ጥሎ ማለፉ ኮከብ አሰልጣኞችን ለፍጻሜ አፋጥጧል
መስከረም 12, 2008ይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት ከአዲስ አበባ ስታዲየም ዝምባብዌ እና ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያደርጉትን የሴካፋ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈ ነው። የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የነበሩትና ትናንት 75ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም በክቡር ትሪብዩን ተሰይመው የሚመለከቱትን ጨዋታ በአቻ ውጤት ቀጥሎ እየተካሄደ ባለበት ሰዓት ከመስመር የተሻገረችን ኳስ አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች በግንባሩ ገጭቶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲልካት የዝምባብዌው ተከላካይ ኳሷ ፍጥነት እንዲኖራት ተባበራትና ጎል ተቆጠረ። በወቅቱ ጨዋታውን በቀጥታ በሬዲዮ ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤም “ገብሬ የመታውን ኳስ የዝምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ….” የሚል ለአድማጭ የሚመስጥና በተለይም ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጽ ከጥልቅ ስሜት በመነጨ አገላለጽ ገለጸው በጊዜው ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ተሰልፎ ይጫወት የነበረውን ገብረመድህን ሀይሌ ያስቆጠረውን ጎል።

በ2003 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሪሚየር ሊጉን የመዝጊያ ጨዋታ በቀጥታ እያስተላለፈ ነው። ጨዋታው የሚካሄደው በኢትዮጵያ ቡና እና በሙገር ሲሚንቶ ክለቦች መካከል ሲሆን ጨዋታውን ቡና ማሸነፍ ከቻለ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያነሳበት በማንኛውም መንገድ ነጥብ ከጣለ ደግሞ የዋንጫውን ጆሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሳልፎ የሚሰጥበት ጨዋታ በመሆኑ ካምቦሎጆ መተንፈሻ እስኪጠፋው ድረስ በተመልካች ተሞልቷል። በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊም ጨዋታውን ከሚጢጢው አዲስ አበባ ስታዲየም ታድሞ መከታተል ባይችል እንኳ በቴሌቪዥን መስኮት እየተከታተለ ነው። ምንያህል ተሾመ እና ሙሉዓለም ጥላሁን ያስቆጠሯቸው ጎሎች ቡናን ዋንጫ እንዲያነሳ አደረጉት። የቡና ደጋፊዎች በወቅቱ ደስታቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ ሲቃ እየተናነቃቸው አሰልጣኛቸውን አሞገሱት። አደነቁት። ይህ አልበቃ ብሏቸው ደግሞ መኪና ሸለሙት። አሰልጣኝ ውበቱ አባተን።

በሴካፋ ዋንጫም ሆነ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ መስራት የቻሉት ሁለቱ ግለሰቦች አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እያሰለጠኑ ካሉ በጣት የሚቆጠሩ ብቃት ካላቸው አሰልጣኞች መካከል ይመደባሉ። ሁለቱም አሰልጣኞች በራሳቸው መንገድ ጠንካራ እና ለተመልካች አዝናኝ ጨዋታ የሚጫወት ቡድን በመገንባት የሚታወቁ ሲሆን በደጋፊዎቻቸውም ሆነ በክለብ አመራሮቻቸው አመኔታን ያገኙ አሰልጣኞች ናቸው። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ዋንጫ በፍጻሜው ያገናኘው እነዚህን ሁለት ኳሊቱ አሰልጣኞች ነው። ገብረመድህን በአዲሱ ተስፋዬ እና በሀይሉ ግርማ ሁለት ጎሎች የቀድሞ ክለቡን ቅዱስ ጊዮርጊስን ሁለት ለአንድ አሸንፎ፤ ውበቱ አባተ ደግሞ ጎረቤቱን ወላይታ ድቻን በበረከት ይሳቅ ብቸኛ ጎል አንድ ለባዶ በማሸነፍ ነው በፍጻሜው ሊገናኙ የቻሉት። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም በፍጻሜው ጨዋታ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክስተቶችንና ከፍጻሜው በኋላ ሊተገበሩ የሚገባቸውን ነጥቦች ከዚህ በታች ይዳስሳቸዋል።

የአሰልጣኞች ታክቲካል የበላይነትን የሚጠይቅ ጨዋታ
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተለመደ የመጣው ነገር ቢኖር እንደ አርብቶ አደር ከክለብ ክለብ ሲንከራተቱ የሚታዩ ተጫዋቾች መብዛታቸው ነው። ትናንት ከአንዱ ክለብ ጋር ሆኖ በተጋጣሚው መረብ ላይ ጎል አግብቶ ደጋፊውን ያስፈነደቀ ተጫዋች ዛሬ ደግሞ ለሌላው ክለብ ፈርሞ ትናንት ያስፈነደቀውን ደጋፊ ሲያሸማቅቅ ይታያል። በዚህም ምክንያት አንድ አሰልጣኝ የሚያሰለጥነውን ቡድን የሚገነባው የተጫዋቾቹን ማንነት በጊዜ ሂደት ገምግሞ ወይም ከሚያሰለጥነው ቡድን ታዳጊና ተስፋ ቡድን ጀምሮ በመመልከት አይደለም። ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በስራቸው የሚሳካላቸው አሰልጣኞች ቁጥር በእጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ከእነዚህ ስኬታማ አሰልጣኞች መካከል ሁለቱ በጥሎ ማለፉ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የሚገናኙት ገብረመድህን ሀይሌ እና ውበቱ አባተ ናቸው።

በፍጻሜው ጨዋታ ተመልካቹ ሊመለከተው የሚችለው ትልቁ ክስተት ሊሆን የሚችለውም ከሁለቱ ቡድኖች ውጤት ጀርባ ያለው የአሰልጣኞች ታክቲካል የበላይነት ይሆናል። ባለፈው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ላይ ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቶ ተጫዋቾችን ቢያስፈርምም ላለመውረድ ሲንገታገት የከረመውና በመጨረሻም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ መሪነት ከመውረድ የተረፈው ሃዋሳ ከነማም ሆነ ምርጥ አማካዩ ተክለወልድ ወይም ጣቁሩ በድንገተኛ ሞት ምክንያት የቡድኑ ስሜት ተረብሾ በመጨረሻ ውጤቱ የከፋበት መከላከያ የጥሎ ማለፉን ዋንጫ አጥብቀው ይፈልጉታል። ለዚህም እምነታቸውን በኮከብ ተጫዋቾቻቸው ላይ ቢጥሉም የእምነታቸውን የመሰረት ድንጋይ የሚያስቀምጡት ግን በአሰልጣኞቻቸው ላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የበሀይሉ ግርማ ትንሳኤ

በሀይሉ ግርማ እንደ ስያሜው ግርማ ሞገስን የተላበሰ ጉልበትን ወይም ሀይልን ቀላቅሎ የሚጫወት የአማካይ ተከላካይ መስመር ተጫዋች ነው። በሀይሉ ግርማ በርካታ ተጫዋቾችን እያፈራ ለታላላቅ ክለቦች በመመገብ የሚታወቀው ሙገር ሲሚንቶ ኮትኩቶ ያሳደገው በሀይሉ ግርማ ፍጥነት የሌለው በመሆኑ “ቀርፋፋ” እየተባለ የሚጠራ ቢሆንም ሜዳ ላይ እይታውና ከኳስ ጋርም ሆነ ያለ ኳስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ማስተዋል የተሞላበት ነው።  በሀይሉ መከላከያን ከተቀላቀለ ዘንድሮ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑን ይጀምራል። ባለፈው ዓመት ከመከላከያ ጋር ስኬታማ ጊዜ ማሳለፍ እንዳይችል ጉዳትና ቦታው በሟቹ ተክለወልድ መያዙ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥረውበት ነበር። በዚህ የውድድር ዓመት ግን ብቃቱን የሚያሳይበት ዓመት እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን ቡድኑ በጥሎ ማለፉ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ ጠንካራውን ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ እንዲወጣ ያስቸለች ጎል በግንባሩ ገጭቶ ማስቆጠር ችሏል። በፍጻሜው ጨዋታም ክለቡን የሚታደግበት እድሎችን መፍጠር ከቻለ ትንሳኤ ይሆንለታል ማለት ነው። ይህን ማድረግ ከቻለ እና በሙገር ሲሚንቶ ቆይታው የነበረውን ብቃት በዚህ የውድድር ዓመትም መድገም ከቻለ በርካቶች በተደጋጋሚ እንደሚናገሩትና እንደሚመኙት የዋልያውን የአማካይ ተከላካይ ክፍል የሚቆጣጠርበት ጊዜ ሩቅ እንዳይሆን ያስችለዋል። ይህም ከፍጻሜው በኋላ ከሚጠበቁ ክስተቶች አንዱ ነው።

የሃዋሳ ትንሳኤ እና የውበቱ ቃል

ከስድስት ወራት በፊት የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በሃዋሳ ከተማ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በተገናኘበት ወቅት አንድ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር፤ በሞት አፋፍ ላይ ያለን ቡድን ለማሰልጠን የተረከብከው ምን ተማምነህ ነው? ሲል ነበር የጠየቀው። አስጣኝ ውበቱ ሲመልስም “እንደማንወርድ መቶ በመቶ አረጋግጥልሃለሁ። በጥሎ ማለፉ ደግሞ ዋንጫውን እናነሳለን” በማለት መለሰ። አሰልጣኙ እንደተናገረውም ክለቡ ከፕሪሚየር ሊጉ ሳይወርድ የቀረ ሲሆን በጥሎ ማለፍ ዋንጫውም በሩብ ፍጻሜ ኢትዮጵያ ቡናን በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ ወላይታ ድቻን በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሷል። በፍጻሜው ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማወቅ የማይቻል ሲሆን የውበቱን ቃል መጨረሻ ለማረጋገጥም ጊዜው ገና ቢሆንም ሃዋሳ ከነማ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከተያዘ በኋላ ያደረገው ጉዞ ግን ክለቡ ከተኛበት የተቀሰቀሰበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል።  

ዋንጫውን ለተክለወልድ ፍቃዱ

መከላከያ ይህን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አጥብቆ ከሚፈልግባቸው ምክንያቶች አንዱ ምናልባትም ቀዳሚው ምክንያት የዋንጫውን መታሰቢያነት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በመኪና አደጋ ህይወቱ ላለፈው ለቀድሞ አማካዩ ለተክለወልድ መታሰቢነት ነው። ተክለወልድ በመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጥ አቋም እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች ቀዳሚው ነበር። የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ክለቡ ማንሳት ከቻለም መታሰቢያነቱን ለዚሁ ልጅ ሊያደርገው እንደሚችልም ይገመታል። ይህን የምንለው ከመሬት ተነስተን ሳይሆን ክለቡ ከተጫዋቹ ህልፈተ ህይወት በኋላ ያደረጋቸውን ተከታታይ ጨዋታዎች ቢያሸንፍ ኖሮ ለተክለወልድ ፍቃዱ መታሰቢያነት ሊያደርግ እንደነበረ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በአንድ ወቅት መናገሩን ታሳቢ በማድረግ ነው።

የአህጉራዊ ተሳትፎ

በጥሎ ማለፉ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን አገሩን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ቅድመ ማጣሪያ የሚሳተፍ ይሆናል። በአህጉራዊ ውድድር ላይ የመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ሁለቱ ክለቦች ከፍላጎት በዘለለ በውድድሩ ማስመዝገብ የሚችሉትን ውጤትም ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በተደጋጋሚ እንደሚባለውና በግልጽም እንደታየው በአህጉራዊ ውድድር ተደሳትፎ የሚያደርጉ ክለቦቻችን ከቅድመ ማጣሪያ እና ከማጣሪያ በዘለለ በምድብ ድልድሉ ውስጥ የመግባት ደካማ ሪከርድ የሚያሻሽሉበትን አስተሳሰብና ቡድን ሊገነቡ ይገባቸዋል እንላለን። አለዚያ እንዲሁ ለጉብኝት ይመስል ለአንድ ወይም ሁለት ጨዋታዎች ሲባል ብቻ በአህጉራዊ ውድድር ላይ ለመሳተፍ እቅድ ማውጣትም ሆነ ቡድን መገንባት የሚገባ አይመስለንም። የጥሎ ማለፉ የፍጻሜ ጨዋታም ለተመልካች የሚያሳየው አንዱ ነጥብ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመሳተፍ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አቅም ያለውን ክለብም የሚያሳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የጥሎ ማለፉ የፍጻሜ ጨዋታ የፊታችን  ይካሄዳል።

 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
alemu [881 days ago.]
 በጣምያምራል

Desalegn mersha [852 days ago.]
 Yamral

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!