በዋልያዎቹና የሀራምቤ ኮከቦች ጨዋታ እነማን ይሰለፋሉ?
ሰኔ 14, 2007

ዛሬ ከቀኑ አስር ሰዓት ታላቁ የባህር ዳር ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኬኒያ አቻው ጋር የሚያካሂዱትን ጨዋታ ያስተናግዳል። በዛሬው ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው የመጀመሪያ ተሰላፊ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ከሰዓታት በኋላ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የሚያሳውቅ ይሆናል። ትናንት አመሻሽ ላይ በግራንድ ሪዞርትና ስፓ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለማወቅ እንደተቻለው ከ23ቱ የቡድኑ አባላት መካከል 18ቱን አሰልጣኙ ይፋ አድርጓል። በዚህ መግለጫ ተመስርተን በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ ቋሚ ተሰላፊዎች እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ እና እድል ከተሰጣቸው 18 ተጫዋቾች መካከል በተለይም የተወሰኑትን ለይተን በማውጣት ወቅታዊ ብቃታቸውንና በጨዋታው ሊያሳኩት የሚችሉትን ነጥቦች እንመለከታለን።

ጀማል ጣሰው ከባድ ጉዳት ስለደረሰበት ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያ ተሰላፊነት እድሉን ያገኘው የሙገር ሲሚንቶው አቤል ማሞ በዛሬው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ግብ ጠባቂው መጠነኛ ጉዳት እንዳስተናገደ የቡድኑ ሃኪም ይፋ ያደረጉ ሲሆን በዚህም መሰረት የደደቢቱ ታሪክ ጌትነት በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያ ቋሚ ተሰላፊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በግቡ ቋሚ መሃል ይቆማል ተብሎ የሚጠበቀው ታሪክ ጌትነት ከዚህ ቀደምም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና ማሪያኖ ባሬቶ የቡድናቸው አባል ያደርጉት ስለነበረ የልምድ ማጣት ችግር ይገጥመዋል ተብሎ አይጠበቅም። ክለቡ ደደቢትም ሲሳይ ባንጫን በስነ ምግባር ጉድለት ሲያሰናብት ዓመቱን ሙሉ የክለቡን የግብ ክልል በብቃት ሲጠብቅ ከርሟል። የታሪክ ጌትነት ትልቁ ድክመቱ የነበረው የጊዜ አጠባበቅ ወይም ታይሚንግ ሲሆን በዚህ ድክመቱ ላይ የግብ ጠባቂዎቹ አሰልጣኝ ዓሊ ረዲ ምን ያህለ እንደሰራ በዛሬው ጨዋታ እናየዋለን።

አሰልጣኝ ዮሃንስ የተከላካይ መስመሩን ካለፈው አሰላለፍ ላይ ማስተካከያ ያደርጋል ተብሎ አይታሰብም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አሰልጣኙ 18ቱን ተጫዋቾቹን ይፋ ሲያደርግ ባለፈው ሳምንት የተሰለፉት አራቱም ተከላካዮች የአንዳቸውም ስም ከ18ቱ ተጫዋቾች ውጭ አልሆነምና ነው። በዚህም መሰረት ስዩም ተስፋዬ በቀኝ በኩል ሳላሃዲን ባርጌቾ እና አስቻለው ታመነ በመሃል እንዲሁም ዘካርያስ ቱጂ በግራ በኩል ይሰለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተከላካይ ቦታ ላይ ምናልባት ለውጥ ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው የሃዋሳ ከነማው ሙጅብ ቃሲም በተለይም ከሳላዲንና አስቻለው አንዳቸውን ተክቶ ሊገባ ይችላል ተብሎ ነው።

በመሃል ሜዳ ላይ ባለፈው ሳምንት ኮከብ ሆኖ የዋለው ጋቶች ፓኖም በዛሬው ጨዋታም በቋሚነት እንደሚሰለፍ ሰፊ ግምት ያገኘ ሲሆን ከጋቶች ፊት ማን ሊሰለፍ ይችላል የሚለውን ጥያቄ አሰልጣኙ ከሰዓታት በኋላ ያሳውቃል። ብሔራዊ ቡድናችን ከዛምቢያ ጋር ሲጫወት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከእረፍት በፊት ጋቶችን እና ምንተስኖት አዳነን አጣምሮ የሞከረ ቢሆንም በሁለቱ ጥምረት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላገኘ ለጋዜጠኞች ተናግሮ ነበር። በዛሬው ጨዋታም ከጋቶች ፊት ሊሰለፍ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው ከፈረሰኞቹ ሁለተኛ  ኮከብ ጎል አግቢው ምንተስኖት አዳነ ይልቅ የመከላከያው ፍሬው ሰለሞን ነው። ፍሬው ሰለሞን በተለይ ከኳስ ጋር ያለው ንክኪ እና ነጻ ሆኖ ለሚገኝ ጓደኛው ኳስን አስተካክሎ በማቀበል ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ የሚሰለፍ ከሆነ ለአጥቂዎቹ ባዬ ገዛኸኝና ቢኒያም አሰፋ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ያደርሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ብሔራዊ ቡድኑ ከሌሴቶ ጋር ባደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሽመልስ በቀለን ከመጠቀም ይልቅ ፍሬው ሰለሞንን መጠቀም ነበረበት የተባለውም ፍሬው ለቡድን አጋሮቹ የተመጠኑ ኳሶችን በሚገባ ስለሚያደርስ ነው።

የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ያጠናቀቀው በሀይሉ አሰፋ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችልም በዛሬው ጨዋታ ተጠባባቂ ወንበር ላይ ይቀመጣል ተብሎ አይጠበቅም። የቡድኑ ምክትል አምበል በመሆኑ እና በዛሬው ጨዋታ ሳላሃዲን ሰይድ ስለማይሰለፍ በሀይሉ አሰፋ ዛሬ ቡድኑን በአምበልነት የሚመራ ይሆናል።

ከበሃይሉ ተቃራኒ ያለውን የመሃል ሜዳ ክፍል ይሸፍናል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮጵያ ቡናው አስቻለው ግርማ ነው። በሜዳው ጥግ ኳስን ይዞ ሲሮጥ ፍጥነቱ ለተከላካዮች “አይጣል” የሆነው የባሌ ጎባው ተወላጅ ለብሔራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጫወት ያሳየውን የወረደ አቋም በዛሬው ጨዋታ አስተካክሎ የሚገባ እንደሚሆን ይጠበቃል። አስቻለው ግርማ በዚህ ዓመት ብቃታቸውን ጠብቀው ክለባቸውን ካገለገሉ እጅግ በጣም ውስን የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን ይህ ብቃቱም አገራዊ አደራ እንዲቀበል አስችሎታል። በዛሬው ጨዋታ የሚያሳየው ብቃትም የወደፊት የእግር ኳስ እድገቱን አመላካች ይሆናል። በዚህ ቦታ አስቻለው ግርማ በቋሚነት የማይሰለፍ ከሆነ የኤሌክትሪኩ ራምኬል ሎክ ይሰለፋል። የጋምቤላው ተወላጅ እሱም እንደ አስቻለው ግርማ ፍጥነቱ ለተከላካዮች ፈታኝ ሲሆን ከኳስ ጋር ያለው ዝምድናም በእጅጉ መልካም የሚባል ነው። ራምኬል ብቸኛ ችግሩ የመጨረሻ ኳሶቹ አድራሻቸው የማይታወቅ መሆናቸው ነው። 

በአጥቂ መስመር ላይ እንደሚሰለፉ ከፍተኛ ግምት ያገኙት የወላይታ ድቻው ባዬ ገዛኸኝ እና የኢትዮጵያ ቡናው ቢኒያም አሰፋ ናቸው። ሁለቱ ተጫዋቾች አንዳቸው ጨዋታን በማንበብ ሌላኛቸው ደግሞ ኳስን በመጨረስ የተካኑ መሆናቸውን በፕሪሚየር ሊጉ አሳይተዋል። በተለይ ወጣቱ ባዬ ጨዋታ የማንበብ ችሎታውንና ለቡድን አጋሮቹ ክፍተትን የመፍጠር ብቃቱን ባለፈው ሳምንት ብሔራዊ ቡድኑ ሌሴቶን ባሸነፈበት ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ አሳይቷል። በዛሬው ጨዋታም ከቡድን አጋሩ ቢኒያም አሰፋ ጋር ጠንካራ ጥምረት እንደሚፈጥር ተስፋ ተጥሎበታል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!