የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ
ጥቅምት 27, 2008

- ዳሽን ቢራ ማህበሩን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስም የድጋፉ ተባባሪ ሆኗል

- አንጋፋውን ጋዜጠኛ ሰለሞን ገብረእግዚያብሔርን የህይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጎ መርጦታል

በይርጋ አበበ                
              
የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ትናንት አመሻሽ ላይ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል አካሂዷል። ማህበሩ በጉባኤው ያለፈውን ዓመት እቅድ አፈጻጸም ገምግሞ የቀጣይ እቅዶችን የተወያየ ሲሆን የማህበሩን የፋይናንስ ሪፖርትም አቅርቧል።

 የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ እንዲያካሂድ ድጋፍ ያደረጉለትን ዳሽን ቢራን እና ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴልን በማመስገን ንግግር ማቅረብ የጀመረው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ፤ ያለፈውን ዓመት የማህበሩን እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርብ የውጭ ጉዞ እድሎችን በመጠቀም በኩል ተስፋ ሰጪ እንደነበረ ተናግሮ ቢሮ የማግኘቱን ጉዳይ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከኪራይ ነጻ ቢሮ ለመስጠት ፈቃደኛ ቢሆንም በጊዜ መጣበብ ምክንያት እንዳልተሳካ ተናግሯል። ማህበሩ ለአባላት ሊሰጥ ያሰበውን የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ከኦሎምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ስልጠና መስጠቱን በስኬት ቆጥሮታል።

Annual Meeting Sport Journalist 2008


የማህበሩ አቃቢ ነዋይ ጋዜጠኛ አመሃ ፍሳሃ ያቀረበው የፋይናንስ ሪፖርትም ባለፈው ዓመት 107 ሺህ 469 ብር ገቢ አስገብቶ ከዚህ ውስጥ 41 ሺህ 441 ብር ለተለያዩ ወጭዎች መዋሉንና ቀሪ 61 ሺህ 028 ብር በማህበሩ አካውንት የሚገኝ ገንዘብ ነው ብሏል። አባላት ወርሃዊ መዋጯቸውን በአግባቡ በመክፈል በኩል ችግር እንዳለባቸውም ተናግሯል።

የ2008 ዓ.ም የማህበሩን እቅድ ያቀረበው የብስራት ስፖርት አዘጋጁ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ነው። የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ዋና ጸሀፊ ጋዜጠኛ መንሱር ባቀረበው የዚህ ዓመት እቅዶች በአራት ዋና ዋና ትኩረቶች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። “በመጀመሪያ አገራችን በየዘርፉ የፖሊሲ አማካሪዎች የላትም ለዚህ ደግሞ በስፖርቱ ዘርፍ የባለሙያውን ክፍተት ለመድፈን በየሶስት ወሩ የሙያተኞች ውይይት ወይም ሲምፖዚየም እናዘጋጃለን። በዚህም መሰረት በእቅዳችን መሰረት በጥር፣ በሚያዝያ እና በሃምሌ ወራት ሶስት የውይይት መድረኮችን እናዘጋጃለን” ሲል ጋዜጠኛ መንሱር ተናግሯል።

ቀሪዎቹ የማህበሩ እቅዶች ደግሞ “የአገር ውስጥ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አባላትን ቁጥር ማብዛት በተለይም የአገር ውስጥ የአባልነት መታወቂያን አባላት ዋጋ እንዲሰጡት የተለያዩ ስራዎችን እንሰራለን” ብሏል። በተለይ አንድንድ ጋዜጠኞች  በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ሳይታቀፉ በግላቸው የዓለም አቀፉ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አባልነት መታወቂያ ለማውጣት ጥረት የሚያደርጉ ጋዜጠኞች መኖራቸውን የገለጸው መንሱር አብዱልቀኒ የአገር ውስጥ ጋዜጦች ማህበር አባልነት መታወቂያን ዋጋ እንዲሰጡት ለማድረግ ከተለያዩ የስፖርት ማህበራት ፌዴሬሽኖች ጋር በስምምነት ለመስራት አቅደናል ብሏል።

የማህበሩ ሶስተኛው እቅድ ሆኖ የቀረበው ደግሞ ቃል የተገባውን የቢሮ ስጦታ ጉዳይ እልባት መስጠት እንደሆነም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፉ ማህበር በኩልም ስራ አስፈጻሚነትና የተሰሚነት ቦታ የኢትዮጵያ ተወካዮች እንዲኖሩ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል። በእለቱም የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ለውይይት የቀረቡ ሲሆን የማህበሩ አመራሮችም መልስ ሰጥተውባቸዋል።

ላለፉት 36 ዓመታትና ከዚያ በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ያገለገለውን አንጋፋውን ጋዜጠኛ ሰለሞን ገብረእግዚያብሔርን የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር “የህይወት ዘመን የላቀ ተሸላሚ” አድርጎ ሸልሞታል። የሰለሞንን ሽልማት በተመለከተ በራሱ አንደበት የተናገረውንና ሌሎች ስለ ሰለሞን የሰጡትን አስተያየት በቀጣዩ ክፍል እናቀርባለን።

በማህበሩ ጠላላ ጉባኤ የእለቱ የመጨረሻ ፕሮግራም የነበረው ባለፈው ዓመት መገባደጃ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲሁም የስፖርት ጋዜጠኞችን ከሙዚቃ አጫዋቾች ወይም ዲጄዎች ጋር በማጫወት አንድ ብዕር ለአንድ ተማሪ የሚል መርህ ይዘው በመነሳት “ለሰዋሰወ ገነት የህጻናትና አረጋዊያን መርጃ ድርጅት” የትምህርት መሳሪያዎችን ያሰባሰቡትን የስፖርት ጋዜጠኞች የእውቅና የምስክር ወረቀት መስጠት ነበር።

ለሁለት ዓመታት የሚያገለግለው አዲሱ የማህበሩ የአገር ውስጥ መታወቂያም ለአባላት ታድሏል። በአሁኑ ሰዓት እስከ 110 የሚደርሱ ጋዜጠኞች በማህበሩ በአባልነት እንዳሉ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ በተለይ ለኢትዮፉትቦል ዶትኮም ተናግሯል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!