ዋልያዎቹ ከብሩንዲ፦ ለኪጋሊ ጉዞ የተደረገ የመጨረሻ ምዕራፍ
ጥቅምት 15, 2008

በይርጋ አበበ

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂደውና በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ወይም ቻን ዋንጫ ከተጀመረ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ይካሄዳል። የዘንድሮው ውድድርም አራተኛው ውድድር ሲሆን የፊታችን የካቲት አጋማሽ ላይ የፖል ካጋሚ ሀገር ሩዋንዳ ታስተናግደዋለች። ለዚህ ዋንጫ ለማለፍ ከኬኒያ እና ከብሩንዲ አቻው ጋር የማጣሪያ ጨዋታ ያካሄደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትናንት ማምሻውን የብሩንዲ አቻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናግዶ ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ጋር ሶስት ለባዶ በማሸነፍ ወደ ኪጋሊ የሚያደርገው ጉዞ አሳክቷል። ዋልያዎቹ ለኪጋሊው ጉዞ ባደረጋቸው አራት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ አንድም ጎል ያላስቆጠረ ሲሆን በአጠቃላይ በማጣሪያው አንድ ተሸንፎ አንድ ኣቻ ወጥቶ ሁለቱን አሸንፏል። ቡድኑ ትናንት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ያካሄደውን ጨዋታ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ሶስት ለባዶ ቢያሸንፍም ከሳምንት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ቡጁንቡራ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸው ብሩንዲዎች ሁለት ለባዶ አሸንፈው ስለነበረ የመልሱን ጨዋታ ለዋልያዎቹ ፈታኝ አድርጎባቸው ነበር። ሆኖም “አዲስ አበባ ላይ በማሸነፍ ወደ ኪጋሊ የምናደርገውን ጉዞ እናሳካለን። ከኪጋሊ የሚያስቀረን የራሳችን ስህተት ብቻ ነው” ሲል አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡጁንቡራ ለተገኙ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር። የዋልያዎቹና የብሩንዲ የትናንት ምሽቱ ጨዋታ ምን መልክ ነበረው? ማንስ ኮከብ ሆኖ አመሸ? አሰልጣኙስ ከጨዋታው በኋላ ምን አሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ከዚህ በታች እንመለከታቸዋለን።

በጊዜ መልስ ያገኘው የአማካይ አጥቂው ክፍል

“የአማካይ አጥቂ ችግር አለብን ከቡጁንቡራ ስንመለስ የቡናውን ኤሊያስ ማሞን እጠራዋለሁ” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድኑን ወደ ቡጁንቡራ ይዞ ሲሄድ ለጋዜጠኞች ተናገረ የተባለው ሃሳብ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በየቦታው ቀዳዳ ያለበት ቡድን ሲሆን በተለይ የአጥቂ እና የግብ ጠባቂ ችግር እስከ ምጽአት ድረስም የሚፈታ አይመስልም ይባላል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ብሄራዊ ቡድኑ በአማካይ አጥቂ መስመር ላይ ተሰልፎ ለጎል አምካኝ አጥቂዎቹ በቂ ኳሶችን የሚያደርስ ወይም ራሱ ወደ ጎል በመሞከር ውጤት ሊቀይር የሚችል የአማካይ አጥቂ ተጫዋች ችግርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየታየበት መጥቷል።

ቡድኑ ለዓመታት የተጠቀመበት ሽመልስ በቀለን ብቻ ሲሆን ሽመልስ ደግሞ በቻን ዋንጫ የመወዳደር እድል ፈንታ የለውም። በዚህ የተነሳም ኳሶችን በሚሊ ሜትር እየለካ ለአጥቂዎች የሚያቀብል ተጫዋች የቸገረው ዮሃንስ ሳህሌ አይኑን ያሳረፈው የመከላከያው ፍሬው ሰለሞን እና በቡናው ኤልያስ ማሞ ላይ ሆነ። የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ አማካይ ጥበበኛው ፍሬው ሰለሞንም ሆነ የቀድሞው ፈረሰኛ ኤልያስ ማሞ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብሔራዊ  ቡድን ማሊያ የመታየት እድላቸው የጠበባቸው ተጫዋቾች ሆነዋል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለበርካታ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን የመጫወት እድል ያልተፈጠረለትን ኤልያስ ማሞን ወደ ቡድኑ በመጥራትም በትናንቱ ትልቅ ሀገራዊ ግዳጅ ላይ የጦሩን መሪነት ሚና አሸክሞ ወደ ሜዳ ላከው። የኳስ አርቲስቱ ኤልያስ ማሞ ግን አሰልጣኙ የጣለበትን እምነትም ሆነ ሀገሩ የሰጠችውን አደራ ሳይበላ በታማኝነት መወጣት ችሏል። በእለቱ ብሔራዊ ቡድኑ ላስቆጠራቸው ሶስት ጎሎችም ቀጥተኛ ሚና የተጫወተ ነበር። የቀድሞው የፈረሰኞቹ ወጣት ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት ያሻገራቸው የተመጠኑ ኳሶች የአምበሉን ስዩም ተስፋዬንም ሆነ የአማካይ ተከላካዩን ጋቶች ፓኖምን ግምባሮች እየለተሙ መረብ ላይ እንዲያርፉ አመቻችቶ ያቀበለ ሲሆን አስቻለው ግርማ ተጠልፎ በመውደቁ ለተሰጠው ፍጹም ቅጣት ምትም ኳሷን አሽሞንሙኖ ያቀበለው ይሄው የቡናዎቹ አማካይ አጥቂ ኤልያስ ማሞ ነው። ኤልያስ ማሞ በትናንት ብቃቱ የዋልያዎቹን የቆየ ጥያቄ መልስ የሰጠ ከመሆኑም በላይ በእለቱ ኮከብ ሆኖ አምሽቷል።

የበርሊን ግንብ

ከወራት በፊት ከኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ የነበረው ዋሊድ አታ አስቻለው ታመነን እና ሳላዲን ባርጌቾን በተመለከተ ከጋዜጠኛው ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “ሁለቱም በጣም ምርጥ ተከላካዮች ናቸው። ወደፊት አብረው በተጫወቱ ቁጥር ይበልጥ እየተዋሃዱ እና እየተናበቡ ሲሄዱ ጠንካራ ጥምረት ይፈጥራሉ” ብሎ ነበር። ትናንት ምሽት አብረው የተሰለፉት ሁለቱ ፈረሰኞች ያሳዩት ጥምረትም ሆነ ብቃት እጅግ የተዋጣለት ሆኖ ታይቷል። ጥምረታቸውም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የታየ የመጀመሪያው ጠንካራ የተከላካይ መስመር ውህደት ያስብለዋል ቢባል ማጋነን አይመስለንም። የሁለቱን ጥምረት ድጋፍ የሰጡት አንጋፋው ስዩም ተስፋዬ እና ወጣቱ ነጂብ ሳኒ ለተከላካይ መሰመሩ የሰጡት ሽፋን እጅግ መልካም የሚባል ነበር። ለዚህም የትናንትናውን የተከላካይ ክፍል ጥምረት እና ውህደት የበርሊን ግንብ ብለነዋል። ቡድኑ ሶስት ጎሎችን አስቆጥሮ እንዲያሸንፍ ያስቻለው የተከላካይ መሰመሩ ጥንካሬ ነው ማለት ይቻላል። የመጀመሪያውን ጎል ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ ከማስቆጠሩም በላይ አማካይ ተከላካዩ ጋቶች ፓኖም ጎሎችን እንዲያስቆጥር በተከላካይ ክፍሉ ላይ እምነቱን ጥሎ ወደ ፊት በመሄዱ ነው።

መልስ ያልተገኘለት አጥቂ

ሀገሪቱ ውስጥ ጨራሽ አጥቂ የለም ሲል ቅሬታውን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር የሚሰማው ዮሃንስ ሳህሌ ቡድኑን በጠንካራ አጥቂ ለመገንባት የተለያዩ አማራጮችን ሲሞክር ታይቷል። ለአብነት ያህልም ከአንጋፋው ቢኒያም አሰፋ እስከ ወጣቱ ባዬ ገዛኸኝ ድረስ ያሉ አጥቂዎችን ለሙከራ የጠራ ሲሆን አሁን ደግሞ የደደቢቱን ዳዊት ፈቃዱ እና የመከላከያውን መሃመድ ናስርን ጥሪ ያቀረበላቸው የቅርብ ጊዜያት አጥቂዎች ናቸው። ዳዊት ፈቃዱ በደረሰበት ጉዳት ከሜዳ ውጭ ሲሆን መሃመድ ናስር ግን ትናንት ተሰልፎ መጫወት ችሏል። ለ45 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ በቆየበት ጊዜ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችልም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ሜዳ እንዳይገባ ተደርጓል። ለምን እንደቀየረው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር “ቡድኑን የተቀላቀለው በቅርቡ በመሆኑ ከአማካይ ክፍሉም ሆነ ከአጥቂዎች ጋር በቀላሉ መዋሃድ አልቻለም። እስከ እረፍት ሜዳ ላይ በቆየባቸው ጊዜያትም የነበረው ሚና አነስተኛ በመሆኑ ነው ልቀይረው የተገደድኩት” ብሏል።

ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ኳስ [782 days ago.]
 ይርጋ ስለተከላካዮቹ ሃላፊነት መወጣት ያቀረብከው ጽሁፍ ጥሩ ነው ጥሩ ምልከታ ነው።

ኳስ [782 days ago.]
 ይርጋ ስለተከላካዮቹ ሃላፊነት መወጣት ያቀረብከው ጽሁፍ ጥሩ ነው ጥሩ ምልከታ ነው።

leul hagos [782 days ago.]
 Iam very happy because walya fc has passed. this is the result of the team & yohannes haile congra to ethiopians.we expect to win the in kigali

Gezegeta [781 days ago.]
 ኧረ ኢትዮ ፉትቦል የሰራችሁት ዘገባ ፌር አይደለም ያሸነፍነው ካሜሮንን ወይም ሞሮኮን ነው ያስመሰላች ሁት. ኧረ ተረጋጉ ኧረ ፍሬኑን ያዙት ለሙገሳው በጣም ነው የቸኮላችሁት ደካማዋን ቡርንዲን ያውም በሜዳችን አሸንፈን ኧረ ይደብራል እስቲ እናያችሁ የለ እንዴ ከአልጄሪያና ከኮንጎ ጋር ከተጫወትን በሃላ ምን እንደምትሉ ! ይሄ አምባገነን አሰልጣኝ ነኝ ተብዬ በዚህ ግትር አቋሙ ብሔራዊ ቡድናችንን ያዋርደዋል ያሰድበዋል በጣም የማዝነው ብሔራዊ ቡድኑን መጥቀም የሚችሉ ስንት ጀግና ተጫዋቾችን መምረጥ እየቻለ የራሱን ቡድን ሰራ ለመባል ስለሚፈልግ ብቻ ልጆቹን ገፋቸው ሃገራችንንም በትንንሽ ቡድኖች ሳይቀር አስደፈረን በጣም የማዝነው አንተን እዚህ ቦታ ላይ አስቀምጦ ያለቦታህ ያላቅምህ ስራ ለሰጠህ ፌዴሬሽን ነው. ቆይ ኮንጎ እና አልጄሪያ ላይ እናይሻለን እኮ ! በቡሩንዲ 2 ለ 0 ቡጁምቡራ ላይ ስትቀምሺ የውሃ ፕላስቲኮችን ስትወረውሪ ከቡሩንዲው ኮች ጋር ድብድብ ካልገጠምኩ ስትዪ ነበር....... ቆይ እናይሻለን እኮ ኮንጎ እና አልጄሪያ ላይ ምን እንደምትሰሪ ?! ምን እንደምትወረውሪ ?! ለሽንፈትሽም ምን ምክንያት እንደምትደረድሪ ???!!!

getachew gamo [780 days ago.]
 hi dear ato gizegeta pls list out who they are not selected by yohannes? and what was the major problem and weakness of last sundays team of the coach? for me ethiofootball.com editors are right to say zat.

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!