ዋልያው ከሀራምቤ ኮከቦች፡- የጎረቤታማቾቹ ፍልሚያ የመጀመሪያ ምዕራፍ
ሰኔ 15, 2007

ይርጋ አበበ

የባህር ዳር ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ክለቦች የተመቸ ስታዲየም የሆነ ይመስላል። ትናንት በተካሄደው የቻን ማጣሪያም ሆነ ከሳምንት በፊት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድኑ ድል የቀናው ሲሆን የብሔራዊ ቡድናችን ተጫዋቾችም ስታዲየሙም ሆነ የቡድኑ መንፈስ የተመቻቸው መሆኑን በጨዋታቸው እያሳዩ ነው። ዛሬ በዚህ ጽሁፍ በትናንቱ ጨዋታ የተመለከትናቸውን ሰናይ ተግባራት የምናወሳበትና ድክመቶችን ደግሞ የምንጠቁምበት ይሆናል።

ቢኒያም አሰፋ የአሰፋ መዝገቡን ታሪክ በባህር ዳር ደገመ

ከዓመታት በኋላ ቢኒያም አሰፋ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ሲለይና ስለ እግር ኳስ ታሪኩ ለልጆቹ ሲናገር “በአንድ ዓመት ለኢትዮጵያ ቡና 16 ጎሎችን አስቆጠርኩ” ከማለት ይልቅ “አንድ ቀን ለብሔራዊ ቡድን ስጫወት ከ70 ሺህ ህዝብ በላይ እየተመለከተን ነበር። በዚያ ጨዋታ ቡድናችን ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ተጋጣሚ የነበረውን የሀራምቤ ኮከቦችን ሁለት ለባዶ አሸነፈ። ጎሎቹን ግን እኔ አላስቆጠርኳቸውም ግን ለሁለቱም ጎሎች መገኘት አስተዋጽኦዬ ከፍተኛ ነበር” ሲል የሚናገር ይመስለኛል። ዓመቱን ሙሉ ከጉዳት ነጻ በሆነባቸው ጊዜያት ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ያጠናቀቀበት ክለቡ 33 ነጥብ ይዞ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ካጠናቀቀው የክለቡ ውጤት እና በግሉ 16 ጎሎችን ካስቆጠረበት ገድል ይልቅ ከ70 ሺህ በላይ ደጋፊዎች ታድመውበት የተጫወተበት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ውጤት ትልቅ ትርጉም ነበረው።
Ethiopia 2-0 Kenya

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1996 እና በ2000 የምድራችን ታላቁ የስፖርት ውድድር ኦሎምፒክ የተካሄደባቸው ዓመታት ናቸው። በእነዚያ ሁለት የተጠቀሱ ዓመታት ኢትዮጵያውያንና ኬኒያውያን በበላይነት ለማጠናቀቅ እርስ በእርስ ፉክክር የገጠሙበት የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አለ። በሁለቱ ሀገራት በኩል ሀይሌ ገብረስላሴ እና ፖል ቴርጋት የተባሉ የምድራችን ልዩ አትሌቶች ተፋጥጠዋል። በሁለቱም ዓመታት ታዲያ የበላይ የሆነው የአሰላው ተወላጅ ሀይሌ ገብረስላሴ ነበር ለሀይሌ ድል ምክንያቱ ደግሞ አንዱ ነው “አሰፋ መዝገቡ” የተባለ የቡድን አጋሩ ኬኒያዊ ተጋጣሚውን ስላደከመለት ነው። በዚህ ጉዳይ ፖል ቴርጋት ጥያቄ ሲነሳበት “አሰፋ ሁለት የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን ወስዶብኛል” ሲል ይናገራል። ምክንያቱም ለሀይሌ ድል የአሰፋ መዝገቡ ድጋፍ ከፍተኛ ስለነበረ ነው።

ከዓመታት በኋላ ደግሞ ሁለቱ ጎረቤት አገሮች ኢትዮጵያና ኬኒያ የጋራ ጎረቤታቸው ሩዋንዳ ለምታስተናግደው አራተኛው የቻን ዋንጫ ለመሳተፍ እርስ በእርስ ተገናኙ። የሁለቱ አገሮች የመጀመሪያ ጨዋታ የተካሄደው በኢትዮጵያ ሲሆን ድሉም በድረ ገጻችን ቀደም ብለን እንደገለጽነው ሁለት ለባዶ ዋልያዎቹ አሸንፈዋል። ሁለቱን ጎሎች ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ አስቻለው ግርማ እና ጋቶች ፓኖም አስቆጥረዋል። በዚህ ጨዋታ ግን ሌላኛው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ቢኒያም አሰፋ የአሰፋ መዝገቡን ገድል ሰርቶ አምሽቷል። እንዴት?

ሀይሌ ፖርቴርጋትን በሁለት ተከታታይ የኦሎምፒክ ውድድሮች ድል እንዲነሳ አሰፋ መዝገቡ ከፍተኛውን ድርሻ እንደተጫወተው ሁሉ በትናንቱ ጨዋታም ፈጣኑ አስቻለው ግርማም ሆነ ግዙፉ ጋቶች ፓኖም ጎሎቹን እንዲያስቆጥሩ የቢኒያም ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ካለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በተለየ በሀይሉ አሰፋ ወደ ምርጥ አቋሙ በተመለሰበት፣ “ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች ፍጹም ቅጣት ምት ፍጹም ማዳን አይችሉም” የሚባለውን አባባል ታሪክ ጌትነት ታሪክ ባደረገበት፣ የኤሌክትሪኩ ራምኬል ሎክ ለኬኒያውያን ተከላካዮች አልያዝ አልጨበጥ ብሎ ባመሸበት እንዲሁም ወጣቱ ተካልኝ ደጀኔ “የቦታው ተተኪና ትክክለኛ ደጀን” መሆኑን ባሳየበት የትናንቱ ጨዋታ ቢኒያም አሰፋ ለሁለቱ ጎሎች መገኘት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለዚህም ነው በጽሁፉ መግቢያ ላይ ቢኒያም አሰፋ ከዓመታት በኋላ ለልጆቹና የልጅ ልጆቹ በኩራት መናገር የሚችለውን ታሪክ ሰርቶ አመሸ ያልኩት።

ተካልኝ ደጀኔ “የቦታው ምትክና ደጀን”

በርካቶች ዳዊት መብራቱ ወይም ገዳዳው የሚባል ስም ሲሰሙ “ታላቁ የፈረሰኞቹ ግራኛ” ብለው የተጫዋቹን ድንቅ ብቃት ለመዘርዘር ቃላት ሲያጥራቸው ይሰማል። የፈረሰኞቹ እና አየር መንገድ ተጫዋች ዳዊት መብራቱ ያለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ምርጡ የግራ መስመር ተከላካይ ነው ማለት መዋሸት አይሆንም። ማንም የዚህን ተጫዋች ብቃት መደበቅ አይችልም። ከዳዊት በኋላ በፈረሰኞቹም ሆነ በዋልያዎቹ የግራ መስመር ተከላካይ ላይ ብቅ ያለው አበባው ቡታቆም ቢሆን የራሱን አሻራ በመልካም አሳርፎ ያለፈ ተጫዋች ነው። ብርሃኑ ቦጋለ ፋዲጋ ደግሞ ሌላው የግራ መስመር ድንቅ ተጫዋች ነው። የተጠቀሱት ሶስቱም ተጫዋቾም ሆኑ እንደ ብርሃኑ ፈየራ ያሉ ቀደምት የግራ መስመር ተጫዋቾች በዚህ ሰዓት ከብሔራዊ ቡድኑ ውጭ ናቸው። ቦታውን ማን ያዘው?

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ አበባው ቡታቆን ሳይዙ ቡድን መገንባት የሚታሰብ አልነበረም። ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ግን “ከአበባው የተሻሉ ተጫዋቾችን ይዣለሁ” ብሎ አበባውንም ሆነ የአበባው ተጠባባቂ የነበረውን ብርሃኑ ቦጋለን ከምርጫው ውጭ ሲያደርጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ለምን? ቢባል አበባው ቡታቆ ጠንካራ ተከላካይ ከመሆኑም በላይ ምርጥ የቅጣት ምት ስፔሻሊስት መሆኑን ሁሉም ስለሚያውቁ ነው። አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ አበባውንም ሆነ በደደቢት ሲያሰለጥን የቡድኑ አምበል የነበረውን ፋዲጋን ከቡድኑ ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ውጭ ሲያደርግ የተማመነው በፈረሰኞቹ ተስፈኛ ዘካሪያስ ቱጂ እና በደደቢቱ ታዳጊ ተካልኝ ደጀኔ ነበር። ቀደም ባሉት ሁለት የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች የተመለከትነውን የዘካርያስን ምርጥ ብቃት ዝግጅት ክፍላችን ማቅረቡ ይታወሳል። በትናንቱ ጨዋታ የተመለከትነውን የተካልኝ ደጀኔን ብቃት ደግሞ እንናገርለት ዘንድ ችሎታው አስገደደን።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የእድሜ ጉዳይ አጨቃጫቂነቱ እንዳለ ሆኖ የተካልኝ ደጀኔ ወቅታዊ እድሜ ከ20 ያልዘለለ መሆኑ ተጫዋቹ ገና ታዳጊ እና ተስፋ የሚጣልበት እንዲሆን ያደርገዋል። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወተ ሲሆን ለክለቡ ደደቢትም ቢሆን ለዋናው ቡድን በቋሚነት መሰለፍ የጀመረው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ነው። እድሉን ሲያገኝ ግን ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለክለቡም ለብሔራዊ ቡድንም ማሳየት ችሏል። በትናንቱ ጨዋታ ከባህር ዳር ባገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ወጣቱ ልጅ ከ70 ሺህ በላይ ህዝብ የድጋፍ ጩኸት ሳይረብሸውና ግዙፎቹ የኬኒያ አጥቂዎች ጫና ሳያንበረክከው ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በብቃት መጨረስ ችሏል።

የራም ኬል ሎክ አዲሱ ቦታ

በርካቶች በትናንቱ ጨዋታ ቢኒያም አሰፋ ከባዬ ገዛኸኝ ጋር ተጣምረው የዋልያውን የፊት መስመር ይመሩታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ግን ከባዬ ይልቅ ሩጦ የማይደክመውን ራምኬል ሎክን በፊት መስመር ከቢኒያም ጋር አጣምሮታል። ከመውረድ ለጥቂት የተረፈው ኤሌክትሪክ ጋር አንዴ በክንፍ አማካይ ሌላ ጊዜ ደግሞ በፊት መስመር እየተጫወተ ያሳለፈውና በክለቡ ብዙም ስኬታማ ጊዜ ያላሳለፈው ራምኬል ሎክ በትናንቱ ጨዋታ የፊት መስመሩን ከቢኒያም አሰፋ ጋር ተጣምሮ ሲመራ የተመለከቱ የስፖርተ አፍቃሪያን ግን በልጁ ብቃት እና በአሰልጣኙ ውሳኔ ተደስተዋል።

ተጫዋቹም የተሰጠውን እድል በሚገባ ለመጠቀም የተዘጋጀ መሆኑን ሜዳ ላይ በቆየባቸው 92 ደቂቃዎች ማሳየት ችሏል። የራምኬል ሎክ ብቸኛ ችግሩ ተብሎ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚነሳውም ሆነ በትናንቱ ጽሁፋችን እንደገለጽነው የመጨረሻ ኳሶቹ አድራሻቸው ጥሩ አለመሆን ነው። ይህ ደግሞ ከተከታታይ ስልጠና እና ከጠንካራ ልምምድ የሚመጣ ሲሆን የክለብም ሆነ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በልጁ ደካማ ጎን ላይ ጠንክረው ከሰሩ ወደ ፊት የተሳለ አጥቂ እንደሚሆን በርካቶች ይስማሙበታል።

የተመልካቾች መጠን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተለያየ ተደርጎ መገለጽ

በነገራችን ላይ በባህር ዳሩ ስታዲየም የሚታደሙ ተመልካቾችን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አኃዞችን ይጠቀማሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትክክልኛውን አኃዛዊ መረጃ መስጠት ቢኖርበትም ይህንን ማድረግ አልቻለም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን ወደ ፊት የምናውቀው ይመስለኛል። ስታዲየሙ ሲገነባ በወንበር 50 ሺህ ተመልካቾችን እንደሚይዝ ተደርጎ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወንበር ስላልተገጠመለት ስታዲየሙ የመያዝ አቅሙ ቢበዛ ከመደበኛው የ20 ሺህ እና 25 ሺህ ሰው ቢይዝ እንጅ እጥፍ ተመልካች ያስተናግዳል ተብሎ አይጠበቅም።

አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ከመቶ ሺህ በላይ ህዝብ በስታዲየሙ ታድሟል ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ ቁጥሩን ከ80 እስከ 90 ሺህ ያደርሱታል። ዝግጅት ክፍላችን ስታዲየሙ ይህንን ያህል ህዝብ ያስተናግዳል ብሎ አያምንም። ምክንያቱም አንደኛ በወንበር 50 ሺህ የሚይዝ ከሆነ ወንበር ሳይገጠምለት ተመልካቾች ተጠጋግተው ቢቀመጡ እንኳ እጥፍ መጠን ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ የለም። ሁለተኛ ደግሞ አንድ ግንባታው ያልተጠናቀቀ ገና አዲስ ስታዲየም ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ ገብቶ  ሲዘልበት ለስታዲየሙ ደህንነት አስጊ መሆኑን የስታዲየሙ ባለቤቶች ያስባሉ። በዚህም ምክንያት ስታዲየሙ መያዝ ከሚችለው በላይ ሰው አስተናግዳል ብሎ ማመን ይከብዳል።

ስለዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴረሽንም ሆነ ከስታዲየሙ ገቢ የ30 በመቶ ድርሻ ያለው የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምን ያህል ህዝብ እንደታደመ እና ምን ያህል ገንዘብ እንደተሰበሰበ ይፋ ቢያደርጉ ከተሳሳተ መረጃም ሆነ ከአሉባልታ እንዲሁም ከተጠያቂነት አኳያ መልካም ነው እንላለን።

ከዚህ በተጨማሪ የባህር ዳር ስታዲየም ለመገናኛ ብዙሃን እንድንጠቀምበት የስታዲየሙን መጠሪያ ስያሜ በትክክል መጠቀም ያለብንም ይመስለኛል። ከአንድ ዓመት በፊት የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እማኘው ይግዛው እንደገለጹልኝ የስታዲየሙ መጠሪያ “የባህር ዳር ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም” ተብሎ ነው። በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ግን “የባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም” እየተባለ ይዘገባል። ይህ ስህተት ነው። ምክንያቱም አንደኛ ስታዲየሙ ከእግር ኳስ መጫዎቻ በተጨማሪ ለሌሎች ስፖርቶችም አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ “ሁለገብ” እንዲባል የሚያደርገው ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ስታዲየሙ የገነባው ባህር ዳር ከተማ ላይ ቢሆንም እና ደረጃው ኢንተርናሽናል ቢሆንም አገልግሎቱ አገር አቀፍ ስለሆነ “ብሔራዊ” እንዲባል ተደርጓል። አንዳንዶች ስታዲየሙ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን ስላስተናገደ እና የስታዲየሙ ደረጃ ዓለም አቀፍ ስለሆነ ብቻ ስያሜውንም “ኢንተርናሽናል” ሲሉት ይሰማሉ።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Mamush [973 days ago.]
 @ tanoo በጣም ታሳፍራለህ ሁልጊዜ የምትፅፋቸው ኮመንቶች ሀገራዊ ስሜትነትን ሳይሆን ክለባዊ ስሜትነታዊነት ይታይባቸዋል ለነገሩ የቡላ ደጋፊ ታሳፍራላችሁ ብሔራዊ ቡድናችን እየተጫወተ ቡና ገበያ እያላችሁ ታላዝናላችሁ ! ብሔራዊ ቡድናችን እየተጫወተ የ ኢትዮጵያን ባንዲራ አርማ መያዝ ሲገባችሁ እናንተ ግን የቡናን አርማ ይዛችሁ ስታዲየም ትታደማላችሁ ምንድነው አላማችሁ ? ምንድነው ድብቅ ተልኳችሁ ? ሶስት ተጫዋች አስመርጣችሁ እንደዚህ የሆናችሁ እንደ ደደቢት ጊዮርጊስ ብዙ ተጫዋቾች አስመርጣችሁ ሀገራችን ለአፍሪካ ዋንጫ ወይም ለአለም ዋንጫ ለማለፍ ጫፍ ላይ ብትደርስ ኦኦኦኦኦኦኦኦ ምን እንደምትሆኑ ለማሰብ ቀላል ነው. እባካችሁ እያስተዋላችሁ ክለባዊ ጭፍን ስሜታዊነታችሁ እዛው ሊጉ ላይ ይቆይላችሁ !

Yonisebeta [972 days ago.]
 @tanoo....abooo atdeberen club ena national team leyeteh eweke. manim geba manim ethiopia hagerachin mashenefua new yemifelegew ! hulgize ant sel ant club techawache new yemetawerawe. Mamush yalewim ewnet new abooo tefatannnn ethiopiawi aydelehem ende ?! lengeru semeh erasu tanoo new ! i think Nepali or Bangeladesh neger nehe ! lol

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!