በትንሹ ተጀምሮ በስኬት የተጠናቀቀው ወገንን የመርዳት ዘመቻ
ነሐሴ 25, 2007

 ይርጋ አበበ

“ስዋስወ ገነት የልማትና የተራድኦ ድርጅት” ይሰኛል። ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ሲሄዱ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደብረ ሊባኖስ ገዳም አቅራቢያ ይገኛል። ከ11 ዓመት በፊት እንደተመሰረተ የሚነገረው ይህ ድርጅት የአእምሮ ህሙማንን፣ አረጋውያንን እና ወላጅ አልባ ህጻናትን ይዞ የሰብአዊ ተግባር ስራ እያከናወነ የሚገኝ ድርጅት መሆኑንም ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ያገኘነው የሰነድ ማስረጃ ያመለክታል። ይህ የልማትና የተራድኦ ድርጅት በውስጡ ከያዛቸው የድርጅቱን አገልግሎት ከሚያገኙ የህብረተሰብ አካላት መካከል በተለይ የመማር ፍላጎት እያላቸው ግን ለመማር የሚያስፈልጉ የትምህርት መርጃ መሳሪያ በማጣት ብቻ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ህጻናት ይገኙበታል። እነዚህን ህጻናት መማር እንዲችሉ የትምህርት መርጃ  መሳሪያዎችን ከወገን ደራሽ የአገራችን ህዝብ ለመሰብሰብ ቆርጦ የተነሳው የስፖርት ጋዜጠኞች ስብስብ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ አካሂዷል።

ሶስት የስፖርት ጋዜጠኞች ማለትም ጋዜጠኛ በአስተባባሪነት በመሩት በዚህ የበጎ አድራጎት ስራ ላይ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ፣ ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ እና የመድረክ መብራትና ድምጽ ቁጥጥሩን ደግሞ ፕላስ ፕላስ ኮምዩኒኬሽን እና ኤቨንትስ ከፕሮግራሙ ጋር የቆሙ ተባባሪ ድርጅቶች  ናቸው። የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ዓላማውን ለህዝብ  በማድረስ በኩል ከፍተኛ ተባባሪ መሆናቸው ተገልጿል።

“ለዓላማ እንጫዎት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ሲኖሩ ጨዋታዎቹን ለመታደም ስታዲየም የተገኙ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም ሲገቡ የተለያዩ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ይዘው በመግባትተባባሪነታቸውን አሳይተዋል።

በእለቱ ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ የተገናኙት የስፖርት ጋዜጠኞች እና ሙዚቃ አጫዋቾች ወይም ዲጄዎች ሲሆኑ ጨዋታውን ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው በዋና ዳኝነት መርተውታል። ውጤቱም ዲጄዎች አራት ለባዶ በሆነ ሰፊ ውጤት ያሸነፉ ሲሆን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በጎል ሙከራ የበላይነትም ይዘው ታይተዋል። በተለይ አጥቂ መስመር ላይ ተሰልፈው የነበሩት የዲጄዎቹ አጥቂዎች ለስፖርት ጋዜጠኞች የተከላካይና የግብ ጠባቂ መስመር አስቸጋሪ ሆነው ነበር የታዩት። ከዚህ ጨዋታ በኋላ የተገናኙት የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድኖች ነበሩ። በቡና አንድ ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በመሃል ዳኝነት መርተዋለች።

በእለቱ የተሰበሰቡትን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ብዛት ይፋ ያደረገው አስተባባሪ ኮሚቴው እንደገለጸው 5172 ደብተሮች፣ 3327 ብዕሮች እና በርካታ እርሳስ እና መቅረጫ እንዲሁም ማጥፊያ ወይም ላጲስ የተሰበሰበ ሲሆን ቃል የተገባው ደግሞ የካቲት የወረቀት ስራዎች ድርጅት 25 ሺህ ደብተሮች ለመስጠት ቃል ገብቷል። በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ላይ  ሚተላለፈው ለዛ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ አንድ ሺህ ደብተሮችን ለግሷል።

በጋዜጠኞች የእግር ኳስ ውድድር ወይም ሚዲያ ካፕ የዋንጫ ባለቤት የሆነው የብስራት ኤፍ ኤም እግር ኳስ ቡድን  የተበረከተለትን የስምንት ሺህ ብር  ሽልማት ሙሉ በሙሉ ለዚሁ የበጎ ዓላማ ተግባር የለገሰ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ደግሞ የአምስት ሺህ ብር እርዳታ  አበርክተዋል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብቸኛዋ  ሴት የወንድ ቡድን አሰልጣኝ የሆነችው መሰረት ማኒ በበኩሏ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የደብተር እና ብዕር ድጋፍ አድርጋለች።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!