የሱፐር ሊጉ ሁለተኛ ምዕራፍ ተሳታፊዎች
ነሐሴ 10, 2007

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚቀላቀሉትን ሁለት ክለቦች ለማወቅ ባዘጋጀው የብሔራዊ ሊግ ውድድር 24 ክለቦች በድሬዳዋ ከተማ ሲጫወቱ ቆይተው 16ቱ ወደመጡበት ሲመለሱ ስምንት ቡድኖች ደግሞ ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግረዋል። ስምንቱ ክለቦች ዛሬ እና ነገ እረፍት ካደረጉ በኋላ የፊታችን ረቡዕ ጀምሮ እርስ በእርስ ተገናኝተው ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚያልፉ አራት ቡድኖች ይለያሉ። ለመሆኑ ወደ ሩብ ፍጻሜ የተሸጋገሩ ክለቦች እነ ማን ናቸው ከየትኛው አካባቢስ ተገኙ ወቅታዊ ደረጃቸውስ ምን ይመስላል የሚሉትን ጥያቄዎች በወፍ በረር እንቃኛለን።

ላለፉት ረጅም ዓመታት የእግር ኳስ ደረጃቸው ወደታች ከተጓዘባቸው አካባቢዎች መካከል የምዕራብ ኢትዮጵያ ዞን ማለትም ጅማ ከተማ እና አካባቢዋ ተጠቃሽ ናቸው። ይህንን ታሪክ ለመቀየር በሚመስል መልኩ ሁለት የአንድ ከተማ ክለቦች ጅማ አባቡና እና  ጅማ ከነማ ወደ ሱፐር ሊጉ መቀላቀላቸው አስገርሞ ሳያበቃ ሁለቱም የአንድ ከተማ ክለቦች የሩብ ጽጻሜ ተፋላሚ መሆናቸው ደግሞ ሌላው አስገራሚ ታሪክ ሆኗል። ከወራት በፊት ከአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው የነበሩት የጅማ ከነማ ክለብ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች “እቅዳችን ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀል ነው” ብለው ነበር። የአሰልጣኞቹ እና የተጫዋቾቹ እቅድ እውን መሆን አለመሆኑን ከቀናት በኋላ የምናየው ቢሆንም ሁለቱ የአንድ ከተማ ክለቦች በሱፐር ሊጉ የሩብ ፍጻሜ ተወዳዳሪ ሆነዋል። ወቅታዊ ብቃታቸውን በተመለከተ ውድደሩ ከሚካሄድበት ድሬዳዋ ከተማ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ሁለቱም ክለቦች ለፕሪሚየር ሊጉ ቆርጠው የተነሱ ይመስላል። በምድብ ማጣሪያ ካካሄዷቸው ጨዋታዎች አብዛኞቹን በድል የተወጡ ሲሆን የጎል ክልላቸውን ተደራጅተው ስለሚጠብቁም መ የጠላት ወረራ መረባቸውን በተደጋጋሚ አልጎበኘባቸውም በአንጻሩ እነሱ ግን በመልሶ ማጥቃት በርካታ ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ወልድያ ከነማ ፕሪሚየር ሊጉን መቀላቀሉን አስመልክቶ ከዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገው የነበሩት የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ያየህ አዲስ “እቅዳችን በየዓመቱ አንድ ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማሳደግ ነው። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ አንድ የባህር ዳር ከተማ ክለብ ፕሪሚየር ሊጉን እንዲቀላቀል እንሰራለን” ብለው ነበር። በዚህ ዓመትም አራት የክልሉ ክለቦች የሱፐር ሊጉ ተወዳዳሪ ቢሆኑም ሶስቱ ማለትም ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው ፋሲል ከነማ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በጊዜ ወደ መጡበት ሲመለሱ መቀመጫውን ባህር ዳር ከተማ ያደረገው የአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ወይም አውስኮድ እግር ኳስ ክለብ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ችሏል። አውስኮድ በሩብ ፍጻሜ የሚወዳደር ብቸኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ተወካይ ክለብ ነው። የቡድኑን ጥንካሬ በተመለከተ የደረሰን ወቅታዊ መረጃ የለም።

ልክ እንደ ጅማ ከተማ ሁሉ አዲስ አበባ ከተማም ሁለት ክለቦችን በሩብ ፍጻሜው ማሳለፍ ችላለች ፌዴራል ፖሊስን እና አዲስ አበባ ከነማን። ሁለቱ ክለቦች በሱፐር ሊጉ አጀማመራቸው ያላማረ ቢሆንም ቀስ ብለው ግን ወደ ትክክለኛው ትራክ በመግባት ከምድባቸው ማለፍ ችለዋል። በተለይ ፌዴራል ፖሊስ የቀድሞው ጥንካሬውና ገናናነቱ ተረስቶ የነበረ በመሆኑ እንደገና በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመግባት ከነባሮቹ ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች በተሻለ ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፉ አስገራሚ ነው። አዲስ አበባ ከነማ በበኩሉ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ውድድር በአሰልጣኝ አንዋር ያሲን እና አብዶ ከድር እየሰለጠነ ለሩብ ፍጻሜ ቀርቦ ነበር። ዘንድሮስ ከአምናው የተሻለ ውጤት ያስመዘግባል ወይስ ሌላ በቀጣዮቹ ቀናት እናየዋለን።

“የኮሚሽናችን የአምስት ዓመት ግቡ በፕሪሚየር ሊጉ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል ግማሹን የደቡብ ክልል ማድረግ ነው” የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ መዝረዲን ሁሴን ነበሩ ይህንን ንግግር የተናገሩት በሱፐር ሊጉ የሚሳተፉ ሶስት ክለቦችን ወደ ድሬዳዋ በላኩበት የሽኝት ፕሮግራም ላይ። ኮሚሽነር መዝረዲን ክልላቸው ሶስት ክለቦችን በሱፐር ሊጉ ያሳተፈ ቢሆንም ደቡብ ፖሊስ ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፍ ዘንድ አልተቻለውምና ሁለቱ ጎረቤታማቾቹ ክለቦች ሃላባ ከነማ እና ሆሳዕና ከነማ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፉ ክለቦች ሆነዋል። ሁለቱ ጎረቤታማች ክለቦች ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል የቻሉ ሲሆን ለፍጻሜ መድረስ ከቻሉ የክልሉን የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ከፍ ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።

ምስራቅ ኢትዮጵያ ከሰው ጋር ተግባብቶ የሚኖር ህዝብ ያለበት ቀጠና ነው እየተባለ ይነገርለታል። የአካባቢው ነዋሪ በተለይ የሀረር እና የድሬዳዋ ህዝብ ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ከእግር ኳስ ጋር ያለው ዝምድናም እጅግ የጠበቀ ነው። ለዚህም ማረጋገጫው ለዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ መንገስ የቻሉ “ተርብ” የሆኑ ልጆችን ማፍራታቸው ሲሆን እንደ ድሬዳዋ ጥጥ እና ጨርቃጨር እንዲሁም ድሬዳዋ ሲሚንቶ እና ሀረር ቢራ የመሳሰሉ ክለቦች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር። ዘመን ተቀይሮ የአካባቢው እግር ኳስ ወደ ታች ሲምዘገዘግ የክለቦቹም ሆነ የተጫዋቾቹ ጥንካሬ “ታሪክ” ሆኖ ከመነገር አልዳነም። በቀጣዩ ዓመት አካባቢውን በፕሪሚየር ሊጉ ለመወከል ድሬዳዋ ከነማ አደራ የተጣለበት ብቸኛው የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ ሆኗል።

የመጀመሪያውን ወሳኝ ምዕራፍ በድል ተወጥተው ወደ ሁለተኛውና እጅግ ፈታኙ ምዕራፍ የተሸጋገሩት ስምንት ክለቦች እነዚህ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ ሚዜ ሁለቱ ሙሽራ ማለትም ሁለቱ የፍጻሜ ተፋላሚዎች የፕሪሚየር ሊግ ተወዳዳሪ ሆነው ውድድሩ የሚጠናቀቀው ከአንድ ሳምንት በኋላ ይሆናል።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ታዲዬስ [918 days ago.]
 ዋንጫ እያግበሰበሱ የሀገራችንን ኳስ የሚያዘቅጡ ቡድኖችን አንፈልግም, በትንሹም ቢሆን የሚማርክ ኳስ ና ፍልሚያ የሚያሳዮንን ቡድኖችንና ተጫዋቾችን እንደግፋለን, በትንሹ ጠቦ የሀገራችን ኳስ ዳግም 31 አመት ወደ ኃላ እንዲጓዝ አንመኝም, ጊዬርጊስም ቢሆን ሀገር ውስጥ ባለው ውጤት ብቻ እኛነን አንደኞች ብሎ ከመፎከር ሀገርቂጥ ያለውን የአፍሪካ champions league ውጤቱን ለማሻሻል ቢጥር የተሻለ ነው, የዛን ጊዜ ኳስ ወዳዱ ተመልካች ሳታወሩ ይደግፋችኃል, ...

ሀሮዬ [918 days ago.]
 @samiflex ምን አይነቱ መንደርተኛ ነገር ነህ?, ተረት ... ኮተት ምናምን ስትል አይደብርህም እንዴ? በመጀመሪያ በዚህ ኮልታፋ አንደበትህ ይህንሚያክል ስያሜ መጠቀምህ ያሳፍራል,

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!