ተስፈኛው ሀብታሙ ረጋሳ ከቡና ጋር ዋንጫን ያልማል
ሐምሌ 17, 2007

ይርጋ አበበ

ትውልድ እና እድገቱ አዲስ አበባ በተለምዶ 22 አካባቢ በሚባለው ሰፈር ነው። እግር ኳስን መጫወት የጀመረው በሰፈር ውስጥ ከሚገኙ እኩዮቹ ጋር ሲሆን ቆየት እያለ ደግሞ በፕሮጀክት ደረጃ ለቦሌ ተስፋ እና እንዲሁም ለመብራት ሀይል ሲ ቡድን መጫወት ቻለ። ከመብራት ሀይል ጋር የነበረው ቆይታ እስከ ዋናው ቡድን የዘለቀ ቢሆንም የኮረንቲውን መለያ ለብሶ ካምቦሎጆ ላይ እንደ ልቡ መፈንጨት አልቻለም ነበር። በዚህም ምክንያት ከፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ወደ ብሔራዊ ሊጉ ዝቅ ብሎ ለአዲስ አበባ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ፈረመ። በአዲስ አበባ ከነማ ቆይታው ከታዋቂው አሰልጣኝ ወርቁ ደርጐባ ጋር አብሮ የመስራት እድል ያገኘ ሲሆን ቆየት እያለ ደግሞ ከአንዋር ያሲን ጋር አብሮ መስራት ቻለ። የዛሬው እንግዳችን ወጣቱ የግራ እግር ተጫዋች ሀብታሙ ረጋሳ።


ሀብታሙ ረጋሳ ከአንድ ዓመት በፊት በአንዋር ያሲን ጠቋሚነት በ50 ሺህ ብር ከአዲስ አበባ ከነማ ቡናን የተቀላቀለ ሲሆን ከቡና ጋር በነበረው የመጀመሪያ ዓመት ቆይታውም ከጉዳት ጋር እየታገለ ቢከርምም ጤነኛ ሆኖ የመሰለፍ እድሉን አግኝቶ ሜዳ በገባባቸው ጨዋታዎች ግን ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ማሳየት ከመቻሉም በላይ ያለፈው ዓመት የቡናን የመክፈቻ ጎል በሲቲ ካፑ ንግድ ባንክ ላይ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። በፕሪሚየር ሊጉም ወልድያ ከነማ ላይ ጎል ማግባት ችሏል። ወጣቱ አማካይ ተጫዋች ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ያደረገውን ቆይታ ሙሉ ቃለ ምልልስ በሁለት ተከታታይ ክፍል ይዘንላችሁ ቀርበናል መልካም ንባብ።

ስለ አስተዳደጉ እና የእግር ኳስ አጀማመሩ

ሰፈራችን ለእግር ኳስ ምቹ ሜዳዎች ስለነበሩት ጧት ከቤቴ ከወጣሁ በኋላ የምመለሰው ማታ ነበር። ቀኑን ሙሉ ስጫወት ነበር የምውለው ለምሳ እንኳ ወደቤቴ አለሄድም ነበር። ምክንያቱም ቤቴ ከሄድኩ ያስቀሩኛል ብዬ ስለምፈራ ነበር ወደ ቤት የማልሄደው። ሰፈር ላይ እየተጫወትኩ ካደኩ በኋላ ወደ መድሃኒያለም ፕሮጀክት ቡድን ገባሁ። ከመድሃኒያለም ጋር ብዙ ከሰራሁ በኋላ ቦሌ ተስፋ የሚባል ፕሮጀክት ቡድን ፈረምኩ። በአጠቃላይ ለረጅም ዓመታት ፕሮጄክት ሰርቻለሁ። 

ስለ መብራት ሀይል ቆይታው

ከፕሮጀክት ካደኩ በኋላ በቀጥታ ያመራሁት ወደ መብራት ሀይል ሲ ቡድን ነው። ከመብራት ሀይል ሲ ቡድን ጀምሮ እስከዋናው ቡድን ድረስ ቆይቻለሁ። በወቅቱ የመብራት ሀይል አሰልጣኝ የነበረው ቡልጋሪያዊው አልጣኝ ለዋናው ቡድን እንድጫወት ፈልጎኝ ነበር። ሆኖም ለዋናው ቡድን የመሰለፍ እድል ስላላገኘሁ ለመጫወት በነበረኝ ጉጉት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከነማ ልዘዋወር ችያለሁ። በአዲስ አበባ ከነማ ቆይታዬም ለሶስት ዓመታት መጫወት ቻልኩ።

ያሰለጠኑት አሰልጣኞች በተለይም ወርቁ ደርጐባ እና ንጉሴ ደስታ

ወርቁ ደርጐባ ሜዳ ላይ እና ከሜዳ ውጭ የተለያየ ባህሪ ያለው ሰው ነው። ትሬኒንግ ላይ ሌላ ሰው ነው ይቆጣል፣ ይናገራል ብቻ በጣም ይከብዳል። በስራ ላይ ቀልድ የሚባል ነገር አያውቅም። ከሜዳ ውጭ ግን በጣም ሰላማዊ ሰው ነው። ቲምን በስርዓት መምራት በሚለው ፍልስፍናው ያምናል። ለአንድ አሰልጣኝም ትልቁ ኳሊቲው በራሱ ፍልስፍና ላይ እመነት አሳድሮ በትጋት ሲሰራ ነው። በዚህ በኩል ወርቁ የተሟላ አሰልጣኝ ነው። እንዲያውም አዲስ አበባ ከነማ ክለብ እሱን መቅጠሩ ትክክለኛ ውሳኔ ነው እላለሁ። ምክንያቱም እሱ ነው ክለቡን ክለብ ያስመሰለው።

ንጉሴ ገብሬ ማለት በጣም ጥሩ ሰው ነው።እንደምታየው አይነት አይደለም ስትቀርበው በጣም የዋህና እንደ አባት የሚመክር ሰው ነው። በአዲስ አበባ ከነማ ቆይታዬ እሱ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ስለነበረ በስራ በደንብ ባንገናኝም በግል በነበረን ቀረቤታ ሳየው ግን በጣም የሚገርም ሰው ነው።

ጉዞ ወደ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና የገባሁት ሶስት ዓመት በአዲስ አበባ ከነማ በነበርኩበት ጊዜ በሁለት አሰልጣኞች ነው የሰለጠንኩት። በመጀመሪያ ዋና አሰልጣኝ ወርቁ ደርጐባ እና ምክትሉ ንጉሴ ገብሬ ሲሆኑ ቀጣይ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት አንዋር ያሲን እና አብዶ ከድር መጡ። አንዋር ቡድኑን እንደያዘ በእኔ ላይ እምነት ነበረው። በውድደሩ ግማሽ ላይ ለቡና መፈረሙ ታወቀ እሱም ለቡናዎች ጥቆማ አደረገላቸው እንዲያዩኝና እንዲያስፈርሙኝ። የብሔራዊ ሊጉ የመጨረሻ ውድድር ባህር ዳር ሲካሄድ የቡና ሰዎች ባህር ዳር ድረስ በመምጣት ተመለከቱኝ በዚያ አማካኝነት እድሉን አግኝቼ ለቡና ልፈርም ችያለሁ።

የቡና ተጫዋች ከመሆኔ በፊት ደጋፊ ሆኜ ስታዲየም ተጋፍቼ ገብቼ አይቸዋለሁ። ለቡና አይደለም መጫወት ማየት ራሱ ይከብዳል። በጣም ከባድ ክለብ ነው በርካታ ደጋፊ ያለው ክለብ ስለሆነ ለክለቡ ስፈርም ይህንን ሁሉ ጠብቄ ነበር። ግን የራሴን አቅም አውቅ ስለነበረ በዚህ ደጋፊ ፊት ለመጫወት እጓጓ ነበር። በርካታ ደጋፊ ባለበት ስታዲየም መጫወት ራስን ያነሳሳል። ምክንያቱም ከደጋፊ የሚደረግልህ አቀባበልና ማነሳሳት በራስህ ላይ እምነት እንዲኖርህ ያደርጋል። እኔም ያንን ነገር እፈልገው ስለነበር በጣም ደስ ብሎኝ ነው ለቡና የፈረምኩት። 

ለቦታ ያደረገው ትግል

ቡና ስገባ በቀጥታ ቋሚ ተሰላፊ እሆናለሁ ብዬ አልነበረም የገባሁት። ባይሆን እድሉን ሳገኝ ማንነቴን ለማሳየት እነሳለሁ ብዬ አስቤ ነው የገባሁት። ምክንያቱም እንደምታውቀው ቡና በእኔ ቦታ ላይ 14 ተጫዋቾች አሉበት። በዚያ ቦታ ላይ ተሽሎ ለመገኘትና ቋሚ ተሰላፊ ለመሆን በጣም ከባድ መሆኑን አውቃለሁ። ግን በተሰጠኝ እድል መጠቀም ከቻልኩ ሌላ ጊዜ አሰልጣኙም ሆነ ደጋፊውና ሀላፊዎች እምነት እንደሚጥሉብኝ አውቅ ነበር።

የሚገርመው ደግሞ ከታዳጊ ፕሮጀክት ጀምሮ እስከ መብራት ሀይል እና አዲስ አበባ ከነማ በዘለቀው የእግር ኳስ ህይወቴ አንድም ቀን ጉዳት ደርሶብኝ አያውቅም ነበር። ነገር ግን ቡና እንደፈረምኩ በመጀመሪያ ጨዋታዬ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ንግድ ባንክን ሁለት ለባዶ ስናሸንፍ የመጀመሪያ ጨዋታዬን አካሂጄ የመጀመሪያ ጎል እንዳስቆጠርኩ ብዙም ሳልቆይ በጉዳት ከሜዳ ወጣሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ በተለያየ ጊዜ በደረሰብኝ ጉዳት በዓመት ውስጥ በድምሩ ለአምስት ወራት ከጉዳት ጋር ስታገል ከረምኩ። 

ከጉዳት አገግሜ ስመለስ ደግሞ ማች ፊትነሴ ወርዶ ስለነበረ ማችፊትነሴን ለማስተካከል ረጅም ጊዜ ወሰደብኝ። ማችፊትነሴ መስተካከል ሲጀምር ደግሞ እንደገና ሌላ ጉዳት ደረሰብኝ። በዚህ የተነሳ በመጀመሪያ ዓመት ቆይታዬ የጠበኩትን ያህል ክለቡን ማገልገል አልቻልኩም ብዬ አስባለሁ። ከጉዳት ነጻ ሆኜ በተሰለኩባቸው ጨዋታዎች ግን ጥሩ መንቀሳቀስ ችያለሁ። አብዛኛውን ጊዜ በጉዳት ላይ በማሳለፌ ያለፈው ዓመት ቆይታዬን ብቃቴን ሙሉ በሙሉ አውጥቼ ተጠቅሜያለሁ ብዬ አላስብም። ነገር ግን አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ ስለሆንኩ በቀጣዩ ዓመት በጥሩ ብቃቴ ወደ ሜዳ ስለምመለስ ለደጋፊዎቻችን ከእኔ የሚፈልጉትን ላሳያቸው ዝግጁ ነኝ።

የቡድናችንን አቋም በተመለከተ ስንጀም ጥሩ አቋም ላይ ሆነን ነበር የጀመርነው። በተለይ በሲቲ ካፑ። እየቆየ ግን በቡድኑ ላይ የተፈጠረው አለመረጋጋት በውጤታችን ላይ መጥፎ አሻራ ጥሎ አልፏል። በዚህም ምክንያት ክለባችን ደጋፊው የሚጠብቀውንም ሆነ ለክለቡ የሚመጥን ውጤት ማስመዝገብ አልቻልንም። በአዲሱ ዓመት ግን ቡድናችን በከፍተኛ ቁጭትና ወኔ ስለሚመለስ ለዋንጫ እንደምንጫወት አረጋግጥልሃለሁ።

ይቀጥለል!! 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!