ከዋልያዎቹና ከሀራምቤ ኮከቦቹ ጨዋታ የተመዘዙ ሰበዞች
ሰኔ 29, 2007

በትናንትናው ጽሑፋችን የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደረገውን ጨዋታ ባዶ ለባዶ በመለያየቱ ዙሪያ የተስተዋሉ ክስተቶችን የመጀመሪያ ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል። በተለይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደተደረገበት የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ቢያንስ አንድ ጎል ማስቆጠር ይገባው ነበር የተባለ ሲሆን በአንጻሩ በዋልያዎቹ በኩል አምበሉ በሀይሉ አሰፋ እና ወጣቱ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ያበከኗቸው ያለቀላቸው የጎል እድሎችም በዋልያዎቹ በኩል የተነሱ ነጥቦች ናቸው።  በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች ዙሪያ ከዚህ በታች የሚከተሉትን ነጥቦች ይዘን ቀርበናል መልካም ምንባብ።

ከ15 ቀን በፊት ሁለቱ ቡድኖች ባካሄዱት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ኬኒያዎች ሁለት ለባዶ ቢሸነፉም እጅግ ወሳኝ ዋጋ ያላት የጎል እድል ተፈጥሮላቸው ሳይጠቀሙበት መቅረታቸው ይታወሳል። በባህር ዳሩ የሁለቱ አገሮች ፍልሚያ የእለቱ ዳኛ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን ለሁለቱም አገሮች መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን ዋልያዎቹ በጋቶች ፓኖም አማካኝነት ወደ ጎልነት ሲቀይሯት የሃራምቤ ኮከቦቹ ግን ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ለዋልያዎቹ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ሲሳይ ማድረጋቸው አይዘነጋም።

ከትናንት በፊት በአገራቸው መዲና ናይሮቢ ላይ የተካሄደውን ጨዋታም በርካታ የጎል እድል ፈጥረው የነበረ ቢሆንም የጎሉን መስመር ለይቶ የሚያውቅ አጥቂ በማጣታቸው በ180 ደቂቃ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኗቸው ከቻን ዋንጫ ውድድር ውጭ መሆን ችለዋል። በተለይ በእለቱ ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት መጠቀም አለመቻላቸው የሃራምቤ ኮከቦቹ በጨዋታው  ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋቸው ሊያንሰራራ የሚችልበትን እድል አምክነዋል። በሁለቱም ጨዋታዎች ካገኟቸው ፍጹም ቅጣት ምቶች አንዳቸውን ማስቆጠር ችለው ቢሆን ኖሮ ምናልባት ነገሩ የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችል ነበር ወይም የዋልያዎቹን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ቀላል አያደርገውም ነበር ማለት ይቻላል።

የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን በእለቱ አንድ ፍጹም ቅጣት ምት ከማምከኑም በላይ በርካታ የጎል እድሎችንም መጠቀም ተስኖት ታይቷል። ለኬኒያዎች ጎል አለማስቆጠር ከራሳቸው ድክመት በተጨማሪም የዋልያዎቹ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ አብሮ ሊነሳ ይገባዋል። ለአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስብስብ የኋላ መስመር ጥንካሬ የመጀመሪያ ተጠቃሽ የሆነው “የአስራት ኃይሌ ውለታ አለብኝ” በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ የሚናገረው ሳላሃዲን ባርጌቾ ሲሆን ሌላው ፈረሰኛ ዘካሪያስ ቱጂም አንዱ የቡድኑ የጥንካሬ ምንጭ ነው። ሁለቱ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮና ወጣቶች ለግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነትም ሆነ አብረዋቸው ከጎናቸው ለሚሰለፉት አስቻለው ታመነ እና ሞገስ ታደሰ የሚሰጧቸው ከለላ ከፍተኛ ሆኖ ታይቷል።

በናይሮቢው ጨዋታ ከተፈጠሩ አዲስ ክስተቶች መካከል የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ የተመለከተው ቡድኑ ጠንካራ ሳይሆንም ውጤት ይዞ መውጣት እንደሚችል ተስፋ ሰጭ ሆኖ ማምሸቱን ነው። መቼም ማንኛውም ቡድን የሚለካው በተጋጣሚው ሚዛን ልክ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዋልያዎቹ መለኪያ ሆኖ የቀረበው የሃራምቤ ኮከቦቹ ኪሎ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው ቢባልም በዚሁ ዝቅተኛ ኪሎ ተመዝነው ማለፋቸውም በራሱ ሌላ ስኬት ሊሆን ይችላል።

ከኬኒያ ጋርም ሆነ ከናይጄሪያ ወይም ከጋና እና አልጄሪያ ቡድኖች ጋር ተጫውቶ መሸነፍም ሆነ ማሸነፍ ያለ ነው። ከእነዚህ ሀገሮች ጋር ተጫውቶ ማሸነፍ የሚሰጠው ስሜት ኬኒያን በማሸነፍ ከሚገኘው ደስታ የላቀ መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ እንዲሉ የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድንም ከኬኒያ ጋር ያደረገውን ጨዋታ ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር ተደጋጋሚ የጎል ማግባት ሙከራ እየተደረገበት ሳይረበሽና በቀላሉ እጁን ሳይሰጥ በሩን አላስከፍት ማለቱ የሚያስመሰግነው ሆኖ ታይቷል።

ከትናንት በስቲያ ናይሮቢ ላይ የተመዘገበው ውጤት የሚያመለክተውም አንድ በራስ መተማመኑ የዳበረ እና የማሸነፍ ስነ ልቦና የተላበሰ ቡድን ሜዳ ላይ ጥሩ ባልሆነበት ጊዜም ውጤት ይዞ መውጣት እንደሚችል ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። ከጨዋታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ልምምድ የሚሰራበትን ስታዲየም መብራት ያጠፋ እና ወደ ውድድሩ ቦታ ሲያመራ “እንኳን ደህና መጣህ” ብሎ የማይቀበል ተጋጣሚን ተፋልሞ የሚፈለገውን ውጤት ይዞ መውጣት ቀላል አይደለም። በተለይ እንደ አፍሪካ አይነት ፕሮፌሽናሊዝምን በሚገባ ባልተረዱ አገሮች የሚካሄዱ ጨዋታዎች ከዳኝነት ጋር እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ጋር ተጣምሮ ለእንግዳው ቡድን ውጤት ይዞ መመለስ ፈተና መሆኑ ግልጽ ነው። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም የዋልያዎቹን ውጤት በአድናቆት የተቀበለው ከእነዚህ መመዘኛዎች በመነሳት ነው።

ሌላው የእለቱ አብይ ክስተት የነበረው የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ አንዳንድ ውሳኔዎች ናቸው። አሰልጣኙ “የሚሰራውን ጠንቅቆ ያውቃል” እየተባለ የሚነገርለት ቢሆንም የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እንደ ጋዜጠኛም ሆነ እንደ ማንኛውም ተመልካች ከተጽእኖ ነጻ ሆኖ የጨዋታውን ሂደት ሲመለከት አሰልጣኝ ዮሃንስ በአንዳንድ ውሳኔዎቹ ራሱን አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ አግኝቶታል። የመጀመሪያው የአሰልጣኙ ከባድ ውሳኔ ባህር ዳር ላይ ውጤት የቀየረለትን አስቻለው ግርማን ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጦ በኤፍሬም አሻሞ ጨዋታውን መጀመሩ ነው። ሁለቱ ተጫዋቾች የራሳቸው የሆነ የተለያየ ኳሊቲ ያላቸው ቢሆንም እንደ ኬኒያ አይነት አጥቅቶ የሚጫወትን ቡድን ለመመከት ከኤፍሬም አሻሞ ይልቅ የአስቻለው ግርማ መኖር ቡድኑን ተጠቃሚ ያደርገው ነበር ብሎ ያስባል።

ውጤት ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ ሁለት የአማካይ ተከላካዮችን የተጠቀመው ብሔራዊ ቡድናችንም ከብሩክ ወይም ከጋቶች አንዳቸውን በፍሬው ሰለሞን በመተካት ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ችሎ ቢሆን ኖሮ የኬኒያዎችን ተደጋጋሚ ሙከራ ማስቀረት ይቻል ነበር ብሎ ያምናል። አጥቂውን ቢኒያም አሰፋን የቀየረበት ሂደትም ተገቢ መስሎ አልታየኝም። ከእነዚህ መጠነኛ ስህተቶች ውጭ በሰለጥኙም ሆነ በቡድኑ አጨዋወት ላይ ተስፋ ሰጭ ጅምር ተመልክቻለሁ ብሎ ያስባል የጽሁፉ አዘጋጅ።

በመጨረሻም

የታሪክ ጌትነት ታሪክ መስራት የሚቀጥል ከሆነ ከዓሊ ረዲ በኋላ ብዙም አስተማማኝ ያልሆነው የዋልያው የጎል ክልል ተተኪ አገኘ ተብሎ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል። ታሪክ ጌትነት ከእድሜው ለጋነትም ሆነ የቋሚ ተሰላፊነት ማግኘት የጀመረበት ጊዜ አጭር መሆኑ ከግምት ሲገባ ግብ ጠባቂው ወደ ፊት ብሩህ ጊዜያት እንደሚጠብቁት ጠቋሚ እንቅስቃሴ አሳይቷል። ለግብ ጠባቂው ችሎታ ማደግ ደግሞ የቀድሞው የኦሜድላ ኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ዓሊ ረዲ ከጎኑ ሆኖ የሚሰጠው ስልጠና ሳይጠቅመው እንዳልቀረ ይታመናል።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ፔሌ [962 days ago.]
 ጋዜጠኛ ይርጋ አሰልጣኙ እኮ በመረጠው ታክቲክ ውጤት አግኝቶበታል። በነበረው የሁለት ጎል ብልጫ በመጠቀም ተጫዋቾቹን እየቀያየረ መሞከሩ ተገቢ ነው። ቡድኑ ቀደም ብሎ ጎል ቢገባበት ኖሮ አስቻለውን ቶሎ ይቀይረው ነበር። ነገር ግን ኤፍሬምን እድል ለመስጠትና ለመፈተሽ ጨዋታውን የተጠቀመበት ነው የሚመስለኝ። ባለው ጨዋታ ለፍሬው ሰለሞንም እድል ሰጥቶታል። አሰልጠኙ ውጤቱን እያስጠበቀ በዛውም በተግባል የተፈተኑ የተጫዋቾች ስብሰብ ለመያዝ እየሰራ ያለ ይመስለኛል።

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!