“ኢትዮጵያውያን ህጻናት ያልተሞረዱ እንቁዎች ናቸው” ዋሊድ አታ
መስከረም 01, 2008

የመጨረሻ ክፍል

በትናንትናው ዝግጅታችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የገንሽርቢርሊ ክለብ የኋላ መስመር ተጫዋች ዋሊድ አታ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ማስነበባችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ ከትናንቱ የቀጠለውን ክፍል ይዘን የምንቀርብ ሲሆን የተለያዩ ግለሰቦች ስለ ዋሊድ አታ የሰጡንን አስተያየትም ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዴት ማደግ እንዳለበት

ብሔራዊ ቡድኑ ከዋናው ቡድን በተጨማሪ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ተመሳሳይ ስትራክቸር ያላቸው ተተኪ ብሔራዊ ቡድኖች ሊዋቀሩ ይገባል። ማለትም ከ21 ዓመት በታች፣ ከ20 ዓመት በታች ጀምሮ እስከ ታች ድረስ ከተዋቀረ የተተኪ ችግር አይፈጠርብህም። ከዚህ በተረፈ ደግሞ በህጻናት ላይ የሚሰራው ስራ በእውቀት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ለምሳሌ እኔ በስዊድን ከስድስት ዓመቴ ጀምሮ ስልጠና የወሰድኩት ከእግር ኳስ ሳይንስ እውቀትና ልምድ ጀምሮ እስከ አካዳሚካል እውቀታቸው የተመሰከረላቸው ባለመያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎችና ህጻናት ደግሞ በቴክኒካል ችሎታቸው የተካኑ ናቸው። በአጭሩ የኢትዮጵያ ህጻናት ማለት ያልተሞረዱ እንቁዎች ናቸው። እነዚህን እንቁዎች መጠቀም የምትችለው በበቂ ደረጃ ስትሞርዳቸው ነው ማለትም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሳይንሳዊ ስልጠና ስትሰጣቸው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ የእግር ኳሱ እድገት ይገኛል።

በፌስ ቡክ አድራሻው ሰዎች አመሳስለው ስለመክፈታቸውና ሰዎች አብዩዝ እንዳይሆኑ መልዕክቱን ስለማስተላለፉ

በደንብ እንዲያውቁት የምፈልገው በእኔ ስም ተመሳሳይ የፌስ ቡክ አድራሻዎች ስለተከፈቱ እኔን የሚገልጹኝ ሁለት አድራሻዎች ብቻ መሆናቸውን ነው። አንደኛው መደበኛው አካውንት ሲሆን አንዱ ደግሞ ፋን ፔጅ ነው። መደበኛው አካውንት መቀበል የሚችለውን የሰው ብዛት ስለተቀበለ ተጨማሪ ጓደኛ መቀበል አይችልም። የጓደኝነት ጥያቄ አቅርበው ከተቀበላቸው ያ የእኔ አካውንት ስላልሆነ ሰዎች በዚህ እንዳይታለሉ።

ፋን ፔጄም ቢሆን ተለይቶ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። በዚህ ፔጅ ጨዋታዎችንና ልምምዶችን ጨምሮ እያንዳንዱን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴዬን ቶሎ ቶሎ ለአንባቢያን እሰጣለሁ ማለትም Update አደርጋለሁ። በዚያ ፔጅ ማንኛውም ሰው መከታተል ይችላል በኢትዮጵያ ማሊያ ነው የከፈትኩት። በዚህ ተለይቶ መታወቅ ይቻላል። ከዚህ ውጭ ያለው ግን የእኔ ፔጅ አለመሆኑን አሳውቃለሁ። 
 
ስለ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ደጋፊዎች

እግር ኳስ የሚወድ ደጋፊ ያለበት አገር ነው። ቡድናቸውን ለመደገፍ አገር አቋርጠይ የሚጓዙ ናቸው ከአዲስ አበባ ውጭም ተዘዋውረው ብሔራዊ  ቡድኑን ይደግፋሉ በዚህ ተገርሜያለሁ። ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምናደርገው ጉዞ አሁንም ከጎናችን እንዲሆኑ በዚህ አጋጣሚ መናገር እፈልጋለሁ። ምክንያቱም እነሱ ለእኛ ተጨማሪ ጉልበት ናቸው። የኢትዮጵያን ማሊያ ለብሰህ ስትጫወት እንደዚህ አይነት ደጋፊ ሲደግፍህ ከፍተኛ ኩራት ይሰማሃል።

ከክለብና ከብሔራዊ ቡድን ጋር ማሳካት ስለሚፈልገው

በክለብ ደረጃ ማሳካት የምፈልገው ከክለቤ ጋር በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ እና በዩሮፓ ሊግ መጫወት ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ክለባችን ባለው አቅም ሁሉ ዝግጅቱን እያካሄደ ነው። ከአገሬ ብሔራዊ ቡድን ጋር ደግሞ በዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካ ዋንጫ መጫወት ነው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ መጫወት እፈልጋለሁ።

Walid Ata


የምግብ ምርጫው

ሽሮ በጣም እወዳለሁ። ምክንያቱም እናቴ ሰርታ ታበላኝ ስለነበረ የሽሮ ጣዕም ደስ ስለሚለኝ በደስታ ነው የምበላው።

የመጨረሻ መልክት

በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚፈጠሩ ክስተቶች ለቀጣዩ ጨዋታ ትምህርት እንደሚሆኑ ማወቅ አለብን። የዛሬ ሽንፈት ለነገ ድል መንደርደሪያ ይሆናል። የነገውን ጨዋታ እንዴት ማሸነፍ እንዳለብህ የሚያስተምርህ የዛሬው ጨዋታ ሽንፈት ነው።
 
ሰዎች ስለ ዋሊድ

መሀመድ ኑርሁሴን ይባላል የዋሊድ አታ የአክስቱ ልጅ ሲሆን ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ጄሞ አካባቢ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ ወደ አውሮፓ ይጓዛል። መሀመድ የዋሊድ የአክስቱ ልጅ ብቻ ሳይሆን በእድሜም ተቀራራቢ ስለሆኑ የጓደኝነት ያህል የጠነከረ ግንኙነት አላቸው። የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በካፒታል ሆቴል ተገኝቶ ከዋሊድ አታ ጋር ቃለ ምልልስ በሚያደርግበት ሰዓት አገኘውና ስለ ዋሊድ የሚያውቀውን ለአንባቢያን እንዲያስተላልፍ ጠይቆት ነበር። መሀመድ እንዲህ ብሏል።
Walid Ata

“ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው እኔም በዋሊድ ችሎታ ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያለኝ። በግል ባህሪው ግን ከሰው ጋር ለመግባባት የማይከብድና የተነሳበትን የማይረሳ ነው። ዋሊድን የማውቀው ህጻን እያለ የአባቱን ዘመዶች ለመጠየቅ ወደ አስመራ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው። በዚያ ጊዜ ያየሁትም ሆነ አዲስ አበባ ላይ የዛሬ ዓመት አካባቢ ያየሁትና አሁን እያየሁት ያለው ዋሊድ ተመሳሳይ ባህሪ እና አመለካከት ያለው ልጅ ነው። አገሩን ይወዳል። ጊዜውን በሙሉ የሚያሳልፈው በእግር ኳስ ነው። ደፋር ነው። በአጭሩ በጣም ጎበዝ ነው። ለሰው ያለው አመለካከት ጥሩ ነው። አዛኝ ነው” ሲል ገልጾታል።

ከመሀመድ በተጨማሪም ዋሊድን ያሰለጠኑት አሰልጣኞች ስለ ዋሊድ በተለያዩ ጊዜያት አስተያየታቸውን ሲጠየቁ “ተጫዋቹ ደፋርና ግልጽ ነው። በኳስ ሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጭ ባሉ የጓደኝነት ግንኙነቶች በቀላሉ መግባባት የሚችል ልጅ ነው። ለቡድናችን መጠናከር የእሱ ሚና ከፍተኛ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ አጋጣሚ አንባቢያን ስለ ዋሊድ አታ እንዲያውቁ የምንፈልገው ዝግጅት ክፍላችን ከዋሊድ ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ያሰበው በኢሜይል ነበር። ሆኖም ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ወደ አገሩ ሲመጣ በአካል እንድናገኘው ፍላጎቱን የገለጸልን ሲሆን በተለይ ብሔራዊ ቡድኑ ከሲሸልስ ጋር ተጫውቶ ጥሩ ያልሆነ ውጤት አስመዝግቦ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰበት ሰዓት ነበር። በዚያ እለት ብሔራዊ ቡድኑ ረጅም የአውሮፕላን ጉዞ አድርጎ ወደ አገሩ የገባበት እለት ሲሆን በዚያው እለት ከሰዓታት በኋላ ዋሊድ ወደ ቱርክ አንካራ ከተማ አቅንቶ ክለቡን የሚቀላቀልበት እለት ነበር። በዚህ ሁሉ የድካም ስሜት ውስጥ ሆኖ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም አንባቢያን ያለውን ክብር ለመግለጽ ሲል ብቻ ድካሙን ተቋቁሞ ቃለ ምልልሱን ስለሰጠን በእናንተ ክቡራን አንባቢያን ስም ዋሊድን በድጋሚ እናመሰግነዋለን።

አንባቢያን ወቅታዊና አስፈላጊ መረጃዎችን በማድረስ የሚታወቀው ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ስለ ዋሊድ አታም ሆነ ሌሎች ተጫዋቾቻችንና አሰልጣኞች ግለ ታሪክን ጨምሮ የእግር ኳስ ታሪካቸውን ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው ወደፊትም እያከታተለ ያቀርባል። አንባቢያንም ሊጠየቅላችሁ የምትፈልጉትን አሰልጣኝም ሆነ ተጫዋች ብትጠቁሙን እንዲጠየቅ የተፈለገውን ግለሰብ ፈልገን ልናቀርብላችሁ እንችላለን።

ይርጋ አበበ
ለኢትዮ ፉትቦል

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
henokm [862 days ago.]
 Walid you are brilliant, we are also proud of you man. We wish all the success in your football life. Best wishes. henok

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!