ክለቦችንና ፌዴሽኑን ያጨቃጨቀው የተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ
ሰኔ 25, 2007

“ችግር እኮ ተከስቷል ያንን ይዘን ወደ ፊፋ  እንሄዳለን ወይም አንሄድም የሚለው ከሚያመጣው ተፅእኖ አኳያ ነው የምናየው።" መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቦርድ ፕሬዘዳንት

 
መጀመሪያም ቢሆን ይህ እቅድ እንዲፀድቅ የጠየቁት ክለቦች ናቸው። አሁን መብቱ የክለቦች ነው። ፌዴሬሽኑ የክለቦችን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ነው። የኢት. እግ. ኳስ. ፌዴ  የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ

 
በፀደቀ መመሪያ ላይ እንደገና ልንወያይ አይገባም ነው። ጸድቆ ወደ ተግባር ይገባ ተብሎ ተነግሮናል መመሪያውም ተሰጥቶናል። አቶ ገዛሃኝ ወልዴ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ

 
ካደረጉት 3ትም ሆነ 5ት ልዩነት የለውም እኛ ሁሉንም ለመቀበል ችግር የለብንም ፌዴሬሽኑ የሚወጣቸውን መመሪያዎች የመተግበር ድፍረቱ ሊኖረው ይገባል የሚል አቋም ነው ያለን። አቶ ሚካኤሌ አምደመስቀል የደደቢት እግርኳስ ክለብ ቴክኒካል ደሪክተር

በኛ በኩል ቀደም ሲል ከሶስት ጊዜ በላይ ለፌደሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተናል። እንደ ባለድርሻ አካል ድምጻችን ሊሰማ ይገባል። አቶ ሰለሞን በቀለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ

ፈለቀ ደምሴ

ሰሞኑን በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ዝውውር ክለቦች ስለሚያዘዋውሯቸው የውጭ አገር ተጫዋቾች ቁጥር ዙሪያ በተነሳው ውዝግብ እና ውዝግቡን ለማብረድ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዲሳ ያደታ በተገኙበት ስብሰባ የኢትዮጵያ ቡና እና የደደቢት ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የዝግጅት ክፍላችን ባልደረባ የሚመለከታቸውን የክለብና የፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎችን አነጋግሯቸዋል። የቃለ ምልልሳቸውን ሙሉ ሃሳብ እነሆ።

ኢትዮ ፉትቦል፡- ወደ ጥያቄዎቼ ከማምራቴ በፊት በቅድሚያ ቃለመጠይቁን ለመስጠት ስለፈቀዱልኝ  በኢትዮፉትቦል ዶትኮም አንባቢያን ስም ላመሰግንዎት እወዳለሁ።

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
                               
Ethiopian Coffee Sport Club President

ኢትዮ ፉትቦል፡-  በትላንትናው ዕለት ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በተደረገው የፕሪሚር ሊግ ክለቦች ተጠርተው በረቀቀው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ሲወያዩ የኢትዮጵያ ቡና እና የደደቢት ተወካዮች ስብሰባውን ለቃችሁ እንደወጣችሁ ተሰምቷል፡፡ ስብሰባውን የጠራው አካል ማነው? የእናንተስ ቅሬታ ምን ነበር?

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- ስብሰባውን የጠራው አካል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ማን እንደፈረመው ግን አላውቅም። ዋናው ጸሐፊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። እኛ ለቀን የወጣንበት ምክንያት የአካሄድ ችግር አለበት በሚል ነው። የአካሄድ ችግር ደግሞ ነገ የአገሪቱን እግር ኳስ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይወስደውና እኛ ደግሞ እዛ ውስጥ መገኘት ስላልፈለግን ነው ለቀን የወጣነው።

ኢትዮ ፉትቦል፡-  የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዲሳ ያደታ በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። እሳቸው እናንተ በነበራችሁበት ሰዓት ስብሰባውን መርተዋል። ጫና ፈጥረዋል?

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- እንደሱ አይደለም። በመቀመጣቸው ብቻ የትላንቱ ስብሰባ የተመራው በሦስት ሊቀ መንበር ነው አቶ ዘሪሁን በቀኝ በኩል፣ በመሃል አቶጁነዲን በግራ በኩል እንዲሁም ክቡር አቶ አብዲሳ ያደታ ነበሩ እኛ የምናየው ስብሰባውን የመምራት ሥራ the chairmanship በሦስት ሰዎች እንደተያዘ ነው።

ኢትዮ ፉትቦል፡- አካሄዱ አግባብ አለመሆኑን ከመውጣታችሁ በፊት ጠይቃችሁ ነበር።

መቶ አለቃ ፈቀደ፡-  እሱን በተመለከተ እኛ በዚህ ትንሽ ጉዳይ ክቡር ኮሚሽነር ሊገኙ አይገባም ነበር ብለናል።

ኢትዮ ፉትቦል፡- ብዙ ጊዜ እንደምናየው በተለያዩ መድረኮች እና ጠቅላላ ጉባኤ ሳይቀር የስፖርት ኮሚሽን ተወካዮች ይገኛሉ ክለቦችም ቅሬታ ሲኖራችሁ ለስፖርት ኮሚሽን ታሳውቃላችሁ የትናንቱ ውይይት ምን የተለየ ነገር ነበረው?  

መቶ አለቃ ፈቀደ ፡- ለብቻቸው ከመድረኩ ውጪ መቀመጥ ነበረባቸው።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- የእናንተ አቋም የስፖርት ኮሚሽን ጣልቃ ገብቷል የሚል ነው።

መቶ አለቃ ፈቃደ፡-  አዎ።

ኢትዮ ፉትቦል፡- ውይይቱ ላይ ያልተስማማችሁ ነገር ነበር ካለስ ምንድን ነው?

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- ይህ ጉዳይ የተጫዋቾች ዝውውር ቁጥርን የሚመለከተው ከቀረበ ወደ 3ኛ አመት ይሆነዋል። በተለያየ ጊዜ ይነሳል ግን እነ አቶ ሳህሉ ፌደሬሽኑን ይመሩት በነበረበት ጊዜ ነው የተጀመረው። የአሁኑ አመራር ፌዴሬሽኑን ሲረከብ ደግሞ ፋይሉ ጠፋ ተባለ ስለዚህ ጉዳዩን እንደ ገና ከዜሮ “ሀ” ብለን መጀመር ነበረብን። “ሀ” ብለን ብንጀምርም እንደገና ሰነድ አልተገኘም ተባለ። ፌዴሬሽኑ ተነጋግሮበት ኮሚቴ አቋቁሞ ክለቦች አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጎ ብዙ ሂደት አልፎ ነው እዚህ የደረሰው ይሄ ጉዳይ ፀድቆ ከሀምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል። ገና በተግባር ሳይፈተሽ የቅ/ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ለስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ ፃፈ በዛ መሰረት ስብሰባ ተጠራ።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ የሚለው ስፖርት ኮሚሽን  የተጠራው እንደ ታዛቢ ነው?

መቶ አለቃ ፈቃደ ፡- አይ እንደዚህ አይነት ማፈግፈግ ችግር እኮ ተከስቷል። ያንን ይዘን ወደ ፊፋ  እንሄዳለን ወይም አንሄድም የሚለው ከሚያመጣው ተፅእኖ አኳያ ነው የምናየው።

ኢትዮ ፉትቦል ፦  የተጫዋቾች የዝውውር ጉዳይን በተመለከተ በተጫዋቾቹ በኩል እኛን አላማከለም የሚል ነገር አለ?

መቶ አለቃ ፈቃደ፡- እኔ እዚህ ውሰጥ አልገባም የአካሄድ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- የአካሄድ ጉዳይ ብቻ ነው እንጂ ለውይይት በቀረበው ጉዳይ ቅሬታ የላችሁም? ኢትዮጵያ ቡናን የሚወሰነው ማሻሻያ የሚጎዳው ነገር ይኖራል?

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- እኛ የምንለው ኢትዮጵያ ፉት ቦል ፌዴሬሽን ውስጥ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሁሉንም ነገር አጥንቶታል ያጥናት የእኛን አቋም ነው የምነግርህ ክለቦችን እንዲጎዳ አንፈልግም። የተጫዋቾችንም ጥቅም እንዲጎዳ አንፈልግም። ነገር ግን ቅሬታ አለኝ የሚል አካል ካለ ደግሞ ማቅረብ ያለበት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እነሱ የሚሉት ምንድን ነው?

መቶ አለቃ ፈቃደ፡- ማንም ምንም ይበል የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ጋር ተጀምሮ ማለቅ አለበት። እኔ ደብዳቤ አስገብቼ ነበር መልስ አልተሰጠኝም ቅር ባለኝ ቁጥር ፌዴሬሽኑን ትቼ ስፖርት ኮሚሽን ልሂድ ነው? በእኔ ጥያቄ ምክንያት ደግሞ የፕሪየሚየር ሊግ አባላት እና ፌዴሬሽኑ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው? ይሄ አይነት አካሄድ አያዋጣም። ችግሩ ትልቅም ይሁን ትንሽ ራሳችን ፊት እናቅርብ ራሳችን በአስተዋይነት እንጨርሰው ነው የኛ አቋም ይሄ ነው።
 
ኢትዮ ፉትቦል ፡-  ኢትዮጵያ ቡና ክለብ የኢንተርናሽናል ተጫዋቾች ቁጥር ገደብ ሦስት ቢደረግ አይጎዳም ወይስ ተጠቀሚ ነው የሚሆነው?

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- ሶስት ያስፈልገናል ብሎ ካለ እንቀበላለን። አይ ሦስት አይደለም ኢትዮጵያ በኳስ ደክማለች 11 ነው የሚያስፈልገን ካለን ደግሞ እንቀበላለን።

ኢትዮ ፉትቦል ፡-
ኢትዮጵያ ቡና ወደ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ውድድር ሲገባ አሁን ባለው እና በፀደቀው ህግ አይጎዳም?

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- ዝርዝር ውስጥ አልገባም አታስገባኝ እኔ በፕሪንስፕሉ ነው መልስ የምሰጥህ።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እዚህ ላይ መቶ  አለቃ እናንተ ያንን ስብሰባ ረግጣችሁ የወጣችሁበት ምክንያት የአካሄድ ችግር ብቻ ነው ወይስ ሌሎችም ችግሮች አሉ?  

መቶ አለቃ ፈቀደ ፡-  እኛ ምንም ችግር የለብንም። ከዚህ በፊት ግን አምቦ ላይ በተደረገ ስብሰባ  በአካሄድ ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ ሁለት አመት ተቀጥታለች። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር በነበበሩበት ጊዜ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንሰትሩ አቶ መላኩ ጴጥሮስ በመገኘታቸው። የትላንቱም እኮ ቢሆን እኛ ተንቀሳቃሽ ፎቶ ግራፍም አለን ለምን ይሄ ይሆናል ነው። የጉዳዩ ትልቅነት  እና ትንሽነት አይደለም። በአካሄድ አንደኛ የኢትዮጵያ ፉት ቦል ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንቡ የፊፋ ዳይሬክት ቅጂ ነው። የFIFA ማንኛውም ደንብና መመሪያ ፌዴሬሽን ውስጥ ተጀምሮ ፌዴሬሽ ውስጥ አልቆ ወደ FIFA ተልኮ ነው የሚያልቀው። ለምን ይሄ procedure  ይጣሳል? ነው። አሁን የሌላ ክለብ ስም አልጥራ እንጂ በተከፈተው መንገድ እኔም ቅር ባለኝ ቁጥር ስፖርት ኮሚሽን ልሄድ ነው ማለት ነው። ይሄ አይነት አካሄድ አያዋጣም ነው የምንለው።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ፊፋ ጣልቃ የሚገባው ሁለት ወገኞች ሳይስማሙ ቀርተው ወደ ፊፋ ክስ ካመሩ ነው?

መቶ አለቃ ፈቀደ ፡- ሳይስማሙ አይደለም ስለማንም ላውራ ያአካል ከእኔ ጋር መገናኘት የለበትም ነው?

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ከዚህ ቀደም አስቸጋሪ ጉዳይ አጋጥሟችሁ ወደ ካፍ እና ፊፋ ከመሄዳችሁ በፊት   ለስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ የፃፋችሁበት ጊዜ የለም?  

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- ጽፈናል ለምሳሌ አልታየም እንዲታይ አድረጉልን የሚል እንጅ ሶስት የሆነው አምስት ይሁንልን የሚል ነገር ግን የለም።

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  
አመሰግናለሁ መልእከት ከለዎት

መቶ አለቃ ፈቀደ፡- እኔምአመሰግናለሁ

ከዚህ በታች ደግሞ ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ ሚኬኤሌ አምደብርሃን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እናቀርባለን መልካም ምንባብ።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እና ተጫዋቾች ጋር በረቀቀው ሰነድ ላይ ለመወያየት ፌዴሬሽኑን ስብሰባ ጠርቶ ነበር ፡፡ የእናንተ ክለብ ስበሰባውን አቋርጣችሁ ወጥታችኋል፡፡ ስብሰባውን ማነው የጠራው እናንተስ ልትቃወሙ የቻላችሁበት ምክንያት ምንድነው ?
                               
Ato Mickias

አቶ ሚካኤል ፡- በተጫዋቾች ዝውውር ላይ ወጥ የሆነ መመሪያ ስላልነበረ በፊት የነበረው የዝውውር ስርዓት ፕሮፌሽናል ስላልሆነ የፊፋን መርህ የተከተለ ስታንዳርድ የሆነ የዝውውሩ መመሪያ አባሪ ተደርጎ ተጫዋቾችንም ይጠቅማል፡፡ ክለባችንም ይጠቅማል በሚል ጥናት ተካሄዶ ከዛ ኮሚቴ ተዋቅሮ የዝውውር ፕሮፖዛል እንዲያቀርብ በማድረግ አንድ ሶስት አራት ልጆች ተመርጠው የፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ም/ፕረዚዳንት እና አመራሮች ባሉበት ኮሚቴ በማዋቀር፤ የተለያዩ ተሞክሮዎችን የደቡብ አፍሪካ፤ የሱዳን፤ የጋና ብቻ የብዙ አገሮችን ሳምፕል አይተው ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በማየት የተወሰነ ረቂቅ ሰነድ አዘጋጁ፡፡ በቀረበው የዝውውር ረቂቅ ሰነድ ላይ አካቶ ውይይት አዘጋጅተው በመጨረሻ ሁሉም ክለቦች ከተወያዩ በኋላ መመሪያ ሆኖ በስራ አስፈፃሚ ፀደቀ፡፡ ይህ የፀደቀው መመሪያ በሸኝ ደብዳቤ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ጥብቅ ደብዳቤ ተፃፈልን፡፡ ይህ ደብዳቤ ከወጣ በኋላ በዮርዳኖስ ሆቴል እዛም ተሳትፈን የዝውውሩ ሂደት ላይ የተለያዩ ገለፃዎች ተደረገዋል፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  የወጣው መመሪያ ላይ እናንተ ቅሬታ አልነበራችሁም? በተጫዋቾች ዝውውር ላይ የተቃወማችሁት ነገር አልነበረም ሙሉ በሙሉ ተስማምታችሁ ተቀብላችሁት ነበር?

አቶ ሚካኤል ፡- አይደለም ሙሉ በሙሉ ተስማምተናል ለማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አንዱ 98% ሊመቸው ይችላል ሌላውም እንዲሁ ግን “መቶ በመቶ ይህ ለኛ የሚመች ነገር ነው” ብለን አንልም የወጣው መመሪያ overall የሚያስኬድ ነው በማስ የፀደቀ ነው፡፡ የማይመቸን አንዳንድ ነገር ቢኖር እንኳን ውይይት ተደርጎ በብዙሃኑ ተቀባይነት አግኝቶ በስራ አስፈፃሚ ፀድቆ ይተግበር ከተባለ አይ 90% ያስኬደናል ይህች ግን አታስኬድም ማለት አንችልም፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  የተሰወነውን ነገር የማስፈፀም ግዴታ ሁሉም ክለቦች አለባቸው ግን እዛ ላይ ምንም እንኳ ብዙሃኑ ቢወስንም እናንተ 98% ተስማምታችሁ 2% ካልተስማማችሁ እዚህች ቦታ ላይ እኔ ቅሬታ አለኝ  ብላችሁ ያደረጋችሁት ነገር አለ ?

አቶ ሚካኤል ፡- የለም

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  ደደቢት ትልቅ ነገር ይዞ የተነሳ ክለብ ነው፡፡ በኢንተርናሽናል ወደ ውድድር ገብቷል፡፡ እናንተ ደግሞ እዚህ ውድድር ላይ ስትገቡ ያየችኋቸው ነገሮች አሉ አስካሁን አንድ ዙር አልፏል ሁለተኛ ሦስተኛ ዙር ለማለፍ እና በአፍሪካ ሻንፒዮንስ ሊግ ለመፎካከር አሁን እኛ አገር ባለን የተጫዋቾች ጥራት  ወደ ምዕራብ  እና ሰሜን አፍሪካ አገራት ስትሄዱ ችግር አይገጥማችሁምን ?

አቶ ሚካኤል ፡- አይፈጥርም ዋናው ነገር በአገር ውስጥም በውጪም ተጫዋቾች ስታሰባስብ በጣም ጥሩ ብቃት ያላቸው ፤ ልምድ ያላቸው ከውጪም እዚህ በአገር ውስጥ ልታገኛቸው የማትችል ጠንከራ ውስን የሆኑ እንደ ሼይቩ ጅብሪል እና ሳሙኤል ሳኑሚ አይነት ወሳኝ ተጫዋቾች ካመጣህ የግድ ኮታ ስላበዛህ እዛ አይደለም፡፡5  አምስትም ሆነ ሶስት ያን ያህል አደጋ የሚፈጥር አይደለም፡፡ የአገራችን ወጣቶች ላይ እንዲሰራ የሚገፋፋ ነው የረጅም ርቀት ሳይሆን አጭር ርቀት ላይ የተወሰነ ነገር እንድንሰራ የሚያደርግ ነው ያን ያህል በውጭም ተሳትፏችን ላይ ተፅእኖ የሚፈጥር አይደለም፡፡ ጥገኛ እየሆንን እንድንሄድ ነው የሚያደርገው ያንን ያህል ችግር የለውም ብለን ስላመንን ትኩረትም አልሰጠነውም፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- የትናንትናው ስብሰባ የስፖርት ኮሚሽን ጣልቃ ገብነት አለ የሚል ነው፡፡

አቶ ሚካኤል፡- አይደለም የProcedure በቅደም ተከተል የሚሰሩ ነገሮች ነው፡፡ የስፖርት ኮሚሽን ጣልቃ ገብነት ብቻ ሳይሆን አንዲውም እሱ Secondary ሁለተኛ ነው ትኩረትም አልተሰጠውም መመሪያ ውይይት ተደርጎ ጥናት ተካሄደ Official Assign የተደረጉ አካላት ያፀደቀውን መመሪያ ወደ ተግባር ይግባ መመሪያው ወጥቶ ደብዳቤ ተፅኖ መመሪያው አተገባበር ላይ ስልጠና ከተሰጠ በኋላ ወደ ተግባር መግባት ነው፡፡ ከተገባ በኋላ ችግር ከተፈጠረ እንደገና ወደ  Procedure ተመልሶ እያወያየ የመፍትሄ ሃሳብ እያበጀ መፍትሄ እየሰጠ ይሄዳል፡፡ ፌዴሬሽን ሙሉ ስልጣን አለው፡፡ አሁን ግን የሆነው ምንድነው? ወደ ስራ ሳይኬድ ምንም ነገር ሳይታይ አቤቱታ ስላቀረበ በአንድ ጊዜ መመሪያው ለምን ይቀየራል፡፡ የInterest  ጥያቄ ሳይሆን የProcedure  ጥያቄ ነው፡፡ አሁንም “አምስት ካደረጉት ሶስትም ከሆነ ልዩነት የለውም እኛ ሁሉንም ለመቀበል ችግር የለብንም ፌዴሬሽኑ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች የመተግበር ድፍረቱ ሊኖረው ይገባል”የሚል አቋም ነው ያለን፡፡

ኢትዮ ፉትቦል፡- የትናንትናውን ስብሰባ እናንተ ረግጣችሁ ከመውጣታችሁ በፊት ፌዴሬሽኑ ሊወስን ሳይሆን ሊያወያያችሁ ነው አሁንም አልወሰነም ይመስለኛል፡፡ እናንተን 14 የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ይሄ ቢሆን እንዴት ይሻላል ብሎ ለማነጋገር ነው እናንተ ደግሞ ንግግሩ ሳይጀምር ነው የወጣችሁት ለምንድን ነው?

አቶ ሚካኤል ፡- የኛ አቋም ወቅቱ የውይይት ወቅት አይደለም ነው፡፡ የትግበራ ወቅት ነው ወደ ኋላ ተመልሰን የምንወያይበት ወቅት አይደልም፡፡ ወደ ስራ ተገብቶ  የተወሰነ ነገር ተግባራዊ ተደርጎ ከዚህ Partition  Negative  አይተን እንማርበታለን፡፡ ይህ Bible ወይም ቁራን አይደልም ይስተካከላል ግን almost ሁሉም ክለቦች ተቀብለውናል፡፡ ፌዴሬሽን አስመልክቶ አንድ ክለብ ወደ መንግስት ሄዶ አቤት ስላለ ተመልሰን እንየው የሚለው ውይይት ወቅት ነው ወይ የትግበራ ወቅት ስለሆነ እኛ መመሪያውን ለመትግበር እንወጣለን እንጂ ለውይይት ወደ ኋላ አንመለስም ብለን ነው የወጣነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል፡-  የስፖርት ኮሚሽኑ ኮሚሽነር በወቅቱ ተገኝተው ነበር፡፡ እኛ  ደግሞ ብዙ ጊዜ እንደምናየው ሌሎች ክለቦችም እናንተም ፕሮግራም ሲኖራችሁ በፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ አንዳንድ ሃሳቦችን በመስጠት እና በእንግድነት ይሳተፋሉ የትናንትናው ላይ ለየት ያለ የማስገደድ ነገር ታይቷል፡፡

አቶ ሚካኤል ፡- በፍፁም

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እንደሱ ከሆነ እናንተ ለምን ቆይታችሁ ችግራችሁን ለማስረዳት አልሞከራችሁም ?

አቶ ሚካኤል ፡- ሀሳባችንን አስረድተን ነው የወጣነው ይህ ስብሰባ Legal ስብሰባ አይደለም፡፡ ተገቢ ስብሰባ አይደለም፡፡ እንጂ “የስፖርት ኮሚሽኑ እንደዚህ እንደዚህ አሉ” አላልንም አይ ተጓባዥ እንግዳ ናቸው ከተባለ ቅድምም ብሄያለሁ እንደ ትልቅ ነገር አልወሰድነውም የኛ ጥያቄ የመርህ ጥያቄ ነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  ቅ/ጊዮርጊስም ያቀረበው ጥያቄ የውጭ አገር ተጫዋቾች ቁጥር ከሶስት ወደ አምስት ይደረግልን ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ያላግባባው ውይይት የተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ ነው፡፡ የወጣውን የዝውውር ጉዳይ እናንተ አምናችሁበት ተቀብላችሁታል፡፡

አቶ ሚካኤል ፡- አዎ ከአሁን በፊት የነበረው የዝውውር አካሄዳችን በጣም የጠራ አይደለም ችግር ያለበት ነው፡፡ እኛ እንደ ደደቢት የዝውውር ብር አከፋፈሉ በመመሪያው እንኳን ባይካተት የእኛ ፍላጎት አንድ ተጫዋች ሁለት አመት እንዲጫወትልህ ተነጋግረህ በይጫወትልህ ብርህ ቀልጦ ይቀራል ማለት ነው ለምሳሌ ፈለቀ ስራ ብትቀጠር በየወሩ ይሄ ይከፈልሃል፡፡ የሰራኸውን ያህል  ታገኛለህ፡፡ ጥሩ ነገር ከሰራህ ደግሞ ተቋምህ ጨምሮ እያበረታታህ ትሄዳለህ የምታገኛው በሰራኸው ልክ ነው፡፡ የኛ ሲስተም ግን አሁን ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ለሚሰራውም ለማይሰራውም አፍሶ የሚሰጥ ነው፡፡ እና ምን ችግር ይፈጥራል ይሄንን ቃላቸውን አክብረው በስርዓቱ የሚያገለግሉ ብዙ ተጫዋቾች አሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ብራቸውን ከያዙ በኋላ ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ሌላ አድርገው ተጎዳሁኝ፤ አመመኝ ቤተሰቤ ችግር አጋጠመኝ በማለት ወደ ሌላ አለም የሚገቡ አሉ እንደገቡ ወደ ሌላ የሚሄዱ አሉ ይህንን ሁሉ ስርዓት የሚያስይዝልን ሰው በሰራው ነገር መክፈል አለበት፡፡ የኛ አቋም እና ፍላጎት ደረቅ ደሞዝ ብቻ ባይሆን ደስ ይለናል፡፡ ለምን? በለኝ እኔ እና አንተ ቢሮ ላይ ነው የምንሰራው ቢሮ ላይ ስንሰራ ያን ያህል ጉዳት የለውም፡፡ ግጭትም የለውም ተጫዋች ወደ ሜዳ ሲገባ ጉዳት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ እስከ ህይወት መስዋትነት የሚያስከፍል ነው፡፡ ሰላማዊ ጦርነት እንደሚባለው ነው፡፡ ስለዚህ ተጫዋች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት በሁለት አመት አንድ ሚሊዮን ብር ያገኝ የነበረ 25% ቀድሞ ቢሰጠው ትንሽ እንዳው መኪና፤ ቤት ለራሱ የሚሆን ነገር የሚፈልጉትን Luxury  ትሁን አንድ ነገር ያገኛል የቀረችው 750,000 ሺህ ለ24 ወር ተካፍሎ 30,000 የሚደርሰው ከሆነ በየወሩ ቢከፈለው የሚል አቋም አለን፡፡ ምክንያቱም ትልቅ ብር ወስደው ሁለት ጨዋታ ያልተጫወቱ ተጫዋቾች በየክለቡ አሉ ፡፡ ግን ይሄ ደግሞ ደሞዝ ብቻ የሚለው ትንሽ ተጨዋቾቹን ይጎዳል እና የተወሰነ ፐርሰንት ቢሰጣቸው ነው፡፤ የምንለው ምክንያቱም ጉዳት እና ግጭት ያለበት  ጨዋታ ነው፡፡ ያን ጊዜ ነፃ ሆነው ይጫወታሉ፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እናመሰግናለን  ተጨማሪ መልእከት ካለዎት

አቶ ሚካኤል ፡- አመሰገናለሁ ጨርሻለሁ፡፡

አቶ ገዛኸኝ ወልዱ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ እና የጥናት ቡድኑ አባል ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ደግሞ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ትናንትና ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት አቋርጠው የወጡት ስብሰባ  አለ ምክንያቱ  ምንድነው? ቅሬታው ምንድነው?
                               

አቶ ገዛኸኝ፡- ስብሰባው ትክክል አይደለም።

ኢትዮ ፉትቦል፡- ማነው የጠራው?

አቶ ገዛኸኝ፡-  ፌዴሬሽኑ ነው የጠራው ። በፀደቀ መመሪያ ላይ ማወያየት እና አወያይ ሆነው  የመንግስት አካላት መገኘታቸው ትክክል አይደለም።

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  በእነሱ በኩል ታዛቢ ናቸው እንጂ አወያይ አይደሉም  ነው የሚሉት

አቶ ገዛኸኝ፡- ለምን ማጣራት ያስፈልጋል? የክለባችን፤ የፌዴፌሽን ጉዳይ ነው ስለዚህ መጥተው የማግባባት ስራም ሆነ የማጣራት ስራም አይጠበቅባቸውም። የአገሪቱን ህግ የጣሰ ነገር ተደርጎ ከሆነ ትክክል ነው፡፡ የፕሮሲጀር ነገር ከሆነ የአገሪቷን ህግ የጣሰ አይደለም ፌዴሬሽኑ የራሱ ህግ አለው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  ወደኋላ ልመልሰዎት እና የስፖርት ኮሚሽኑ ብዙ ጊዜ ድጋፍ ሰጪም ነው ያግዛል እና እናንተም በተለያየ ችግር ሲደርስባችሁ ወደ ስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ ትፅፋላችሁ አማክሩልን፤ አቅጣጫ አስይዙልን ያላችሁበት ጊዜ አለ በዚህኛው ላይ ለየት ያለው ነገር ምንድነው

አቶ ገዛኸኝ፡- አንደኛ ነገር በፀደቀ መመሪያ ላይ እንደገና ልንወያይ አይገባም ነው፡፡ ፀድቆ ወደ ተግባር ይገባ ተብሎ ተነግሮናል መመሪያውም ተሰጥቶናል፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ያፀደቀው ማነው

አቶ ገዛኸኝ፡- ፌዴሬሽኑ  ከሃምሌ አንድ ጀምሮ ስራ ላይ ይውላል የሚል ደብዳቤ ሰጥቶናል። ስለዚህ ለምን ወደኋላ ይመለሳል? ነው።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- መመሪያውን ጥናት ካደረጉት ውስጥ አንዱ እርሰዎ ነበሩ  ጥናቱ  ሲጠና የግል አስተያየተዎትን ሰጥተዋል። አጨቃጫቂው የሆነው አምስት ፕሮፌሽናል ተጫዋቶችን መገደቡ ላይ ነው ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ራዕይ ያለው ክለብ ነው፡፡ በርካታ ደጋፊዎችም አሉት፡፡ እና ወደ ፊት ትልቅ ደረጃ የመድረስ ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀስ ክለብ አሁን ባለው የሊግ ደረጃ ባሉን  ተጫዋቾች  እነ ደደቢት እና ቅ/ጊዮርጊስ እንኳን የትም ሳይደርሱ በሁለተኛ ዙር ላይ ሲያቋርጡ ነው የምናየው  ብዙ አፍሪካ አገሮች በተለይ የምእራብ እና የሰሜን አፍሪካ አገሮች አምስትም ሰባትም ስምንትም የሚይዙበት ሁኔታ  በግለዎ  በሶስት ተጫዋቾች ተገድበው ክለቦቻችን ረጅም ጉዞ ይጓዛሉ ብለው ያስባሉ?

አቶ ገዛኸኝ፡- እየውልህ ይሄ እኔ በግል አቋሜ  አሁን ያልኳቸው ከሰሜን አፍሪካ ሀገሮች  ግብፅ ሶስት ተጫዋቾች ነው የሚፈቅዱት ከዛ በኋላ ደግሞ በረኛ ማምጣት አትችልም መመሪያውን ላሳይህ እችላለሁ፡፡ አልጄርያ አራት ይቻላል ደቡብ አፍሪካ አምስት ይችላሉ ኬንያ እየተጨቃጨቁ ነው በአምስት እና በሰባት። ይሄ መመሪያ እንደዚህ አይነት አሰራሮች እንደ አገሩ ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል፡፡ የእኛ አገር ፉትቦላችንን ማሳደግ የምንችለው ፕሮፌሽናል ተጫዋቶችን በማምጣት ነው ወይንስ ከታች ከመሰረቱ ላይ በመስራት ነው? ለምሳሌ ቅ/ጊዮርጊስም ሆነ ቡና የውጪ ተጫዋቾችን ይዘው የፈለጋቸውን ጥሩ ውጤት ቢያመጡ ብሄራዊ ቡድናቸው እኮ የተሻለ ደረጃ ላይ አይደርስም፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ መድከም ያለባቸው ግራስ ሩት ላይ ነው። በዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ ያለን ነን አቅማቸው ተመሳሳይ የሆኑ ልጆችን ማውጣት ይቻላል፡፡ ዛሬ እኮ እነ ጋቶች፤ ራምኬል ሎክን  አግኝተናል አይደል እንዴ? በእነሱ አካባቢ ላይ ብትሰራ  ከውጭ አገሮች ተጫዋቾች በላይ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን  ስለዚህ እዛ ላይ ትኩረት አድርጎ እዲሰራ  መመሪያ ሊኖረን ይገባል ከሚል ነው፡፡ በነገራችን ላይ መመሪያ ስታወጣ ክለቦችን ቅ/ጊዮርጊስ ፤ቡናን ደደቢትን መሰረት አድረገህ አይደለም፡፡ እናውቃቸዋለን እኛ ሀገር እየመጡ  ቤት ተከራይተው የሚቀመጡ የውጪ ተጫዋቾች  ተፈጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የስራ እድል መጠቀሚያ አድርገውታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ሁሉ እየገቡ የልጆቻችንን እድል እየዘጉ የፊርሚያ ገንዘብ ማግኚያ መንገድ አደርገውታል የሙስና መንገድ አድርገውታል ስርዓት መያዝ አለበት፡፡

እንዳውም ልንገርህ ቅ/ጊዮርጊስ እኮ በአንድ ተጫዋች ውጤት ይቀይራል፡፡ ሶስት ደረጃቸውን የጠበቁ የእውነት ፕሮፌሽል የሚባሉትን ማለት ነው እንዲሁ መጥተው ተሞክረው የሚሄዱበት አይደለም ልክ እንደ ኦዶንካራ አይነት ፕሮፌሽናል የሆኑ ተጫዋቾችን ማምጣት ይቻላል።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- በእነሱ በኩል የሚሉት ከዚህ በፊት ጥያቄ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ሶስት ተጫዋቾ  አሉ የሚባሉ ይምጡ ቢባል የአገሪቱ ሊግ ከመውረዱ ሁለተኛ ደግሞ ሜዳዎቻችን ብቁ ባለመሆናቸው የፈለግነውን አይነት ብር ብንሰጣቸው እንኳን ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ አይመጡም ነው?

አቶ ገዛኸኝ፡- እውነት ነው፡፡ ልክ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለው ነገር በርካታ ተጫዋቾች ላይመጡ ይችላሉ ከስር በመስራት እና በማሰልጠን ጠንክረን ከሰራን ውጤት ማምጣት ይቻላል።  

ኢትዮ ፉትቦል፡ ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ ክለቦች እዚህ ላይ  ምን ያህል  እየሰሩ ነው?

አቶ ገዛኸኝ፡- እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡ ሁላችንም ጋር ይሄ ነገር የለም  ለውጥ እንዲመጣ ምን  ብንሰራ ይሻላል? በማለት፡ ክለቦች ይህን እንዲሰሩ መመሪያ ላይ  አካተን አስገብተናል፡፡

ኢትዮ ፉትቦል፡- ከታች ከመሰረቱ ላይ ለመስራት ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ከአምስት ወደ ሶስት በመገደብ ወይም በማስገደድ ለውጥ ማምጣት ይችላል?

አቶ ገዛኸኝ፡- ይሄ እኮ የጊዮርጊስ እና የቡና ብቻ ችግር አይደለም፡ የሁሉም ችግር ነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል፡-  ይሄ ግልፅ ነው፡፡ ኢንተርናሽናል ውድድር ያላቸው ክለቦችን በተለይ ጊዮርጊስ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና አንድ እና ሁለት ዙር እየሄዱ በአፍሪካ ደረጃ ውጤት ማምጣት አልቻሉም፡፡ ለዚህም ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ማምጣት ጀመረ ደደቢት፣ ቡና እያለ ሁሉም ክለቦች ማምጣት ጀመሩ፡፡

አቶ ገዛኸኝ፡- ቆይ አንተ እያልክ ያለኸው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያላቸው ክለቦችን የሚገድብ ነው መመሪያው እያልከኝ ነው?

ኢትዮ ፉትቦል፡- እኔ ሳልሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንዳሉት ነው

አቶ ገዛኸኝ፡- የውጪ ተጫዋቾች በማምጣት ነው ውጤት የሚመጣው እያልከኝ ነው?

ኢትዮ ፉትቦል ፡- አይደለም በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከሚያቀርባቸው ምክንያቶች አንዱ እሱ ስለሆነ ነው፡፡

አቶ ገዛኸኝ፡-  ስለዚህ በምንም አይነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውድድር ማድረግ የለበትም ማለት ነው በራሳችን ልጆች የማናምን ከሆነ አደዚህ እያልከኝ ነው በሌላ አነጋገር

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እነሱን እንዳናገርናቸው  ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ስንካፈል ትልቁ ችግር የሀገራችን ሊግ ደካማ ስለሆነ ያሉንም ተጫዋቾች ብቃት አስተማማኝ ስላልሆነ ከሰሜን እና ከምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ጋር ስንወዳደር መፎካከር አልቻልንም ነው የሚሉት?

አቶ ገዛኸኝ፡- የኛ ተጫዋቾች ላይ ጠንክሮ በደንብ ከተሰራ እና የተሻሉ ሶስት ጥሩ ተጫዋቾች ማምጣት ከተቻለ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ ይቻላል፡፡ ጉዳዩ የሶስት እና የአራት ተጫዋቾች ጉዳይ አይደለም፡፡ ለሀገር ይጠቅማል ከተባለ 10 ቢሆንም እኔ ችግር የለብኝም፡፡ ዋናው ችግር የአደራጃጀት ላይ ነው እነ ግብፅ እኮ በሶስት ተጫዋቾች ገድበው በረኛ ማስመጣት ከልክለው በራሳቸው መንገድ ውጤታማ ሆነው እየተወዳደሩ ነው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡-  እነ ግብፅ ግራስ ሩት  ላይ በሚገባ ሰርተው በርካታ አካዳሚዎች ገንብተው በሂደት ወደዚህ መጥተዋል፡፡ እኛ ሀገር በክለቦችም ሆነ በፌዴሬሽን የተሰራ ነገር ሳይኖር ህግ በማውጣት በመገደብ ለውጥ ማምጣት ይቻላል? ምናልባት ጥናቱን ካጠኑት አራት ሰዎች አንዱ እርሰዎ ስለሆኑ ይሄንን እንዴት አያችሁት?

አቶ ገዛኸኝ፡- ማለት መመሪያዎች አደረጃጀቶች ወደዛ ሼር እንድታደርግ ያደርጉሃል፡፡ በሀገራችን ላይ አምስት አደረግከው ሶስት በኛ ሀገር ለውጥ አያመጣም፡፡ አምስት ተጫዋች ይዞ እኮ ጊዮርጊስ ተሳትፏል፣ ደደቢት 4 ይዞ ተሳትፏል፡፡ ንገረኝ ምን ለውጥ መጣ፡፡ እሱ አይደለም ችግሩ መለወጥ ያለበት አሰራሩ እና አመለካከታችን በልጆቻችን ላይ ያለው አመለካከት ለልጆቻችን የምንሰጠው እድል ግራስ ሩት ላይ ብንሰራ በአንድ እና በሁለት አመት ለውጥ ማምጣት እንችላለን እነ ጋቶች፣ እነ ቶክ በሁለት አመት ነው እዚህ ደረጃ የደረሱት፡፡ አስተሳሰቡን መቀየር ነው እኔ አምስት ተጫዋች ማምጣት ላይ ችግር የለብኝም አስተሳሰቡን ካልለወጥን ለውጥ አናመጣም፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እናንተ ጥናቱን በኮሚቴ ስታጠኑ እያንዳንዱን ክለብ ጠይቃችኋል፡፡ የውጪውን ልምድ ማየታችሁ ጥሩ ነው፡፡ አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንስ  አይታችኋል ወይ?

አቶ ገዛኸኝ፡- በመጀመሪያው ውይይት የጊዮርጊስ ተወካይ አቶ ንዋይ ነበር፡፡ አብረን በኮሚቴ ደረጃ ሰርተን በኋላ መመሪያ ይዘጋጅ ለዚህም ፌዴሬሽን ባለሙያዎች ይመድብ ብለን በየክለቡ ተወካዮች ካፀደቅን በኋላ ነው ወደፌዴሬሽኑ የመለስነው

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ከፌዴሬሽኑ የሰማነው አራት ባለሙያዎች እየጠናችሁት እርሰዎ የቡድኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ ከስፖርት ኮሚሽን አቶ አበባው ከልካይ ከአዲስ አበባ ስፖርት  ኮሚሽን አቶ ንጉሴ ዓለሙ መሆናችሁን ነው፡፡

አቶ ገዛኸኝ፡- እኮ እሱ መመሪያ አዘጋጅ ኮሚቴ ነው፡፡ በፌዴሬሽኑ ተመርጠን በክለቦች እና በፌዴሬሽኑ በኩል ያለ እና ጠቅላላ ችግሮችን ካጠና በኋላ መመሪያ አዘጋጅ ኮሚቴ ፌዴሬሽኑ በመረጠን አራት ሰዎች በደብዳቤ ተሰጥቶን በባለሙያ ደረጃ ነው የተመረጥነው እኔም በግሌ ነው ቡናን ወክዬ አይደለም አቶ አበባውም በግሉ እንጂ ስፖርት ኮሚሽኑን ወክሎ አይደለም ሌሎችም እንደዛው ነው የተመረጡት።

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ምናልባት መሀከላችሁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተወካይ ቢኖር የተፈጠረውን ችግር እና አለመግባባት አያጠራውም ይላሉ?

አቶ ገዛኸኝ፡- እሱን ፌዴሬሽኑን ጠይቃቸው፣ ምን አውቃለሁ ይሄ ግን የክለብ ውክልና አይደለም። የባለሙያ ውክልና ነው ማንም አጠናው ማንም ለሀገር የሚጠቅም ከሆነ መቀበል ነው። እኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምርጥ ጥናት አጥንቶ ቢያመጣ ለእግር ኳስ እድገት የሚያስብ ክለብ ነው ብዬ ስለማምን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
ኢትዮ ፉትቦል ፡-  ጥናቱን አጥንታችሁ መቼ ነበር ያስገባችሁት?

አቶ ገዛኸኝ፡- ከጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም በፊት አስገባንላቸው ክለቦች ተጠሩ ውይይት አድርገንንበት ተግባራዊ ይደረጋል ከተባለ በኋላ ሀሳቦች ይሰብሰቡ በመባሉ በርካታ ሰዎች ሀሳብ ሲሰጡ ሚዲያውም ጭምር ተጨማሪ ሀሳቦችን ስለሰጠን የሁሉንም ሀሳብ አካተን ለፌዴሬሽኑ ሰጠን። ፌዴሬሽኑም መጋቢት ላይ ለሁሉም አካላት ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ህጉን አጽድቄያለሁ ብሎ ላከልን። እና አሁን በፀደቀ ነገር ላይ መወያየት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? በፊት እንደውም አንዳንድ ክለቦች አልገባንም ስላሉ ፌዴሬሽኑ ሥልጠና ስጡልኝ ብሎ ከብሔራዊ ሊግ ወደ ሀምሳ ክለቦች ከፕሪሚየር ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በስተቀር ሁሉንም ክለቦች ተገኝተው ስልጠና ሰጥተናል። በሥልጠናው ላይ ጥያቄዎችን በመቀበልና በማስረዳት ተወያይተን የፀደቀን ነገር እንደገና የውይይት መድረክ ለመፍጠር ለምን አስፈለገ? ውሳኔውን ወደ ተግባር ቀይሮ አካሄድ ላይ ችግር ካለ በሂደት ማስተካከል ይቻል ነበር።

ኢትዮፉትቦል፡- ህጉ እንደገና ተሻሽሎ ቢቀርብ በእናንተ በኩል የሚኖራችሁ አቋም ምንድነው?
አቶ ገዛኸኝ፡- እሱ ሲደርስ የምናየው ይሆናል።

ኢትዮፉትቦል፡- እናመሰግናለን። መልዕክት ካለዎት።
አቶ ገዛኸኝ፡- ለጊዜው ይሄን ያህል ይበቃናል። ስለሰጠኸኝ እድል እመሰግናለሁ።

 
ከቅዱስ ጊዮርጊስ  ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ  ሰለሞን  በቀለ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ደግሞ እንደሚከተለው ቀርቧል።
 
 
ኢትዮ ፉትቦል፡-  ለጥያቄ ስለተባበሩን እናመሰግናለን፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን ያሰባሰበ ውይይት ተደርጓል፡ በዚህ ውይይት የስፖርት ኮሚሽን ጣልቃ ገብነት ይታይበታል አካሄዱ ትክክል አይደለም በማለት ሁለት ክለቦች አቋርጠው ወጥተዋል በናንተ በኩል እንዴት አያችሁት? ጥሪውን የጠራውስ ማነው? ስፖርት ኮሚሽን በጉዳዩ ጣልቃ ገብቷል?  
 
 
አቶ ሰለሞን፡- እሺ አመሰግናለሁ በመጀመሪያ ጥሪውን የጠራው የኢትዮጵያ እግር ኳሽ ፈደሬሽን ነው፡፡ ስብሰባውን የመሩት የፌደረሽኑ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አላየንም እግር ኳስ ፈደሬሽን ቀደም ብሎ መመሪያውን ሲያስጠና የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ባለሙያ አቶ አበባው ከልካይ ለአንድ ዓመት ያህል በኮሚቴው ተካተው አብረው ሲያረቁ ነበር፡፡ በተለያዩ መድረኮች ላይም ም/ኮሚሽነሩ በምክርና አቅጣጫ በማስያዝ ሲያግዙ ነበር፡፡ እዚህ ላይም የተለየ ነገር የለም ኮምሽነሩ ሀሳብ በመስጠት እንጂ ጣልቃ ተገባ የሚባለው ምን ላይ እንደሆነ አልገባኝም፡፡
 
 
ኢትዮ ፉትቦል፡-  ውይይቱ በፀደቀው ሕግ ላይ  በተጨዋቾች ዝውውር እና በፕሮፌሽናል  ተጨዋቾት ገደብ በእናንተ በኩል ያልተመቻችሁ በመሆኑ በተደጋጋሚ ቅሬታ ስታሰሙ ነበር፡፡ በትናንትናው መድረክ ላይ ያቀረባችሁት ምንድነው ውጤቱስ ምን ነበር?
   
 
አቶ ሰለሞን፡-  በኛ በኩል ቀደም ሲል ከሶስት ጊዜ በላይ ለፌደሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ እንደ ባለድርሻ አካል ድምጻችን ሊሰማ ይገባል፡፡ ያቀረብነው ሀሳብ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጣቃሚ ነው ብለን ያቀረብነውን ሀሳብ በአብዛኛው ተሳታፊዎች  በፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ጉዳይ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን አብላጫውን ጊዜ የወሰደው ግን በተጨዋቾች የዝውውር ጉዳይ የተወሰነው የገንዘብ አከፋፈል እንደሚጎዳቸው ተጨዋቾቹ አበክረው ስለተከራከሩ ፈደሬሽኑ ጉዳዩን በአንክሮ በማየት ከተወካዮቻቸው ጋር በመነጋገር ምላሽ እንደሚሰጥ ተስማምተው ተለያይተዋል፡፡
   
 ኢትዮ ፉትቦል፡- አንዳንድ ወገኖች እናንተ ችግሩን ለማሳወቅም ሆነ ለመከራከር ዘግይታችኋል መጀመሪያ ክለቦች ሲወያዩ ተሳትፋችሁ ነበር ፌደሬሽኑ ባለሙያዎች መርጦ ጥናቱን ካስጠና በኋላ ክለቦችን ጠርቶ ሲያወያይ በቦታው በመገኘት ለምን አልተወያያችሁም?
   
  አቶ ሰለሞን፡- ለፌደሬሽኑ ረቂቁ ይሰጠን ብለን ጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም ላይ ነው በወቅቱ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለማግኘታችን እንደገና ጥር 20 ቀን ሰነዱ ይሰጠንና ለስራ አመራር ቦርዳችን አቅርበን የቦርዱን ውሳኔ ይዘን እንቅረብ ብለን ብንጠይቅም አልተሳካልንም፡፡ ረቂቅ ሰነዱን ከጋዜጠኞች በማግኘታችን በባለሙያዎች በኩል አስጠንተን ማሻሻያ ሀሳቦችን ለፌደረሽን አቅርበን ለሰጠነው ሀሳብ መልስ አላገኘንም፡፡
   
 
ኢትዮ ፉትቦል፡- ባለፈው ጊዜ ያላችሁን ቅሬታ ለኢ.ፌ.ዲ.ሬ ስፖርት ኮሚሽን በማስገባት የደብዳቤውን ኮፒ ለመገናኛ ብዙሃን በኢ-ሜይል ልካችኋል የደብዳቤው መንፈስ ስፖርት ኮሚሽን ውሳኔ እንዲሰጥ ነው ወይስ ዓለማው ምንድነው አግባብነትስ አለው ወይ?    
 
አቶ ሰለሞን፡-  ቅድም ለመግለጽ እንደሞከርኩት ከሶስት ጊዜ በላይ ደብዳቤ ካስገባን በኋላ የፌደራል ስፖርት ኮሚሽንን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ መሰረት ያንን ተንተርሰን እንዲሁም የፌደራል ስፖርት ኮሚሽን ራሱ ስለ ስፖርት ማህበራት እና ፌደሬሽኖች ማድረግ የሚገባቸውንና ያላቸውን ስልጣን ወስኖ ያስቀመጣቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ስላሉ ኮሚሽኑ ጣልቃ ገብቶ እንዲወስን ሳይሆን ያለንን ቅሬታ ለማሳወቅ ነው ያስገባነው፡፡
 
ኢትዮ ፉትቦል፡- አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት እንደዋና ችግር እናንተ የምታነሱት ጉዳይ ላይ ሳይሆን ችግሩ ያለው አካሄዱ ላይ ትክክል አይደለም ደንቡ ከፀደቀ በኋላ በአንድ ወገን ጥያቄ ውደኋላ ለምን ይመለሳል ነው የሚሉት ችግር ካለም ቅ/ጊዮርጊስ በሌላ መልክ ማካካስ ይችላል፡
 
 
አቶ ሰለሞን፡-   ቆይ ቆይ ማካካስ ማለት በምን መልኩ ነው የምናካክሰው?
     
 
ኢትዮ ፉትቦል፡-  ማለት ግራስ ሩት ላይ መስራት ወጣቶችን በማሰልጠን የውጭ ተጨዋቾችን ቀንሶ ለአገር  ውስጥ ተጨዋቾች እድል መስጠት አለበት ነው የሚሉት? የውጭ ተጨዋቾችን ቁጥር መገደቡ በናንተ በኩል ጥቅሙና ጉዳቱ ምን ያህል ነው ይላሉ ?
     
 
አቶ ሰለሞን፡-  ታዳጊ ወጣቶችን ማፍራት ላይ ከፍተኛ ሥራ የሰራው ቅ/ጊዮርጊስ ነው፡፡ ምክንያቱም ታዳጊ ወጣቶችን እያሰለጠነ ይሳተፋል ከዛ ውጭ የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያ የታዳጊዎች ውድድር በየዓመቱ ክረምት ላይ እያደረገ ከነዛም የሚገኙትን ታዳጊዎች ለበጋው ውድድር የሚመለምልበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌላው እንደሚታወቀው በዘጠኝ ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ 2400 ታዳጊ ወጣቶችን ለማየት የተዘረጋው ዕቅድ በወቅቱ ግቡን መትቷል፡፡ እነ አበባው ቡጣቆ የወጡትም ከዛው ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በታዳጊ ወጣቶች ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሰራን ነው፡፡ አሁንም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት  የታዳጊ ወጣቶች አካዳሚ ገንብተን እያጠናቀቅን ነው፡፡ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ጠንክረን እየሰራን ሲሆን የውጭ ውድድርን በተመለከተ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡ ያ ጥረታችን አልተሳካም፡፡ ምክንያቱም የሚገጥሙን ቡድኖች በርካታና ጠንካራ የውጭ ተጨዋቾችን ይዘው ስለሚጠብቁን ነው፡፡ የእኛ በዚህ መልክ ገፈት ቀማሽ መሆን ለሌላው ላይታየው ይችላል፡፡ ብዙም ቁስሉ አይሰማውም እኛ ግን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ እና በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ በርካታ ጊዜ ስለደረስንና ችግሩን ስላየነው የተጨዋቾት ምርጫ እድል ሰፋ ማለት አለበት፡፡ የበርካታ አገር ተሞክሮዎችን ለማሳየት ሞክረናል አልፎ ተርፎም አካባቢያችን ካሉ ጎረቤቶቻችን ኡጋንዳ እና ታንዛንያም ቢሆኑ ሰባት እና ከዛ በላይ ተጨዋቾችን ነው የሚፈቅዱት፡፡ እኛ የተለየን ደሴት ልንሆን አይገባም፡ በኢንተርናሽናል ውድድር ተሳትፈን ውጤታማ እንሁን ካልን ዕድሉን ማስፋቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው፡፡ ለምሳሌ በኮንፈደሬሽን ካፕ በሚቀጥለው ዓመት መከላካያ ወላይታ ዲቻ ወይም ሐዋሳ ከነማ ናቸው የሚሳተፉት፡፡ እነኝህም ክለቦች ቢሆኑ የተጨዋቾች ምርጫ ዕድሉ ቢሰፋላቸው ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌላው እንደምታውቀው አልጀሪያና ቱንዚያ ክለቦች በኢንተነርናሽናል ጨዋታ ውጤታማ ስለሆኑ ለሀገራቸው ክለቦች ተጨማሪ ኮታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እኛም ተግባብተን ከሰራንና ውጤታማ ከሆንን የሚሰጠን ኮታ ያድጋል ተሳታፊነታችን ይበለጽጋል፡፡ የሀገራችን የእግር ኳስ ሁኔታም ይጠነክራል፡፡ ባለፉት ዓመታት እነኝህን የውጭ ተጨዋቾች ማምጣት ከጀመርን በኋላ ስንት የኛ ተጨዋቾች ፕሮፌሽናል እየሆኑ እንደወጡ ይታወቃል፡፡ በነ ባዩ ሙሉ ጊዜ ጀምሮ እነ አሸናፊ ሲሳይ ተስፋዬ ኡርጌቾ ሳላዲን ሰኢድ ሽመልስ በቀለ አበባው ቡጣቆ እነዚህ ሁሉ ሲወጡ ለኛ ቢጎዳንም ከክለቦቻችን ወጥተው ቢያንስ አሁን ላለው ትውልድ በርካቶች ፕሮፌሽናል እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ ፉክክሩንም ከፍ እያደረገው ነው፡፡ፉክክሩ በዚሁ ከቀጠለ ፕሪሚየር ሊጉ ያለውንም ደረጃ ሊያሳድገው ይችላል፡፡ ከዚህ ሌላ የኢንዱስትሪው እድገት ይጨምራል የተጨዋቾች ኑሮ ይሻሻላል እኛ በአስተሳሰብም ሆነ በሌላ ከሌላው ተለይተን አይደለም  ለሁሉም አካል እና ለአገራችን እግር ኳስ እድገት ይጠቅማል ብለን ነው የምናምነው፡፡    
 
ኢትዮ ፉትቦል፡-  የተጨዋቾችን ደመወዝ እና የፊርማ ከፍያ  በተመለከተ አዲስ ደንብ ፀድቋል በዚህ በኩል የቅ/ጊዮርጊስ አቋም ምንድነው?    
 
አቶ ሰለሞን፡- ይህን አሁን ለመናገር ይከብደኛል በትናንትናው ስብሰባ ተጨዋቾቹ አበክረው ፌደሬሽኑን ጠይቀዋል፡፡ ወደፊት ከተጨዋቾቹ ተወካይ ጋር ለመነጋገር ተስማምተዋል፡፡   
  
አቶ ሰለሞን፡-  ፌደሬሽኑ ጥናቱን ለማስጠናት ለባለሙያ ሲሰጥና ሲያስጠና በሚጠናው ጥናት ላይ በወቅቱ ምንም ዓይነት ቅሬታ  አላሰሙም አሁን ዘግይተው ነው ቅሬታ ያመጡት በማለት አንዳንድ ባለድርሻ አካላት ቅሬታ እያሰሙ ነው፡፡     
 
አቶ ሰለሞን፡-  አልዘገየንም ጥር ወር 2007 ዓ.ም ከተቆጠረ ገና ጥቂት ወራቶች ናቸው ይህንን ቀደም ብዬ ነግሬሀለሁ ሰነዱን ሳናገኝ ምን ብለን ነው ቅሬታም ሆነ ማሻሻያ የምናቀርበው?   
  
ኢትዮ ፉትቦል፡-  ይህ ጉዳይ የተጀመረው ከሶስት ዓመት በፊት ቀደም ብለው በነበሩት የሥራ አሥፈፃሚዎች ነው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእናንተ እንቅስቃሴና ተሳትፎ ምን ይመስል ነበር?
  
 አቶ ሰለሞን፡-  ልክ ነህ አፋር ላይ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የኛ ተወካዎች ተገኝተው ይህ ጉዳይ የሁለት አካል መሰረታዊ ጥያቄ ነው በተጨዋቾችና በክለቦች ስለዚህ ተጨዋቾችን በተመለከተ እነሱን አሳታፊ የሆነ ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለን በአፋር ስብሰባ ላይ ተናግረናል ሆኖም ምንም ዓይት መድረክ ለተጨዋቾች ባለመሰጠቱ ነው ነገሩን ያጓተተው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ክለባችን ድምፁን ለማሰማት በተቻለው ሁሉ ጥረት አድርጎአል፡፡ ፌደሬሽኑ የሚያወጣውን ሕግ እየተገበርን አስቸጋሪ የሚሆን ጉዳይም ካለ በኛ በኩል ድምፃችንን እና ችግሮቻንን ማሰማት እንቀጥላለን፡፡
   
ኢትዮ ፉትቦል፡- ለጥያቄዎቻችን መልስ በመስጠት ስለተባበሩን እናመሰግናለን በእርስዎ በኩል የሚያስተላልፉት ነገር ካለ?
   
አቶ ሰለሞን፡- ቅ/ጊዮርጊስ ሕዝባዊ ክለብ ነው ለሀገራችን ስፖርት እድገት ይበጃል ተብሎ የሚታሰበውን ሁሉ እንቀበላለን፡፡ አስቸጋሪ የሆኑ እንቅፋቶች ሲያጋጥሙን ግን በየጊዜው ለመጠየቅና መፍትሄ ለማግኘት ወደ ኋላ አንልም፡፡ እናንተም ይህን እድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ
  
ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ጋር ያደረገውን አጠር ያለ ቃለ መጠይቅ እነሆ
 
 
ኢትዮ ፉትቦል ፡- አቶ ወንድምኩን ለጥያቄ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡ ትናንትና የተጠራውን የክለቦች ውይይት የጠራው አካል ማነው?
 
አቶ ወንድምኩን፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡
   
 ኢትዮ ፉትቦል ፡- ደብዳቤው ለክለቦች የተበተነው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ነው?
 
አቶ ወንድምኩን፡- አዎ የተጠራው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ነው፡፡ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽንም ጉዳዩን እንዲያውቀው አድርገናል   
 
ኢትዮ ፉትቦል ፡- የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ስብሰባውን መርተዋል፣ አስተያየት ሰጥተዋል አሊያም ፕሮግራሙን መርተዋል?
 
አቶ ወንድምኩን፡- ክለቦች ያደረጉት ውይይት ላይ የራሳቸውን የማዳበሪያ እና የማግባቢያ ሀሳብ ሰጥተዋል እንጂ ስብሰባውን አልመሩም  
 
ኢትዮ ፉትቦል ፡- ጥናቱን ያጠናው ክፍል ማነው

አቶ ወንድምኩን፡- ፌዴሬሽኑ ለባለሙያዎች ሰጥቶ ነው ያስጠናው

ኢትዮ ፉትቦል ፡- ባለሙያዎቹ እነማን ናቸው

አቶ ወንድምኩን፡- የኢትዮጵያ ቡና ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዱ የኢትዮጵያ መድን ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ አለሙ  ከኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን አቶ አበባው ከልካይ፣ ከአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን አቶ ንጉሴ ዓለሙ  ናቸው፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡- እነዚህ ባለሙያዎች የተመረጡት በምን መስፈርት ነው?

አቶ ወንድምኩን፡- መጀመሪያ ክለቦች በሙሉ ተወያይተው በባለሙያ እንዲጠና ለፌዴሬሽኑ ስላቀረቡ ፌዴሬሽኑ  እነዚህን ባለሙያዎች በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አጥንተው እንዲያቀርቡ  አድርጓል፡፡

ኢትዮ ፉትቦል ፡-
የትናንትናው ስብሰባ ላይ የትኞቹ ክለቦች ነው የተገኙት

አቶ ወንድምኩን፡-
ለ14 የፕሪሚየር ሊግ ጥሪ አድርገን 11 ተገኝተው 2ቱ ባለመስማማት ጥለው ወጥተዋል

ኢትዮ ፉትቦል ፡-
9ኙ ምን ወስነው ወጡ

አቶ ወንድምኩን፡- ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮ ፉትቦል፡-
በሀሳባቸው መሠረት ምን ተወሰነ

አቶ ወንድምኩን፡- መመሪያው በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው ውይይቱ ግን አጠር ያለ ነበር፡፡ በተሰጠው አስተያየት ላይ እንደሁኔታው መሻሻል ሊደረግ ይችል እንደሆን ነው እንጂ የተጠናው መመሪያው መፅደቁ አይቀርም

ኢትዮ ፉትቦል፡- 
ስፖርት ኮሚሽን በፌዴሬሽኑ ሥራ ላይ ጣልቃ ገብቷል?አቶ ወንድምኩን፡-በፍፁም አልገባም፡፡ ሊገባም አይችልም፡፡ መጀመሪያም ቢሆን ይህ እቅድ እንዲፀድቅ የጠየቁት ክለቦች ናቸው፡፡ አሁን መብቱ የክለቦች ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የክለቦችን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ነው፡፡

ኢትዮ ፉት ቦል፡-
በትናንትናው ውይይት የፀደቀ ነገር የለም ውይይት ብቻ ነው የተደረገው ብለዋል ጠቀሜታው ምንድን ነው?
አቶ ወንድምኩን፡-  የክለቦችን ቅሬታና የተፈጠሩ ግርታዎችን ለማወያየትና ተጨማሪ ሀሳቦችን ለመሰብሰብ ብቻ ነው፡፡
ኢትዮ ፉት ቦል፡- ለጥያቄ ስለተባበሩን አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ወንድምኩን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Yoni [965 days ago.]
 መቶ አለቃ ፈቀደ and አቶ ገዛኸኝ betam tasaferalachu tnx Journalist ፈለቀ ደምሴ really i appreciate you ... u are a real journalist afatehachewalle ! kefat mekegnent yetem ayadersenim pls sra sertchu real tefokakari hunu !

ፔሌ [965 days ago.]
 ቢራ ምን ልሁን ነው የሚለው በግድ የኔን ሀሳብ ብቻ ተቀበሉኝ ማለት ይቻላል እንዴ ፕሮፌሽናል ፕሮፌሽናል የምትሉት ከሶስት በላይ 5ት ከተሰለፈማ ቡድኑ ሌላ ሆነ ማለት ነው የኢትዮጵያ ቢራ መሆኑ ቀርቶ የኡጋንዳ ቢራ ሆነ እኮ ማለት ነው። ነገሩ ደላላዎቹ በዝውውር የእንትናን ገንዘብ ለመካፈል ሳይሆን አይቀርም ለኳሱ ተብሎ አይመስልም መቶ አለቃ ሲሰለቻቸው መሆን አለበት ስትፈልግ 3ት ስትፈልግ 11 አድርገው ያሉት። ምን ያድርጉ የሚሰማ ሲጠፋ እንደፈለክ አድርገው ያስብላል።

kassahun [964 days ago.]
 እኔ የሚገርመኝ ኢትዮጵያ ቢራ የሚባል ክለብ አለ ? የማታውቁትን ነገር ለምን እንደምታወሩ አይገባኝም ፡፡ የ ኛ ክለብ ትክክለኛ ስሙ #ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ነው የሚባለው፡፡ እናንተ ሌላ ክለብ ካላችሁ ንገሩን

eldana [964 days ago.]
 አፍ ሲከፈት እንደሚባለዉ ነዉ ችግሩ የቀረበዉ ሀሳብ ሳይሆን ማለትም ሀሳቡ ጥሩ ሆኖ ሳለ ምንያረጋል ያቀረበዉ ጊዬርጊስ ሆነ አረ ባካችሁ በየት ሀገር ነዉ በጸደቀ ህግ ላይ አስተያየት /ዉይይት/ማድረግ አይቻልም የተባለዉ መጀመሪያ እንሳሰት እና ከዛ ባይሆን እናስተካክላለን ማለት ምን ማለት ነዉ ከጅምሩ እንደማያሰራ እየታወቀ ለምን ለምን ሌላዉ አጥኒዉ ቡድን የተመረጠበት መስፈርት ምንድነዉ እንዴት ነዉ ዉድድር የተደረገዉ ግልጽነት በእየአንዳንዱ ስራ ቢኖር ይህ ሁሉ እንኪያ ሰለምታ ባልነበረ

Tesfaye [964 days ago.]
 Buna & Dedebit are talking as if they have got a well implemented youth programme.Surprisingly,St.George is nearly inaguratina a youth academy & seems to understand how many years it takes to produce quality players.

solomon [964 days ago.]
 Egna eyalen yalenew eko hagerachen beki techawachoche alu edelun ensetachew ebakachehu tegegna atehunu yezachehu zefezefachehu yasekmetachewachewen lejoche tetekemu new balachehu yebalseltenena genzeb tegen bemadereg balmoya geza wesdo atento, federeshen amenobet tegbarawe endehon weseno lekleboche baweredew gudaye kelbochem zegejetachewen bejmerubet seat enante endegmel shent wedewhala yemtemlesut lemendenew? Ere edmako bezu yemenmarebet collag new cherashe ahunema keshemglena alfachehu jajachehuko masebem tesanachehu. Hageren lelwet yemichelew yehager lej new serubachew. Parasait atehunu

together [963 days ago.]
 Together we shall grow let us not split let us be one and work towards the development of the football

together [963 days ago.]
 Together we shall grow let us not split let us be one and work towards the development of the football

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!