጠቀመበት ስታድየሙን መገንባቱ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ዝግጅቶች በማዘጋጅት ከተጠቀመበት በጥቂት አመታት ውስጥ ትርፋማ እንደሚያደርገው ያሳያል፡፡ ምሽት ክበቦች በየዘፈኑ ጣልቃ ለዋሊያዎቹ ሲጨፍሩ እና ሲያስጨፍሩ ላስተዋለ በእውነትም የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ለእግር ኳስ ያለው ፍቅር ከግምት በላይ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ወደፊት ባህር ዳር ከተማን የሚወክል ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ብቅ ቢል በገቢ ደረጃ ከሁሉም የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።

የእለቱ እለት እሁድ ሰኔ ሰባት ቀን

 ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ተነስቼ በኒውላንድ ሆቴል ህንፃ ከጓደኞቼ ጋር ቁርስ ለመብላት  ወደ ምግብ ቤት ስንገባ ሆቴሉ ግጥም ብሎ ስታድየም ይመስል ነበር የዋልያዎቹ ማልያ ከለበሰው ይልቅ ያለበሰውን መቁጠር ይቀላል አስተናጋጆቹ እና ሃላፊዎቹ በጠዋቱ ከጠበቁት ሰው በላይ በመምጣቱ ስራው ከአቅማቸው በላይ ሆኗል።

እኛም የምንፈልገውን አዘን ከህንፃው ላይ አይናችንን ወደ አስፋልቱ ስንወረውር ያየነውን ማመን ነው ያቃተን ህዝቡ እዛው ያደረ ይመስላል። የስታድየሙን የውጪ ክፍል አልፎ አስፋልቱን በረጅሙ ተያይዞታል የትኬት ወረፋ እንዲህ ሊሆን እንደሚችል ብንገምትም በጠዋት 1 ሰዓት ግን ያማይገመት ነበር። በፍጥነት ቁርሳችንን በልተን ሁኔታውን ለመታዘብ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ህዝቡ ለመቀላቀል ብናስብም 1 ሰዓት ያዘዝነው ምግብ ግን 2፡20 ነው የደረሰልን። እዛው ህንፃ ላይ ሆነን በርካታ ትዕይንቶችን ፎቶግራፍ ማንሳት ላይ እያለን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስፋልቱ የአዲስ አበባ የሰንበት ገበያዎችን መስሏል፡፡ የዋሊያዎቹ ቲሽርቶች፤ኮፍያዎች፤የእጅ ጌጣጌጦች ፤የፊት ቀለም ቀቢዎች ንግዱን ያጧጡፉት ነበር።
 
እግር ኳስ ምን ያህል የሰውን ልጅ እንዳስተሳሰረው እና መግነጢሳዊ ሃይል እንዳለው ያሳየ ነበር። የዘገየውን ቁርስ ቀማምሰን ወደ ስታድየሙ ስንሄድ ብዙሃኑ ጨዋ ደጋፊ የያዘው ሰልፍ 10 በማይሞሉ ወጣቶች ተተረማምሶ ሁሉም ሩጫውን ወደ ግዙፍ ስታድየም መሮጥ ጀመረ ሰልፉ በመተራመሱ በጠዋት የተሰለፉ የዋልያዎቹ አድናቂዎቹ በቂ ስርአት አስከባሪ የፖሊስ ሃይል ባለመኖሩ እና ስርዓት አልበኞች በሰሩት እያዘኑ ሲበሳጩ ተመልክተናል።

ቢሆንም በዙሪያው ያለው የስታድየሙ ድባብ ግን በቦታው ለተገኘ ከጨዋታው የበለጠ የሚያስደስት ሃይል ነበረው ማልያዎች የእጅ ላብ መጥረጊያዎች፤ የሀገረ በህል ኮፍያዎች በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቀው በገፍ ይቸበቸባሉ። የደጋፊዎች ፊት በቀለም የሚያስውብ በርካታ ወጣቶች ነበሩ የሁሉም ነጋዴዎች የማሻሻጫ ቃል ግን አነድ እና አንድ ነው አሱም ድል ለዋሊያዎቹ ድል ለዋሊያዎቹ የሚል  ነበር።

ይህንን ደስ የሚል ትዕይንት ታዝበን 4 ሰዓት ላይ  አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ 11  የመጨረሻ ተሰላፊ ተጫዋቾችን ስለሚያሳውቁ ወደ ግራንድ ሆቴል አመራን እዛም ስንደረስ  ሆቴሉ በወከባ እና በውጥረት ታጅቧል። የኢፊድሪ ስፖርት ኮምሽን ኮሚሽነር አቶ አብዲሳ ያደታን ጨምሮ  የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት  እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ከሌሎች የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች ጋር በመሆን  በቦታው ተገኝተው ይወያያሉ ፤ ይመካከራሉ። በኛ በኩል ለአመራሮቹ ስታድየሙ በቂ ጥበቃ ሃይል እንደሌለ ነግረናቸው። በቂ የስነስርአት አስጠባቂ ሃይል ወደ ቦታው እንደሚላክ ለሚመለከተው አካል እንደሚያሳወቁ መልስ ሰጥተውን ነበር።

አሰልጣኙ ዮሃንስ ሳህሌ ከምክትል አሰልጣኛቸው ፋሲል ተካልኝ እና አሊ ረዲ  ጋር በመሆን መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የእለቱን አጨዋወት በጥቁር ሰሌዳ በመሳል ሲያስረዱ የፌዴፌሽኑ አመራሮች በሌላ ክፍል ለተጫዋቾች ስለሚሰጠው ሽልማት እና ስለ እለቱ ፕሮግራም ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ሃላፊዎች ጋር ሲማከሩ ነበር።

በቦታው የተገኙ አንዳንድ ሰዎች ከተጫዎቾች ጋር ፎቶግራፍ ለመነሳት ይጠባበቃሉ። ጋዜጠኞችም የአሰለጣኞቹን 11 ተሰላፊዎች  ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ  ከህዝብ ግንኙነቱ በኩል እንደደረሳቸው  ሩጫቸውን ቀጠሉ። እኛም በዊብ ሳይታችን ይህንኑ አሳውቀን በድጋሚ  ወደ ስታድየም ስንሄድ አስፋልቱ ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ በህዝብ እና በማልያ ሻጮች ተወሯል።

ከጎንደር  እና ከተለያዩ ከተሞች በርካታ ተመልካቾች በአውቶቢስ እና በአውቶሞቢል ይገባሉ። ያለው ድባብ በጣም ደስ ይላል። አንዳንድ ተመልካቾችን ስንጠይቃቸው ስታድየም ገብተው እንደማያውቁ እና ለኳስ ፍቅር ባይኖራቸውም የአገር ጉዳይ ስለሆነ እና ድባቡ ስለመሰጣቸው ትኬት በትርፍም ቢሆን ገዝተን እንገባለን ሲሉ አድምጠናል።

የትርፍ ነገር ከተነሳ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያሳተማቸው ትኬቶች ላይ ዋጋ መብዛቱ ተቃውሞ ስለበረታ  ቅናሽ በመደረጉ ባለ300 ባለ200 እና ባለ50 ብር ትኬቶችን ከነበራቸው ዋጋ ቀንሶ  ሲሸጥ ነበር። አትራፊዎች ግን ትክክለኛ ዋጋው ነው በማለት በተፃፈው ዋጋ ስለቸበቸቡት መግቢያ በር ላይ  ከፍተኛ ጭቅጭቅ እና ውዝግብ ነበር። በጉልበት አንዳዶች ገፍትረው ሲገቡም ተመልክተናል።

ወደ 6፡00 ሰዓት አካባቢ ከግማሽ በላይ ህዝብ በስታድየሙ ስለታደመ እና ፌዴሬሽኑ ያዘጋጀው ትኬትም እየተገባደደ ስለነበረ የቀረው ህዝብ እንዴት እንደሚሆን አሳሳቢ ነበር ትኬት በሌለባቸው በሮች ጠበቅ ያለ ጫና እና ቁጥጥር ባለመኖሩ ጨዋታው እስከሚጀምርበት 10፡00 ሰዓት ድረስ ደጋፊው እንዲገባ በመደረጉ ግዙፉ የባህር ዳር እስታድየም ከ80ሺ በላይ ህዝብ በማስተናገድ ሪከርዶችን የሰባበረ ሆኗል። 700 ብር የተተመነበት ክቡር ትሪቩን ከሌሎች ቦታዎች የሚለይበት የኢትዮ ፕላስቲክ ወንበሮች በመደርደራቸው እና መሃል ለመሃል በመሆኑ ብቻ መሆኑ አስገራሚ ነበር። 
 
ከባለ 100 እና 200 እንዲሁም 10 ብር  ከፋዮች  ጋር ፀሃይ እና ዝናብ ከመመታት ያተረፈው ነገር አላስተዋልንም። አንድ ነገር ግን ነበር ዝናብ በጀመረበት ሰዓት ወንበሮች ተገልብጠው የዝናብ መጠለያ ሆነው የ700 መቶ ብር ወሮታ በጥቂቱም ቢሆን አካክሰዋል። የባህርዳር ስታድየም የመፀዳጃ ፤የውሃ እና ሌሎች በርካታ ያልተሟሉ ነገሮች አሉት ወደፊትም ብዙ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ስለሚያስተናግድ የክልሉ መስተዳድር አሁንም ያስቡበት እንላለን። ባጠቃላይ የሰኔ 7 ቀን የኢትዮጵያ እና የሌሴቶ ጨዋታ ቅድመ ዝግጅት ባጭር ጊዜ የተጀመረ በመሆኑ  እና የቅንጅት ችግር የነበረበት ቢሆንም በነበረው የህዝብ ጨዋነት እና የውጤት ጉጉት ተደምሮ ጨዋታው እስከተጀመረበት ሰዓት የነበረው ሁኔታ በሠላም ተጠናቋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት እና በየመሃሉ ከ80 ሺህ እስከ 101 ሺህ ገብቷል ተብሎ የተወራለትን ህዝብ የኢቢኤስ የሰፖርት ጋዜጠኛ እና የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት መድረክ መሪ ምስግና መብራቱ የድምፅ ማጉያ ማይክራፎኑን በመያዝ ታዳሚውን በሚገባ እየመራ እና እያስተባበረ የአዲስ አበባ ስታድየም  አድማቂዎች አቼኖ እና አዳነን በመጋበዝ ህዝብን ሲያነቃንቀው በጣም የሚያስደስት እና የሚማርክ ስለነበር  ለብሄራዊ ቡድኑ ውጤጥ ማማር  በረካቶች  ፈጣሪያቸውን ሲማፀኑ አስተውለናል። የሰርጋቸውን ፕሮግራም አቋርጠው ከነቬሎአቸው አጃቢዎቻቸውን አስከትለው በስቴዲየሙ የታደሙት ሙሽሮች ክስተት የነበሩ ሲሆን አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ በማለት ተመልካቹ አቀባበል አድርገላቸዋል።

የሌሴቶ እና የዋሊያዎች ጨዋታ

ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ተከላካዮች አስቻለው ታመነ ዘካርያስ ቱጂ  ሳለዲን፥ነ ባርጊቾ  አና ስዩም ተስፋዬ አማከዮች ጋቶች ፓኖም ሽመልስ በቀለ በሃይሉ አሰፋ እና በግራ ዘመም ኡመድ ኡከሪን ተደራቢ አጥቂ ሲሆን ሰላዲን ሰኢድ አና ጌታነህ ከበደ የፊት አጥቂውን መሰመር እንዲመሩ በማድረግ  ያሰለፉት የዋሊየዎቹ አሰልጠኝ ዮሀንሰ ሳህሌ ስብስብ በአጭር ቅብብል ኳስን በራሱ ሜዳ  በማንሸራሽር በአንደ ሁለት ቅብብል ወደ ፊት በመሄድ ለማጥቃት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የአማካይ ክፍሉን መሳሳት እና ከአጥቂ ክፍሉ ጋር ያለመናበብ እና ያለመግባባት ታይቶበተል። ለዚህም ልምምድ ዘግይተው መጀመራቸው እና ያለመቀናጀታቸው እንደምክንያት ቢጠቀስም ጌታነህ ከበደ እና ኡመድ ኡክሪ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው ወደኃላ በመመለስ አማካይ ክፍሎን ከሚመራው ከሽመልስ በቀለ ጋር ተግባብተው መጫወት ያለመቻላቸው በተለይም የጌታነህ አቋም መውረድ ሳላዲን ሰይድ ኳሶችን ሲያገኝ ተጠግቶ የሚቀበለው ባለመኖሩ በግል ጥረቱ ለማለፍ እና ወደቦክስ ለመግባት ሲሞክር የሚያስቆጩ እድሎች በሌሴቶ ተከላካዮች ከሽፈውበታል።

የሌሴቶ ተጫዋቾች ታክቲካል ዲሲፒሊን ላይ ጠንካራ መሆናቸው እና የአሰልጣኛቸውን ትዕዛዝ የሚተገብሩ ስለነበሩ በአንድ ሁለት ቅብብል በቀላሉ ተከላካዩ ከአማካዩ አማካዩ ከአጥቂው ክፍተት የነበረውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቀላሉ በማለፍ አንድ ሁለት ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ተሳክቶላቸውም 1 ግብ በማስቆጠር  ለመምራት ችለዋል። ቡድኑ  1 ጎል ሲቆጠርበት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቆፍጠን ኮስተር በማለት  ወደ ሜዳው ተጠግቶ ለተጨዋቾቹ መመሪያ ሲሰጥ አስተውለናል።

ከእረፍት በፊት እየተመራ ወደ መልበሻ ክፍል የገባው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሁንም በሶስቱ አጥቂዎች ለውጥ ለማምጣት ጥረት ቢያደርግም ለጥቂት ደቂቃዎች የተለየ ነገር ማሳየት ባይችልም  የዝናብ ማየል እና የሌሴቶ ቡድን የተከላከይ መስመሩ ጥንከሬ የዋሊየዎቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ  አላቀዘቀዘውም። ከእረፍት መልስ በተሻለ እንቅስቃሴ በህዝብ ድጋፍ ሰጪነት በአሰልጣኙ ተከታታይ ማነሳሳት እና ጥረት በሞራል ይጫወቱ የነበሩት ዋሊያዎች በተደጋጋሚ አዲስ አበባ በልምምድ ወቅት ያሳዩን የነበረውን ከቦክስ ውጪ አክርሮ የመምታት አዲስ ባህል የተጠቀመ በሚመስል ሁኔታ በእለቱ ድንቅ ከነበሩት ተጫዋቾች አንደኛው ጋቶች ፖኖም በ68ኛ ደቂቃ ላይ  ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ ስታርፍ በጣም ድንቅ እና አስፈላጊ በመሆኗ የተወሰኑ ደጋፊዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኖአቸው ወደሜዳ ስለገቡ ለጥቂት ደቂቃ ጨዋታው ተቋርጦ ነበር። እዚህ ላይ እነ ሳላዲን ሰኢድ የገባውን ሰው እየተማፀኑ ሲያስወጡ አስተውለናል ደጋፊው የገባው በረብሻ ምክንያት ቢሆን በነበሩት  የፀጥታ ሃይሎች ሁኔታው በቁጥጥር ስር ይውላል ተብሎ አይታሰብም በጋቶች ፓኑሜ ግብ ያተነቃቃው የዋልያዎቹ ጦር ከሚዘንበው ዝናብ ጋር እየታገለ ወደፊት ባጭር ቅብብል ኳሷን ወደፊት እያሻገረ በተደጋጋሚ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውስጥ ከጋቾች ግብ 10 ደቂቃ ዘግይቶ ሳላዲን ከሽመልስ የተቀበለውን ኳስ በጌታነህ ተቀይሮ ለገባው ባዬ ገዛኽኝ ሰጥቶት ባዬም የተቀበለውን ለሳላዲን በፍጥነት መልሶ ሲያሻግርለት ሳላዲን በምርጥ እንቅስቃሴ የሌሴቶውን ተከላካይ በማለፍ ያስቆጠራት ግብ ድንቅ ነበረች።

የሳላዲን የማሸነፊያ ጎል ህዝብን ከዳር እስከ ዳር የስፈነደቀች ስትሆን የስፖርት አመራሮች ሳይቀር በደስታ ሲቦርቁ አስተውለናል። ዋሊያዎቹ በቀሩት አስራ ሁለት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር።  አሰልጣኝ ዮሃንስም ጌታነህን በባዬ መቀየራቸው የተሳካ ውጤት አስገኝቶላቸዋል። 

ከጨዋታ መጠናቀቅ ቦኃላ በስታድየሙ የታየው ድባብ በጣም የሚያስደንቅ ነበር ተጫዎቾቻችን ግን ጨዋታው ቢያልቅም ሌላ አድካሚ ጨዋታ ተደቅኖባቸው ነበር ወደ ሜዳ ከገባው ህዝብ ጋር የመጎተት እና የመጉላላት ነገሮች ተስተውለዋል። ከተጫዋቾቹ ጋር ፎቶግራፍ ለመነሳት መጓተቱ በጣም ከልክ በላይ የበዛ ነበር።

ከድሉ ቦኃላ ባህር ዳር በደስታ እየተንቦገቦገች ነበር ለሳላዲን ሰይድ ከህዝቡ የእለቱ ኮኮብ ተብሎ ዋንጫ ተሰጥቶታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ  ፌዴፌሽን አመራሮችን በተለይ አቶ ጁነዲን በሻህን ከበርካታ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ሲጎርፍላቸው ነበር የኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አቶ አብዲሳ ያደታም ህዝብን እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ከአማራ ክልል የስፖርት ኮሚቴን ከአቶ ያየህ አዲስ ጋር እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ህዝቡ ይሰበሰብባቸው በነበሩት ቦታዎች በመዘዋወር ህብተሰቡን በስቴድየሙ ተገኝቶ ላሳየው ጨዋነት የተሞላበት ድጋፍ ምስጋና ሲያቀርቡ አስተውለናል። 

በቀጣይ ለቻን ውድድር ማጣሪያ ከኬንያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የፊታችን እሁድ በዚሁ በባህር ዳር አስቴዲም ስለሚከናውን አመራሮች ተቀናጅተው የተሻለ ስራ መስራት አለባቸው እንላለን። ለዛሬ በዚህ ይብቃን ድል ለዋሊያዎቹ !!! 

ፈለቀ ደምሴ 
ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
kinfealemu [978 days ago.]
 Betamdesymilchwayaneber

Babi [977 days ago.]
 nice zegeba Ethio sport ! beretu ketelubet !

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!