አስሩ ባለጸጋ የአፍሪካ ክለቦች
ሐምሌ 01, 2007

ዛሬ የምንመለከተው በአፍሪካ አህጉር ያለው የእግር ኳስ እድገት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለውን ይሆናል። በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት በአፍሪካ የሀብት መጠናቸውም ሆነ በህዝቡ ያላቸውን ተቀባይነት ከግምት በማስገባት ከአንደኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙትን የአፍሪካ ክለቦች ይፋ አድርጓል።

Africa Richest Clubs


እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም የግብጹን አል አህሊ በሀብት ክምችት የሚደርስበት አልተገኘም። አብዛኛውን የፈርኦኖቹን ስብስብ በማስመረጥና የአህጉሩን ቻምፒዮና በመቀዳጀት ቀዳሚ የሆነው የግብጹ ዋና ከተማ ክለብ የአፍሪካ ቀዩ ሰይጣን ዘንድሮም ተወዳጁና ሀብታሙ የአህጉሪቱ ክለብ ሆኗል። በአገሪቱ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የእግር ኳስ እድገቷ አስጊ ደረጃ ላይ የምትገኘው ግብጽ ብሔራዊ ቡድኗም ሆነ ክለቦቿ በውጤት ደረጃ ባይሳካላቸውም አል አህሊ ግን 13 ነጥብ 95 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ በመሰብሰብ የአህጉሩ ባለ ጸጋ ሆኗል። በ1904 እ.ኤ.አ የተመሰረተው ውጤታማው አል አህሊ ኢትዮጵያዊው ሳላዲን ሰይድ እየተጫወተበት የሚገኝ ክለብ ነው።

ከአል አህሊ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የያዘው ደግሞ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከግብጽ ቀጥላ የተቀመጠችዋ ቱኒዚያ ንብረት የሆነው ኤስፔራንስ የሚባለው ክለብ ነው። በፈረንሳውያን የበጎ አድራጎት ተማሪዎች እንዳቋቋመ የሚነገርለት ኤስፔራንስ 12 ነጥብ 75 ሚሊዮን ዩሮ በማጋበስ ሁለተኛው የሰሜን አፍሪካም ሆነ የአፍሪካ ክለብ መሆን ችሏል። ሌላው የቱኒዚያ ክለብ የሆነው ክለብ አፍሪካ ደግሞ በ11 ነጥብ 80 ሚሊዮን ዩሮ አስመዝግቦ በባለጸግነት የነሃስ ሜዳሊያውን ወስዷል።

የደቡብ አፍሪካው ካይዘር ቺፍ 10 ነጥብ 48 ሚሊዮን ዩሮ እንዳለው አስመስክሮ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ከሰሜን አፍሪካውያን ክለቦች ውጭ የመጀመሪያው የአህጉሪቱ ባለጸጋ ክለብ ሆኗል። በሀብት ብቻ ሳይሆን በውጤት ደረጃም ቢሆን የማይታማውን ካይዘር ቺፍን ተከትሎ ያለውን ደረጃ የያዘው ደግሞ ሌላው የባፋና ባፋናዎቹ መመኪያ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ነው። ይህ የደቡብ አፍሪካ ክለብ የ10 ነጥብ 35 ሚሊዮን ዩሮ ባለቤት ነው። 

ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ንብረት የሆነው የግብጹ ዛማሌክ 10 ነጥብ 30 ሚሊዮን ዩሮ ይዞ በመገኘቱ ስድስተኛው የአህጉሩ ባለ ጸጋ ክለብ ሆኗል። ዛማሌክ በግብጽ ያለው አለመረጋጋት ባይጎዳው ኖሮ ከደቡብ አፍሪካዎቹ ክለቦች በላይ መቀመጥ የሚያስችለው እድል ነበረው። በርካቶች ዛማሌክን የምናስታውሰው በ1992 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የደርሶመልስ ጨዋታ ሲሆን በወቅቱ ሁለቱ ክለቦች ካይሮ ላይ ዛማሊክ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ቡና በተመሳሳይ ሁለት ለአንድ ተሸናንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፈው ቡድን የተለየው በመለያ ምት ነበር። በወቅቱ የቡናን የጎል መስመር ይጠብቅ የነበረው የአሁኑ የብሔራዊ ቡድን የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ዓሊ ረዲ ነበር።

ከዛማሊክ ቀጥሎ ያሉትን ሁለት ተከታታይ ደረጃዎች የያዙት ሁለቱ የአልጄሪያ ክለቦች ናቸው። ዩ ኤስ ኤም አልጀር የተባለው የአልጄሪያው ክለብ 9 ነጥብ 65 ሚሊዮን ዩሮ ስላለው ከአገሩ የመጀመሪያውነ ደረጃ ከአህጉሩ ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን በመያዝ ዛማሌክን እየተከተለ ነው። ኤስ ኤስ ስታፍ የሚባለው ሌላው የአልጄሪያ ክለብ ደግሞ 8 ነጥብ 60 ሚሊዮን ዩሮ ሰብስቦ ከአህጉሩ ስምነተኛነትን ከአገሩ ደግሞ የብር ሜዳሊያውን ይዟል።

ምስጦፋ ሐጂን በርካቶች እናውቀዋለን። የቀድሞውን የሞሮኮ ሰባት ቁጥር ለባሽ የግብ ጠባቂዎች ጠላት ማን ይረሳል። ከሙስጦፋ ሐጂ ስም ጋር አብሮ የሚነሳው ደግሞ ራጃ ካዛ ብላንካ የተባለው የሞሮኮ ክለብ ነው። ቀደም ባሉት ዓመታት በበርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ስሙ ተደጋግሞ ይታወቅ የነበረው የሞሮኮው ራጃ ካዛብላንካ 8 ነጥብ 13 ሚሊዮን ዩሮ ይዞ ዘጠንኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ከምዕራብ አፍሪካ ክለቦች መካከል የመጀመሪያውና ብቸኛው ቱጃር ክለብ ሆኖ የተመዘገበው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊኩ ቲፒ ማዜምቤ ነው። ከአንድ ዓመት በፊት ለሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ዓመታዊ በዓል ማድመቂያ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተጫውቶ ሶስት ለአንድ አሸንፎ የተመለሰው ማዜምቤ 7 ነጥብ 70 ሚሊዮን ዩሮ በማስመዝገብ ነው አስረኛ ደረጃን መያዝ የቻለው። ከዓመት በፊት አዲስ አበባ ላይ ከቡና ጋር ተጫውቶ ሶስት ለአንድ ባሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛዋን የቡና ጎል ያስቆጠረው በአሁኑ ወቅት ከክለቡ የተሰናበተው ዳዊት እስጢፋኖስ ነበር።

ወደፊት ስለ አፍሪካ ክለቦች አወቃቀርና የገቢ ምንጭን ጨምሮ የእድገታቸውን ደረጃ የሚያመላክቱ መረጃዎችን ለማቅረብ እንሞክራለን።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

soccerafrica.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Fikre Moga [893 days ago.]
 betam miyasazinew ke ethiopia 1 club inkuan alemenoru new

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!