“በሲሸልሱ ጨዋታ ያጣናቸው ሁለት ነጥቦች የሚያበሳጩ ናቸው” ዋሊድ አታ
ነሐሴ 30, 2007

ይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ቡድን የሲሸልስ አቻውን ባለማሸነፉ እንደተበሳጨ ተከላካዩ ዋሊድ አታ ተናገረ። ለቱርኩ ገንሸለርቢርሊ እግር ኳስ ክለብ  የሚጫወተው የ29 ዓመቱ ዋሊድ አታ ትናንት ማምሻውን ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ጥሩ ጨዋታ አልነበረም። በውጤቱ በግሌ ደስተኛ አይደለሁም ተከፍቻለሁ ማሸነፍ ነበረብን” ያለ ሲሆን የሲሸልስ ብሔራዊ  ቡድን በእነሱ ላይ ጫና እንዳላሳደረም ተናግሯል።

ጨዋታውን ላላማሸነፋችን በርካታ እድሎችን መጠቀም ባለመቻላችን ነው ያለው ዋሊድ “በጨዋታው ያጣናቸው ሁለት ነጥቦች የሚያበሳጩ ናቸው” ሲል ተናግሯል። በእለቱ በርካታ ደጋፊ ወደ ወደባማዋ የሲሸልስ ከተማ ቪክቶሪያ በማቅናት የኢትዮጵያን ብሔራዊ  ቡድን መደገፉ አስገራሚ እንደሆነበት የተናገረው ዋሊድ አታ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እድሉ በእጁ መሆኑንም አስታውቋል። “ደጋፊው እስካሁን ያደረገልንን ድጋፍ ማቋረጥ የለበትም። ከፊታችን በርካታ እድሎች አሉን” ሲልም ወደ ጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ የሚወስደው መንገድ ሰፊ መሆኑን ጠቁሟል።

Walid Ata

አርቲፊሻል ሳር የለበሰው የሲሸልሱ ሜዳ ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑ በመጠኑም ቢሆን በጨዋታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳደረባቸውም ተናግሯል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለት ጨዋታዎች በሰበሰበው አራት ነጥብ እና አንድ ተጨማሪ የጎል ክፍያ ከመሪው አልጄሪያ ቀጥሎ ምድቡን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አልጄሪያ በስድስት ነጥብና ስድስት ንጹህ ጎል ትመራለች። በርካታውን የጨዋታ ክፍለጊዜ በአስር ተጫዋች ተጫውቶ ከዋልያዎቹ ላይ አንድ ነጥብ የወሰደው የሲሸልስ ብሔራዊ ቡድን በአንድ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሌሴቶ ያለምንም ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የገንሽለሩ ተከላካይ ዋሊድ አታ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ሙሉውን ክፍል በቀጣዮቹ ተከታታይ ቀናት የምናቀርብ ይሆናል። ዋሊድ ከኤርትራዊ አባት እና ግማሽ ኤርትራዊና ግማሽ ኢትዮጵያዊት እናት መወለዱን፣ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ከክሮሽያው ዳይናሞ ዛግሬብ ጋር የመጫወት እድል ገጥሞት በጉዳት መቀነሱን፣ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የአሰልጣኝነት ዘመን ለብሔራዊ በቡድን ለመጫወት ጥያቄ አቅርቦ ለምን እንዳልተፈቀደለት፣ ስለ ምግብ ምርጫው በተለይም ለሽሮ ስላለው ፍቅር እና ሌሎች ስለሱ ያልሰማናቸውን መረጃዎች ይዘን ከነገ ጀምሮ የምንመለስ ይሆናል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!