የአዲስ አበባ ከተማ አምበር ዋንጫ የመጀመሪያ ቀን ውሎ
መስከረም 23, 2008

በይርጋ አበበ

አስረኛ ዓመቱን የያዘው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዘንድሮ “አዲስ አበባ ከተማ አምበር ዋንጫ” በሚል ስያሜ ውድድሩን እያኬሄደ ይገኛል። የውድድር መደራረብ በፈጠረው ምክንያት የምድብ አንድ ቡድኖች ሁለት ሁለት ጨዋታ ከተጫወቱ በኋላ ምድብ ሁለቶች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያኬሂዱበት የዘንድሮው ውድድር ትናንት አንድ ለእናቱ በሆነው አዲስ አበባ ስታዲየም ተጀምሯል። በመክፈቻው እለትም ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደው በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ጨርሰዋል። የትናንትናውን ጨዋታ በተመለከተ መጠነኛ ዳሰሳ ከዚህ በታች እናቀርባለን።

ቡና ከደደቢት

በአንድ ጨዋታ ሰባት ተጫዋቾችን መቀየር እንደሚቻል የሚፈቅደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በትናንቱ ጨዋታ የማሊያ ጉዳይም አሳሳቢ ሆኖ ነበር የታየው። ለወትሮው ሰማያዊ ማሊያ ላይ የተጫዋቾቹን ስም ለጥፎ ይጫወት የነበረው ደደቢት እግር ኳስ ክለብ በትናንትናው ጨዋታ ተጫዋቾቹ ለብሰውት የገቡት ማሊያ በእስክብሪቶ የተጻፈ ማሊያ ነበር። ይህን ማሊያ ለብሶ የገባው ደደቢት ጭራሽ ቋሚ ግብ ጠባቂው ተጎድቶ ሲወጣ እሱን ተክቶ የገባው ግብ ጠባቂ ደግሞ ሌላ አይነት ቀለም ያለው መለያ ለብሶ ገብቷል። የእለቱ ዳኛም ሆኑ የውድድሩ አዘጋጆች የደደቢትን ማሊያ እያዩ ጨዋታውን ማካሄዳቸው አስገራሚ ነው። ምክንያቱም በፊፋ መመሪያ የአንድ ቡድን ተጫዋቾች የሚለብሱት መለያ ተመሳሳይ መሆን እንደሚገባውና የተጫዋቾቹ ቁጥርም በጉልህ ለተመልካች መታየት እንዳለበት ይደነግጋል። የትናንቱ የደደቢት ተጫዋቾች የለበሱት ማሊያ ከህጉ ውጭ የሆነ በመሀኖ ለውድድሩ ትኩረት ያልሰጡ አስመስሏቸዋል።

የደደቢት ድክመት እና የቡና ወጣቶች ተስፋ ሰጭነት

ደደቢት የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቡናው ኤፍሬም ወንድወሰን በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠረለት ጎል አንድ ለባዶ መምራት ችሎ ነበር። ይህን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት ያደረገው ጥረትም እስከ ጨዋታው መጠናቀቂያ ውስን ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ ተሳክቶለት ነበር። ሆኖም ተጫሪ ግብ ከማስቆጠር ይልቅ ያለውን ሲጠብቅ ባሳየው ድክመት መጠቀም የቻሉት የቡናው ድራገን ፖፓዲች ሰባት ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት የደደቢትን የግብ ክልል ደጋግመው መፈተን ችለዋል። በመጨረሻም ተሳክቶላቸው በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ውስጥ ፍጹም ቅጣት ምት አግኝተው ኣ መሆን ችለዋል።

በዚህ ጨዋታ የታዘብነው ደደቢቶች ልምድ የሌላቸውን የቡና ተከላካዮችን ጫና ፈጥረው ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አለመቻላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የተከላካይ መስመራቸውን ተደራጅተው መጠበቅ አለመቻላቸውም በመጨረሻ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ችሏል። በሌላ በኩል ቡና በዚህ ዓመት ከተስፋ ቡድን ያሳደጋቸውና ከሌላ ክለብ በተለይም ከብሔራዊ ሊግ ያስፈረማቸው ወጣቶች ያሳዩት ብቃት ተስፋ ሰጭ ሆኖ ታይቷል። በተለይ በግራ መስመር የተከላካይ ክፍል ተሰልፎ የተጫወተውና ቡድኑ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ዮሴፍ ደምሌ በራስ መታመኑ እና ለአጥቂዎች የሚሰጠው ሽፋን በተመልካች አድናቆት አስችሮታል። ከሸር ኢትዮጵያ የፈረመው ወጣቱ አጥቂ ትክነህ ፍርዱም ተመልካቾች አድናቆታቸውን የቸሩት ሲሆን አዲሱ የኤፍሬም አሻሞ አጣማሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ወንድይፍራው ጌታሁን ደግሞ የተረጋጋ እና ፍርሃት የሌለበት ተከላካይ መሆን እንደሚችል አሳይቷል።ከውጭ የተገዙት ሶስት ተጫዋቾች ግብ ጠባቂውና ሁለቱ አጥቂዎች በቡና ቡድን ላይ ተጨማሪ ሀይል ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ እንዲጣልባቸው የሚያስችል ብቃት አሳይተዋል።

የቡናው አሰልጣኝ ድራገን ፖፓዲች ቡድናቸውን “የድሬዳዋ ፍሬ” ሲሉ ከጨዋታው በኋላ ገልጸውታል። አብዛኞቹን ተጫዋቾች በብሄራዊ ሊግ የመጨረሻ ውድድር ላይ ድሬዳዋ ሂደው ማስፈረማቸውን ለመግለጽ።

ዳሽን ከኤሌክትሪክ

ይህ ጨዋታ በርካታ የጎል እድል የተፈጠረበትና ጨዋታው እንደተካሄደበት ሰዓት የአየር ጸባይ ቀዝቀዝ ያለ እና ለተመልካች አዝናኝ ያልነበረ ጨዋታ ነበር። በተለይ በዳሽን ቢራ በኩል የተፈጠሩትን የጎል እድሎች መጠቀም የሚችል አጥቂ አለመኖሩ ቡድኑ እድለኛ እንዳይሆን አድርጎታል። ከተገኙት የግ እድሎች መካከል አንጋፋው መድሃኔ ታደሰ ብቻ ሶስት ያለቀላቸው እድሎችን ማምከን ችሏል።

ውድድሩ ማክሰኞ ቀጥሎ የሚውል ሲሆን ከዚሁ ከምድብ አንድ ኤሌክትሪክ ከደደቢት እና ቡና ከዳሽን ቢራ ይጫወታሉ። ረቡዕ ደግሞ የምድብ ሁለት ቡድኖች ይጫወታሉ።  

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!