“ለኢትዮጵያ ለመጫወት በመወሰኔ ኩራት አደረብኝ” ዋሊድ አታ -ክፍል አንድ-
ነሐሴ 30, 2007

ክፍል አንድ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ቡድን እና የቱርኩ ገንሸርቢርሊ ክለብ የኋላ መስመር ተጫዋች የሆነው ዋሊድ አታ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፊ ቃለ ምልልስ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር አድርጓል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ ቡድኑ በእድሜ አንጋፋው እኔ ነኝ የሚለው ዋሊድ አታ ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ዘጋቢ ይርጋ አበበ ጋር በካፒታል ሆቴል ያደረጉትን ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቃለ ምልልስ በተከታታይ ክፍሎች እንደምናቀርብ ቃል በገባነው መሰረት ለአንባቢያን በሚመች መልኩ የመጀመሪያውን ክፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

ስለ ትውልድና እድገት

አባቴ ኤርትራዊ ሲሆን እናቴ ደግሞ ግማሽ አርትራዊና ግማሽ ጎንደሬ ነች፡፡ ወላጆቼ የተጋቡት አስመራ ሲሆን እኔ የተወለድኩት ግን ሳዑዲ አረቢያ ነው፡፡ ከተወለድኩ በኋላ ቤተሰቦቼ ወደ ስዊድን በመጓዛቸው እድገቴ ስዊድን ነው፡፡
Walid-ata3


የእግር ኳስ አጀማመር

እንደነገርኩህ ያደኩት ስዊድን ነው፡፡ ገና በልጅነቴ ጀምሮ እግር ኳስ መጫወት እወድ ስለነበረ ቤተሰቦቼ በስድስት ዓመቴ ጀምሮ ነው በእግር ኳስ አካዳሚ ገብቼ እንድሰለጥን እድል የፈጠሩልኝ፡፡ ከስድስት ዓመቴ ጀምሮ እሰከ 19 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ በሁሉም የአካዳሚው ደረጃዎች ውድድር መሳተፍ ችያለሁ፡፡ 19 ዓመት ሲሆነኝ ግን በስዊድን ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ለሚወዳደረው ግኑዜ ለሚባል ክለብ ተመልምዬ መጫወት ቻልኩ፡፡ ከግኑዜ ጋር ለሁለት ዓመታት ከተጫወትኩ በኋላ ደግሞ ወደ ሶና በመዘዋወር በስዊድን ዋናው ሊግ መጫወት ቻልኩ፡፡

ጉዞ ወደ ክሮሽያ

ለመጀመሪያ ጊዜ ከስዊድን ወጥቼ መጫወት የቻልኩት ለክሮሽያው ግዙፍ ክለብ ዳይናሞ ዛግሬብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዛግሬብ የእነ ሉካ ሞድሪች ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ትልቅ ሲሆን በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግና ዩሮፓ ሊግ መወዳደር ይችላል፡፡ ግን እንዳለመታደል ሆኖ ለዛግሬብ እንደፈረምኩ ጉዳት ደረሰብኝ፡፡ ዓመቱን ሙሉ ከጉዳቴ ለማገገምና ክለቡ የሚፈልገውን ብቃት ለማሳየት ብሞክርም በቀላሉ ከጉዳቴ ማገገም ባለመቻሌ ወደ ስዊድን ለመመለስ ተገድጃለሁ፡፡

በጉዳት የተነሳም በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ የመወዳደር ህልሜን ብቻ ሳይሆን አግኝቼው የነበረውን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጫወት እድልም አበላሽቶብኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ባዝንም እንደሚታወቀው ሁሉም ነገሮች ሲከናወኑ በምክንያት ነው እኔም አሁን ባለሁበት ሁኔታ ደስተኛ ነኝ፡፡

ስለ መጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታው

እንደምታስታውሰው ጨዋታውን ተሸንፈናል፡፡ ጨዋታውን መሸነፋችን በጣም የሚያበሳጭ ቢሆንም ለአገሬ የመጀመሪያ ጨዋታ በማድረጌ ግን ደስተኛ ነኝ፡፡ ጥሩ ተጫውተን ነበር፡፡ የደጋፊው ድባብ ልዩ ነበር፡፡ ከጨዋታ በፊት ለደጋፊው አዲስ ብሆንም በሁሉም የስታዲየሙ ክፍል የሚገኙ ደጋፊዎች ስሜን እየጠሩ ሲደግፉኝና ሲያበረታቱኝ ነበር፡፡ ያኔ ለኢትዮጵያ ለመጫወት በመወሰኔ ኩራት አደረብኝ፡፡ ውሳኔዬ ትክክል ነበር ያልኩት ያኔ ነው፡፡ ምንም እንኳ ጨዋታውን ብንሸነፍም በአጠቃላይ በመጀመሪያው የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዬ ደስተኛ ነኝ፡፡

በስዊድን የነበረ ቆይታ እና ጉዞ ወደ ቱርክ

ከዛግሬብ ከወጣሁ በኋላ ወደ ስዊድን ተመልሼ ከጉተንበርግ ጋር መጫወት ቻልኩ፡፡ ከዚያም ባሳየሁት አቋም ወደ ቱርክ ሊግ ላመራ ችያለሁ፡፡ በመጀመሪያ የዝውውሩ እድል ለእኔ በጣም ትልቅ እድል ነው፡፡ የቱርክ ሊግ እንደ ፌነርባቼ፣ ጋላታሳራይ፣ ቤሺክታሽ እና ሌሎች ታላላቅ ክለቦች ከብራዚልና ከአውሮፓ ታላላቅ ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙ ክለቦች ያሉበት ክለብ ነው፡፡ በዚያ ሊግ መጫወት በራሱ ትልቅ እድል ነው፡፡ ምክንያቱም ልምድ የምታገኝበትና የመወዳደር አቅምህን የምታጎለብትበት መድረክ ነው፡፡
Walid Ata


ከአዲሱ ክለቡ ጋር ስላለው የመጀመሪያዎቹ ወራት ቆይታ

ከገንሽርቢርሊ ጋር ያሳለፍኩት የቅድመ ውድድር ጊዜ ስኬታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ቅድም እንደነገርኩህ በቱርክ ሊግ ታላላቆቹ ክለቦች እንደ ማርኮ ማሪን፣ ቫን ፐርሲ፣ ናኒ፣ ፖዶልስኪ እና ያኩቡ አይነት ታላላቅ ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙ ክለቦች ያሉበት ሊግ ነው፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች ጋር የምታደርገው ጨዋታ ቀላል አይሆንም፡፡ እኛም የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ ብናካሂድም ሊጉ ሲጀመር ያደረግናቸውን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ተሸንፈናል፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች የተሸነፍነው ተጋጣሚዎቻችን ባላቸው ልምድ እና ታላላቅ ተጫዋቾች ታግዘው ነው፡፡ ምክንያቱም በሁለቱም ጨዋታዎች አስር ደቂቃ እስከሚቀረው ድረስ እኩል ለእኩል ሆነን ነበር የተጓዝነው፡፡ በቅርቡ ያካሄድነውን ጨዋታ ደግሞ አሸንፈናል፡፡ በአጠቃላይ ግን የእኛ ክለብም በአለው አቅም ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የውድድር ዓመቱን ማጠናቀቅ እንችላለን፡፡   

ለዋልያዎቹ ለመጫወት ያቀረበውን ጥያቄ ስለመከልከሉ

በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከናይጀሪያ ጋር ከመጫወቱ በፊት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ጥያቄዬ አልተመለሰም፡፡ ሊሳካ ያልቻለው ደግሞ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ምክንያት ሳይሆን በጊዜው ከፌዴሬሽኑ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አልጀመርኩም ነበር፡፡ የእኔን ፍላጎት ይዞ ወደ ፌዴሬሽኑ የሚቀርብ ሰው ነበር፡፡ ማለትም በመካከላችን ሌላ ሶስተኛ ወገን ነበረ ማለት ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ፕሮሰሱ ተጓተተ እና ለብሔራዊ ቡድን ሳልጫወት ቀረሁ፡፡

ስለ ማሪያኖ ባሬቶ ቡድን

በማሪያኖ ባሬቶ አሰልጣኝነት ሶስት ጨዋታዎችን ተጫውቻለሁ፡፡ ከማሊ ጋር በደርሶ መልስ እና ከአልጀሪ ጋር ደግሞ አልጀርስ ላይ፡፡ በተለይ አልጀርስ ላይ ከአልጀሪያ ጋር እና አዲስ አበባ ላይ ከማሊ ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች መሸነፍ ያልነበረብን ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ማሊን ባማኮ ላይ ማሸነፋችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብዙዎች በውጤቱ ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እንዲያውም የተበሳጩም አሉ፡፡ ልክ ነው መሸነፍ ያበሳጫል ግን ቡድኑ ጊዜ ቢሰጠውና ቢዋሃድ  ኖሮ ጥሩ ቡድን ይሆን ነበር፡፡ አሰልጣኙም ቢሆን ጥሩ አሰልጣኝ ነው፡፡

ስለሚያደንቀው ተጫዋች

የማንቸስተር ሲቲ እና የቤልጀም ብሔራዊ ቡድን አምበል ቪንሶ ኮምፓኒ በአሁኑ ሰዓት ሁሉን ነገር ያሟላ ተከላካይ ነው፡፡ በጣም አደንቀዋለሁ፡፡ ከኮምፓኒ በፊት ግን የጣሊያኖቹን ፓውሎ ማልዲኒን እና ኤሳንድሮ ኔስታን እያደነቅኩ ነው ያደኩት፡፡ በእነ ማልዲኒ ጊዜ የጣሊያን ተከላካይ ክፍል ጠንካራ ነበር፡፡ ከተከላካይ ውጭ ቢሆንም ከልጅነቴ ጀምሮ በጣም አደንቀው የነበረው የአርሴናል አምበል የነበረውን ፓርቲክ ቬይራን ነው፡፡ ቬይራ ታጋይና እልኸኛ ተጫዋች ነበር፡፡ በቃ ምሉዕ ተጫዋች ነበር፡፡

ስለ ብሔራዊ ቡድን አጣማሪዎቹ

በብሔራዊ ቡድን ከሳላዲን ባርጌቾ እና አስቻለው ታመነ ጋር ነው መጫወት የቻልኩት፡፡ ሁለቱም ጎበዝ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በቴክኒካል ችሎታቸው በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ የአስቻለውንና የሳላዲን ባርጌቾን በተመለከተ ግን አስቻለው ገና ወጣት ነው ልምድ ይጎድለዋል፡፡ ግን ለመማርና ለመሻሻል ዝግጁ ነው፡፡ ሳላዲን ደግሞ የተሟላ ተከላካይ ነው፡፡ ልምድ አለው፤ ብስል ነው፤ በዚያ ላይ ጠንካራም ነው፡፡ ወደፊት ጠንካራ ጥምረት መፍጠር ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
tanoo [828 days ago.]
 Interesting, I saw Walid playing against Mali at Addis Ababa Stadium, he was superb on the field defending his backyard, The way he played was likable, he has a strong defender characteristics and quality. He is a kind of player who plays for his jersey just like the best defenders in the world he admired Maldini, Viera and Nesta from local players Like Adane Girma with great responsibility. Other players can learn a lot from him. I think Walid you should not be worried we are with you the Walyas no matter what, Our support will continue , just do all your best with the rest of the players to qualify.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!