የሲቲ ካፑ ታላቅ ጨዋታ እና ተያያዥ ነጥቦች
ጥቅምት 09, 2008

ካሳ ሀይሉ ለኢትዮፉትቦል

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገቢውን ለማሳደግ ካቀዳቸው የገቢ ማስገኛ መንገዶች አንዱ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሚሳተፉ የከተማዋ ክለቦች መካከል ውድድር ማካሄድ ነው። ይህን ይትባህሉንም የዘንድሮውን ጨምሮ ለአስር ዓመታት አካሂዷል። የዘንድሮው የሲቲ ካፕ ውድድር በአምበር ቢራ ስም ተሰይሞ እየተካሄደ ሲሆን የፊታችን ሀሙስ ደግሞ ፍጻሜውን ያገኛል። ትናንት ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን አካሂዶም ኢትዮጵያ ቡናን እና ዳሽን ቢራን ለፍጻሜ አድርሷል። ትናንት ከተካሄዱት ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ያካሄዱትን ጨዋታ አንዳንድ ነጥቦች አንስቼ እዳስሳለሁ።

የቡና አሰላለፍ እና ታክቲካል ዲስፕሊን

ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያካሄዱትን ጨዋታ በርካቶች የአሸናፊነት ግምቶችን የሰጡት ለፈረሰኞቹ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ፈረሰኞቹ በፕሪሚየር ሊጉም ሆነ በቻምፒዮንስ ሊጉ ይዘው የሚቀርቡትን ቋሚ ቡድናቸውን ይዘው የገቡ ሲሆን በአንጻሩ ቡናማዎቹ በወጣት የተገነባውንና ልምድ የለውም ተብሎ የሚነገርለትን ቡድናቸውን ይዘው ገብተዋል። ይህ ደግሞ የአሸናፊነቱ ትንበያ ለፈረሰኞቹ እንዲሆን አድርጎታል። ነገር ግን ወጣቶቹ የፖፓዲች ልጆች ልምድ ካላቸው የፈረሰኞቹ ክዋክብት ጋር ያደረጉትን ፍልሚያ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችለዋል።
Ethiopian Coffeee

ቡና አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ያደረገበትን አሰላለፍ እና የጨዋታ ታክቲካል ድስፕሊን ለማየት ስንቃኝ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ቡናማዎቹ በወጣቶች የተገነባውን ቡድናቸውን ልምድ ካላቸው መዑድ መሃመድ፣ ጥላሁን ወልዴ እና ኤሊያስ ማሞ ጋር በማጣመር የገቡ ሲሆን ወጣቶቹ ቡናማዎችም ፈጣን የኳስ ቅብብል እና ከፍተኛ የማሸነፍ ስነ ልቦና ተላብሰው ታይተዋል።

በተለይ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ እየተከላከሉ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የተከተሉት ቡናማዎቹ በዮሴፍ ደሙዬ አማካኝነት የመጀመሪያ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። ይህ ወጣት ተጫዋችም በሲቲ ካፑ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በእያንዳንዱ ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አግቢነቱን ከመከላከያው መሀመድ ናስር እኩል ሆኖ እየመራ ይገኛል።

ከዮሴፍ በተጨማሪም የቡድኑ አባላት በሙሉ በጋራ ሲያጠቁ እና ሲከላከሉ የታዩ ሲሆን ይህም በቡና ውስጥ አዲስ አብዮት የተፈጠረ አስመስሎታል። ክለቡ በርካታ አንጋፋ ተጫዋቾችን ካሰናበተ በኋላ  ቡድኑን በወጣቶች ገንብቷል። ወጣቶቹ ተጫዋቾችም ከአሰልጣኛቸው የተሰጣቸውን አደራ በሚገባ የተወጡበትን ጨዋታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ የፖፓዲች ስራቸውን በሚገባ እነደሚሰሩ ያሳየው ገና ለዋንጫ ማለፋቸውን ሳያውቁ ለዋኝጫ ተፋላሚ ሊሆኗቸው የሚችሉትን የመከላከያና የየዳሽንን ሙሉውን ጨዋታ  ቁጭ ብለው ሲከታተሉና የቡድኖቹን ታክቲክና ቴክኒክ ሲመዘግቡ ተስተውለዋል። በመጨረሻም እንደሀሳባቸው ሆኖላቸው እዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው ለዋንጫ በማለፍ  በርግጥም ብቃት ያላቸው አስልጠኝ መሆናቸውን ያስመሰከሩበት ምሽት ነበር።

የፈረሰኞቹ መነሳት እና ጫና መፍጠር

ፈረሰኞቹ በሩብ ፍጻሜው መከላከያን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወሳል። የአሸናፊነት ግምት ባገኙበት የትናንቱ ጨዋታም ከረፍት በፊት የተለመደውን ጫና ፈጥሮ የመጫወት ልምዳቸውን አላሳዩም ። በአብዛኛው  የቡናን የመልሶ ማጥቃት ወረራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር   የበለጠ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል።  ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የቀረቡት ፈረሰኞቹ በ56ኛው ደቂቃ የቡና ተከላካዮች ኳስ በእጅ በመንካታቸው የተሰጣቸውን ፍጹም ቅጣት ምት በአዳነ ግርማ አማካኝነት አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል።
St.George

ከጎሏ በኋላ ይበልጥ የተጠናከሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጨዋታውን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ያደረጉት ጥረት በቡናው አዲስ ፈራሚ ግብ ጠባቂ አማካኝነት ከሽፎባቸዋል። በመለያ ምትም ማሸነፍ ያልቻሉት በዚሁ ግብ ጠባቂ አማካኝነት ነው ሶስቱን የፍጹም ቅጣት ምቶች ስለመከተባቸው።
St.George Head Coach

ምክትል አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝ  በቀደሙ ጨዋታዎች ላይ የቀጣይ ተጋጣሚ ቡድን ጨዋታን  ለመመልከት ሲፈልግ በዋናው አሰልጣኝ ወደ ካምፕ እንዲሄዱ ሲጠይቁት ታይቷል። ዋናው አሰልጣኝ  የተጋጣሚን አጨዋወት ለማየትና ለመገምገም አለመፈለጋቸው ብዙዎችን ሲያስገርም። በተቃራኒው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ሥራቸውን ሲሰሩ በመታየታቸው አድናቆትን አትርፈዋል።

ለነገ የማይባለው ከባድ የቤት ስራ!

ኢትዮጵያ ቡና ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቡድን ከመገንባቱም በላይ ካምቦሎጆን በድምቀት የሚያስውቡ ደጋፊዎች ባለቤት መሆኑ እሙን ነው። በዚህ የተነሳም ከሶስት ዓመት በፊት በሱዳን እንግሊዛዊው ከበርቴ ሞሃመድ ኢብራሂም ስም በየዓመቱ የሚያዘጋጀው “ሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን” በአዲስ አበባ ዝግጅት ሲያካሂድ በእግር ኳስ ጨዋታ ዝግጅቱን ለማድመቅ ባደረገው ጥያቄ መሰረት የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በኩል የተመረጠው ኢትዮጵያ ቡናን ነበር። ቡና በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎው ቱጃር ክለብ ቲፒ ማዜንቤ ጋር እንዲጫወት የተመረጠው ከላይ በገለጽኩት መመዘኛ በተለይም በደጋፊዎቹ ብዛት እና ውበት እንደሆነ የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ አዲስ ዘመን ከሚባለው መንግስታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር።

ክለቡ እንደዚህ አይነት እጹብ ድንቅ መገለጫዎች ቢኖሩትም ትናንት በተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የቡና ጨዋታ ላይ የታየው የቡና ደጋፊዎች በተለይም የግራ ጥላ ፎቅ ተመልካቾች ያሳዩት ስነ ምግባር ግን ለእግር ኳስ ቤተሰሰቡ ያሳዘነ ነበር። ደጋፊዎቹ ያሳዩት የስነ ምግባር ጉድለት የግለሰቦችን ስም እየጠሩ በተለይ የፈረሰኞቹን አጥቂ አዳነ ግርማን በመጥራት ሲያሰሙት የነበረው ስድብ በእጅጉ አሳዛኝ እና ሊደገም የማይገባው ጸያፍ ድርጊት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በአቶ ክፍሌ አማረ የሚመራው የክለቡ የደጋፊዎች ማህበር አዲሱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ሆነ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና የእነዚህን ደጋፊዎች መረን የሳተ ድርጊት በጋራ ሊያርሙት ይገባል እላለሁ። ምክንያቱም የደጋፊዎቹ ድርጊት ድሮውንም በእንቅርት ላይ የሆነውን እግር ኳሳችንን ከመጉዳቱም በላይ ክለቡን በተለያዩ መንገዶች እንዲጎዳ ደርገዋል። ይህ ድርጊታቸው ካልታረመ ወደ ፊት የሚደገም ከሆነ የክለቡን መልካም ስም በክፉ እንዲነሳ ከማድረጉም በላይ በነጥብ እና በገንዘብም እንዲቀጣ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም ደጋፊዎች ከልባቸው ክልባቸውን የሚወዱ ከሆነ ከትናንቱ ድርጊታቸው ሊታረሙ የሚገባቸው የቤት ስራ ሲሆን የቤት ስራውን ለመስራት ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ መነሳት ይገባቸዋል። ከዚህ በተረፈ ግን በተለይ የሚስማር ተራ ደጋፊዎች ለነበራቸው መልካም ስነ ምግባር ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም።

በተጫዋቾቹም በኩል ከተመልካች ጋር እልህ በመጋባት በምልክት መበሻሸቅን መተው ይገባቸዋል። አዳነ ግርማ ከቡና ተመልካቾች ጋር እልህ በመጋባት አይኖርበትም። በዚህ እረገድ አሉላ ግርማ ትላንት ለቡድኑ ጥሩ በተንቀሳቀሰበት ጨዋት የቡና ደጋፊዎች ስሙን እየጠሩ ቢነቁሩትም በትእግስት ጨዋታው ላይ ብቻ በማተኮር ያሳየው ዲሲፒሊን ለሌሎችም ተጫዋቾች እንደ አርአያነት ሊወሰድ ይገባል። ምክንያቱም ተጨዋቾች ከተመልካች ጋር እንካ ሰላምቲያ ከገቡ ተመልካችን ለአላስፈላጊ የማይገባ ስድብና ጩኽት ስህተት ይዳርጉታል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Gizegeta [787 days ago.]
 ለምን የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ይህን ስድ መረን ጋጠወጥ የሆነ ቡና የተባለ የመንደር ክለብ አስፈላጊውን ቅጣት ለምን እንደማያከናንበው ብቻ ነው ዘወትር የሚገርመን ?!!! ስታዲየሙን የስድብ የድንጋይ የባለጌ መንደር ካደረጉት ቆይተዋል ፌዴሬሽኑ ለምን ይሄን ክለብ መቅጣት እንደሚፈራ ዘወትር የስፖርት ቤተሰቡ ግርምትና የዘውትር ጥያቄ ነው !!!!!!!!!! ሌሎች ክለቦች ይሄን ያደረጉ ቢሆን ፌዴሬሽኑ ወዲያሁኑ እርምጃ ሲወስድ ይታያል:: ቡና የተባለ ክለብ ላይ ግን ምንድነው የሚያስፈራቸው ??????!!!!!!!! ጋጠወጥ ደጋፊ .... ጋጠወጥ ተጫዋች ..... በጋጠወጥ አመራር ..... የተነሳ የስታዲየሙ ሰላም ከደፈረሰ ቆየ !የስንቱ ስፖርት ወዳድ ደም ፈሰሰ ! የስንቱ ክለብ አመራር : ተጫዋች ተሰደበ ተደበደበ ! ኧረ ባካችሁ እነዚህን ጥጋበኛ መረን የቡና ደጋፊዎችን አንድ በሉልን ?!!!!!!!!!!!! አሁን አዳነ ግርማ በነዚህ ስድ ባለጌ ደጋፊዎች ስሙ መጠራት እንዴት ያሳፍራል ያሳዝናል !!!!!!!!!!!!!!!!!!!!! አዳነ ግርማ ማለት እኮ ሃገራችንን ከ 24 አመት በሃላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያሳለፈ ጀግናችን ነው !!!!!!!!!!!!!!!!!

Babi [787 days ago.]
 ከቻላችሁ በየአመቱ ድንጋይ ከምትወረውሩ ከምትሳደቡ ለዋንጫ ተፎካከሩ ስራ ሰርታችሁ ስድብ ድንጋይ ውርወራ አይነፋም !

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!