ዋልያዎቹ አንድ ደረጃ ከፍ ያሉበትን ውጤት ያስመዘገቡበት ጨዋታ እና አንዳንድ ነጥቦች
ጥቅምት 01, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሶስት ቀናት በፊት ወደ ምዕራብ አፍሪካ አምርተው ትንሿን አገር ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፒን ገጥመው አንድ ለባዶ ተሸንፈው ተመለሱ። ውጤቱን ተከትሎም በርካታ ስፖርት አፍቃሪያን ስሜታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገለጹ። የአስተያየት ሰጭዎቹ ቅሬታ ቡድኑ እንደ ሳኦቶሜ አይነት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውን አገሮች ማሸነፍ ከተሳነው ታዲያ እንዴት ወደ ፊት ሊጓዝ ይችላል? የዋልያው መዋያ ተራራ መሆኑ ቀርቶ እንደ እንቁራሪት ኩሬ ውስጥ እንዳይሆን በመስጋት ነው። ይህ ደግሞ ከንጹህ ህሊና እና ከሀገር ፍቅር በመነጬ ስሜት ከሆነ አስተያየቶቹ እና ቁጣዎቹ ተገቢ ናቸው እንላለን። በዚህ መሃል ግን ዋልያዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ለማካሄድ ለትናንት በተቆረጠላቸው ቀነ ቀጠሮ መሰረት ጨዋታው ትናንት ከቀኑ አስር ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሄደ። ጨዋታው እንዴት ነበር? የቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ምን ሊመስል ይችላል? ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ምን አለ? የሚሉትን እና ሌሎች ሊነሱ የሚገቡ ነጥቦችን አንስተን እንዳስሳለን። መልካም ንባብ!!

የጨዋታው ጅማሮ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሃሙስ ምሽት በሳኦቶሜ የተሸነፈውን ቡድን የአሰላለፍ ለውጥ ሳያደርግ ነበር በትናንቱ ጨዋታም ቡድኑን ወደ ሜዳ ያስገባው። ጨዋታው እንደተጀመረ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ በእለቱ ኮከብ ሆኖ ያመሸው ሽመልስ በቀለ ያሻገረለትን ኳስ ዳዊት ፈቃዱ አስቆጥሮ የዋልያዎቹን ሞራል ከፍ ማድረግ ጀመረ። በመጀመሮያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይም በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃ ዋልያዎቹ በተጋጣሚያቸው ላይ የመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ይዘው እንዲያመሹ ያስቻለው አማካዩ ሽመልስ በቀለ ነበር። የቀድሞው የሃዋሳ ከነማ ተጫዋች ሽመልስ በቀለ በእለቱ ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በምርጥ አቋሙ ሆኖ ያመሸ ቢሆንም በተለይ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ግን ፍጹም ምርጥ ብቃት አሳይቷል።

በዚሁ የጨዋታው የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ዋልያዎቹ የኳስ ቁጥጥር እና ወደ ተጋጣሚ የጎል መስመር ቶሎ ቶሎ በመድረስ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ቢሆንም መረቡ ላይ ማረፍ የምትችል ኳስ መምታት የሚችል አጥቂ ግን አልተገኘም። በዚሁ ክፍለ ጊዜ ዋልያዎቹ ያገኟቸውን ተደጋጋሚ የጎል ሙከራዎች ያባከነው የሀዋሳ ከነማው በረከት ይሳቅ ነው። ሌላው በዚሁ ክፍለ ጊዜ የተፈጠረው አብይ ክስተት ለዋልያዎቹ መሰለፍ በጀመረባቸው ጨዋታዎች ሁሉ በምርጥ ብቃት ሆኖ ጨዋታን የሚጨርሰው ወጣቱ ተካልኝ ደጀኔ በጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ ነው። ወጣቱ የደደቢቱ ግራኛ ልጅ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ ሲወጣ ቦታውን የተካው የቀድሞው የወላይታ ድቻ አማካይ ተከላካይ የነበረው ብሩክ ቃልቦሬ ነው።

ከእረፍት መልስ የተደረገው ስኬታማ የተጫዋች ቅያሪ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እንደ ሳላዲን ሰይድ እና ኡመድ ኡክሪ አይነት ልምድ ያላቸውን አጥቂዎች በቡድኑ ባለማካተቱ ተተችቶ ነበር። በትናንቱ ጨዋታም የእነ ሳላዲንን ቦታ ተክተው የገቡት ዳዊት ፈቃዱ እና በረከት ይሳቅ ጥሩ አለመሆናቸው በተለይም የበረከት ይሳቅ ብቃት ወርዶ መታየቱ በደጋፊው ቁጣን ቀስቅሶ ነበር። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከእረፍት ሲመለስ አስቻለው ግርማን በበረከት አዲሱ ቀይሮ በማስገባት የፎርሜሽን ለውጥ አድርጓል። ለዚህም ወደ መስመር ወጣ ብሎ እንዲያጠቃ ተደርጎ የነበረው አዲሱ ፈረሰኛ ራምኬል ሎክን ወደ ፊት መስመር አሸጋግሮ የመስመሩን ቦታ በአስቻለው ግርማ እና ኤፍሬም አሻሞ እንዲሸፈን ማድረግ ችሏል። የፈረሰኞቹ አዲስ ፈራሚ ራምኬል ሎክ ወደ ፊት ተጠግቶ መጫወት ደግሞ የሳኦቶሜን ተከላካዮች ጫና እንዲበዛባቸው ያደረገ ሲሆን የዋልያዎቹን የኳስ ቁጥጥርም ፍጥነትን የተላበሰ እንዲሆን አድርጎታል።

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደተጀመረ ዳዊት ፈቃዱ ከርቀት አክርሮ የመታት ኳስ ያስደነገጣቸው የሳኦቶሜ ተከላካይ ክፍሎች በ47ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ወደ ግብ የላካትን ኳስም በእጃቸው በመንካታቸው ዋልያዎቹ ፍጹም ቅጣት ምት አገኙ። የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምትም የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም ወደ ጎል በመቀየር የዋልያዎቹን መሪነት ማስፋት አስቻለው። ከዚህች ጎል በኋላ ዋልያዎቹ ለተጨማሪ ጎል ሳኦቶሜዎች ደግሞ ጎል አስቆጥረው ከሜዳ ውጭ ጎል ባስቆጠረ በሚለው የፊፋ ህግ ተጠቅመው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው የጎል ክልል ደጋግመው መሞከር ጀመሩ።

በዋልያዎቹ በኩል ዳዊት ፈቃዱ እና ጋቶች ፓኖም ከርቀት አክርረው በመምታት ጎል ለማግባት የሞከሩ ሲሆን በተለይ ከ69ኛው እስከ 72ኛው ደቂቃ ውስጥ አራት ጊዜ ወደ ተጋጣሚያቸው የጎል ክልል መቅረብ ቢችሉም አንዱንም የጎል ድል ወደ ጎልነት የሚቀይር አጥቂ አልተገኘም። በሳኦቶሜ በኩል ደግሞ ውስን ሙከራዎችን ወደ ዋልያዎቹ የጎል ክልል ቢያደርጉም የታሪክ ጌትነትን እጆች አልፈው መረብ ላይ ማረፍ አልቻሉላቸውም።

74ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ ከቢኒያም በላይ ጋር ተቀባብሎ ለዳዊት ፈቃዱ ያሻገረለትን ኳስ ዳዊት ፈቃዱ የሳኦቶሜዎችን ግብ ጠባቂ አታልሎ ለራምኬል ሎክ አቀብሎት የቀድሞው የኤሌክትሪክ ተጫዋች ሶስተኛዋንና የእለቱን የመጨረሻ ጎል አስቆጥሯል። ከዚህ በኋላም ቢሆን ዋልያዎቹ በዳዊት ፈቃዱ እና በቢኒያም በላይ አማካኝነት ሙከራዎች አድርገው ከግቡ መስመር ውጭ ልከዋቸዋል። ሺመልስ በቀለ እና አስቻለው ግርማ ያደረጓቸውን ሙከራዎችም የሳኦቶሜው ግብ ጠባቂ ይዞባቸዋል። ወጣቱ ቢኒያም ሀይሉ በትናንትናው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ያሳው ብቃት በተመለረካች ውዳስን አስችሮታል።

የጨዋታው ሌላ ገጽታ

ዋልያዎቹ የትናንቱን ጨዋታ አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ቢችሉም ቡድኑ ግን ገና ሊደፍነው የሚገባ ትልቅ ቀዳዳ ያለበት እንደሆነም ታይቷል። ከዓመታት በፊት ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ሆነ ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለቻን ዋንጫ ማጣሪያዎችን አካሂዶ ስኬታማ የሆነው ብሔራዊ ቡድን ታላላቅ ቡድኖችን ሲያገኝ ወገቤን የሚል በመሆኑ ለተደጋጋሚ ትችት ሲዳረግ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቡድኑ ከገጠማቸው ጠንካራ ቡድኖች አንዳቸውንም ማሸነፍ አለመቻሉ አስተችቶት ነበር።

በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የሚመራው የወቅቱ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ገና እየተገነባ ያለ ቡድን በመሆኑ ከታላላቅ አገሮች ጋር ሳይሆን በታናናሽ አገሮችም በእጅጉ ሲፈተን እየታየ ነው። በትናንትናው ጨዋታ የታየው የቡድኑ ድክመትም ከዚህ የመነጨ ነው።

የቡድኑ የመጀመሪያ ችግር አጥቂዎቹ ጎል ከማግባት ይልቅ ኦፍሳይድ መግባት የሚቀላቸው ሆነዋል። በተደጋጋሚ ጊዜ የኦፍሳይድ አጨዋወት መግባታቸውም የቡድኑን የማጥቃት ሀይል ገድበውታል።ሌላው የቡድኑ ችግር ምናልባትም ቶሎ ይቀረፋል ተብሎ የማይጠበቀው የአጥቂው ክፍል ነው። አጥቂው ክፍል የተጋጣሚን የጎል ክልል ለይቶ አያውቀውም እየተባለ ይተቻል። ለዚህ ችግር ጥያቄ የቀረበለት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም ችግሩ መኖሩን አምኖ አገሪቱ ውስጥ ያሉት አጥቂዎች እነዚህ ብቻ ናቸው ከየት ላመጣ እችላለሁ ያለ ሲሆን አያይዞም ልጆቹ ገና ልምድ የሚጎድላቸው ስለሆነ እናንተ ጋዜጠኞችም ሆናችሁ ህዝቡ ሊታገሳቸው ይገባል ብሏል።

የአሰልጣኙ መግለጫ

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከጋዜጠኞች ለቀረቡለት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። አሰልጣኙ የእለቱን ጨዋታ በተመለከተ በጥሩ ብቃት ተጫውተን አሳምነን አሸንፈናል ያለ ሲሆን ተጋጣሚዎቻችን በሜዳቸው አስቸግረውን ነበር በግል ብቃትም ሆነ እንደ ቡድን በመጫወት እና በፍጥነት በልጠውን ነበር።በመልሱ ጨዋታ ግን እኛ የህዝባችንን ድጋፍ እና የአገራችንን አየር ንብረት ተጠቅመን ውጤት መቀልበስ እንደምንችል እናውቅ ነበር ሲል ተናግሯል። የነበረን ብቸኛ እድል አንድ እና አንድ ብቻ መሆኑ ማለትም ማሸነፍ ብቻ መሆኑ በልጆቼ ላይ ጫና በዝቶባቸው ነበር። ሆኖም የህዝቡንም ሆነ የጋዜጠኞችን ተጽእኖ እና የአገርን አደራ ተቋቁመው ላስመዘገቡት ውጤት ልጆቼን አደንቃቸዋለሁ። ውጠጤቱ የእነሱ ነው አከብራቸወዋለሁ ሲል ተናግሯል።

ከጋዜጠኞች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል እነ ሳላዲንን መቀነሳቸውን በተመለከተ ነበር። አሰልጣኙ ሶስቱን አጥቂዎች ከስብስቡ የቀነሰበትን ምክንያት ሲናገርም “በፊፋ ካላንደር የሚመራ የወዳጅነት ጨዋታ ባለማድረጋችን የተጫዋቾቹን ብቃት መገምገም አልቻልንም። የልጆቹን ብቃት የመዘንነው በቀጥታ በነጥብ ጨዋታ ነው። በነጥብ ጨዋታ ያሳዩን ብቃትም አስደሳች አልነበረም። ገና ከሌሴቶው ጨዋታ ጀምሮ ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት አቅርቤ ነበር” ያለ ሲሆን ነገር ግን በሲሸልሱ ጨዋታ በድጋሚ ለማየት በመወሰኑ ለሁለተኛ ጊዜ ተጠሩ እንጅ የአጥቂዎቹ መቀነስ ቀደም ብሎ የታሰበ እንደነበረ ገልጿል። አሰልጣኝ ዮሃንስ “ብሄራዊ ቡድን እርስት አይደለም” ብሎ በጠራው የተጫዋቾቹ ቅነሳ “እኔ የሚቆጨኝ ለቡድናችን ጠቀሜታ መስጠት እየቻሉ በተለያየ ምክንያት ከስብስቤ ውጭ ቢሆኑ ነበር እንጂ የተጫዋቾቹ አለመመረጥ ወቅታዊ ብቃትን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ አልቆጭም” ሲል መልሷል። የአጥቂ ችግር ግን አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ተናግሯል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በቡድኑ ላይ ያየውን ለውጥ ሲናገርም “ጠንካራ የቡድን ስሜት ወይም ቲም ስፕሪት አለ። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ቡድኑን ከያዝኩ በኋላ ባደረግናቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አንድም ተጫዋች በቀይ ካርድ አልወጣብኝም። ይህ የሚያሳየው የተጫዋቾቼ ዲስፕሊን መሻሻል እያሳየ መሆኑን ነው” ሲል ገልጿል።

የአሰልጣኙን መግለጫ ቀጣይ ክፍል በነገው ዝግጅታችን ይዘን እንመለሳለን።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Melaku [864 days ago.]
 Idiot ahuin ant coach nehe ?! “እኔ የሚቆጨኝ ለቡድናችን ጠቀሜታ መስጠት እየቻሉ በተለያየ ምክንያት ከስብስቤ ውጭ ቢሆኑ ነበር እንጂ የተጫዋቾቹ አለመመረጥ ወቅታዊ ብቃትን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ አልቆጭም” ሲል መልሷል " ቆይ ጠብቅ ኮንጎና አልጄሪያ 10 ጎል ያቀምሱሃል !

yilkal [863 days ago.]
 Dear Coach Yohanes I watched your press conference. According to your press conference Let me show you some point. Under your leadership you Saladin said played two games score one goal. Dawit Fikadu was Sewnet Bishaw team more than three year but he never score single goal. How you come conclusion in one game to drop all of them Baye, Saladin, Getaneh and Umed. I advise you to bring back, if not it will be difficult to overcome Congo and Algeria. before let, think about your decision. We love Ethiopian team, the way you insult the supporter is not right. because they pressurize you to think about next game. If you are not change your attitude we will embarrassed the next two games, and you will lose your position.

daniel [863 days ago.]
 doog sport but the football is ander so taker

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!