“እንኳን ወደ ቤታችሁ በደህና መጣችሁ” የአርባምንጭ ከነማ ደጋፊዎች
ነሐሴ 26, 2007

ይርጋ አበበ

ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ይሰኛሉ ከዓመታት በፊት ፈረሰኞቹን በማሰልጠን ውጤታማ የሆኑት አሰልጣኝ። በወቅቱ ፈረሰኞቹ በርካታ ኮከብ ተጫዋቾችን የያዙ ቢሆንም የዳዊት መብራቱ ወይም ገዳዳውን የመሰለ ተጫዋች ግን በመብራት ተፈልጎ የሚገኝ ቢሆንም በአንድ አጋጣሚ ግን ሰርቢያዊው አሰልጣኝ እና ገዳዳው አይን እና ናጫ ሆኑ። በሁለቱ ዝሆኖች ማለትም ኮከቡ ተጫዋችና ኮከብ አሰልጣኙ ግጭት የተነሳ በመጠኑም ቢሆን ክፍተት የተፈጠረ ቢሆንም ቀጭኑ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ግን ከአርባ ምንጭ ከተማ ገና በታዳጊነቱ ጀምሮ የሚያውቁትን አበባው ቡታቆን ተማምነው ዳዊትን ገፉት። በሚቾ እምነት የተጣለበት ወጣቱ አበባው ቡታቆ ከዚያች እለት ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም መገባደጃ ድረስ የፈረሰኞቹን ግራ ኮሪደር እንደፈለገ ሲቦርቅበት ቆይቷል።

“አንድ ቀን ለኢትዮጵያ ቡና መጫወት እፈልጋለሁ ምክንያቱም ደጋፊዎቻቸው አስገራሚዎች ናቸው” ሲል አስተያየት በመስጠት በቡና ደጋፊዎች ዘንድ በእጅጉ ይወደድ የነበረውና በክለቡም ሲፈለግ የቆየው የደደቢቱ ታደለ መንገሻ ነው። ከአርባ ምንጭ ከተማ ገና በልጅነቱ ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ኮትኩተው ያሳደጉት ፈረሰኞቹ ቢሆኑም ጥበበኛው እግረ ቀጭን አማካይ ግን ፍሬውን መስጠት የጀመረው ለደደቢት እግር ኳስ ክለብ ነው።

 ከሰማያዊ ለባሾቹ ጋር አንድ የፕሪሚየር ሊግ እና አንድ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን ያነሳው ታደለ መንገሻም ሆነ ከፈረሰኞቹ ጋር ቁጥር ስፍር የሌለው ድል የተጎናጸፈው አበባው ቡታቆ ጀርባቸውን ለአዲስ አበባ ሰጥተዋል። ሳምንታዊው እንግሊዝኛው ካፒታል ጋዜጣ ለንባብ እንዳበቃው ከሆነ ሁለቱም ተጫዋቾች እጅግ ከፍተኛ በሆነ የዝውውርና የክፍያ ውል የትውልድ ከተማቸውን ክለብ ተቀላቅለዋል። አበባው ቡታቆ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ተከፍሎት የጋሞጎፋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችውን የአርባምንጭ ከነማን እግር ኳስ ክለብ ሊያገለግል ሲስማማ ታደለ መንገሻ በበኩሉ በወር 75 ሺህ ብር ወይም በድምሩ ከአበባው በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ሊከፈለው ተስማምቶ ፊርማውን ወረቀት ላይ አኑሯል። ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም ሁለቱ ኮከብ ተጫዋቾች የትውልድ ከተማቸውን ያገለግላሉ ማለት ነው።  

የሁለቱ ኮከቦች አርባምንጭ ከነማን መቀላቀላቸውን ተከትሎም የከተማው እግር ኳስ አፍቃሪ “እንኳን ወደ ቤታችሁ ደህና መጣችሁ” ብሎ የተቀበላቸው መሆኑን አርባምንጭ የሚገኙ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች የገለጹ ሲሆን ደጋፊዎቹ አክለውም “የአርባ ምንጭ ፍሬዎችን ወደ ቤታቸው የመመለሱ ሂደት ይቀጥላል” ሲሉ መናገራቸውንም ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ጠቁሟል።

ከፈረሰኞቹ ከተለየ በኋላ ወደ ሱዳን አቅንቶ ከአል ሂላል ጋር ያልተሳካ አንድ የውድድር ዓመት አሳልፎ ወደ አገሩ የተመለሰውን አበባው ቡታቆንም ሆነ፤ በደደቢት ስኬታማ ጊዜ ሲያሳልፍ የቆየውን ጥበበኛውን ታደለ መንገሻን ለማስፈረም በርካታ ታላላቅ ክለቦች ፍላጎታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆኑም ተጫዋቾቹ ግን ቅድሚያ ለትውልድ ከተማቸው ክለብ መስጠታቸውን ከካፒታል ጋዜጣ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Getaneh Girma [899 days ago.]
 It is good news for us, wish you all the best!!!

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!