የሎዛ አበራ እግሮች ሉሲዎቹን ወደ ዓለም ዋንጫ አንደረደሩ
ሐምሌ 20, 2007

ይርጋ አበበ

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከ20 ዓመት በታች ባለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የተዘበራረቁ ስሜቶች ነበሩ። በአንድ በኩል ታዳጊዎቹ ሉሲዎች ወደ ያውንዴ ተጉዘው መረባቸውን ሳያስነኩ ክብራቸውን ጠብቀው ከሜዳ መውጣታቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ክብራቸውን አስጠብቀው ከካሜሩን አለመውጣታቸው ነበር። በያውንዴ ኢንተርናሽናል አየር ማረፊያ ላይ ከፍተኛ መጉላላት እና መንገላታት ደርሶበት የነበረው የብሔራዊ ቡድኑ አባላት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይም ፕሬዚዳንቱ እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ባደረጉት ጥረት ቡድኑ ወደ አገሩ መግባቱ ይታወሳል።


ከሁለት ሳምንት በፊት በምዕራብ አፍሪካ ድብልቅልቅ ስሜቶችን ይዞ የተመለሰው ብሔራዊ ቡድን ትናንት ደግሞ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ባህር ዳር ከተማ ላይ መላው ደጋፊውን ጮቤ ያስረገጠ ውጤት አስመዝግቧል። ለቡድኑ ውጤት ማማር ደግሞ የደደቢቷ ወጣት ሎዛ አበራ ያስቆጠረቻቸው ጎሎች ተጠቃሽ ናቸው። የወጣቷ ሎዛ አበራ እግሮች ወደ ካሜሩን የግብ ክልል የላኳቸው ኳሶች ማረፊያቸውን መረብ ላይ በማድረጋቸው ሁለት ለአንድ ያሸነፈው የሉሲዎቹ ቡድን አሁን ፊቱን ወደ ዓለም ዋንጫው ማድረግ ጀምሯል። በዚህም ከወራት በኋላ “ፓፓኒው ጊኒ” የተባለችው የደሴት አገር በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረስ የቻለው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ጨዋታውን ከአልጀሪያ ወይም ከቡርኪናፋሶ ጋር ያካሂዳል

ስለ ጨዋታው ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም በስልክ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ “ቡድናችን ቀድሞ ካገባ በኋላ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መገባደጃ ደቂቃ ላይ ስለተቆጠረበት በመጠኑ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር። ሆኖም በእረፍት ሰዓት ከአሰልጣኙ በተደረገላቸው የማበረታቻ ምክር የተነቃቁት ተጫዋቾቻችን ጨዋታውን ማሸነፍ እንደሚችሉ አምነው ሁለተኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጀምረዋል” ያሉ ሲሆን አቶ ወንድም ኩን አያይዘውም በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የሆነው የካሜሩንን ብሔራዊ ቡድን ማሸነፍ ታላቅ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል። ሁለተኛውን ጎል ሎዛ ካስቆጠረች በኋላ ቡድኑ በተጋሚው ላይ በታክቲካል ዲስፕሊን የበላይነትን መውሰዱን አቶ ወንድምኩን ተናግረዋል።   

በስታዲየሙ ከ30 ሺህ በላይ ተመልካች ጨዋታውን እንደተመለከተው የገለጹት አቶ ወንድምኩን ለድሉ መገኘት ከደጋፊው ይደረግ የነበረው የማበረታቻ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። ደጋፊው ቡድኑን ከማበረታታት በዘለለም በፍጹም የስፖርታዊ ጨዋነት ታጅቦ ጨዋታውን በመከታተሉ ሊመሰገን እንደሚገባውም አስታውቀዋል


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
dires gebeye [935 days ago.]
 KETYBET

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!