ድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ምሽት ተጫዋቾቹንና አሰልጣኟን ይሸልማል
መስከረም 04, 2008

ይርጋ አበበ
ከፕሪሚየር ሊጉ ከወረደ በኋላ ወደ ላይ መመለስ ተስኖት ባለበት ሲረግጥ የቆየው ድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ባለፈው ወር አጋማሽ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያሳለፈውን ውጤት ማግኘቱ ይታወሳል። ዛሬ ከድሬዳዋ በደረሰን መረጃ ለማወቅ እንደቻልነው ከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ምሽት ለዚህ ክብር ያበቁትን አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ይሸልማል። የሽልማት መጠኑንና አይነቱን ማወቅ ባይቻልም ለተጫዋቾቹ እና ለአሰልጣኟ ከሚደረገው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ ክለቡ ለሰርቪስ የመሚጠቀምበት አውቶብስ ሳይበረከትለት እንደማይቀር ይጠበቃል።

ክለቡ ለዋንጫ የቀረበውን ሆሳዕና ከነማን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ዋንጫ በማንሳት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያለፈ ሲሆን በውድድሩም አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ኮከብ አሰልጣኝ ሆና ስትመረጥ ሁለት ተጫዋቾቹ ደግሞ ከከብ ጎል አግቢ እና ተጫዋች ሆነው ተመርጠውለት ነበር። ዛሬ የገንዘብ ሽልማት ከተበረከተለት በኋላ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በቡድኑ ተጫዋቾች ላይ የህክምና ምርመራ በማድረግ ወደ ዝግጅት እንደሚገባ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም በስልክ ተናግራለች። ቡድኑን ለማጠናከርም ውላቸውን ካደሱት ተጫዋቾች በተጨማሪ ሌሎች ተጫዋቾችንም በማስፈረም ላይ መሆኗን የገለጸችው አሰልጣኝ መሰረት የቀድሞውን የሀረር ቢራ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋን ማስፈረሟን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቀጣዩ ጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን በዚህ ዓመት የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ሳይል እንደማይቀር በበርካታ እግር ኳስ ተከታታዮች ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም በዚህ የውድድር ዓመት የሚሳተፉ ክለቦችን ቁጥር ለማወቅ ባደረገው ጥረት ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ባይችልም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወልድያ ከነማ እና ሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ የሚያቆያቸውን የማረጋገጫ ደብዳቤ ሳይጽፍላቸው እንዳልቀረ ለክለቦቹ ቅርበት ያላቸው የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ገልፀውልናል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!