የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵ ፕሪሚየር ሊግ ይዘት ምን ሊሆን ይችላል? ክፍል አንድ
ጥቅምት 17, 2008

በይርጋ አበበ

ክፍል አንድ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2008 ዓ.ም ውድድር ዛሬ በይፋ ይጀመራል። ሊጉ 14 ክለቦችን የሚያሳትፍ ሲሆን በዘንድሮው ሲዝንም አብዛኛውን ቁጥር የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች ሲቆጣጠሩት የደቡብ ክልል ደግሞ አምስት ክለቦችን በማሳተፍ ይከተላል። ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ አማራ ክልል እና ኦሮሚያ ክልል አንድ አንድ ክለቦችን ያሳትፋሉ። ሌላው ክስተት የክለቦቹ ባለቤቶች ጉዳይ ነው። በሊጉ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል አምስቱ  ማለትም ድሬዳዋ፣ አርባ ምንጭ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ እና ሀላባ ከነማ የከተማ አስተዳደር ወይም የማዘጋጃ ቤት ክለቦች ናቸው። ሊጉ ዛሬ ሲጀመር እስከ ዓመቱ መጨረሻ ለእግር ኳስ ተመልካችም ሆነ ለእግር ኳሱ ምን አይነት ክስተቶችን ይዞ ይቀርባል? በውድድሩስ እነማን ይሳካላቸዋል እነማንስ ወደ ታች ይወርዳሉ? ኮከብ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ማን ይሆናል? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን ከዚህ በታች ሙያዊ በሆነ መልኩ እንዳስሳቸዋለን። አብራችሁን ቆዩ!!

ብዙ ማይል የሚያቋርጠው ዳሽን

በኢትዮጵያ ትልቁ ተራራ ራስ ዳሽን ተራራ ሲሆን ከፍታውም ከባህር ጠለል በላይ ከ4250 ሜትር በላይ ይደርሳል። በዚህ ተራራ ግርጌ ላይ የተቋቋመው በክልሉ ብቸኛ የሆነው የቢራ ፋብሪካም ለህብረተሰቡ እየሰጠ ካለው የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች አንዱ ፋብሪካውን የሚያስተዋውቅለትን የእግር ኳስ ክለብ ማቋቋም ነው። በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት ወደ ውድድር የሚገባው ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ መገኛው በአገሪቱ ግዙፍ ተራራ ግርጌ እንደመሆኑ መጠን በፕሪሚየር ሊጉም እጅግ በጣም በርካታ ርቀቶችን አቋርጦ የሚወዳደር ክለብ ያደርገዋል። ክለቡ 13 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ከጎንደርም ሆነ ከአማራ ክልል በመውጣት የሚጫወት ሲሆን ስድስት ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ይጫወታል። ይህም ማለት 763 ኪሎ ሜትር ከአገሪቱ ርዕሰ መዲና ከምትርቀው ጎንደር በመነሳት ስድስት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ በድምሩ ከ4570 ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም ድሬዳዋ ድረስ ይጓዝና ድሬዳዋ ከነማን ይገጥማል። ወደ ሀዋሳ፣ ሆሳዕና፣ ይርጋዓለም፣ ወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ ከተማ ድረስ ይጓዛል። ወደ አዳማ ተጉዞም ከአዳማ ከነማ ጋር የሚጫወት ይሆናል። ይህ ሁሉ ጉዞውም በድምሩ ከስድስት ሺህ በላይ ኪሎሜትሮችን የሚጓዝ ክለብ ያደርገዋል።
 
ክብሩን ለማስጠበቅ የሚጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዘንድሮ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የውድድር ዓመቱን የጀመረው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋነጫን በማንሳት እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ደግሞ በዘወትር ተቀናቃኙ ኢትዮጵያ ቡና በመሸነፍ ነው። ፈረሰኞቹ በዚህ የውድድር ዓመት ያለፈውን ዓመት የሊጉን አሸናፊነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ እንደሚጫወቱ ይጠበቃል። ለዚህ ሀሳብ ማጠንከሪያ የመሆነው ደግሞ ክለቡ በዚህ ዓመት የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸው ተጫዋቾችን ስንመለከት ነው። ፈረሰኞቹ በደጉ ደበበ እና አይዛክ ኡሴንዴ የሚመራ እና ለዓመታት የማይደፈር የተከላካይ መስመር ገንብቶ ቆይቷል። ከዚህ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ወጣቱን ሳላዲን ባርጌቾን ከመድን ላይ በማስፈረም የተከላካይ ክፍሉን ይበልጥ ጠንካራ አድርገውት ቆይተዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ የተከላካይ መስመሩን ይበልጥ ለማጠንከር በብሔራዊ ቡድን ከሳላዲን ጋር ጠንካራ ጥምረት የፈጠረውን የደደቢቱን አስቻለው ታመነን አስፈርመውታል።
የአስቻለው፣ ሳላዲን፣ ቢያድግልኝ፣ ደጉ እና አይዛክ ኡሴንዴን ጠንካራ የመሃል ተከላካይ ክፍል እንዲያጠናክርለት ደግሞ የቀድሞውን ተጫዋቹን አበባው ቡጣቆን ከሱዳኑ ክለብ ላይ አስፈርመውታል። የአጥቂውን ክፍል ለማጠናከር ደግሞ የኤሌክትሪኩን ራምኬል ሎክን ያስፈረሙ ሲሆን ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩት ደግሞ ልምድ ያላቸው ማርቲን ኩፕማን ናቸው። ይህ ሁሉ አዲስ ፊት እና የቀድሞዎቹ ኮከቦች ምንያህል፣ ተሾመ፣ ናትናኤል፣ ተስፋዬ፣ ሳላዲን ባርጌቾ እና አንዳርጋቸው ይላቅ ውላቸውን ማደሳቸው ቡድኑ የውድድር ዓመቱን ከሊጉ ዋንጫ ክብር ጋር ለማጠናቀቅ ቆርጦ የተነሳ አስመስሎታል።

ሀዋሳ ከነማ እንደገና ወደ ዋንጫው ለመመለስ የተዘጋጀ ክለብ

ባለፈው የውድድር ዓመት ዝብርቅርቅ ባለ ስሜት ተሞልቶ የውድድር ዓመቱን ያጠናቀቀው የደቡብ ክልል ዋና ከተማው ክለብ ሀዋሳ ከነማ በዚህ ዓመት ግን በሊጉ ለዋንጫ ፉክክር ከሚያደርጉ ሶስት ወይም አራት ክለቦች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። አስቻለው ግርማን እና ሀይማኖት ወርቁን በአማካይ መሰመር ያስፈረመው የውበቱ አባተ ቡድን ታፈሰ ሰለሞንን ደግሞ በሊጉ እጅግ ከፍተኛ ተከፋይ በማድረግ ውሉን እንዲያድስ አድርጎታል። አንጋፋውን የመሃል ሜዳ ሞተር ሙሉጌታ ምህረት ውሉን አድሶ ለቡድኑ ወጣቶች ልምዱን እንዲያካፍል ያደረገ ሲሆን ግርማ በቀለ እና አዲስ አለም ተስፋዬ ደግሞ ሌሎቹ ውላቸውን ካደሱት ተጫዋቾች መካከል ናቸው። ካለፈው ዓመት ቡድን ላይ አብዛኞቹ ውላቸው የተጠናቀቀ ቢሆንም ውላቸው እንዲታደስ ያደረገው ሀዋሳ ከነማ በግብ ጠባቂ በኩል ያለውን የሚያፈስ ቀዳዳ ለመድፈን ከደቡብ አፍሪካ በወር ሶስት ሺህ ዶላር እየከፈለ የሚያጫውተውን ግብ ጠባቂ አስፈርሟል። ሁለት ሜትር ሊሞላ ስምንት ንዑስ ሜትሮች ብቻ የጎደሉት ግዙፉ ደቡብ አፍሪካዊ የዙሉ ግዛት ተወላጅ በዚህ ዓመት ለሀዋሳ ከነማ ጥንካሬ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው የሀዋሳ ከነማ ለድሉ እንዲገመት ያደረገው በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንታት የሚያደርጋቸውን አራት ጨዋታዎች ስንመለከት ነው። ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ አራት የሊጉ ጨዋታዎቹ የሚጫወተው በቅርቡ በተጠናቀቀው የሀዋሳ ሴንትራል ካፕ ተሳትፎ በውድድሩ ከገጠማቸው ክለቦች ጋር በድጋሚ በመገናኘት ነው። ይህም ማለት በሀዋሳ ሴንትራል ካፕ በግማሽ ፍጻሜ ያሸነፈውን ሲዳማ ቡናን  በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ማለትም ነገ ይገጥምና በሴንትራል ካፕ ፍጻሜ ያሸነፈውን ድሬዳዋ ከነማንም በሁለተኛው ሳምንት የሚያገኘው ይሆናል። በዚሁ ሴንትራል ካፕ በምድብ ጨዋታው ያገኛቸውን ወላይታ ድቻን እና ሆሳዕና ከነማንም የሚያገኘው በመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንታት ጨዋታዎቹ ነው። ከእነዚህ ክለቦች ጋር በቅርብ ጊዜ ልዩነት መገናኘቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው አሰልጣኝ ውበቱ አባተም እምነቱን ገልጿል። በእነዚህ አራት ጨዋታዎች የተጠበቀውን ያህል ውጤት መሰብሰብ ከቻለ ቡድኑን ለዋንጫ እንዲጠበቅ ያደርገዋል። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሀዋሳ ከነማ ደስተኛ መሆኑ እና ተረጋግቶ መስራቱም ለክለቡ ጥንካሬ ይሆነዋል።

ከአዲስ አሰልጣኝ ጋር በአዳዲስ ተጫዋቾች የቀረበው ቡና

አሰልጣኝ ድራገን ፖፓዲች በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ይዘውት የቀረቡት ቡድን እና ለዝግጅት ሀዋሳ በነበሩበት ጊዜ የተመለከትነው ቡድን በአሰልጣኙ ከባድ ስልጠና በተቸገሩ ተጫዋቾች የተሞላ መሆኑን ነው። አንዳንዶች የአሰልጣኙ ስልጠና ከባድ ነው እያሉ ቢተቹም እንደ ዮሴፍ ደሙዬ እና እያሱ ታምሩ አይነት ወጣት ተጫዋቾች እና ጋቶች ፓኖም አይነት ልምድ ያላቸው ኮከቦች በስልጠናው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ሶስት ተጫዋቾች በተለየ ደግሞ የኳስ አርቲስቱ ኤልያስ ማሞ እና ለወጣት ተጫዋቾች አርዓያ ይሆናል የሚባለው አመለ ሸጋው መስዑድ መሀመድ በአሰልጣኙ አሰለጣጠን የተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተለይ ኤልያስ ማሞ ባለፈው ዓመት ከነበረው የክብደት መጨመር ጋር ተያይዞ የተጠበቀውን ያህል ብቃቱን ማሳየት አለመቻሉ ያስተቸው ቢሆንም በዚህ ዓመት ግን ከአሰልጣኝ ፖፓዲች ጋር መስራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአካል ብቃቱ የተሻሻለ ከመሆኑም በላይ ክብደቱንም በመቀነስ በብሔራዊ ቡድንም የተዋጣለት እንቅስቃሴ ማድረግ አስችሎታል።

በዚህ ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በእንደዚህ አይነት ስልጠና የተዋቀረ ቡድን ይዞ የቀረበው ኢትዮጵያ ቡና አሁንም ለዋንጫው የሚፎካከር ክለብ ነው ማለት ይቻላል። ክለቡ በአጥቂ መስመሩ ላይ ያለውን ክፍተት ማረም ባይችልም በወጣቶች የተዋቀረው የቡድኑ አማካይ እና ተከላካይ ክፍል የጥንካሬው ምንጮች ሲሆኑ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የቡድኑ የጥንካሬ ምንጭ የሚሆነው የግብ ጠባቂው ክፍል ነው። ከዓሊ ረዲ በኋላ የጎሉን መስመር በንቃትና በብቃት የሚጠብቅለት ግብ ጠባቂ በማጣቱ ሲሰቃይ የኖረው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ዓመት ከቤኒን ያስፈረመው ግዙፉ ሞሰን ኩርሶ የተባለው ግብ ጠባቂው ነው። ግብ ጠባቂው በሲቲ ካፑ ያሳየው ብቃትም ሆነ በልምምድ ሜዳ ላይ የሚያሳየው ታክቲካል ዲስፕሊን በዚህ ዓመት ቡና ጥሩ ውጤት ያስመዘግባል ተብሎ እንዲጠበቅ ያደርገዋል።

ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!