የእግር ኳስ ፈርጦች መፍለቂያ እየሆነ የመጣው ሴንትራል ካፕ
መስከረም 06, 2008

ይርጋ አበበ

ከአንድ ዓመት በፊት ነው የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ወደ ደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና ሀዋሳ በማቅናት ከሶስት ታዳጊዎች ጋር የተገናኘው። ታዳጊዎቹ እድሜያቸው ከ10 እስከ 12 ዓመት የሚደርሱ ሲሆን ከዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ጋር የተገናኙት በየዓመቱ ክረምት ወቅት ላይ በሚካሄደው የሴንትራል ካፕ ውድድር  የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ነበር። በውድድሩ ከ12 ዓመት በታች እና ከ14 ዓመት በታች የሚገኙ አራት ቡድኖች ለፍጻሜ እየተፋለሙ በነበረበት ሰዓት ከጋዜጠኛው ጋር የተገናኙት ሶስቱ ታዳጊዎች “በግማሽ ፍጻሜው በረኛችን ባይጎዳ ኖሮ እኛ ነበርን ይህንን  ዋንጫ የምንበላው” ሲሉ መናገር ጀመሩ።

Central Cup

ታዳጊዎቹ በዚያው ዓመት ለፍጻሜ ቀርበው የዋንጫ ተፋላሚ አይሁኑ እንጅ የእግር ኳስ ፍጻሜያቸው ግን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፈው በመጫወት አገራቸውን በዓለም ዋንጫ እና አፍሪካ ዋንጫ ማገልገል ሲሆን በግላቸው ደግሞ ለታላላቆቹ የአርውሮፓ ክለቦች መጫወት እንደሆነ የጸና እምነት አላቸው። ለዚህ ራዕያቸው እውን መሆን ደግሞ በሴንትራል ካፕ ላይ ተስፋ ጥለዋል። ለመሆኑ ሴንትራል ካፕ ምንድን ነው? ከሴንትራል ካፕ የተገኘ ፍሬስ ምንድን ነው? የውድድሩ አዘጋጆች ምን ይላሉ? ውድድሩን በበላይነት  የሚመራውስ ማን ነው? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ከዚህ በታች ይዘን ቀርበናል።

ለህጻናት ትኩረት የሰጠው ሴንትራል ካፕ ማነው?

ኢትዮፉትቦል ዶትኮም በተለያዩ ጊዜያት በአዘጋጆቹ  እንደሚናገረውም ሆነ እንግዳ አድርጎ የሚጋብዛቸው የእግር ኳስ ባለሙያዎች ደጋግመው እንደሚናገሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ  እድገቱ ከልጅነቱ ነው። ልጅነቱ ላይ ከተቀጨ በወጣትነቱ  ወይም በጎልማሳነቱ ላይ እድገት መጠበቅ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደመውጣት ነው። ለዚህም ነው ደጋግመን በህጻናት  ላይ ይሰራ የምንለው። ቀደም ሲል በዚሁ ጉዳይ ላይ   ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዶ የነበረው  ዋሊድ አታ “ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ያልተሞረዱ   እንቁዎች ናቸው” ብሎ መናገሩን መዘገባችን ይታወሳል። የእግር ኳስ ሳይንሱ የሚገልጸውም በህጻናት ላይ ከተሰራ  የሚፈለገው ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ነው። ነገር ግን በአገራችን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች  በሚሰሩ የህንጻ ግንባታዎች ምክንያት ለህጻናት መጫወቻ
ሜዳ እንዳይኖር በአዋጅ የተደነገገ እስኪመስል ድረስ ሜዳዎቹ  በሙሉ በግንባታ ተይዘዋል። ከግንባታ ነጻ የሆኑ ውስን  ቦታዎችም በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው አካል ባለመኖሩ ሊሰጡ የሚገባቸውን ጥቅም ሲሰጡ አይታዩም።

በእነዚያ ሜዳዎች የሚጫወቱ ጥቂት ህጻናትም ቢሆኑ “የት ወደቃችሁ ምን አማራችሁ ምንስ ያስፈልጋችኋል?” ብሎ የሚጠይቃቸው አካል የለም። ይህ በመሆኑም ምክንያት በርካታ  የተሰጥኦ ባለቤት የሆኑ ታዳጊዎች ችሎታቸውን አውጥተው ሳያሳዩ ጠፍተው ይቀራሉ። በዚያው ልክ የኢትዮጵያ እግር  ኳስም እድገቱ እየቀጨጨ ይሄዳል።

ከላይ ለተገለጸው ቅሬታ አዘል እውነታ መልስ ለመስጠት ባሰበ  መልኩ ሀዋሳ ከተማ ላይ ለታዳጊዎች የክረምት ወቅት እግር ኳስ ውድድር የሚያዘጋጅ ሆቴል አለ “ሴንርትራል ሆቴል ሀዋሳ”  የሚባል። ሴንትራል ሆቴል ተማሪዎች ከትምህርት ቤት  መዘጋት በኋላ ጊዜያቸውን በሌላ ቦታ ከሚያሳልፉ በማለት ከ80 ያላነሱ የታዳጊ ቡድኖችን በተለያዩ ቁሳቁሶች በመደገፍ የእግር ኳስ ውድድር እንዲያካሂዱ ያደርጋል። ይህን ይትባህሉንም  ላለፉት ስድስት ዓመታት በቋሚነት ሲያካሂድ ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታትም አራት ተጫዋቾች ከ17 ዓመት በታች ላለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድል ያገኙ ሲሆን ከ14 ያላነሱ ታዳጊዎች ደግሞ ለሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ታዳጊ እና ተስፋ ቡድን የመመረጥ እድል አግኝተው እየተጫወቱ  ይገኛሉ። ሴንትራል ካፕ በእጭሩ ይህ ሲሆን በውድድሩ  የተመዘገቡ አብይ ክስተቶችንና ውጤቶችን እንዲሁም  የዘንድሮውን ውድድር በዝርዝር የሚገልጽ ዘገባ ነገ ይዘን  የምንመለስ ይሆናል። መረጃዎቹን በማድረስ የተባበሩንን የሴንትራል ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍትህ ወልደ ሰንበትን
በአንባቢያን ስም እናመሰግናለን።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!