አስገራሚው የሲሸልስ እና የዋልያዎቹ ጨዋታ
ነሐሴ 30, 2007

ይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ እየተመራ አራት የነጥብ እና ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አካሂዷል። በነጥብ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ደግሞ አቻ ወጥቷል። በወዳጅነት ጨዋታዎች ግን ሁለቱንም ተሸንፏል። ብሔራዊ ቡድኑ ካደረጋቸው የነጥብ ጨዋታዎች መካከል በአንዱም የተሸነፈ ባይሆንም ትናንት ከሲሸልስ ጋር ያደረገውን ጨዋታ አለማሸነፉ ግን አሰልጣኙንም ሆነ ተጫዋቾቹን ከትችት የሚያድናቸው አልሆነም። ምክንያቱም ለ31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ካለው ጠባብ እድል እና የዋልያዎቹ ቀጣይ ተጋጣሚ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከመሆኑ አኳያ የትናንቱን ጨዋታ ማሸነፍ ነበረባቸውና ነው። ተጫዋቾቹም ሆነ አሰልጣኙ በውጤቱ ምክንያት ለምን ይተቻሉ? ውጤቱ ይህን ያህል የከፋ ነው ወይ? በቡድኑ ላይ የታየው ግልጽ ድክመት እና የአሰልጣኙ ታክቲካል ስህተት ምን ነበር? የሚሉትን ጥያቄዎች ከዚህ በታች እናቀርባቸዋለን።

ከ90 ሚሊዮን እና 90 ሺህ ማን ይበልጣል

አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ አለማደጉን አስመልክቶ በቁጭት ሲናገር “እንዴት ከ60 ሚሊዮን ህዝብ 11 ኳስ የሚችል ሰው ማግኘት እናጣለን?” ብሎ ነበር። ደምሴ እውነቱን ነው። ላቲን አሜሪካውያኑ ብራዚል እና አርጀንቲናም ሆነ አውሮፓውያኑ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ጀርመን፣እንግሊዝ እና ጣሊያን የህዝብ ብዛታቸው በእግር ኳሳቸው ላይ አወንታዊ ተጽእኖ ሲያሳርፍ አይተናል። አፍሪካውያኑ ናይጄሪ እና ግብጽም ቢሆን ከአህጉሩ በርካታ የህዝብ ብዛት ካላቸው አገሮች ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ የእግር ኳስ ደረጃቸውም የሰሞኑን አያድርገውና ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ነበር። እንደዚህ ሲባል ግን እንደ ፖርቹጋል እና ኬፕ ቨርዴ አይነት አነስተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው አገራትም የእግር ኳስ ደረጃቸው ዝቅተኛ ነው ለማለት ተፈልጎ እንዳልሆነ ይታሰብ። በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ከናይጄሪያ ቀጥላ በሁለተኝነት ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያስ በእግር ኳስ  ረጃዋ ከአህጉሩ ስንተኛ ናት? የሚል የቁጭት ጥያቄ ማቅረብ ስህተት ይመስለኝም። ስህተት ከሆነም የተሳሳትኩበትን ምክንያት ሊያቀርብልኝ የሚችል ሰው ሊሞግተኝ ይችላል። ለማንኛውም ግን ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋቦን ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ አስር ከአልጄሪያ፣ ሌሴቶ እና ሲሸልስ ጋር የተደለደለ ሲሆን ከሁለቱ ባለ ዝቅተኛ የህዝብ ቁጥር አገሮች ጋር ማለትም ሌሴቶ እና ሲሸልስ ጋር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ አራት ነጥብ ብቻ ማግኘት ችሏል።

በአንጻሩ ትናንት በሜዳው ቪክቶሪያ ከተማ ላይ ተጫውቶ አንድ ጎል እና አንድ ነጥብ ማግኘት የቻለው የሲሸልስ ብሔራዊ ቡድን አገሪቱ ያላት የህዝብ ቁጥር በአፍሪካ ዝቅተኛ ከሚባሉት አንዱ ነው። የሲሸልስን ህዝብ በእግር ኳስ ቋንቋ እንግለጸው ቢባል የብራዚሉ ማራካኛ ስታዲየም ጠቅልሎ ቢይዛቸው እንኳ ስታዲየሙን መሙላት የማይችሉ ናቸው። ማለትም ከ90 ሺህ የማይበልጡ። የዋልያዎቹ አባላት ከ90 ሚሊዮን ህዝብ ተውጣጥተው ሲመረጡ ሲሸልሶች ግን ከ100 ሺህ በታች ህዝብ ባላት አገር ተውጣጥተው የተመረጡ ናቸው ማለት ነው። 

ሌላው የሲሸልስና የዋልያዎቹን ጨዋታ ውጤት በዋልያዎቹ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲያሳድር የሚያደርገው የሲሸልስ እግር ኳስ በፊፋ ያለው ወርሃዊ ደረጃ ነው። ዋልያዎቹ 103ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሲሸልሶች በበኩላቸው 199ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው። እነዚህ ሁለት ቡድኖች የሚያካሂዱት ጨዋታ መጠናቀቅ የነበረበት ያለምንም ጥርጥር በዋልያዎቹ የበላይነት መሆን ሲገባው ሜዳ ላይ የታየው እውነታ ግን መሳ ለመሳ ሆኖ ተገኘ።

የጎሉ መስመር የጠፋባቸው አጥቂዎች

በእግር ኳስ ሁሉንም የሚያስማማ አንድ ነጥብ አለ “ከተጋጣሚው የበለጠ ጎል ያገባ ቡድን አሸናፊ ይሆናል” የሚለው ሎጂክ። እግር ኳስ በውጤት ሲለካ ሂሳብ ነው። ሂሳብ ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝቅተኛ መጠን ያለውን አኃዝ እንደሚበልጥ ግልጽ ነው። ለዚህም ነው በእግር ኳስ ዓለም በየሜዳው ጠርዝ ያሉ የቡድኑ ተጫዋቾች እኩል ድርሻ አላቸው የሚባለው። አጥቂው ጎል ሲያመርት ቢውልና የቡድኑ የኋላ መስመር ወንፊት ሆኖ የተጋጣሚ ቡድን ኳሶችን መቋጠር ካልቻለ የአጥቂው ድካም በዜሮ የተባዛ ይሆናል። ተከላካዩ ካቴና ሆኖ አጥቂው በፖሊዮ የታሸ ከሆነም የተከላካዩ ክፍል ልፋት “የውርንጭላ ድካም” ይሆናል። የመሃል ሜዳው ወገቡ ከተሰበረ ደግሞ የቡድኑ የኋላ እና የፊት መስመር ከወንዝ ወዲያ ማዶ እና ወዲህ ማዶ የቆሙ ጎሳዎች ያስመስላቸዋል። በትናንትናው የዮሐንስ ሳህሌ ቡድን የታየውም ይሄው ነው።

በአስቻለው ታመነ እና በዋሊድ አታ የሚመራው የዋልያዎቹ የኋላ መስመር ከተካልኝ ደጀኔ እና ስዩም ተስፋዬ ጋር በሚገባ የተቀናጀ ነበር። የመሃል ሜዳው ደግሞ በጋቶች ፓኖም እና ሽመልስ በቀለ የተዋጣለት ጥምረት እንደፈጠረለት ጨዋታውን ከስፍራው ሲያስተላልፉ የነበሩ ጋዜጠኞች እና ጨዋታውን ስታዲየም ተገኝተው የመመልከት እድል ካገኙ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ለማወቅ ችለናል። ሆኖም ግን የፊት መስመሩ የተጋጣሚው የጎል መስመር ጠፍቶበት ነበር ያመሸው። አምበሉ ሳላዲን ሰይድም ሆነ ዑመድ ኡክሪ እና ኤፍሬም አሻሞ በእለቱ ፍጹም ጥሩ ያልነበሩ ሲሆን ከሁሉ የባሰው ደግሞ የጌታነህ ከበደ ጉዳይ ነበር።

የቀድሞው የደደቢት እና ደቡብ ፖሊስ አጥቂ ቀደም ሲል ለዋልያዎቹ ሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ባለውለታ እንደነበረ ማንም አይዘነጋውም። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያሳየው አቋም ከሚጠበቀው በታች ቢሆንም ብሔራዊ ቡድኑን የማሰልጠን እድል ያገኙ አሰልጣኞች ግን ተጫዋቹን ለብሔራዊ ቡድን እንዲጫወት ከመጥራት ቦዝነው አያውቁም። መጥራታቸው ሳያንስ ደግሞ የፊት መስመሩን በቋሚነት እንዲመራ እድል ሲሰጡትም ይታያሉ። ሆኖም ተጫዋቹ የአሰልጣኞቹን እምነት ቢያገኝም ውለታቸውን ግን ሊመልስ የሚያስችለው ብቃት ላይ አይገኝም ውጤታማ እየሆነ ያለው እንደ መስቀል ወፍ ከስንት አንዴ ነው። አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም ይህን ተጫዋች መጥራቱ ስህተት ባይሆንም ለጌታነህ የሰጠው የመጫወት እድል መጠን ግን ልጁ ለቡድኑ  በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ቁጣ የቀሰቀሰ ሆኗል። በእለቱ በርካታ የጎል እድሎችን መጠቀም ያልቻለውን አጥቂ በጊዜ አለመቀየሩ ደግሞ የአሰልጣኙን ውሳኔ አስገራሚ አድርጎታል።

ማንም ሰው በሚሰራው ሙያ በራሱ እምነት ሲኖረውና በስራው ሙሉ ነጻነት አግኝቶ ሲሰራ ውጤታማ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ሆኖም ግን መጽሀፍ ቅዱስ “ቁጭ ያለ ሰው ሃሳብ ለመስጠት ይፈጥናል” እንደሚለው ከአሰልጣኙ ስራ ውጭ ያሉ እግር ኳስ ተከታታዮች ከተጽእኖ ነጻ ሆነው ጨዋታውን ስለሚመለከቱ የማን ስህተት ከባድ ዋጋ እንዳስከፈለ እና ያንን ስህተት ለማረም ማን ቢገባ የተሻለ እንደሆነ ይታያቸዋል። በዚህም የተነሳ በአንድ ጨዋታ ላይ የሚፈጠሩትን ደካማውንና ጠንካራውን ክፍል በትክክል የማየት እድል ያላቸው የሚጫወቱት ወይም የሚያሰለጥኑት ሳይሆኑ ከእነዚህ ውጭ ያሉት ተመልካቾች ናቸው። እንዲህ ሲባል አሰልጣኞች ሚና የላቸውም ወይም ከተመልካች ያነሰ ሚና አላቸው ለማት እንዳልተፈለገ ይሰመርልን። እንዲህ ከሆነማ የአሰልጣኝ ሚና ተሰረዘ ማለት ይሆናል። ነገር ግን ተመልካቾችም በነጻነትና በተቆርቋሪነት የሚሰጡት አስተያየት ሊናቅ የሚገባው አለመሆኑን ለማሳየት ተፈልጎ ነው።

ቡድኑ በልምምድም ሆነ በዝግጅት ወቅት በጉዳት የተቀነሰ ተጫዋችም ሆነ ሌላ እክል የገጠመው ተጫዋች እንደሌለ የተገለጸ ሲሆን አሰልጣኝ ዮሃንስ ግን በእለቱ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለውን ጌታነህን ለ86 ደቂቃ ሲያጫውትና ወጣቱን ባዬ ገዛኸኝን አግዳሚ ወንበር ላይ እንዲቀመጥ ሲወስን ተመልካች በቁጣ ቢናገር  ይፈረድበትም። ምክንያቱም ከሁለት ወራት በፊት ባህር ዳር ላይ ዋልያዎቹ ከሌሴቶ ጋር ሲጫወቱ በተመሳሳይ ጌታነህ ከበደ ያሳየው አቋም ጥሩ ባለመሆኑ እስከ እረፍት ድረስ ቡድኑ በተጋጣሚው ቡድን የጨዋታም ሆነ የጎል ሙከራ የበላይነት ተወስዶበት ከቆየ በኋላ ባዬ ገዛኸኝ ተቀይሮ ሲገባ ውጤትም ሆነ ጨዋታ ተቀይሮ ታይቷል። ያ አጋጣሚ ሁልጊዜ ይደገማል ማለት ባይቻልም በትናንትው ጨዋታ ግን ጌታነህ ከነበረው እጅ….ግ የወረደ አቋም ባዬ ባይገባ እንኳ እንደ አስቻለው ግርማ ያሉ ተጫዋቾችን አስገብቶ የፎርሜሽን ለውጥ በመፍጠር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ነበር።

አላስፈላጊው የተጫዋቾች እገዳ እና የዝግጅት ጊዜ ሳላዲን ባርጌቾም ሆነ ናትናኤል ዘለቀ እና ራምኬል ሎክ በክለቦቻቸው እና በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ለመሆኑ የሚጠራጠር የለም። ሶስቱ ወጣት እና ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች ካላቸው ወቅታዊ ብቃት እና የመጫወት ፍላጎት አኳያ ዋልያዎቹ ወደ ሲሸልስ ሲጓዙ የቡድኑ አካል መሆን ይገባቸው ነበር። ሆኖም ሶስቱ የቅዱስ
ጊዮርጊስ ወጣት ተጫዋቾች ወደ ሲሸልስ ከሚጓዘው አውሮፕላን እንዲወርዱ እና አዲስ አበባ ላይ እንዲጠብቁ ተዳርገዋል። ምክንያት ቢባል ሶስቱም ተጫዋቾች ከአውሮፓ የመጣላቸውን የሙከራ ጊዜ ለመጠቀም ወደ ፖርቹጋል በመሄዳቸው የብሔራዊ ቡድን የዝግጅት ጊዜ ስላባከኑ የሚል ነው።

ይህን ውሳኔ ማንም ጤነኛ እና ማገናዘብ የሚችል አእምሮ ያለው ሰው ሊዋጥለት የሚችል ውሳኔ ባይሆንም ውሳኔው ግን ጸና። የውሳኔው አድራጊ ፈጣሪ ማን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ከውሳኔው ጀርባ ያለው አካል ለትላንቱ የተበላሸ ውጤት የራሱን አሉታዊ አስተዋጽዎ ማድረጉን ሊገነዘብ ይገባል። ተጠያቂነትም እንዳለበት ሊታወቅ ይገባል። ምክንያት ቢባል ከዚህ በታች እነሆ!!

ለአንድ አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድር ለሚደረግ የማጣሪያ ጨዋታ አንድ ወር እና ከዚያ በላይ በሆቴል ተቀምጦ ዝግጅት የሚያደርግ ብሔራዊ ቡድን የየትኛው አገር ቡድን ነው? ብሔራዊ ቡድኑ በዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት እነ ሳላዲን ሰይድ፣ ኡመድ፣ ሽመልስ እና ዋሊድ የት ነበሩ? ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት መጥፋት ተጠያቂ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚ የሆነው ጌታነህስ የት ነበር? እነዚህ አምስት ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ውጭ ስለሚጫወቱ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ልምምድ አልሰሩም ምክንያቱም ክለቦቻቸው ወርሃዊ ምንዳ ስለሚቆርጡላቸው ለአንድ ወርም ሆነ ለሁለት ወር ተጫዋቾቻቸውን መልቀቅ አያስቡትም። ቡድኑ ወደ ሲሸልስ ሊያቀና ሲል ግን ብሔራዊ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በተቃራኒው እነ ሳላዲን ባርጌቾ ግን የአውሮፓ እድል መጥቶላቸው ለሙከራ ሲሄዱ ለምን ሄዳችሁ የሚል እጅግ የተሳሳተ ተቃውሞ ገጠማቸው። ሲጀመር ፕሪሚየር ሊጉ የተጠናቀቀው በቅርቡ ሲሆን ተጫዋቾቹ የእረፍት ጊዜያቸው ነው። በእረፍት ጊዜያቸው ለወደፊት የእግር ኳስ ህይወታቸው የሚበጃቸውን ውሳኔ ማሳለፍ  ሚችሉት ተጫዋቾቹ ቢሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ወይ የወዳጅነት ጨዋታ አላዘጋጀ አለዚያ ደግሞ ተጫዋቾቹ የእረፍት ጊዜያቸውን እንዲጠቀሙበት አላደረገ ዝም ብሎ እንደ “ሐመር የሴት ሙሽራ” በሆቴል አስቀምጦ ሲቀልብ እና ሙከራ አልባ ልምምድ ሲያሰራ ከረመ። ይህንን የዝግጅት ጊዜ ጥላችሁ ሄዳችኋል ሲል እነ ሳላዲን ባርጌቾን የመሰለ ተጫዋች ከስብስቡ መቀነስ ምን ይባላል?

ተጫዋቾቹ በጉዳትና በብቃት ወይም የዲስፕሊን ግድፈት አሳይተው ከተቀነሱ ምንም ጥርጥር የለውም ውሳኔው ትክክል ነው። ምክንያቱም ብሔራዊ ቡድን ሆስፒታል ወይም ማረሚያ ቤት አይደለም ጉዳተኛ እና አመለ ብልሹ ተጫዋች የሚሰበሰብበት። ብቃቱ የወረደ ተጫዋች የሚጠራቀምበት ቤትም አይደለም። ሆኖም ግን ሳላዲን ባርጌቾም ሆነ ናትናኤል ዘለቀ እና ራምኬል ሎክ የተጠቀሰው ችግር የለባቸውም። እነዚህን ተጫዋቾች ከስብስቡ ቀንሶ ወደ ውድድር የገባው ብሔራዊ ቡድን ግን በሁለት ጨዋታ አራት ገብቶበት ሁለት ብቻ አግብቶ አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘት ቻለ።

እድል ፊቷን ያዞረችበት ዋልያ

በትናንቱ የዋልያዎቹ እና የሲሸልስ ጨዋታ በመጠኑም ቢሆን እድል ከዋልያው ጋር አልነበረችም ማለት ይቻላል። “ለመከራ የጻፈው ቢነግድ አይተርፈው” እንዲሉ አበው፤ እድል ፊቷን የዞረችበት ቡድንም የቱንም ያህል ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ቢያደርግም ኳሷ እና መረቡ ሊገናኙለት አይችሉም።

ቀደም ሲል የተጠቀሱት የተጫዋቾቹ፣ የአሰልጣኙ እና የፌዴሬሽኑ ድክመቶች እንዳሉ ሆኖ እድልም ዋልያውን ሸሽታው ነበር ማለት ይቻላል። በእለቱ በዋሊድ አታ እና ዑመድ ኡክሪ የተመቱ ሁለት ኳሶች ሰፊው መረብ ላይ ማረፍ ሲገባቸው ጠንካራውን ብረት ለትመው ተመለሱ። እነዚህ ሁለት ኳሶች በየትኛውም መመዘኛ ቢታዩ የዋልያዎቹን እድለ ቢስነት እንጅ የተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬን እና ታታሪነት የሚያሳዩ አይደሉም።

የዋልያው ተመሳሳይ እጣ የደረሳቸው ቡድኖች

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ካለፈው አርብ ምሽት ጀምሮ ሲካሄዱ የቆዩ ሲሆን ዛሬም በተለያዩ አገራት ይካሄዳሉ። ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል እንደ ዋልያዎቹ ሁሉ ያልተጠበቀ ውጤት የደረሰባቸው ቡድኖች ቀላል አይደሉም። ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዱ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ባፋና ባፋና ነው። ደቡብ አፍሪካውያን ብሔራዊ ቡድናቸው ከሞሪታኒያ ጋር ሊጫወት አውሮፕላን ሲሳፈር በልባቸው የሰነቁት ተስፋ ነበር በሞሪታኒያ ግብ ጠባቂ ላይ ስንት ጎል ማስቆጠር እንደሚችሉ በአይነ ህሊናቸው እያሰቡ መደሰት። ሆኖም ዓለም የማትገመት ስለሆነች ሞሪታኒያውያን ሶስት ጎል ሲያስቆጥሩ የእነ ቤኔዲክት ማካርቲ አገር ደቡብ አፍሪካውያን ግን አንድ ጎል ብቻ አስቆጥረው ሶስት ለአንድ ተሸንፈው አገራቸው ገቡ።

ሌላው አስገራሚ ተሸናፊ የሆነችው ደግሞ ቡርኪናፋሶ ናት። በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ከጥቅም ውጭ አድርገው ያመሹት የእነ ባንሴ እና ፒትሮፒያ ስብስብ ቡርኪናፋሶ በቦትስዋና አንድ ለባዶ ተሸንፏል። በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመሰውና ዜጎቿን ለስደት የዳረገችው የእኛ ጎረቤት ደቡብ ሱዳንም ኢኳቶሪያን ጊኒን አንድ ለባዶ ማሸነፍ የቻለች ሲሆን  ላይቤሪያም ቱኒዚያን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችላለች።

 ከላይ የተጠቀሱት ውጤቶች ይመዘገባሉ ተብለው የተጠበቁ ባይሆንም የእግር ኳስ ነገር ሆኖ ያልታሰቡት ሲቀናቸው የተጠበቁት ተዋረዱ። ዋልያዎቹም ካስመዘገቡት ደካማ ውጤት አገግመው ቀጣይ ጨዋታዎቻቸውን ማሸነፍ ከቻሉ የትናንቱ ክስተት የአንድ ቀን ስለሆነ ለነገው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከዋልያዎቹ የከፋ ውጤት ያስመዘገበም አለ ናይጄሪያ። ንስሮቹ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሲያቀኑ የሚያሸንፉት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ብቻ ነው መሰል። ከዓመታት በፊት በኬኒያ ነጥብ ሲጥሉ ትናንት ምሽትም በታንዛኒያ ነጥብ ጥለዋል ባዶ ለባዶ በመለያየት።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Yoni sanjawe [899 days ago.]
 አላስፈላጊው የተጫዋቾች እገዳ እና የዝግጅት ጊዜ ሳላዲን ባርጌቾም ሆነ ናትናኤል ዘለቀ እና ራምኬል ሎክ በክለቦቻቸው እና በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ለመሆኑ የሚጠራጠር የለም። ሶስቱ ወጣት እና ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች ካላቸው ወቅታዊ ብቃት እና የመጫወት ፍላጎት አኳያ ዋልያዎቹ ወደ ሲሸልስ ሲጓዙ የቡድኑ አካል መሆን ይገባቸው ነበር። ሆኖም ሶስቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ተጫዋቾች ወደ ሲሸልስ ከሚጓዘው አውሮፕላን እንዲወርዱ እና አዲስ አበባ ላይ እንዲጠብቁ ተዳርገዋል። ምክንያት ቢባል ሶስቱም ተጫዋቾች ከአውሮፓ የመጣላቸውን የሙከራ ጊዜ ለመጠቀም ወደ ፖርቹጋል በመሄዳቸው የብሔራዊ ቡድን የዝግጅት ጊዜ ስላባከኑ የሚል ነው። wooooooooooooow tnx Ethio sport really i appreciate Ye hezeboun besote new yegeletachute ! nice.....nice.....zegebba

Alex [899 days ago.]
 first of all 10 Q ethio sports እኔ እኮ በጣም ግርም የሚለኝ የኮቹ ነገር ነው ገና በባዶ ሜዳ ገና ውጤት ሳያስመዘግብ እንደ አሪፍ ኮች አክት የሚያደርጋቸው ነገሮች ናቸው የሚያናዱት አንተ ጎበዝና ምርጥ አሰልጣኝ ብትሆን ኖሮ ሳላሃዲንና ጌታነህን በወረደና በሞተ አቋማቸው አታሰልፋቸውም ነበር. በተለይ ጌታነህ እንደዛ ሲቀልድ ደፍሮ ለመቀየር ወኔህ ከድቶህ ነበር. የአንተ ወኔ የአንተ ጀግንነት አማተሮቹ ላይ ነው ማለት ነው ??? ሃ ሃ ሃ ሃ እነ ሳላሃዲን ባርጌቾ..... እነ ናቲ .....እነ ራምኬል ..... እነ ምንተስኖት ላይ..... እነ ቢኒያም ላይ ..... ነው ማለት ነው ??? ማፈሪያ ነገር ነህ እንደ ፕሮፌሽናል ኮች ይሰራራሃል ግን ስራህ ሁሉ ያልተማረ ሰው ስራ ነው ! በጣም የሚያናደው ቅሽምናክ 3ቱን ልጆች የቀነስክበት ምክንያት ነው በጣም ነው ያፈርኩብህ ሃገራችንንም አሰደብካት ! በ 10 ተጫዋች ኳስ የማያውቁት ሲሸልሶች ኳስ አስተማሩክ ማፈሪያ ነገር ነህ ! long live for Sir coach Sewinet Bishawe !

tilyo [899 days ago.]
 yohannes besem alamnem yalkew ena tegbareh aygenagnem. please improve this

Naod [899 days ago.]
 በአስቸኳይ 3 ቱ ልጆች ወደ ቡድኑ ተመልሰው ዮሃንስ ለሰራው ስ-ህ-ተ-ት ይቅርታ መጠየቅ አለበት ልጆቹንም ቡድኑንም !!!

Mulugeta [898 days ago.]
 በጣም ያስቃል እኮ 3 ቱ ልጆች የተቀጡበት ምክንያት....... ልጆቹ እኮ ጭፈራ ቤት በርጫ ቤት አይደለም የሄዱት የፕሮፌሽናል ህልማቸውን ለማሳካት ተገቢው ቦታ እንጂ. ኮች ዮሃንስ ግን እነ ሳላሃዲንን ቀንሶ የራሱን ጡንቻ ሃይል ማሳየት ፈለገና በሯንዳም በትንሿም ሲሸልስ አስደበን. ማፈሪያ ነገር ነህ ዮሃንስ ! tnx Ethiosport በጣም እናምሰግናለን ምርጥ ዘገባ ነው የሰራችሁት !

tanoo [898 days ago.]
 ይርጋ እንደዘገባህ ከሆነ የተቀነሱት ተጫዋቾች የነሳላዲን፣ እና ናቲ ወይም ራምኬሎ አለመካታት በሲሸልሱ ጨዋታ ውጤት ላይ ለውጥ የሚያመጣ አልነበረም። ምክንያቱም እንደአጻጻፍህ ከሆነ ተሰልፈው የተጫወቱት የሇላ ተከላካይ እና የመሃል ተጫዋቾቹ ጥሩ ነበሩ። በርግጥ ውጤታማ ያልነበሩት የአጥቂው ክፍል ነበር። እድልም ጠሞባቸው ነበር ብለሃል። ምናልባት ጨዋታው ምንም ሳይቀየር አጥቂዎቹ እንሳላዲን ጌታነህ ከሳቱት የጎል ብዛት አንዷ ማሸነፊያ ጎል ሆና ቢሆን ኖሮ ስለተቀነሱት ተጫዋቾች ብዙ ባላወራን ነበር። እነ በርጊቾ እና ናቲ የተቀነሱት አይችሉም አይጠቅሙም በሚል አይመስለኝም። እንደሚመስለኝ ጨዋታው ከሲሸልስ ጋር ስለነበረና ሲሸልስን በቀላሉ ማሸነፍ እንችላለን ከሚል መነሻ ሆኖ በዛውም የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ስነስርአት ለማስያዝ እነዮሃንስ ያደረጉት ነው የሚመስለኝ። ጨዋታው ከአልጄሪያ ጋር ቢሆን ኖሮ በርግጠኝነት ዮሃንስ እነበርጊቾን ትቷቸው አይሄድም ነበር። በትላንቱ ጨዋታ የዮሃንስ ጥፋት ይርጋ እንዳልከው እድል ጠማ ውጤቱን መቀየር ባይቻል እንኳን ገዛህኝ እና አስቻለውን ከረፍት በሇላ ተቀይረው መግባት ነበረባቸው።

tanoo [898 days ago.]
 ይርጋ እንደዘገባህ ከሆነ የተቀነሱት ተጫዋቾች የነሳላዲን፣ እና ናቲ ወይም ራምኬሎ አለመካታት በሲሸልሱ ጨዋታ ውጤት ላይ ለውጥ የሚያመጣ አልነበረም። ምክንያቱም እንደአጻጻፍህ ከሆነ ተሰልፈው የተጫወቱት የሇላ ተከላካይ እና የመሃል ተጫዋቾቹ ጥሩ ነበሩ። በርግጥ ውጤታማ ያልነበሩት የአጥቂው ክፍል ነበር። እድልም ጠሞባቸው ነበር ብለሃል። ምናልባት ጨዋታው ምንም ሳይቀየር አጥቂዎቹ እንሳላዲን ጌታነህ ከሳቱት የጎል ብዛት አንዷ ማሸነፊያ ጎል ሆና ቢሆን ኖሮ ስለተቀነሱት ተጫዋቾች ብዙ ባላወራን ነበር። እነ በርጊቾ እና ናቲ የተቀነሱት አይችሉም አይጠቅሙም በሚል አይመስለኝም። እንደሚመስለኝ ጨዋታው ከሲሸልስ ጋር ስለነበረና ሲሸልስን በቀላሉ ማሸነፍ እንችላለን ከሚል መነሻ ሆኖ በዛውም የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ስነስርአት ለማስያዝ እነዮሃንስ ያደረጉት ነው የሚመስለኝ። ጨዋታው ከአልጄሪያ ጋር ቢሆን ኖሮ በርግጠኝነት ዮሃንስ እነበርጊቾን ትቷቸው አይሄድም ነበር። በትላንቱ ጨዋታ የዮሃንስ ጥፋት ይርጋ እንዳልከው እድል ጠማ ውጤቱን መቀየር ባይቻል እንኳን ገዛህኝ እና አስቻለውን ከረፍት በሇላ ተቀይረው መግባት ነበረባቸው።

jaimibarca [898 days ago.]
 @ Tanoo በጣም ትገርማለህ ሁልጊዜ የምትሰጣቸው ኮመንቶች ከክለብ ወገንተኝነት የፀዱ አይደሉም። የተቀነሱት ልጆች ለቡድኑ ቁልፍና ወሳኝ ተጫዋቾች መሆናቸው ለማንም ግልፅ ሆኖ ሳለ የዚህ አይነት ኮመንት መስጠትህ ያሳዝናል። አንተ እውነተኛ ሰው ለብሔራዊ ቡድናችን አሳቢ ሆነክ ቢሆን ኖሮ የቢኒያም መቀነስን እራሱ ትቃወም ነበር ። ግን ዝም ያልከው ለምን እንደሆነ ግልፅ ነው። ቢኒያም በአሁኑ ሰዓት የቡና ተጫዋች ስላልሆነ አይደል ??? ha ha ha ha ግን ይደብራል የምትሰሩት ስራ !!! ቢኒያም በአሁኑ ሰዓት ያለው አቋም ከእነ ጌታነህ ቢሻል እንጂ አያንስም ይህ ደግሞ ለሁላችንም ግልፅ ነው !!!

biss [897 days ago.]
 እኛ እንደሰማነው ልጆቹ የተቀነሱት ልልምምዱን አቋርጠው ስለሄዱ ሳይሆን ከተፈቀደላቸው ቀናት አሳልፈው በመምጣታቸው ነው። ይህም አይነት ቅጣት በፕሮፌሽናል ፉትቦል ስንሰማ የመጀመሪያችን አይደለም። ባይሆን በድንቅ ብቃት ላይ የሚገኙት ባዬ እና አስቻለው የተሻለ የመጫወት እድል ተሰጥቷቸው ቢሆን ውጤት ማስቀልበስ ይችሉ ነበር ብለን መገመት እንችላለን። አሁንም ግን ማሸነፍ የሚችል የቡድን አቋም አለን። በቻን ውድድር ላይ ያየነውን እንዲሁም በሌሴቶ ጨዋታ ላይ የታየው የተቀንናጀ ቡድን አስሬ መቀያየሩ ቀርቶ ዘላቂ አቋም እንዲኖረው ማድረግ ከተቻለ አልጄርያንም ተዳፍረን ማሸነፍ እንችላለን። ድል ለዋልያዎች!!

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!