የመንግስት ክለቦች ለወጣቶች ትኩረት መስጠት አለባቸው
ሐምሌ 18, 2007

ይርጋ አበበ

“መብራት ኃይል ሳላዲን ባርጌቾን ያለ ጥርጥር በራሱ ጊዜ አጥቶታል” ሀብታሙ ረጋሳ

“የመንግስት ክለቦች ውጤትም ወጣትም የላቸውም” ሀብታሙ ረጋሳ

 በትናንቱ ዝግጅታችን ከኢትዮጵያ ቡናው ወጣት አማካይ ተጫዋች ሀብታሙ ረጋሳ ጋር ያደረግነውን ቆይታ የመጀመሪያ ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል። በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ሃብታሙ ስለ መስዑድ መሃመድ ስለ ሳላዲን ባረጌቾ ስለ ብሔራዊ ቡድን ስለ ራሱ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ያወራንን ይዘን ቀርበናል። ከትናንት የቀጠለውን ተከታይ ክፍል ደግሞ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ለወጣቶች እየተሰጠ ስላለው እድል

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ክለቦች የመንግስት ክለቦች ናቸው። የመንግስት ክለቦች ደግሞ መስራት የነበረባቸው ለእግር ኳሱ እድገት እንጅ ለውጤት መሆን አልነበረበትም። ምክንያቱም የእኛን አገር እግር ኳስ ስትመለከት በገንዘብ በኩል ለክለቦች በገንዘብ በኩል የሚገያስገኘው ትርፍ የለም። ስለዚህ ክለቦቹ ገንዘብ አውጥተው ትርፍ ማግኘት ካልቻሉ ትኩረት ማድረግ የነበረባቸው ለውጤቱ ሳይሆን እግር ኳሱን ለማሳደግ ለወጣቶች እድል መስጠት ላይ ነበር።

ክለቦቹ የመንግስት ቢሆኑም የሚተዳደሩት ግን በግለሰቦች ፍላጎት ላይ ተንጠልጥለው ነው። በድርጅቱ ውስጥ ያለው ኃላፊ ለእግር ኳስ ፍቅር ካለው ክለቡን ያጠናክራል እግር ኳስ የማይወድ ኃላፊ ሲመጣ ደግሞ በተቃራኒው ቡድኑን እንደ ቀላል ነገር “ይፍረስ” ብሎ ያፈርሰዋል ለምሳሌ አየር መንገድ የፈረሰውን ታስታውሳለህ። ውጤትም የሌላቸው ክለቦች ወጣት ላይ ትኩረት ማድረግ ቢችሉ ኖሮ ለእግር ኳሳችን እድገት የሚኖረውን ጠቀሜታ አስበው።

ለምሳሌ በዚህ ዓመት ከእኛ ክለብ እንደ አስናቀ ሞገስን እና አህመድ ረሽድን ተመልከት። በብሔራዊ ቡድን ደግሞ እንደ ዘካሪያስ ቱጂ ተካልኝ ተጀኔ እና ጋቶች ፓኖም አይነት ተጫዋቾችን ማግኘት የቻልነው ክለቦቹም ሆነ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለወጣቶች እድል ስለሰጧቸው ነው። ደደቢትም ሆነ ጊዮርጊስ ለእነ ዘካሪያስ እና ተካልኝ አይነት ተጫዋቾች እድል ባይሰጡ ኖሮ እነዚህን ልጆች አናገኛቸውም ነበር ማለት እኮ ነው።

በዚህ በኩል የውጭ አገር አሰልጣኞች ወደ አገራችን ሲመጡ ለወጣቶች የሚሰጡትን እድል ታያለህ። ለምሳሌ ባሬቶ ለናትናኤል ዘለቀ እና አንዳርጋቸው ይላቅ እድል ሲሰጣቸው አይተሃል። ኦፌም ኦኑራ ለተስፋዬ አለባቸው ለሽመልስ በቀለ እና ኡመድ ኡክሪን ወደ ብሔራዊ ቡድን የጠራቸው እሱ ነበር። የጊዮርጊሱ ሚቾም ቢሆን ለእነ አሉላ እና አበባው ቡታቆ የሰጣቸውን እድል ተመልከት።

በአጠቃላይ ግን የኢትዮጵያ ወጣቶች በጣም ያሳዝኑኛል። ምክንያቱም በየሰፈሩ እና በየትናንሽ ሜዳዎቹ ብትዘዋወር አገራቸውን መጥቀም እየቻሉ ሳይጠሙ የቀሩ መሆናቸውን ታያለህ። ለዚህ ነው ክለቦች ለወጣቶች እድል መስጠት አለባቸው የምለው።

ስለ አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ

ብዙ ጊዜ የውጭ አገ አሰልጣኞች ሲያሰለጥኑ ብዙ ጊዜ የእውቀት ሽግግር ይኖራል። ክለቡም የውጭ አሰልጣኝ መቅጠሩ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ነገ ግን ስለ ክለቡ አዲስ አሰልጣኝ የአጨዋወት ፍልስፍናም ሆነ የግል ባህሪ እና የስራ ዘመን እውቀት የለኝም። ስለዚህ ስለ አዲሱ አሰልጣኝ ከወዲሁ መናገር አልችልም። አሰልጣኙ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሰማሁት ግን ኳስን ይዞ ለመጫወት ፍላጎት እንዳለው ሲናገር ነው። ኳስን ይዞ የሚጫወት ቡድን የሚገነባ ከሆነ ከቡና የቆየ ፍልስፍና ጋር ይስማማል። ይህ ከሆነ ደግሞ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። 

ስለቡድኑ ወጣት ተጫዋቾች

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በርካታ ሲኒየር ተጫዋቾቻችን በመቀጣታቸውና በመሰናበታቸው ምክንያት ቡድናችን በወጣቶች የተሞላ ነበር ማለት ይቻላል። የቀጣዩ ዓመት የቡድናችን ስብስብም በወጣቶች እንደሚገነባ አሰልጣኙ ተናግሯል። እንደዚህ ከሆነ በጣም ጥሩ ቡድን ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ወጣት በጣም መሮጥ ይወዳል ራሱን ማሳየት ይፈልጋል ስለዚህ በትኩስ ጉልበት ስለሚጫወት ለቡድናችን ጥሩ ነው የሚሆነው። ወጣቶች ሊሰሩ የሚፈልጉትን እንዲሰሩ ግን ከአሰልጣኙ እምነት ሊጣልባቸው ይገባል። እየተጠራጠርክ የምታስገባው ከሆነ ግን ጥሩ ውጤት ማምጣት አይችልም።

ስለወቅቱ ብሔራዊ ቡድን

በዘንድሮው ብሔራዊ ቡድን የተመለከትኩት አዲስ ነገር ቢኖር አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በወጣቶች የተገነባ ቡድን መስራቱን ነው። ከግብ ጠባቂዎቹ ጀምሮ እስከ አጥቂ መስመር ያለውን ቦታ ብትመለከት አብዛኞቹ ለብሔራዊ ቡድን ሲጫወቱ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። እነ ተካልኝ ደጀኔን ዘካሪያስ ቱጂ አስቻለው ታመነ አስቻለው ግርማ ጋቶች ፓኖም አቤል ማሞ አታሪክ ጌትነት እና ራምኬል ሎክን ብትመለከት ለብሔራዊ ቡድን ሲጫወቱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። ቅድምም እኮ የኢትዮጵያ ወጣት ያሳዝነኛል ያልኩህ ለዚህ ነው። ዮሃንስ ሳህሌ በደደቢት ቆይታው እንደ ተካልኝ እና አስቻለው ታመነን በሚገባ ስለሚያቅዋቸው ነው የመረጣቸው። ዮሀንስ ሳህሌ ለእነዚህ ወጣቶች እድል ባይሰጣቸው ኖሮ የት ታገኛቸው ነበር። በወጣቶች ላይ ደፍረን ከሰራን እንደነዚህ አይነት ልጆችን በብዛት ማግኘት እንደምንችል ማሳያ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ቡድኑ ከሌሶቶም ሆነ ከኬኒያ ጋር በነበረው ጨዋታ በአጭር ጊዜ ዝግጅት ነው የተጫወቱት። በዚህ ውስን ጊዜ ጥሩ ሊባል የሚችል ውጤት ሊያመጡ ችለዋል። ቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታዎቹ ግን ሰፋ ያለ ጊዜ ስላላቸው በሚገባ ተዘጋጅተው ጥሩ ውጤት እንደሚያመጡ ተስፋ አድርጋለሁ።

ስለ መስዑድ መሃመድ

መስዑድን ኤሌክትሪክ እያለ ጀምሮ አውቀዋለሁ። ከችሎታው እስከ ባህሪው ድረስ አርአያ መሆን የሚችል ልጅ ነው። በጣም ስርዓት ያለው እና ስራውን በሚገባ አክብሮ የሚሰራ ልጅ ነው። መስዑድ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ተጫዋች ነው። ከእሱ ጋር በመጫዎቴ በራሱ እድለኛ ነኝ ብዬ ነው የማምነው። ለእኛ ለወጣቶቹ ልምዱን ከማካፈል ጀምሮ የሚሰጠን ምክር እና አስተያየት በጣም ጥሩ ነው።

ስለ ሳላዲን ባርጌቾ

ከሳላዲን ባርጌቾ ጋር በመብራት ሀይል ወጣት ቡድን አብረን ተጫውተናል። ፈረንጁ አሰልጣኝ እንደመጣ ከሲኒየሮቹ  ሶስት ተጫዋቾችን እና ከወጣቶች ደግሞ ሳላዲንን አልፈልገውም አለ። የሚገርምህ ነገር ክለቡ ሶስቱን ሲኒየሮች አሰልጣኙን ተለማምጦ ሲያስቀጥላቸው ሳላዲንን ግን ሳያስቀጥለው ቀረ። እሱም በብስጭት ለውሃ ስራዎች ፈረመ። ከዚያ ወደ መድን ሂዶ ከአስራት ኃይሌ ጋር በመስራት ራሱን አሳየ። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ኤሌክትሪክ ለሲኒየሮቹ ያደረገውን ጥረት ለሳላዲን አድርጎ ቢሆን እና በክለቡ እንዲቆይ ቢደረግ ኖሮ ክለቡ ምን ያህል በሳላዲን ይጠቀም ነበር? ብዬ እጠይቃለሁ። ለዚህ ነው ቅድም የመንግስት ክለቦች ለወጣቶች ትኩረት መስጠት አለባቸው ያልኩህ። ካለው ችሎታ ብቃት እና ጥንካሬ አኳያ በእርግጠኝነት መብራት ኃይል ሳላዲን ባርጌቾን አጥቶታል። የሚገርምህ እኮ ደግሞ ሳላዲን ያለው ባህሪ ፕሮፌሽናል ነው።

ደካማ እና ጠንካራ ጎን

በመጀመሪያ ደረጃ በሁሉም መልኩ መሻሻል እፈልጋለሁ። ገና ብዙ ላሻሽላቸው የሚገቡ ስራዎች አሉ።  በጉልበት ጠንካራ መሆን እፈልጋለሁ በሁለት እግሬም መጫወት እፈልጋለሁ የምጠቀመው ግራ እግሬን ብቻ ስለሆነ። ከዚህ ውጭ ግን ልጅ እያለሁ የምጫወተው በሰውነትና በጉልበት ከእኔ ከሚበልጡ ተጫዋቾች ጋር ነበር። እንደዚህ አይነት ተጫዋቾች ጋር ስትጫወት ደግሞ ኳስን ቶሎ ቶሎ የመልቀቅና የመቀበል ልምድ ታዳብራለህ። ያ ጠቅሞኝ ይመስለኛል ፈጥኖ በማሰብ በኩል ጥሩ ነኝ።

የመጨረሻ ራዕይ

ለብሔራዊ ቡድን በመጫዎት አገሬን ማገልገል እና ወደ ውጭ ሂጄ መጫዎት እፈልጋለሁ። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!