ለባለውለታዎች የተሰጠ የመጀመሪያው አደራ
ሰኔ 18, 2007

ይርጋ አበበ

ታሪክ ጌትነት ከሳላዲን ባርጌቾ እና ሌሎች ሶስት የክለቡ ጓደኞቹ ኋላ በመሆን የዋልያውን የግብ ክልል በንቃት እየጠበቀ ነው። በአራት የደደቢት ተጫዋቾች ማለትም ተከላካዮቹ ስዩም ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነ እና ተካልኝ ደጀኔ እንዲሁም በግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት የተከበበው የቀድሞው የኢትዮጵያ መድንና የውሃ ስራዎች ፍሬ አዲሱ የፈረሰኞቹ የኋላ ደጀን ሳላሃዲን ባርጌቾ የተከላካይ መሰመሩን በአደራነት እየተወጣ ነው። ከሳላሃዲን በእድሜም በሰውነት ግዝፈትም የሚስተካከለው ጋቶች ፓኖም ደግሞ ከኣራቱ ተከላካዮች ትንሽ ወደ ፊት ገፋ ብሎ የቡድኑን ተከላካይና አጥቂ መስመር ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

ከሶስት የተለያዩ ክለቦች ጋር አራት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት ብቸኛ የሆነው የ2007 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች በሀይሉ አሰፋ ደግሞ ከቡድን አጋሩ ምንተስኖት አዳነ እና ከፈጣኑ የቡናዎቹ አማካይ አስቻለው ግርማ ጋር በመሆን የአጥቂውን ክፍል ያደራጃል። ሮጦ መድከም የማያውቀው ወጣቱ የኤሌክትሪክ አጥቂ ራምኬል ሎክ በዚህ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ከሆነው አንጋፋው ቢኒያም አሰፋ ጋር የፊት መስመሩን ይመራል።

ከላይ የተጠቀሰው አሰላለፍ ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኬኒያ አቻው ጋር ሲጫወት ከእረፍት በፊት እስከ 32ኛው ደቂቃ የነበረው አሰላለፍ ነው። ሁለቱን ወጣት አማካዮች ጋቶችንና ምንተስኖትን በአንድ ላይ ማሰለፍ ውጤታማ እንዳልሆነ የተረዳው ጎልማሳው አሰልጣኝ  ምንተስኖትን በማስወጣት ፍሬያማ ኳሶችን የሚጫወተው የመከላከያውን ፍሬው ሰለሞንን አስገባ እና ይበልጥ የአጥቂውን ክፍል በደንብ እንዲያደራጅ አደራ ሰጠው።

ብሔራዊ ቡድኑ የኬኒያ አቻውን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ የመልሱን ጨዋታ ያቀለለበትን ውጤት ሲያስመዘግብ በባህር ዳሩ ሁለገብ ብሔራዊ ስታዲየም የታደመውን ህዝብም ሆነ በቀጥታ በሬዲዮ እና በኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጨዋታውን ሲከታተል የነበረውን ህዝብ ያስፈነደቀ ነበር። ከኬኒያ ጨዋታ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሌሴቶ አቻውን ሁለት ለአንድ የረታው ብሔራዊ ቡድናችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ተከታታይ ድል ማስመዝገቡን ተከትሎ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ መነቃቃትን የፈጠረ ሲሆን በቡድኑ ስነ ልቦና ላይም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል። ይህንን የተረዳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የደስታ ምንጭ የሆኑትን የቡድኑን አባላት የምስጋና ማበረታቻ ሽልማት አበርክቶላቸዋል። እኛም ከዚህ በታች ባለው ጽሁፍ ስለ ሽልማቱ ጠቀሜታ እና የሽልማት አሰጣጥ ስርዓቱን በተመለከተ ሙያዊ ዳሰሳ እናቀርባለን።

የፈጠነው ሽልማት?

ብሔራዊ ቡድኑ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፉን ተከትሎ የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን ይህም ገና ምንም ሳይያዝ የሽልማት ጋጋታ ምን ይሉታል? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ኢትዮፉትቦል ዶትኮምም ሆነ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በግሉ የሽልማቱ መዘጋጀት ስህተት ነው ብለን አናምንም። ሽልማት ማዘጋጀቱ ፈጠነ ለሚሉ ወገኖችም ሽልማት በመዘጋጀቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካለፉት ስህተቶቹ እና ትችቶቹ ተማረ እንላለን እንጅ ገና ሁለት  ጨዋታዎችን በሜዳው ለተጫወተ ቡድን ሽልማት ማዘጋጀቱን አንተችም።

“ሽልማቱ አነስተኛ ነው የሽልማት አሰጣጡም ወጥነት የለውም” የሚሉ አስተያየቶችን የሚናገሩ የስፖርት አፍቃሪያንን ሰምተናል። በእርግጥ ለአንድ የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ 25 ሺህ ብርም ሆነ ሁለት ጎሎችን ላስቆጠረ ተጫዋች 20 ሺህ ብር መሸለም የገንዘቡ መጠን አነስተኛ ሊመስል ይችላል። እኛም  በገንዘቡ ማነስ እንስማማለን። ሆኖም ግን ፌዴሬሽኑ የቡድኑን ውጤት እንደዚህ እውቅና የሚሰጥና የሚያበረታታ ከሆነ በቀጣይነትም የቡድኑ አባላት መነሳሳት ስለሚያድርባቸው ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት የሚፈልጉ ባለሃብቶችን  መሳብ ይችላል። ያኔ የሽልማት መጠኑን ማሳደግ እንደሚል እምነት አለን። እንደታሰበው ቡድኑ ለቻን ዋንጫም ሆነ ለጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ መቅረብ ከቻለ የሽልማቱ መጠን ከአሁኑ  በእጅጉ የተሻለና የተጫዋቾቹንም ህይወት ማስተካከል የሚችል ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ተስፋ እናደርጋለን። አሁን ለተደረገው የማበረታቻ ሽልማት ግን እውቅና እና ክብር እንሰጣለን።

የሽልማት አሰጣጡ መጠን ወጥነት የለውም ለሚለው አስተያየት ግን የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም ሆነ ዝግጅት ክፍላችን የሚለው ይኖራል። ያለፉትን አምስት ዓመታት ብቻ ብንመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥበት ጎል እንደተቆጠረበት ግልጽ ነበር። ለአብነት ያህል በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከናይጄሪያ ጋር በተደረገ ሶስት ጨዋታ ናይጄሪያ ስድስት ጎሎችን አስቆጥሮብን ነበር። የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ካስቆጠረብን ስድስት ጎሎች ውስጥ አራቱን ያስቆጠረው በፍጹም ቅጣት ምት ነው። በእሁዱ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ፍጹም ቅጣት ምት አድኗል በታሪክ ጌትነት አማካኝነት።

እኛም ለፌዴሬሽኑ እንደ ማሳሰቢያ መናገር የምንሻው ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት ሽልማት ሲያበረክት ለምክትል አሰልጣኞች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ መሸለሙን ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ላስመዘገበው ተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት የግብ ጠባቂዎቹ አቤል ማሞ እና ታሪክ ጌትነት ድርሻ ከፍተኛ ነበር። በተለይ በኬኒያው ጨዋታ ታሪክ ጌትነት ፍጹም ቅጣት ምት ከማዳኑም በላይ ከአምስት ያላነሱ ያለቀላቸው የጎል  ድሎችን አድኗል። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች ብዙም ያልተለመደ እና አዲስ ክስተት ነው ማለት ይቻላል። ለግብ ጠባቂዎቹ መሻሻል የግብ ጠባቂዎቹ አሰልጣኝ ዓሊ ረዲ እገዛ ከፍተኛ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

ስለዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሁለቱ ምክትል  አሰልጣኞች የተለያየ መጠን ያለው ሽልማት ማበርከቱ ምክንያታዊ ሆኖ አላገኘነውም። ምናልባት ፌዴሬሽኑ አሳማኝ ምክንያት ካለው ሊነግረን ይገባል ካልሆነ ግን እንደዚህ አይነት ትንንሽ የሚመስሉ “መለያየቶች” ልዩነቶችን የሚያሰፉ  ስህተቶች ናቸውና በጊዜ ሊታረሙ ይገባል።

ሌላው ፌዴሬሽኑ ወደፊት እንዲያስብበት የምንፈልገው “የልዩ ሽልማት ተሸላሚ” ብሎ ሽልማት እንዲያዘጋጅ ነው። ይህም ማለት ፍጹም ቅጣት ምት ለሚያድን ግብ ጠባቂ፣ ጎል ላስቆጠረ ተጫዋች፣ ለጎል የተመቸ ኳስ ያቀበለ፣ ጎል ሊሆን የነበረን ኳስ ያደነ እና በእለቱ ኮከብ ሆኖ የዋለን ተጫዋች ልዩ ማበረታቻ  ቢሸልም መልካም ነው። ይህ ደግሞ በሌሎች ዓለማትም  የተለመደ ሲሆን የተጫዋቾችን ሞራል ማነሳሳት እንደሚችል በጥናት የተረጋገጠ እውነታ ነው።

ቀጣይ የቤት ስራ

በሁሉም የስፖርት ቤተሰብና ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚጠበቀው የቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደ ናይሮቢ ተጉዞ ከሃራምቤ ኮከቦች ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል። ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ደግሞ ከአልጄሪያ እና ሲሸልስ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ይጠብቀዋል። እነዚህን የመጀመሪያ የቤት ስራዎች በድል መወጣትና የስፖርት አፍቃሪውን ደስታ ማስረዘም  ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ የታዩ ክፍተቶችን በተለይም ኳስ ፈጣሪ አማካይ ተጫዋች እጥረት እና ጎል አስቆጣሪ አጥቂዎችን እጥረት በሚገባ ለመፍታት ነገ የሚጀመረውን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ጨምሮ በቡድኑ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችንም ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ማድረግ የአሰልጣኞቹ የቤት ስራ ነው።

የትናንቱ ሽልማት ዓላማም በተመዘገበው ውጤት በመደሰት ሳይሆን ለቀጣዩ ጉዞ አደራ ለማስቀመጥ እንደሆነ በቡድኑ አባላት ዘንድ ሊታወቅ ይገባል። “የዋልያዎቹ አባላት ጎረቤታችን ኬኒያን ጨምሮ ሌሴቶን በማሸነፋችሁ ባለውለታችን ናችሁ። ነገር ግን ይህ ስራችሁ በቂ አይደለም ለአራተኛው የቻን ዋንጫ እና ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንድታደርሱን አደራ እያልናችሁ ነው” የሚል አደራ ነው።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
sami [904 days ago.]
 Our national team missed so much Adane Girma ! Aduuuuuuu pls come back ! Adane Girma he can play every where except goal keeper !

FUTMALL [894 days ago.]
 You started it ! FUTMALL https://www.linkedin.com/in/futmall

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!