10ኛው የአዲስ አበባ አምበር ዋንጫ ታላላቆቹን በፍጻሜ እንደማያገናኝ ታወቀ
ጥቅምት 05, 2008

በይርጋ አበበ

ለ10ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘውና ቢጂአይ ኢትዮጵያ በአምበር ቢራ ስም ስፖንሰር ያደረገው አዲስ አበባ ከተማ አምበር ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የተሸጋገሩ አራት ክለቦች ይፋ ሆኑ። ሶስት የአዲስ አበባ ክለቦችንና አንድ የአማራ ክልል ክለብ ይዞ በአንደኛው ምድብ ተደልድሎ የነበረው ምድብ አንድ በኢትዮጵያ ቡና ፊት አውራሪነት እና በዳሽን ቢራ ተከታይነት ሁለቱን ለግማሽ ፍጻሜ አሳልፎ ደደቢትን እና ኤሌክትሪክን ከግማሽ ፍጻሜው ውጭ አድርጓል።

ሶስት የአዲስ አበባ ክለቦችን እና አንድ የኦሮሚያ ክልል ክለብን ይዞ በሌላኛው ምድብ ያፋለመው ምድብ ሁለት ደግሞ የጥሎ ማለፉን አሸናፊ መከላከያን የምድቡ መሪ አድርጎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ሲያሳልፍ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ 54 ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚ የሆኑት ፈረሰኞቹ ደግሞ ከምድባቸው ሁለተኛ ሆነው ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግረዋል። በዚሁ ምድብ ያለፈው ዓመት የውድድሩ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምድቡ ካለማለፉም በላይ የምድቡን ግርጌ ይዞ ማጠናቀቁ አስገራሚ ሆኗል። የአሸናፊ በቀለ ቡድን አዳማ ከነማ ደግሞ በውድድሩ ባሳየው ብቃት የተወደሰ ቢሆንም ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል።

St.Georege vs Deence


St.George Vs Defence


            በውድድሩ ህገ ደንብ መሰረትም የምድብ አንድ አንደኛን ከምድብ ሁለት ሁለተኛ ስለሚያገናኝ ምድብ አንድን በመሪነት ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ከምድብ ሁለት ሁለተኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በግማሽ ፍጻሜው ይገናኛሉ። መከላከያ ደግሞ ዳሽን ቢራን ይገጥማል። የውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ድልድል ይፋ መሆኑን  ተከትሎ ከጻሜው ይልቅ ግማሽ ፍጻሜው አጓጊ እንዲሆን አድርጎታል። ምክንያቱም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ በርካታ ደጋፊ ያላቸውና ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች ማለትም ፈረሰኞቹ እና ቡናማዎቹ በፍጻሜው ቢገናኙ ኖሮ ፍጻሜውን ማድመቅ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃልና ነው። ሆኖም ሁለቱም በግማሽ ፍጻሜው የተገናኙ በመሆናቸው የውድደሩ ፍጻሜ የሚሆነው ከሁለቱ ክለቦች አንዳቸውን በግማሽ ፍጻሜው አሰናብቶ ይሆናል።

ከፍጻሜው በፊት የሚካሄድ የፍጻሜ ጨዋታ

የዛሬ ዓመት ተካሂዶ በነበረው የሲቲ ካፕ ውድድር ኢትዮጵያ ቡና ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ፈረሰኞቹ ደግሞ ሁለተኛ ሆነው በማለፋቸው በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ነበር። በዚያ ጨዋታም ፈረሰኞቹ በወጣቱ ዳዋ ሁጤሳ ሁለት ጎሎች እና ቡናዎች ደግሞ በሻኪሩ እና ቢኒያም አሰፋ ሁለት ጎሎች እኩል ለእኩል ተለያይተው በመለያ ምት ቡና ማሸነፉ ይታወሳል። በዚህ ዓመት ደግሞ ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ ውድድር ያለፈውን ዓመት ጉዞ በማድረግ በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸው የተደገመው ታሪክ በውጤትስ ምን ሊሆን ይችላል? ጨዋታውም ከፍጻሜው በፊት የሚካሄድ የፍጻሜ ጨዋታ ሆኗል።

4 ለ3 የሁለቱ ቡድድኖች የሲቲ ካፕ ጎሎች

ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አንድም ጎል ሳያስቆጥር በእሱ ላይም አንዳች ኳስ በሩ ላይ ሳትደርስ ባዶ ለባዶ በመለያየት ሁለት ነጥቦችን ይዞ ነበር የምድቡን ሶስተኛ ጨዋታ ያካሄደው። ቡና በበኩሉ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አንድ አንድ ጎል እያስቆጠረ በእሱ ላይ ደግሞ ተመሳሳይ የጎል መጠን ተቆጥሮበት ለሶስተኛው የምድብ ጨዋታ ደረሰ። ሁለቱ ክለቦች በውድድሩ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎቻቸው እኩል አራት አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል። ቡና ካስቆጠራቸው አራት ጎሎች ሶስቱን ያስቆጠረለት የቀድሞው የፈረሰኞቹ ተስፋ ቡድን ፍሬ የሆነው ዮሴፍ ደሙዬ ነው ፈረሰኞቹ ካስቆጠሯቸው አራት ጎሎች መካከል ሶስቱን ያስቆጠሩለት ሁለት የውጭ አገር ተጫዋቾች ማለትም ብሪያን አሙኒ እና አይዛክ ኡሴንዴ ናቸው። ይህ ማለት ቡና ዮሴፍን ባያሰልፍ እና ጊዮርጊስ ደግሞ የውጭ ተጫዋቾችን ባያካትት ኖሮ የጎሎቻቸው መጠን አንድ አንድ ብቻ ይሆን ነበር ማለት ነው።

ከክለቦች ጋር የተስተካከለው መሀመድ ናስር

ቁመተ መለሎውና ቀጭኑ የመከላከያ አጥቂ የጎሉን መረብ ሲያይ እግሮቹ ይሰሉለታል ይባላል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ እስከ ኢትዮጵያ ቡና እና መድን ኢትዮጵያ ተጫውቶ ያሳለፈውና ወደ ሱዳን ተጉዞ ለአንድ ዓመት ከተጫወተ በኋላ እንደገና ወደ አገሩ ተመልሶ ለመከላከያ የሚጫወተው መሀመድ ናስር በዘንድሮው የሲቲ ካፕ ውድድር ለበረኞች የሚቀመስ አልሆነም። ለክለቡ በተጫወተባቸው ሶስት ጨዋታዎች አራት ጎሎችን አስቆጥሮ የውድድሩን ኮከብ ጎል አግቢነት ከዮሴፍ ደሙዬ በአንድ ጎል በልጦ እየመራ ይገኛል። በክለብ ደረጃ ደግሞ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ካስቆጠሯቸው ጎሎች ሲጋራ ያለፈው ዓመት የሲቲ ካፑ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዳሽን ቢራ ካስቆጠሯቸው ጎሎች የበለጠ ጎል አስቆጥሯል። በዚህ ውድድር ሶስት ክለቦች እኩል አራት ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ከምድብ አንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ደደቢት እና አምስት ጎሎችን ማስቆጠር ቢችልም ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ተስኖታል። ከምድብ ሁለት አንደኛ ሆኖ የጨረሰው መከላከያ ደግሞ በሶስቱም ጨዋታዎች ጎል ያስቆጠረ ሲሆን በእሱ ላይመ ጎል ተቆጥሮበታል። መከላከያ በውድድሩ ሰባት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ኤሌክትሪክ በጎሉ መስመር የለም። በመሆኑም ምድብ አንድን ያለምንም ጎል እና በአንድ ነጥብ ግርጌው ላይ ተረጋግቶ ጨርሷል። ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ንግድ ባነክ ደግሞ አንድ ጎል ብቻ አስቆጥሮ አምስት ጎል ተቆጥሮበት ከምድቡ ግርጌውን ይዞ ጨርሷል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!