አባይ ፈርጦቹ ከማበረታቻው ሽልማት ማግስት
ጥቅምት 14, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወይም የአባይ ፈርጦቹ ከፌዴሬሽኑ በተደረገላቸው የማበረታቻ ሽልማት ማግስት አበረታች ውጤት አስመዘገቡ። በአሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመሩት ታዳጊዎቹ ትናንት ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከጋና አቻዎቻቸው ጋር ተጫውተው ያስመዘገቡት ውጤት የተጫዋቾቹን ስነ ልቦናዊ ዝግጁነት እና ወደፊት ተስፋ ያላቸው መሆናቸውን ያስመሰከረ ነው ማለት ይቻላል።

ከአፍሪካ እጅግ ጠንካራ የሆነውንና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያለውን የጋናን ብሔራዊ ቡድን ያስተናገደው ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታው እንደተጀመረ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠራት ጎል መመራት የጀመረ ቢሆንም ጎሏ አሉታዊ ተጽእኖ ሳትፈጥርበት ከኋላ ተነስቶ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር መምራት ችሎ ነበር። ይህም ቡድኑ በራስ መተማመንን እያዳበረ መሆኑን እና የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ እያገኘ መምጣቱን አመላካች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በጫና ውስጥ ሆኖ መጫወትን መቋቋም እያቻሉ መሄዳቸውን ያሳያል። እስከ ጨዋታው የመጠናቀቂያ ሰዓት ድረስም መምራት ችሎ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም በግብ ጠባቂዋ ስህተት ጋናዎች ነጥብ የተጋሩባትን ጎል አስቆጥረዋል።
የኣባይ ፈርጦቹ ትናንት በተደረገው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው የወጡት በራሳቸው ስህተት እንደነበረም ታይቷል። በ2016 ወደባማዋ እና በአውስትራሊያ አህጉር ተወሽቃ የምትገኘዋ ፓፓዋ ኒው ጊኒ የምትባለዋ ወደብ መሰል አገር የምታስተናግደውን የታዳጊዎች የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የትናንቱ የማጣሪያ ጨዋታ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድናችን በሰራቸው ሁለት ስህተቶች የጋናን ብሔራዊ ቡድን አንድ ነጥብ መርቀው ሸኝቶታል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከ15 ቀናት በኋላ በጋና ርዕሰ መዲና አክራ የሚካሄድ ሲሆን በደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሆነ ወይም ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው የፊፋ ህግ ተጠቃሚ የሆነ ቡድን ወደ ፓፓዋ ኒው ጊኒ የሚወስደውን ቲኬት የሚቆርጥ ይሆናል። ለመልሱ ጨዋታም የአስራት አባተ ልጆች ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ይታመናል።

ታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ በአካል ብቃት እና ጎሎችን በማስቆጠር በኩል ድክመት የታየበት ሲሆን እስካሁን ባደረጋቸው አምስት የማጣሪያ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን አስቆጥሮ ሶስት ጎሎች ብቻ የተቆጠሩበት ቢሆንም ያስቆጠራቸውን ሁሉንም ጎሎች ያገኘው ከአንዲት ተጫዋች ብቻ መሆኑ ቡድኑ በአጥቂ መስመሩ ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ያመለክታል። አምበሏ ሎዛ አበራ በሶስት ብሔራዊ ቡድኖች በእያንዳንዳቸው መረብ ላይ ሁለት ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ታሪክ የሰራች ቢሆንም የሎዛን ጫና የሚያቀልላትና ጎል በማስቆጠር የሚያግዛት ተጫዋች ግን ያስፈልጋታል። አሰልጣኝ አስራት አባተም ሆነ ምክትል አሰልጣኟ ለዚህ ቦታ በቂ ተጠባባቂዎችንና አማራጮችን መያዝ የሚገባቸው መሆኑን የትናንቱ ጨዋታ በተለየ መልኩ አሳይቷቸዋል ብለን እናምናለን። ምክንያቱም በትናንቱም ሆነ ከሳምንት በፊት ከቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድን ጋር በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች እንደታየው ብሔራዊ ቡድኑ በሎዛ አበራ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑን አስመስክሯል። 

ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑ ችግር ሆኖ የታየው ደግሞ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት የሚወሰድበት መሆኑ ነው። ባህር ዳር ላይ ከካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ጋርም ሆነ አዲስ አበባ ላይ ከጋና እና ከቡርኪናፋሲ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች እንደተመለከትነው ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይወሰድበታል። ይህ ደግሞ የቡድኑን ህብረት እና ጥንካሬ የሚፈታተነው ይሆናል። በእነዚህ ሁለት ድክመቶቹ ላይ መዘጋጀት ከቻለም ወደ ዓለም ዋንጫው የሚያደርገው ጉዞ የሰመረ እንደሚሆንለት ይታመናል። ለመልሱ ጨዋታም የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ኤዲቶሪያል በአንባቢያን ስም መልካም እድል ተመኝቷል።ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!