የ2007 ዓ.ም የሴንትራል ካፕ ፍጻሜ ድባብ
ግንቦት 08, 2008

ይርጋ አበበ

በትናንትናው ዝግጅታችን በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው ሴንትራል ሆቴል ድጋፍ የሚያደርግለት የታዳጊዎች እግር ኳስ ውድድር ያለፉትን ስድስት ዓመታት ጉዞ መዳሰሳችን ይታወሳል። በትናንትናው ጽሁፋችን ሴንትራል ካፕ በስድስት ዓመታት ጉዞው አራት ተጫዋቾችን ለወጣት ብሔራዊ ቡድን 14 ተጫዋቾችን ደግሞ ለሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ተስፋ እና ታዳጊ ቡድን ማፍራቱን ዘግበን ነበር። ዛሬ ደግሞ ባለፈው ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ዓ.ም ፍጻሜ ስላገኘው ሰባተኛው የሴንትራል ካፕ ውድድር ከውድድሩ አዘጋጆች የደረሰንን መረጃ ይዘን ቀርበናል።

በሶስት የእድሜ ክልል ማለትም ከ12 ዓመት በታች፣ ከ14 ዓመት በታች እና ከ16 ዓመት በታች በሆኑ በድምሩ 56 ቡድኖች ሲሳተፉ መቆየታቸውን የገለጹት የውድድሩ ስፖንሰር ሴንትራል ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍትህ ወልደሰንበት እንደገለጹት በፍጻሜው ከደቡብ ክልል የሚገኙ ክለቦች መልማዮቻቸውን ልከው የታዳጊዎቹን ውድድር ተከታትለዋል። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከ37 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ጎል በማስቆጠር ታሪክ የሰራው አዳነ ግርማ እና በዚህ ዓመት ሀዋሳ ከነማን ከመውረድ የታደገው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በክብር እንግድነት ተገኝተው የተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል።

በፍጻሜው እለት ከ12 ዓመት በታች ውድድር ህይወት ብርሃን እና ኤልዩሲን የተባሉ ቡድኖች ተገናኝተው ህይወት ብርሃን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። ከ14 ዓመት በታች የተገናኙት ደግሞ ታቦር እና ዛማ ስፖርት አካዳሚ ሰሆኑ ታቦር ስድስት ለሁለት በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ከፍተኛ ፉክክር እንደታየበት የተገለጸው ከ16 ዓመት በታች የፍጻሜ ውድድር ኤልሚ ፍራሽ እና ቤስት የተባሉ ቡድኖች ተገናኝተው ኤልሚ ፍራሽ ሶስት ለሁለት በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የፍጻሜው ውድድር ማራኪ ጨዋታ እና ከፍተኛ ፉክክር የታየበት እንደነበረም አቶ ፍትህ ያደረሱን መረጃ አመልከቷል።

ውድድሩን ለማድመቅና ታዳጊዎቹ በትልቅ ደረጃ የመጫወት ልምድ እንዲያዳብሩና በራሳቸው እንዲተማመኑ አዳነ ግርማን እና ውበቱ አባተን ጨምሮ የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዱሬሳ ዱከም፣ የኢትዮጵያ ዳኞች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ትግል ግዛው እና ውድድሩን ስፖንሰር ያደረገው የሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ተወካዮች ተገኝተው ታዳጊዎቹን አበረታተዋል። የሃዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዱሬሳ ዱከም ባደረጉት ንግግር “ይህ ውድድር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና በተሳታፊ ቡድኖች እንዲሁም በተመልካች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ውድድሩም ደማቅ እየሆነ መጥቷል። ተተኪዎችንም በበቂ ሁኔታ እያፈራ ይገኛል” በማለት ተናግረዋል።

በውድድሩ ኮከብ ተጫዋቾች፣ ኮከብ ግብ ጠባቂዎች፣ ኮከብ ተከላካዮችና ከፍተኛ ግብ አግቢዎች እንዲሁም ኮከብ አሰልጣኞች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በውድድሩ መዝጊያ እለት ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የሴንትራል ሆቴል ሀዋሳ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍትህ ወልደሰንበት “ለዚህ ውድድር ስኬት ለደከሙት አስተባባሪዎች እና ቡድኖቹን አዘጋጅተው ላቀረቡት የንግድ ድርጅቶችና መስሪያ ቤቶች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ይህ ውድድርም በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ የሚካሄድ ይሆናል” ብለዋል። ሴንትራል ካፕ ከሰባት ዓመታት በፊት ሲጀመር በሆቴሉ ባለቤት ወይዘሮ አማረች ዘለቀ አስታባባሪነትና ሀሳብ አመንጭነት ነበር። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!