የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵ ፕሪሚየር ሊግ ይዘት ምን ሊሆን ይችላል? ክፍል ሁለት
ጥቅምት 18, 2008

በይርጋ አበበ

ክፍል ሁለት

አዳዲስ ኮከቦች የሚታዩበት የውድድር ዓመት?

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በየዓመቱ ከክለብ ክለብ እየተዘዋወሩ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ተለይቶ ይታወቃል ቢባል ከእውነታው መራቅ አይሆንም። በዚህ የተነሳም ሊጉ አዲስ ተጫዋቾችን ከማሳየት ይልቅ በየጊዜው በአዲስ ክለብ ማሊያ የሚቀርቡ ታዋቂ ተጫዋቾችን ብቻ ሲያሳይ ቆይቷል። በዚህ የውድድር ዓመት ግን ሊጉ አዳዲስ እና ወጣት ተጫዋቾች የሚደምቁበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በደደቢት ማሊያ እየጎመራ ያለው ተካልኝ ደጀኔ ከሚጠበቁት አንዱ ሲሆን የመከላከያዎቹ ምንይሉ ወንድሙ እና ነጂብ ሳኒ በዚህ የውድድር ዓመት ብቃታቸውን አውጥተው ያሳያሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ይመደባሉ። ሁለቱ ወጣቶች ባለፈው የውድድር ዓመትም ሆነ በዚህ ዓመት በጥሎ ማለፉ ዋንጫ እና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ያሳዩት ብቃት ዓመቱን በከፍተኛ ብቃት ያሳልፋሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል እንዲመደቡ ያደርጋቸዋል። ከወዲሁም ለብሔራዊ ቡድን እንዲጫወቱ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ፈረሰኞቹ አዲስ ያስፈረሟቸው አስቻለው ታመነ እና ራምኬል ሎክ ባለፈው ዓመት ምርጥ ብቃቱን ካሳየው ዘካሪያስ ቱጂ እና ናትናኤል ዘለቀ ጋር ተጣምረው ክለባቸውን ወደ ድል ያመራሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ሲሆን አራቱ ወጣት ተጫዋቾችም በግላቸው የውድድር ዓመቱን በስኬት ያጠናቅቃሉ ተብለው ይጠበቃሉ። ሳላዲን ባርጌቾ አሁንም ከፈረሰኞቹ በውድድር ዓመቱ ደምቀው ከሚታዩ ተጫዋቾች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው አዳማ ከነማ ከታዳጊነቱ ጀምሮ ያሳደገውን ታከለ ዓለማየሁን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በክለቡ የሚያቆየውን ኮንትራት አስፈርሞታል። ታከለ ዓለማየሁም በዚህ የውድድር ዓመት ለእግር ኳስ ተመልካቹ ምርጥ ብቃቱን በማሳየት የውድድር ዓመቱ ፈርጥ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ተጫዋቾች አንዱ ሊሆን ይችላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ተጫዋቾች በተጨማሪ በዚህ የውድድር ዓመት ምርጥ ብቃታቸውን ለእግር ኳስ ተመልካቹ ያስኮመኩማሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾችን በብዛት የያዙት ክለቦች ሀዋሳ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ናቸው ማለት ይቻላል። ሁለቱ ክለቦች በዚህ የውድድር ዓመት ቡድኖቻቸውን በበርካታ ወጣት ተጫዋቾች አዋቅረዋል። በሀዋሳ ሴንትራል ካፕ ሀዋሳ ከነማ የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ከታዳጊ ቡድን ያሳደገው ፍርድአወቅ አዲሱ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሲሆን ከጅማ ከነማ ያስፈረመው ወጣቱ ሀይማኖት አወቀ ደግሞ የውድድሩን ኮከብ ተጫዋችነት ዘውድን መጎናጸፍ ችሏል። በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የውድድሩን ኮከብ ጎል አግቢነትና ተጫዋችነት ዘውድን የተቀዳጀው የኢትዮጵያ ቡናው ዮሴፍ ደሙዬ ነው። ቡና ከዮሴፍ ደሙዬ በተጨማሪ እንደ አህመድ ረሺድ፣ እያሱ ታምሩ እና ወንድይፍራው ጌታሁን አይነት ወጣቶችን የያዘ ሲሆን ሀዋሳ ከነማ ደግሞ በዚሀ ዓመት ስድስት ወጣቶችን ከተስፋ ቡድኑ አሳድጓል። ከላይ የተጠቀሱት ወይም ደግሞ ሌሎች ወጣት ተጫዋቾች በዚህ ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ጎል አግቢነቱን ወይም የኮከብ ተጫዋችነቱን ክብር ሊቆጣጠሩት ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚያሰለጥኑ 14 አሰልጣኞች መካከል አንዱ አሰልጣኝ በዓመቱ መጨረሻ የውድድር ዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝነትን ክብር መቀዳጀቱ የማይቀር ይሆናል። በዚህ የውድድር ዓመትም በዓመቱ መጨረሻ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝነትን ክብር ማን ሊያገኝ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ በቅድሚያ በሊጉ የሚያሰለጥኑትን አሰልጣኞች የገነቡትን ቡድን እና የሚያስመዘግቡትን ውጤት መመልከት የሚገባ ቢሆንም ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ግን ቅድመ ትንበያውን ለማቅረብ ይወዳል። በፕሪሚየር ሊጉ ከሴቷ መሰረት ማኒ እና የውጭ አገር ዜግነት ካላቸው የቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኞች በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያኑ ገብረመድህን ሀይሌ እና ጸጋዬ ኪዳነ ማርያም ወይም አሸናፊ በቀለ እና ውበቱ አባተ የውድድር ዓመቱን ኮከብ አሰልጣኝነት ዘውድ የመድፋት እድል ይኖራቸዋል ብሎ ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ያምናል።

ማን ይወርዳል?

በአገራችን አንድን ክለብ ይወርዳል ወይም ያልተሳካ ጊዜ ያሳልፋል ብሎ መናገርም ሆነ መተንበይ አልተለመደም። እንዲያውም በሌላ መልኩ ሊያስፈርጅ ይችላል። ግን ደግሞ እውነው እውነት ከሆነ ይነገር ወይም ይገለጽ ዘንድ ግድ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ የግል አስተያየትም ቢሆን ከቀና አመለካከት የመነጨ ከሆነ ለሚተቸው ክለብም ሆነ ቡድን አስተያየቱን ቢቀበል መልካም ነው ብዬ አምናለሁ። የፕሪሚየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ዓመቱን በስኬት ያጠናቅቃሉ ብዬ ቅድመ ግምት ከሰጠኋቸው ክለቦችና ግለሰቦች በተጨማሪ የውድድር ዓመቱን በስኬት ላያጠናቅቁ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸው ክለቦች የሚከተሉት ናቸው። ክለቦቹ በውድድር ዓመቱ ላይሳካለቸው ይችላል ብዬ ያስቀመጥኩት ባላቸው የቡድን ጥልቀት ነው።

አርባምንጭ ከነማ እና ሀላባ ከነማ ከደቡብ ክልል እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዲስ አበባ የውድድር ዓመቱ የሚከብዳቸው ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ። አርባምንጭ ከነማ ታደለ መንገሻን ከደደቢት ማዘዋወር ቢችልም ኮከቡን ሙሉዓለም መስፍንን ለሲዳማ ቡና አሳልፎ መስጠቱ እና ክለቡ አሁንም አሰልጣኝ አልባ መሆኑ የውድድር ዓመቱን የሚያከብድበት ሲሆን ሀላባ ከነማ ደግሞ ለፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ከመሆኑ የተነሳ በሊጉ ለመቆየት የሚያስችል የቡድን ጥልቀት ይገነባል ተብሎ አይገመትም። ሀዋሳ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የሀዋሳ ሴንትራል ካፕ ዋንጫ ላይ ያሳየው ብቃትም የቡድኑ ስብስብ ከላይ የገለጽኩትን ይመስላል።

ኤሌክትሪክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያስመዘገበ ያለው ደካማ ውጤት እና ቡድኑ ባለው ቢሮክራሲ የተነሳ ሜዳ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረበት ሲሆን በዚህ የውድድር ዓመትም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከተመለከትነው ኤሌክትሪክ የተሻለ ቡድን በሊጉ ያሳየናል ተብሎ አይጠበቅም። ሶስቱ ክለቦች የመውረድ ስጋት በቅርብ ርቀት የሚከታተላቸው ቡድኖች ይሆናሉ። ከሶስቱ ክለቦች በተጨማሪ ዋና አሰልጣኙን ዘላለም ሽፈራውን በጉዳት እስከ ዓመቱ አጋማሽ ያጣው ሲዳማ ቡናም ሆነ በርካታ ኮከብ ተጫዋቾቹን ለታላላቅ ክለቦች አሳልፎ የሰጠው ወላይታ ድቻ በውድድር ዓመቱ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ቡድኖች ይሆናሉ። የአሰልጣኝ መሰረት ማኒው ድሬዳዋ ከነማም ሆነ የታረቀኝ አሰፋው ዳሽን ቢራ በ2008 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ከፈለጉ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅቸዋል።
አንባቢያን መጨመር ከፈለጉ መድረኩ ክፍት ነው። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ሀይማኖት አወቀ [192 days ago.]
 ሀይማኖት አወቀ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!