ዳሽን ቢራ በታሪኩ የመጀመሪያውን ዋንጫ አነሳ
ሰኔ 23, 2008

በይርጋ አበበ

ለአስረኛ ጊዜ የተካሄደው የ2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አምበር ዋንጫ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ፍጻሜ አግኝቷል። በፍጻሜው የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ዳሽን ቢራ ሲሆኑ ዳሽን ቢራ ተከላካዩ ያሬድ ባዬ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል የእለቱ አሸናፊ ሆኗል። የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ዳሽን ቢራን የልዩ ዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ሲያበረክትለት ኢትዮጵያ ቡናን ደግሞ የብር ሜዳሊያ እና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተሸላሚ አድርጎታል። በእለቱ ኮከብ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የተሸለሙ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡናው ተስፈኛ ወጣት ዮሴፍ ደሙዬ ኮከብ ተጫዋች እና ባስቆጠራቸው አራት ጎሎች ደግሞ ከመከላከያው መሃመድ ናስር ጋር በጣምራ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ በድጋሚ ተመርጧል። የኮከብ አሰልጣኝነቱን አሸናፊነት የወሰደው የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ነው። በእለቱ የተካሄዱ አብይ ክስተቶችን እና የተሰጡ አስተያየቶችን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል።

የዳሽን ከፍታ

ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ በአሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ እየተመራ ባካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አምስት ጨዋታዎችን አካሂዶ አንዱንም ሳይሸነፍ በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል። ቡድኑም በታሪኩ የመጀመሪያ የሆነውን ዋንጫ ማንሳት ችሏል። ቡድኑ የመክፈቻ ጨዋታውን ከመብራት ሀይል ጋር በአቻ ውጤት አጠናቅቆ ደደቢትን ደግሞ አሸንፎ እና ከቡና ጋር በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ወደ ግማሽ ፍጻሜ መሸጋገር የቻለ ሲሆን በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ የጥሎ ማለፉን አሸናፊ መከላከያን ሁለት ለአንድ ማሸነፍ ችሏል። በፍጻሜውም ትናንት ምሽት ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለባዶ በማሸነፍ የልዩ ዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። ዳሽን ቢራ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጎሎች ብቻ ተቆጥረውበት እና ስድስት ጎሎችን አስቆጥሮ ያጠናቀቀ ሲሆን ይህም የቡድኑ ጥንካሬ የተከላካይ መስመሩ እንደሆነ አመላካች ነው።

ከጨዋታው በኋላ በተለይ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም አስተያየቱን የሰጠው የዳሽን ቢራው አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ “ቡናዎች ጥሩ ነበሩ ሆኖም እኛ የአጨዋወት ታክቲካል ዲሲፕሊን አክብረን በመጫወታችን ነው ያሸነፍነው” ሲል የተናገረ ሲሆን አያይዞም “የአጥቂ መስመራችን የጠበቅነውን ያህል ባይሆንም በተከላካይ መስመራችን ጥንካሬ እና በጨዋታ ታክቲካል ዲስፕሊን የተሻልን ነበር” ሲል ተናግሯል።

የተገፋው ዮሴፍ ለቡና መዳን ሆነ

በ2007 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በብራዚላዊው አሰልጣኝ ዶ ሳንቶስ እየተመራ የነሃስ ሜዳሊያ ሲያገኝ ክለቡ ለተመልካች ካስተዋወቃቸው ተጫዋቾች መካከል ዮሴፍ ደሙዬ አንዱ ነበር። ዮሴፍ በወቅቱ 10 ቁጥር ማሊያ ለብሶ በክንፍ መስመር እና ከአጥቂ ጀርባ ተሰልፎ ሲጫወት ያሳይ የነበረው ብቃት በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች አድናቆትን ያሰጠው ነበር። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን ፈረሰኞቹ እና ዮሴፍ ደሙዬ መለያየታቸው ተሰማ። የልጁ ማረፊያም ንግድ ባንክ መሆኑ ተነገረ።

በፈረሰኞቹ የተገፋውና በንግድ ባንክም እንደ ባከነ ንብረት ተቆጥሮ ለሁለተኛ ጊዜ የተገፋው የጭርቆስ ሰፈሩ ልጅ ዮሴፍ ደሙዬ ማረፊያውን ኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን አደረገ። በቡና ማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ ደረጃ መጫወት የጀመረው ትናንት በተጠናቀቀው ሲቲ ካፕ ላይ ሲሆን በዚሁ ውድድርም በአምስት ጨዋታዎች አራት ጎሎችን በማስቆጠር እንደገና ከእግር ኳስ አፍቃሪው ቤተሰብ ጋር በድጋሚ መገናኘት ቻለ። ቡና በውድድሩ ካስቆጠራቸው አምስት ጎሎች አራቱን ብቻውን በማስቆጠር በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የቡና ታዳጊ መሆኑን አስመስክሯል። በሁለቱ ክለቦች የተገፋው ዮሴፍ ደሙዬም ከአዲሱ ክለቡ ጋር ስኬታማ ጅማሮ እያደረገ ይገኛል። ከጨዋታው በኋላም ለጋዜጠኞች በሰጠው አስተያየት “የቡና ደጋፊዎችን አመሰግናለሁ። አዲሱ አሰልጣኝም ለሰጡኝ የመሰለፍ እድል እና እምነት አመሰግናለሁ። ይህንን ብቃቴን ጠብቄ ለክለቡ ጥሩ ነገር ለመስራት ጠንክሬ እሰራለሁ” ሲል ተናግሯል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!