ሀዋሳ ከነማ በሀዋሳ ሴንትራል ካፕ ድርብርብ ድሎችን ተቀዳጀ
ጥቅምት 09, 2008

በይርጋ አበበ

በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ብቸኛ ስፖንሰርነት የተካሄደው የ2008 ዓ.ም የሀዋሳ ከተማ ሴንትራል ዋንጫ ውድድር ከትናንት በስቲያ በተካሄደ የፍጻሜ ጨዋታ ሀዋሳ ከነማ ድሬዳዋ ከነማን ሶስት ለባዶ በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል። በእለቱ የተካሄደውን ጨዋታ ተጋባዡ ድሬዳዋ ከነማ ካለፉት ቀናት ጨዋታዎቹ በመጠኑ ተዳክመው የታዩበት በአንጻሩ ባለሜዳው ሀዋሳ ከነማ ደግሞ ይበልጥ ተጠናክሮ ነበር የቀረበው። የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባዶ ለባዶ የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች ከእረፍት መልስ ግን ሀዋሳ ከነማ ተቀይሮ በገባው ፍርዳወቅ አዲሱ አማካኝነት ጨዋታውን መቀየር ችሏል። በመሆኑም በእለቱ ኮከብ ሆኖ ባመሸው ታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት የመጀመሪያውን ጎል ማግኘት ችሏል። ታፈሰ ላስቆጠራት ጎል አመቻችቶ ያቀበለው ፍርዳወቅ አዲሱ ነው።

ከጎሏ መገኘት በኋላ ደግሞ ሀዋሳ ከነማ ይበልጥ ተጭኖ በመጫወት ፍርዳወቅ አዲሱ ተጠልፎ በመውደቁ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት አንጋፋው የቡድኑ አምበል ሙሉጌታ ምህረት አስቆጥሯል። ሶስተኛዋን ጎል ደግሞ የውድደሩ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ፍርዳወቅ አዲሱ በማስቆጠር የሀዋሳ ከነማን አሸናፊነት በጊዜ እንዲያረጋግጥ አድርጓል። ፍርዳወቅ አዲሱ ከሀዋሳ ከነማ ታዳጊ ቡድን ጀምሮ ያደገ ወጣት ሲሆን በዚህ ዓመት ነው ዋናውን ቡድን የተቀላቀለው። በዚህ ውድድርም አራት ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።

ኮከብ ተጫዋች
Hawassa Central Hotel Cup

ሀይማኖት ወርቁ ይባላል። እድገቱ እና ትውልዱ ባህር ዳር ሲሆን እግር ኳስን በሳይንሳዊ ደረጃ መማር የጀመረው በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እግር ኳስ አካዳሚ ተምሮ ያለፈ ልጅ ነው። ከአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከነማ እና በጅማ ከነማ ተጫውቶ ያለፈው ወጣቱ ሀይማኖት ወርቁ የሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ወጣቱ ልጅ በመሃል ሜዳው ክፍል ከአንጋፋው ሙሉጌታ ምህረት ጋር በፈጠረው ጥምረት በርካቶች አድናቆታቸውን የቸሩት ሲሆን በውሳኔ አሰጣጡ እና በኳስ ቁጥጥሩ ደግሞ ፍርሃት የሌለበት አማካይ ተጫዋች ነው።

ኮከብ አሰልጣኝ
Webetu Abate Hawassa City Head Coach

ውበቱ አባተ ሲነሳ በበርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ስሙ በይበልጥ ገንኖ የሚወጣው በ2003 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባነሳው የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ነው። ከቡና በኋላ በደደቢት እና በአልሃሊ ሻንዲ ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፎ ወደ ደቡብ ክልል መዲናዋ ሀዋሳ በማምራት ሀዋሳ ከነማን ከውርደት የታደገበት ያለፈው ዓመት የውድድር አጋማሽ ስኬቱም በርካቶች አድናቆታቸውን እንዲሰጡት አድርጓል።

እሁድ አመሻሽ በተጠናቀቀው የሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫ ደግሞ ሀዋሳ ከነማ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱንም ሳይሸነፍ ሶስቱን አሸንፎ አንዱን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ቡድን ገንብቶ ቀርቧል። በፍጻሜውም ድሬዳዋ ከነማን በሰፊ የጎል ልዩነት እና በጨዋታ ብልጫ ጭምር አሸንፎ ዋንጫ ሲያነሳ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ ተመርጧል። በመሆኑም ሀዋሳ ከነማ የውድድሩን ዋንጫ ከማንሳቱም በላይ ኮከብ አሰልጣኝ ተጫዋች እና ጎል አግቢን በማስመረጥ የድርብ ድል ባለቤት ሆኗል። በነገራችን ላይ የፊታችን ጥቅምት 18 ቀን በሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሀዋሳ ከነማ የመጀመሪያዎቹን አራት ጨዋታዎች የሚያካሂደው በሀዋሳ ሴንትራል ሲቲ ካፕ የገጠማቸውን ድሬዳዋ ከነማን፣ አርባ ምንጭ ከነማን እና ሲዳማ ቡናን ነው። የፕሪሚየር ሊጉን ፕሮግራም ቃል በገባነው መሰረት ከነገ ጀምሮ በድረ ገጻችን ይፋ እናደርጋለን።

አዲሱ ታሪክ

ሀዋሳ ሴንትራል ካፕ በዚህ ዓመት በዚህ ስያሜው ከመካሄዱ በፊት ደቡብ ክልል ዋንጫ ተብሎ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱን ይዟል። ካለፉት አራት ዋንጫዎች የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ሀዋሳ ከነማ በዘላለም ሽፈራው አሰልጣኝነት የዋንጫው ባለቤት መሆን የቻለ ሲሆን ተከታዮቹን ሁለት ዋነጫዎች ደግሞ ሲዳማ ቡና በዘላለም ሽፈራው አሰልጣኝነት እየተመራ ዋንጫውን አንስቷል።

የደቡብ ክልልን ዋንጫ ለአራት ዓመታት ሁለት ቡድኖች ብቻ ያነሱ ሲሆን ሁለቱንም ቡድኖች ያሰለጠነው ደግሞ ዘላለም ሽፈራው ነበር። ዘንድሮ ግን ውድድሩ ሌላ አሸናፊ ቡድን ባያገኝም ሌላ አሰልጣኝ ማግኘት ችሏል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
dawit ayele [624 days ago.]
 311411

dawit ayele [624 days ago.]
 311411

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!