በድሬዳዋ ስታዲየሞችን ያደመቁት የአውስኮድና የወሎ ኮምቦልቻ ክለብ ደጋፊዎች
ነሐሴ 04, 2007

ድሬዳዋ ሰሞኑን ደምቃለች። ዳሩ ድሬ እንኳንም እንደዚህ አይነት አገር አቀፍ የእግር ኳስ ውድድር ተካሂዶባት ድሮውንም የደመቀችና የሞቀች ከተማ ነች። የከተማዋ ነዋሪ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር ከ እስከ የሚባል እንዳልሆነ መናገር አንባቢን ማሰልቸት ተናጋሪውንም ጉንጭ ማልፋት ይሆናል። ከአስራት ሀይሌ እሰከ መሀመድ ሚግ ከአሰግድ ተስፋዬ እሰከ አሸናፊ ግርማ ከስምኦን አባይ እስከ ታናሽ ወንድሙ ዮርዳኖስ አባይ ያሉ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማፍራት የቻለው የድሬዳዋ የእግር ኳስ ማህጸን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየመከነ ይመስላል። ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የእግር ኳስ አኬር ከድሬ ተነስቶ ወደ ደቡብ የዞረ ቢመስልም የህዝቡ የእግር ኳስ ፍቅር ግን “እያደር አዲስ” የሚባል አይነት ነው። ለዚህ አነጋገሬ አስረጅ ምሳሌ እንዳቀርብ ብጠየቅ የመጀመሪያ መልሴ ከአራት ወራት በፊት ለ11ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች ማጣሪያ ለማድረግ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ የተጫወተውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተደረገለትን አቀባበል ማንሳት ይሆናል። ቡድኑ ከሱዳን አቻው ጋር ተጫውቶ “ያለ አቻው የተጋጠመ ይመስል በሜዳው ሁለት ለባዶ ቢሸነፍም የድሬ ልጆች ግን “ከ13 ዓመታት በኋላ በቤታችን የተደገሰውን ዓለም አቀፍ ውድድር በድብርት አንሸኘውም ያሉ ይመስል ስታዲየሙን አጣበው ከተማዋን አድምቀው ታይተዋል። በድሬዳዋ ልጆች የእግር ኳስ ፍቅር የተደመሙት የሱዳኑ አሰልጣኝ “በደጋፊዎቹ ድርጊት ተገርሜያለሁ እናንተንም በዚህ መልኩ እንቀበላችኋለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ፕረሚየር ሊግ ተወካይ ያጣችው ድሬዳዋ በቀጣዩ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ የሚወክላትን ክለብ ለማግኘት በሜዳዋ ያዘጋጀችውን ድግስ እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የተዘጋጀች ቢሆንም የአማራ ክልሎቹ ተወካዮች ግን “ቡድናቸውን በቤታቸው ሳይሆን ከቤታቸው ወጥተውም ማበረታታት የሚችሉ ደጋፊዎች አሉን” ያሉ ይመስላሉ።  ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ከዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ እና ውድድሩ ከሚካሄድበት ከደሬዳዋ ባገኘው መረጃ መሰረት ከደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ እና ከባህር ዳር ተጉዘው ድሬዳዋ የደረሱ ደጋፊዎች ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቡድኖቻቸውን በማበረታታት አቻ አልተገኘላቸውም።

አማራ ክልል በዚህ የሱፐር ሊግ ውድድር አራት ክለቦችን ማለትም በጥንካሬያቸው አድናቆት ያተረፉትን ፋሲል ከነማን እና ወሎ ኮምቦልቻን እንዲሁም የአማራውሀስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት እና ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲን ያሳትፋል። ከእነዚህ ክለቦች መካከል የጎንደሩ ፋሲል ከነማ በውጤት በኩል ሁለቱንም ጨዋታዎቹን ያሸነፈ ሲሆን ወሎ ኮምቦልቻም ጠንካራ ተፎካካሪነቱን በማሳየት ላይ ይገኛል። ከዚህም በላይ ግን የስፖርት ቤተሰቡን ትኩረት የሳበው ከጎንደር ከባህር ዳር እና ከኮምቦልቻ ተጉዘው ድሬዳዋ የደረሱት የሶስቱ ክለብ ደጋፊዎች ቡድኖቻቸውን ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እየዘመሩ መደገፋቸው ነው። ይህ ባህል ደግሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተደጋግሞ እንዲታይ የሚፈለግ ድርጊት በመሆኑ በርካቶች ለደጋፊዎቹ አድናቆታቸውን ቸረውላቸዋል። በተለይ የዎሎ ኮምቦልቻ እና የአውስኮድ ደጋፊዎች የስታዲየም ድምቀት ሆነው ተገኝተዋል።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮፉትቦልethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!