ዋልያዎቹን በቻን ውድድር የትኞቹ ቡድኖች ይደርሷቸዋል
ጥቅምት 24, 2008

በይርጋ አበበ

የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስብስብ ኬንያን ሁለት ለአንድ እና ብሩንዲን ደግሞ ሶስት ለሁለት በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት አሸንፎ ለቻን ዋንጫ ማለፉ ይታወቃል። የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪው ካፍም በዚህ ውድድር የሚሳተፉትን 16 አገራት ማንነታቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደ ፈረንጆቹ የዘመን ስሌት የፊታችን ጥር ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት 16ቱ አገራት በአራት ምድብ እንዲደለደሉ የእጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ቀነ ቀጠሮ ቆርጦላቸዋል። አሁንም በእነሱ የዘመን አቆጣጠር ኖቬንበር 15 በውድድሩ አስተናጋጅ አገር ሩዋንዳ ዋና መናገሻ ከተማ ኪጋሊ ላይ የእጣ ማውጣቱ ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ ካፍ አሳውቆኛል ሲል የእኛው ፌዴሬሽን በህዝብ ግንኙነት ክፍሉ በኩል ደብዳቤ ልኮልናል።

በአቶ ወንድምኩን አላዩ በኩል ለሁሉም የስፖርት ጋዜጠኞች ከተላከው ደብዳቤ ለመረዳት እንደቻልነው ውድድሩ ከጃነዋሪ 16 እሰከ ፌብሩዋሪ 7 ቀን 2016 ድረስ በሩዋንዳ ሶስት ከተሞች ይካሄዳል። ውድድሩ የሚካሄድባቸው ከተሞች የአገሪቱ መንግስት መቀመጫ ከተማ የሆነችው ኪጋሊ አንዷ ስትሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ጊሰኒ እና ቡታሬ ይባላሉ። በእነዚህ ከተሞች የሚካሄደውን የቻን ውድድር ለመሳተፍ ቀደም ሲል ትኬቱን የቆረጠው የዮሃንስ ሳህሌ እና ፋሲል ተካልኝ ስብስብም በየትኛው ምድብ ይደለደላል? ከምድቡስ የትኞቹ አገራት ይገጥሙት ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ማወቅ የሚቻለው ካፍ በያዘው የጊዜ ሰሌዳ ይሆናል። እኛ ግን ከዚህ በታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ በውድድሩ የሚሳተፉትን አገራት ስም ዝርዝር እናስቀምጣቸዋለን።

በቻን ውድድር ያለፈው አሸናፊ ሊቢያ በዘንድሮው አልተሳተፈችም። የዋንጫ ተፋላሚ የነበረችዋ ጋና ግን ዘንድሮም ተገኝታለች። ያኔ ጋናም ሆነች ሊቢያ በውድድሩ ከዋልያዎቹ ጋር በአንድ ምድብ ተደልድለው የነበረ ሲሆን ሁለቱም ዋልያውን አሸንፈውታል ለዚያውም በጨዋታ ብልጫ ጭምር። ለማንኛውም በዘንድሮው ውድድር ምዕራብ አፍሪካ የተባለው ክፍለ አህጉር ስምንት አገሮችን በማሳተፍ የሚስተካከለው አልተገኘም። ጋቦን፣ ናይጀሪያ፣ ኒጀር፣ ማሊ፣ ኮት ዲቯር፣ ካሜሩን፣ ጊኒ እና ዴሞክራሲ ሲያልፍ የማይነካት ግን ራሷን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብላው የምትጠራው ኮንጎ  ናቸው። ደቡብ አፍሪካው ደግሞ አንጎላን፣ ዛምቢያን እና ዝምባብዌን ያሳትፋል። ምስራቅ አፍሪካ ደግሞ ከሰሜን አፍሪካው በአንድ በመብለጥ ኢትዮጵያን ዩጋንዳንና ሩዋንዳን ሲያሳትፍ ጠንካራው የሰሜን አፍሪካው ግዛት ግን ሞሮኮን እና ቱኒዚያን ነው ያሳተፈው።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!