የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማሮ
ጥቅምት 19, 2008

በይርጋ አበበ

11 ጎሎች ተቆጥረውበት የጀመረው የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአገሪቱ ርዕሰ መዲና ሶስት ጨዋታዎችን እና በክልል ስታዲየሞች ደግሞ አራት ጨዋታዎችን በመጀመሪያው ሳመንት መርሃ ግብሩ አስተናግዷል።

በሁሉም ጨዋታዎች ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ስድስቱ ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቅቀው አንዱ ብቻ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የሊጉን የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ከዚህ በታች መጠነኛ ቅኝት አድርገንባቸዋል!!

የመጀመሪያው ቀን በካምቦሎጆ

 ሊጉ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኤሌክትሪክ እና መከላከያን በማገናኘት የጀመረ ሲሆን በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሰባት ቢጫ ካርዶች ተመዝዘውበትና አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሮበት ተጠናቋል። የሊጉን የመጀመሪያ ጎልም ናይጄሪያዊው ፒተር ኦኮቾኮ በማስቆጠር የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያዋን ቢጫ ካርድ የተመለከተውም የኤሌክትሪኩ ተስፋዬ መላኩ ተመልከቷል።

አሁንም ኤሌክትሪክ በመጀመሪያው ጨዋታው አምስት ቢጫ ካርዶችን በመመልከቱ የሊጉን የመጀመሪያ የአምስት ሺህ ብር ቅጣት የተቀበለ ክለብ ሆኗል። የኤክትሪክ እና የመከላከያ ጨዋታ ለተመልካች የማይማርክ ከመሆኑም በላይ የጎል ሙከራዎች በብዛት ሳይካሄዱበት ከተጠናቀቀ በኋላ ደደቢት እና ወላይታ ድቻ ተገናኙ። ይህን ጨዋታ ኢትዮፉትቦል ዶትኮምን ጨምሮ አንዳነደ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ያስተላለፉት ጨዋታ ሲሆን በርካታ የወላይታ ድቻ እና ጥቂት የደደቢት ደጋፊዎች በስታዲየም ተገኝተው የተከታተሉት ጨዋታ ነው። ጨዋታውም ለተመልካች አዝናኝ እና ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ የተደረጉበት ሲሆን በኳስ ቁጥጥርም ጥሩ የሚባል ጨዋታ ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ ከግቡ መስመር በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘችዋን ቅጣት ምት የደደቢቱ ሳምሶን ጥላሁን በመምታት የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ስህተት ተጨምሮበት የጨዋታው የመጀመሪያ ጎል ተቆጠረ። በእለቱ ወላይታ ድቻዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በጎል ሙከራ ከባለሜዳው ደደቢት የተሻሉ ቢሆንም የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት የሚቀመስ አልሆነላቸውም። ገና ጨዋታው በተጀመረ በ16ኛው ደቂቃ ጀምሮ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች የታሪክ ጌትነት አልበገር ባይነት ድካማቸውን ፍሬ እንዳያፈራ አደረገባቸው እንጂ ቢያንስ ሶስት ለሁለት አሸንፈው መውጣት ይችሉ ነበር። በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብቻ ሶስት ያለቀላቸው ሙከራዎች በሀይለየሱስ ብርሃኑ እና በበዛብህ ሙላየሁ አድርጎ ነበር። ሁሉንም የጎል ሙከራዎች ያመከነው የብሔራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ነው።

ከእረፍት መልስ የተካሄደው የጨዋታው ቀጣይ ክፍል በተለይ ወላይታ ድቻ ውጤቱን ለመቀየር እያጠቃ ሲጫወት ደደቢት ደግሞ ከቻለ ለመጨመር ካልቻለ ደግሞ የያዛትን አስጠብቆ ጎመን በጤና ብሎ ለመውጣት እየተከላከለ ሲያጠቃ አምሽቷል። የወላይታ ድቻ ጥረት ሰምሮለትም ገና በ61ኛው ደቂቃ ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ሀይከየሱስ ብርሃኑ አስቆጥሮ ነጠብ መጋራት ችለው ነበር። ሆኖም ተጫሪ ጎሎችን ከመፈለግ ይልቅ አዲስ አበባ ድረስ መጥተን አንድ ነጥብ ይዘን መሄድ ለእኛ ስኬት ነው ብለው ነው መሰል ሰዓት ለማባከን ሲደክሙ ታይተዋል። ሰዓት የማባከን ድካማቸው ግን ፍሬ ማፍራት አልቻለም በ82ኛው ደቂቃ በራሳቸው የጎል ክልል ውስጥ ኳስ በእጃቸው በመንካታቸው ፍጹም ቅጣት ምት ተሰጠባቸው። ፍጹም ቅጣት ምቱንም ናይጄሪያዊው ሳሙኤል ሳኑሜ አስቆጥሮ ደደቢትን ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አደረገው። በአጠቃላይ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ይህን መስሎ ከተከናወነ በኋላ ለሁለተኛው ቀን ተላለፈ።

ሁለተኛው ቀን

የሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎው በምስራቅ ሰሜን እና ደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ሲካሄድ አምሽቶ ፍጻሜውን በመሃል አገር አድርጓል። ክልል ላይ የተካሄዱት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ተካሂደዋል። ወደ ምስራቅ ያቀናው ያለፈው ዓመት የዋንጫው ባለቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮም አዳማ ላይ ጎል ማስቆጠር ሳይችል ተመልሷል። አዳማ ከነማ ወንዶሰን ሚልክያስ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ያስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች በፈረሰኞቹ ላይ ጣፋጭ ድል እንዲጎናጸፍ አድርጎታል። ከስፍራው በደረሰን መረጃ ለማወቅ እንደቻልነው በጨዋታው ፈረሰኞቹ በብሪያን አሙኒ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም የአዳማ ከነማው ግብ ጠባቂ አካሌ ላይ ንክኪ ያደረገብኝ ፈረሰኛ አለ በማለቱ የብሪያን ጎል ከጸደቀች በኋላ ተሽራበታለች።

ጎረቤታማ ክለቦችን ያገናኘው ሁለት የደቡብ ደርቢ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ዘንድሮም ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ባዶ እጁን አልተመለሰም። እስከ እረፍት በበረከት ይሳቅ ጎል ሲመራ የቆየው ሀዋሳ ከነማ ከእረፍት መልስ አንዷለም ንጉሴ ወይም አቤጋ ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በሌላ የደቡብ ደርቢ ጨዋታ አርባምንጭ ላይ አሰልጣኝ የለሌለው አርባምንጭ ከነማ ጎረቤቱን ሆሳዕና ሀድያን አንድ ለባዶ አሸንፎ ሸኝቶታል። ከምስራቅ ኢትዮጵያ ተነስቶ ከ1300 ኪሎ ሜትር በላይ የተጓዘው የመሰረት ማኒው ድሬዳዋ ከነማ ለ92 ደቂቃዎች መረቡን ሳያስደፍር ቢቆይም ለዳሽን ቢራ የማታ ሲሳይ የሆነችዋን ጎል ይተሻ ግዛው በ92ኛው ደቂቃ አስቆጥሮበት ድሬዳዋ ከነማ በባዶ ተመልሷል።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የተካሄደው እዚሁ ሁሉን ቻይ አዲስ አበባ ስታዲየም ነው። ከአመሻሹ 11፡30 ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ናቸው። ጨዋታው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ሆኖ ዘግይቶ ይምጣ እንጂ የውድደሩን ፈጣን ጎል ያስተናገደ ጨዋታም ሆኖ አልፏል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተጀምሮ ገና ተጫዋቾች ቦታ ቦታቸውን ይዘው ሳይረጋጉ የቡናዎቹ ጥላሁን ወልዴ እና አህመድ ረሺድ ተቀባብለው የሰጡትን ኳስ ዮሴፍ ደሙዬ ወደ ጎል የሞከራትን ኳስ የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ኢሜኑኤል ፌቦ በእጁ ነክቶ በመትፋቱ የቡናው ያቡን ዊሊያም በ23ኛው ሰከንድ ወደ ጎል ቀይሯታል። የዊሊያም ጎልም በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ እጅግ ፈጣኗ ጎል ሳትሆን እንደማትቀር ይገመታል። እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር የማይቻለው የፌዴሬሽናችን የመረጃ አያያዝ ጉድለት ስላለበት ነው።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በንግድ ባንክ ተደጋጋሚ የጎል ሙከራ አድራጊነት እና የቡናው ግብ ጠባቂ አልደፈርባይነት ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን የዳኝነት ስህተትም የጨዋታው አንዱ አካል ነበር። ዳኛው በእለቱ ወደ ውጭ የወጣውም ሆነ ለእጅ ውርወራ ከመስመር የወጡት ኳሶች የማንኛው ቡድን የነካው እንደሆነ ካለማወቅ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡናው ዮሴፍ ደሙዬ በንግድ ባንኮቹ ቶክመ ጄምስ እና ቢኒያም ሲራጅ ተጠልፎ ቢወድቅም ፍጹም ቅጣት ምት ለመስጠት አልደፈሩም ነበር። ከዚህ በተረፈም ያለምንም መታከት ሌሎች በርካታ ስህተቶችን ሲሰሩ አምሽተው ጨዋታውን ጨርሰውታል።

በእለቱ በቡና በኩል በተለይ መስዑድ መሀመድ እጅግ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታየ ሲሆን በንግድ ባንክ በኩል ሼይቩ ጂብሪል አህመድ እና ፍሊፕ ዳውዚ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። የቡናዎቹ ወጣቶች ከነባሮቹ እና ልምድ ካላቸው የቡድን አጋራቸው ጋር ያሳዩት ጥምረት ተወድሶላቸዋል። ከጨዋታው በኋላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም የቡናዎች ፈጣን እንቅስቃሴ እና የአጨዋዎት ታክቲክ እንዲሁም ገና ሳንረጋጋ የተቆጠረብን ጎል ያሰብነውን እንዳናሳካ አድርጎናል ሲል የቡና አቻው ድራገን ፖፓዲች ደግሞ ወጣቱ ቡድናቸው እየተዋሃደ ሲሄድ መልካም ጨዋታ እንደሚያሳያቸው ገልጸው በትናንቱ ጨዋታ ግን መደሰታቸውን ተናግረዋል። ቡድናቸው ያሳየው አጨዋወትም እንዳስደሰታቸው ሳይናገሩ አላለፉም። የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ውሎ ከሞላ ጎደል በዚህ መልኩ ተካሂዷል። ሁለተኛው ሳምንት ውድድር ነገ ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ እና
በክፍላተ አገራት የሚካሄድ ይሆናል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!